Tuesday, March 28, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኦርኪድ እንዲከፍል የተወሰነበት የ42 ሚሊዮን ብር ክርክር ተቀለበሰ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

–  ውሳኔውን የተቃወሙት ጀርመናዊ ይግባኝ እላለሁ ብለዋል

በኦርኪድ ቢዝነስ ግሩፕ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበርና በትውልድ ኢትዮጵያዊ በሆኑት የጀርመን ዜግነት ያላቸው አቶ ዮናስ ካሳሁን መካከል፣ በይግባኝ ለአንድ ዓመት ክርክር ሲደረግበት የነበረው የ1.7 ሚሊዮን ዩሮ (42 ሚሊዮን ብር) ክፍያ የፍትሐ ብሔር ክርክር፣ በኦርኪድ አሸናፊነት ሐምሌ 30 ቀን 2007 ዓ.ም. ተጠናቀቀ፡፡

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሰኔ 2 ቀን 2006 ዓ.ም. ኦርኪድ ቢዝነስ ግሩፕ ለጀርመናዊው ዜጋ አቶ ዮናስ 42 ሚሊዮን ብር ከዘጠኝ በመቶ ወለድ ጋር እንዲከፍል ያስተላለፈውን ውሳኔ በመሻር፣ መክፈል እንደሌለበት ፍርድ የሰጠው ዳኛ ደስታ ገብሩ፣ ዳኛ ገበየሁ ፈለቀና ዳኛ በዕውቀት በላይ የተሰየሙበት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አንደኛ ፍትሐ ብሔር ችሎት ነው፡፡

የክርክሩ ምክንያት እ.ኤ.አ. ሐምሌ 9 ቀን 2011 ከተከበረው የደቡብ ሱዳን የነፃነት ቀን በዓል አከባበር ጋር የተገናኘ ነው፡፡ የደቡብ ሱዳን መንግሥት የነፃነት ቀኑን አስመልክቶ ያወጣውን ዓለም አቀፍ የመስተንግዶ ዝግጅት ጨረታን ያሸነፈው፣ ተቀማጭነቱ ዱባይ የሆነውና ኢትዮጵያዊቷ ነጋዴ ወ/ሮ አኪኮ ሥዩም ከፍተኛ ባለድርሻ የሆኑበት፣ ሶልዳን ኢንተርናሽናል ጄኔራል ትሬዲንግ መሆኑ በክርክሩ ወቅት ተገልጿል፡፡

አቶ ዮናስና ወ/ሮ አኪኮ በነበራቸው የሥራ ግንኙነት መሠረት ለበዓሉ አገልግሎት የሚውሉ ቁሳቁሶችንና መሣሪያዎችን፣ አቶ ዮናስ ከሚኖሩበት ጀርመን ከሚገኙ ኩባንያዎች ጋር በመደራደር በራሳቸው ገንዘብ ገዝተው ማቅረባቸውን ገልጸዋል፡፡ የኦርኪድ ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ አኪኮ አቶ ዮናስ ለሠሩበት ሥራና ላወጡት ወጪ 42 ሚሊዮን ብር ለመክፈል መስማማታቸውን ለፍርድ ቤት ያቀረቡት ሰነዶች ይገልጻሉ፡፡ አቶ ዮናስ ክፍያውን በሚመለከት በኦርኪድ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ እንግዳ ወርቅነህ ፊርማ የተዘጋጀ መተማመኛ ሰነድ፣ እንደደረሳቸው አስረድተዋል፡፡ የተሰጣቸው የመተማመኛ ሰነድም ‹‹ለደቡብ ሱዳን ነፃነት ቀን እ.ኤ.አ. ጁላይ 9 ቀን 2011 በዓል አከባበር፣ በእርስዎ አማካይነት በጀርመንና በደቡብ ሱዳን መካከል ዱባይ ባለው እህት ኩባንያችን በሆነው በሶልዳን ኢንተርናሽናል ትሬዲንግ አማካይነት፣ ለሠሩት ሥራና ላወጡት ወጪ ማግኘት ከሚገባዎት ጥቅም ጋር 1.7 ሚሊዮን ዩሮ መክፈል እንዳለብን የሚታወቅ ነው፡፡ ነገር ግን ከደቡብ ሱዳን መንግሥት ክፍያ መዘግየት ስለገጠመን፣ እስካሁን ለነበረዎት ትዕግሥትና ትብብር ከልብ እያመሰገንን፣ ይኼንንም ክፍያ በስድስት ወራት ውስጥ ከፍለን የምንጨርስ መሆናችንን ዛሬ መስከረም 9 ቀን 2004 ዓ.ም. ይኼንን መተማመኛ ሰነድ ሰጥተንዎታል፤›› የሚል መሆኑንም ለሥር ፍርድ ቤት አቅርበው ነበር፡፡

ኦርኪድ በጠበቆቹ አማካይነት ሰነዱ የሐሰት መሆኑንና በመካከላቸው ምንም ዓይነት ውል እንደሌለ በመግለጽ ተከራክሮ ነበር፡፡ የሥር ፍርድ ቤት መተማመኛ ሰነዱ ላይ ያረፈው ፊርማ የምክትል ሥራ አስኪያጁ መሆን አለመሆኑንና ማኅተሙ የድርጅቱ መሆን አለመሆኑን በፎረንሲክ ምርመራ እንዲጣራ ካደረገ በኋላ፣ ፊርማው የምክትል ሥራ አስኪያጁ፣ ማኅተሙም የድርጅቱ መሆኑን በማረጋገጥ፣ ኦርኪድ የተጠቀሰውን ገንዘብ ከነወለዱ ለአቶ ዮናስ እንዲከፍል ውሳኔ ሰጥቶ ነበር፡፡

ኦርኪድ ቢዝነስ ግሩፕ በሥር ፍርድ ቤት የተሰጠውን ውሳኔ በመቃወም፣ ባለፈው ዓመት ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያቀረበው የይግባኝ አቤቱታ ተቀባይነት በማግኘቱ፣ ሁለቱም ወገኖች የጽሑፍ ማስረጃ ካቀረቡ በኋላ የቃል ክርክርም አድርገዋል፡፡

ተከራካሪ ወገኖች ባደረጉት የቃል ክርክር፣ ኦርኪድ ቢዝነስ ግሩፕ በጽሑፍ ባቀረበው የክርክር ነጥብ፣ በደቡብ ሱዳን መንግሥት የወጣውን ጨረታ ያሸነፈው መቀመጫው ዱባይ የሆነው ድርጅት ከኦርኪድ ቢዝነስ ግሩፕ ጋር ምንም የሚያገናኘው ነገር እንደሌለ አመልክቶ ነበር፡፡ ድርጅቱ የፈጸመው ተገቢ ያልሆነ ነገር ቢኖርና በሕግም ተጠያቂ የሚሆን ከሆነ፣ የዳኝነት ሥልጣኑ የኢትዮጵያ ስላልሆነ በአገሩ ወይም ዓለም አቀፍ የሕግ ሒደት መሆን እንዳለበት አስረድቷል፡፡ አቶ እንግዳ ወርቅነህም የሶልዳን ምክትል ሥራ አስኪያጅ ሳይሆኑ፣ የኦርኪድ ምክትል ሥራ አስኪያጅ እንደሆኑ ገልጿል፡፡ ሶልዳንን በሚመለከት ምንም ዓይነት ፊርማም ሆነ ኃላፊነት መውሰድ እንደማይችሉ፣ እሳቸው ፈረሙት የተባለው ሰነድ የሐሰትና ሊሆን የማይችል መሆኑን፣ ኦርኪድ የሶልዳን እህት ኩባንያ ባልሆነበትና ሁለቱ ድርጅቶች በጋራ የሚሠሩበት ሁኔታም ሆነ የሕግ ውል ሳይኖራቸው፣ ኦርኪድ የሶልዳንን ዕዳ እንዲከፍል የሚጠየቅበት የሕግም ሆነ ሌላ ምክንያት እንደሌለ በመጥቀስ ተከራክሯል፡፡

አቶ ዮናስ የወ/ሮ አኪኮን የኤሌክትሮኒክ አድራሻ ወይም ኢሜይልና የይለፍ ቃል ባልታወቀ መንገድ የመረጃ መረብ ሰብረው በመግባት፣ በዳታ መጥለፍ ወንጀል ተከሰውና ጥፋተኛ ተብለው፣ በሁለት ዓመታት ጽኑ እስራትና በገንዘብ መቀጣታቸውን አክሎ፣ በመተማመኛ ሰነዱ ላይ ምክትል ሥራ አስኪያጁ እንደፈረሙ የተገለጸውን ነጥብ ከሳቸው ባህሪ አንፃር እንዲታይለት በመግለጽ ኦርኪድ ተከራክሯል፡፡

ጀርመናዊው አቶ ዮናስም በጠበቆቻቸው አማካይነት በሰጡት ምላሽ፣ ኦርኪድ የሶልዳን እህት ኩባንያ መሆኑን ምክትል ሥራ አስኪያጁ አቶ እንግዳ በመተማመኛ ሰነዱ ላይ ከመግለጻቸውም በተጨማሪ፣ ወ/ሮ አኪኮ የሁለቱም ድርጅቶች ሥራ አስኪያጅና ከፍተኛ ባለድርሻ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ መተማመኛ ሰነዱ ደግሞ በፍትሐ ብሔር ሕግ በ1675 እና 1731 መሠረት ውል መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ የሥር ፍርድ ቤት መንግሥታዊ ተቋም በሆነውና ፍፁም እምነት በሚጣልበት የፌዴራል ፎረንሲክ ምርመራ መሥሪያ ቤት ተመርምሮና ትክክለኛ ሰነድ መሆኑ ተረጋግጦ ውሳኔ የተሰጠበት በመሆኑ ሊፀና እንደሚገባ ተከራክረዋል፡፡ አቶ ዮናስ የወ/ሮ አኪኮን ኢሜል ሰብረው መረጃ ወስደዋል የተባለው ከዚህኛው ክርክር ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የሌለውና በራሱ በኩል ፍፃሜ ያገኘ በመሆኑ ሊነሳ እንደማይገባና ተገቢ አለመሆኑን በመግለጽ ውድቅ እንዲደረግላቸው ተከራክረዋል፡፡ የደቡብ ሱዳን የነፃነት ቀን ሲከበር ስለሠሩት ሥራና በመተማመኛ ሰነዱ ላይ ስለሰፈረው ገንዘብ ማጠናከሪያ የሚሆንና ወ/ሮ አኪኮ በዓሉ ሲከበር አቶ ዮናስን በሚመለከት ያደረጉትን ንግግር የሚያሳይ የቪዲዮ ግራፊና የፎቶ ማስረጃ እንዲያቀርቡ ጠይቀው ፍርድ ቤቱ ተቀብሏቸው አያይዘው ነበር፡፡

ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሁለቱንም ወገኖች ክርክር ከሰማና በሥር ፍርድ ቤት የተሰጠውን ውሳኔ ከመረመረ በኋላ፣ ምክትል ሥራ አስኪያጁ የሶልዳን ኢንተርናሽናል ጄኔራል ትሬዲንግን ዕዳ እንከፍላለን የሚል መተማመኛ ሰነድ ለመስጠት ሥልጣኑ አላቸው? ወይስ የላቸውም? ሰጥተው ቢገኙ ኦርኪድ ለመክፈል የሚገደድበት የሕግ አግባብ አለ ወይስ የለም? በኦርኪድና በሶልዳን መካከል ያለው ግንኙነት ምንድነው? በሰነዱ በሰፈረው የኦርኪድ ግዴታ ላይ የሚኖረው ውጤትና ፎረንሲክ አረጋግጧል መባሉ አግባብነት አለው ወይስ የለውም? አቶ ዮናስ የኢሜል የመረጃ መረብ ሰብረው በመግባት ዳታ በመውሰድ ተከሰው ጥፋተኛ መባላቸውና በመተማመኛ ሰነዱ ተዓማኒነት ላይ የሚያስከትለው ውጤት አለ ወይስ የለም? የሚለውን ጭብጥ ይዞ መመርመሩን በፍርዱ አስፍሯል፡፡

በሁለቱ ወገኖች ክርክር ማወቅ የተቻለው፣ የደቡብ ሱዳን የነፃነት በዓል አከባበር ዝግጅትን አስመልክቶ ከአገሩ መንግሥት ጋር ውል የተዋዋለው ኦርኪድ ሳይሆን፣ ሶልዳን መሆኑን ፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡ በመተማመኛ ሰነዱ ላይ ኦርኪድ የሶልዳን እህት ኩባንያ መሆኑ ከመገለጹና ወ/ሮ አኪኮ ሥዩም የሁለቱም ድርጅቶች ሥራ አስኪያጅ ወይም ባለድርሻ መሆናቸው ከመገለጹ ውጪ፣ በበዓሉ አከባበር ዝግጅቱ ላይ፣ በንዑስ ተቋራጭነት ተዋውሎ ስለመሳተፉ አለመገለጹንም ጠቁሟል፡፡ ሶልዳንን ሆኖም ክፍያዎችን እንዲፈጽም የተሰጠው ሥልጣን ስለመኖሩም የሚያረጋግጥ ማስረጃ አለመቅረቡንም አክሏል፡፡ ሶልዳንና ኦርኪድ በሁለት የተለያዩ አገሮች ሕጐች መሠረት የተቋቋሙና የየራሳቸው ሕጋዊ ሰውነት ያላቸው መሆኑም ሁለቱን ወገኖች እንዳላከራከራቸውም ፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡

አቶ ዮናስ በበዓል አከባበሩ ላይ የሠሩትን የሚገልጽ፣ ከሶልዳን ጋር የተዋዋሉበትን የሚያሳይ አንድም ሰነድ አለማቅረባቸውን፣ መተማመኛ ሰነድ ያሉትም፣ ኦርኪድ ላይ የሶልዳን ዕዳ ነው የተባለውን የመክፈል ግዴታ ከሚጥልበት በቀር፣ ኦርኪድ ዕዳውን ከከፈለ በኋላ አቶ ዮናስን ተክቶ ከሶልዳን ገንዘቡን መጠየቅና ማስመለስ የሚያስችል ምንም ዓይነት መብት እንደማያጐናጽፈው ፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡ አቶ እንግዳ ወርቅነህ በንግድ ሕግ ቁጥር 528(1) መሠረት ሥልጣን እንደተሰጣቸው የጠቆመው ፍርድ ቤቱ፣ ከተሰጣቸው ሥልጣን ውጪ የሚያደርጉት ተግባር ውጤት እንደማይኖረው መደንገጉንም ጠቁሟል፡፡ በድርጅት መመሥረቻ ጽሑፍም ሥራ አስኪያጅ ስለሚኖረው ሥልጣን መዘርዘሩን ገልጾ፣ ከሌለው ሥልጣን ውጪ ሊሠራ እንደማይችልም አብራርቷል፡፡ የኦርኪድ ቢዝነስ ግሩፕ መመሥረቻ ጽሑፍም በዝርዝር ያስቀመጠ መሆኑን ገልጾ፣ አቶ እንግዳ ሶልዳንን ወክለው ግዴታ ገብተዋል የተባለው የማይወክሉትን ሦስተኛ ወገን የሶልዳን ኢንተርናሽናልን ዕዳ ለመክፈል ግዴታ ቢገቡም፣ አቶ ዮናስ ለሶልዳን ኢንተርናሽናል ኩባንያ ለሰጡት አገልግሎት 1.7 ሚሊዮን ዩሮ ዕዳ ቀርቶ፣ ጥቂት የገንዘብ ዕዳ መኖሩን የሚያረጋግጥ ማስረጃ እንደሌለ ፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡

በመሆኑም ሥራ አስኪያጅ ማኅበሩን መወከል ስለቻለ ብቻ ከማኅበሩ ወሰን ውጪ ለማኅበሩ ጥቅም የማያስገኝና ግዴታን ብቻ የሚያስከትል መተማመኛ ሊሰጥ እንደማይችል ፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡ በመሆኑም አቶ እንግዳ ለሦስተኛ ወገን ዕውቅና የሰጡበትና ለመክፈል የገቡት ግዴታ ከማኅበሩ ዓላማ ወሰን ውጪ በመሆኑ፣ በንግድ ሕግ ቁጥር 528(1) መሠረት የተሰጠው መተማመኛ ሰነድ ኦርኪድን ሊያስገድደው እንደማይችል አስረድቷል፡፡ ኦርኪድና ሶልዳን የየራሳቸው ህልውና ያላቸው በመሆኑ፣ ኦርኪድ በሶልዳን ዕዳ ሊጠየቅ እንደማይችል፣ እህት ኩባንያዎች እንደሆኑ በመተማመኛ ሰነዱ ላይ የተጠቀሰ ቢሆንም፣ አንዱ የአንዱ ቅርንጫፍ መሆኑ ወይም አንዱ ለአንዱ ተጠያቂ ሊሆን የሚችልበት የፍሬ ነገርና የሕግ አግባብ መኖሩ አለመረጋገጡን አስታውቋል፡፡ በበዓል አከባበሩ ላይ የኦርኪድ ሠራተኞች መሳተፋቸውን አቶ ዮናስ ገልጸው ኦርኪድ ኃላፊነት እንዳለበት የገለጹ ቢሆንም፣ ኦርኪድ ሠራተኞቹን በውል ኃላፊነት ወስዶ ያሠራ ወይም ሠራተኞቹ በውሰት ሄደው እንደሠሩ የተረጋገጠ ነገር አለመኖሩን ገልጾ፣ ኦርኪድ የሶልዳንን ዕዳ የመክፈል ኃላፊነት እንደሌለበት ፈርዷል፡፡

በመተማመኛ ሰነዱ ላይ ያረፈው ፊርማ የምክትል ሥራ እስኪያጅና ማኅተሙም የድርጅቱ መሆኑ በፎረንሲክ ምርመራ መረጋገጡንና የፎርንሲክ ምርመራ ውጤትም ጠንካራ ማስረጃ መሆኑን የገለጸው ፍርድ ቤቱ፣ መተማመኛ ሰነዱ ትክክለኛ ስለመሆኑና የተባለው ግዴታ ስለመኖሩ ግን ፍፁም የሆነ ማረጋገጫና ሊስተባበል የማይችል ማስረጃ አለመሆኑን አስረድቷል፡፡

ኦርኪድ ሌላው በማስረጃነት ያቀረበውን አቶ ዮናስ የወ/ሮ አኪኮን ኢሜይል ሰብረው በመግባት የተለያዩ መረጃዎችን ወደ ራሳቸው ኢሜይል አሸጋግረዋል የሚለውን፣ ፍርድ ቤቱ በድርጊቱ አቶ ዮናስ በፍርድ ቤት ጥፋተኛ የተባሉበትና የተቀጡበት መሆኑን ጠቁሞ፣ ድርጊቱ ከመተማመኛ ሰነዱና አሁን ክርክር ከሚደረግበት ጉዳይ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንደሌለው አስረድቷል፡፡ ድርጊቱ የአቶ ዮናስን ባህሪ ለማሳየት ግን የቀረበ መሆኑን ገልጿል፡፡ የወ/ሮ አኪኮን ዳታዎች ሳይፈቀድላቸው ወስደው መገኘታቸው፣ ቅንነት የጐደላቸው መሆናቸውንና አቅሙ ካላቸው የመተማመኛ ሰነዱንም በሕገወጥ መንገድ ለማግኘት ወይም ለማዘጋጀት ወደኋላ የማይሉ መሆኑን፣ ፍርድ ቤቱ ግንዛቤ መውሰዱንና በመተማመኛ ሰነዱ ተዓማኒነት ላይ ጥርጣሬ የሚፈጥር መሆኑን አብራርቷል፡፡

አቶ ዮናስ በተጨማሪ ያቀረቧቸው የቪዲዮና የፎቶግራፍ ማስረጃዎች፣ አቶ ዮናስ ለዝግጅቱ ሥራዎች ሲሠሩ የሚያሳይና ወ/ሮ አኪኮ በምሥጋና ፕሮግራም ላይ ባደረጉት ንግግር፣ አቶ ዮናስ ለአንድ ኩባንያ የነገሩላቸውን በማመን፣ ገንዘብ ከመክፈላቸው በፊት ዕቃዎችን ያስለቀቁላቸው መሆኑን ለአብነት በመግለጽ ማመስገናቸው የሚያሳይ መሆኑን ፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡ ይኼ ማስረጃ ኦርኪድ ስለሶልዳን ኢንተርናሽናል ሆኖ ክፍያ መፈጸሙን የሚያስረዳ አለመሆኑን ጠቁሟል፡፡ አቶ ዮናስም በንዑስ ተቋራጭነት የተወሰነ ሥራ በክፍያ ለመሥራት ተዋውለው መሥራታቸውንም እንደማያረጋግጥ ፍርድ ቤቱ አክሏል፡፡ በመሆኑም በአጠቃላይ በተዘረዘሩ ምክንያቶች የሥር ፍርድ ቤት የሰጠው ውሳኔ መሻሩንና ኦርኪድ እንዲከፍል የተወሰነበት የ1.7 ሚሊዮን ዩሮን (42 ሚሊዮን ብር) ሊከፍሉ እንደማይገባ ውሳኔ ሰጥቶ መዝገቡን ዘግቷል፡፡ በውሳኔው ቅር የተሰኙት ጀርመናዊው አቶ ዮናስ ካሳሁን፣ ግልጽ የሆነ የሕግ ስህተት መፈጸሙን ጠቁመው፣ ለሰበር ሰሚ ችሎት ይግባኝ እንደሚሉ ተናግረዋል፡፡ ግንኙነት የሌለው ማስረጃን ለውሳኔ ማጠናከሪያ የወሰደው ፍርድ ቤቱ፣ እሳቸው ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው ማስረጃ አቅርበው መታለፉ እንዳሳዘናቸውም ገልጸዋል፡፡             

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች