በተጠረጠሩበት የሽብርተኝነት ድርጊት ወንጀል በቁጥጥር ሥር ከዋሉበት 2004 ዓ.ም. መጨረሻ ወራትና ክስ ከተመሠረተባቸው ጥቅምት 15 ቀን 2005 ዓ.ም. ጀምሮ፣ የብዙዎችን ትኩረት ስቦ የነበረው የእነ አቡበከር አህመድ የፍርድ ቤት ክርክር ከሰባት ዓመታት እስከ 22 ዓመታት በሚደርስ የጽኑ እስራት ቅጣት ውሳኔ ሐምሌ 27 ቀን 2007 ዓ.ም. ተጠናቀቀ፡፡
ከሁለት ዓመታት በላይ የፈጀውና በአብዛኛው በዝግ ክርክር ሲያስችልና ሲመረምር የከረመው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቦሌ ምድብ አራተኛ ወንጀል ችሎት፣ ሐምሌ 27 ቀን 2007 ዓ.ም. የቅጣት ውሳኔውን ያስተላለፈው ተከሳሾቹን አራት ቦታ ከፍሎ ነው፡፡
ዳኛ ሀብቴ ፊቻላ (የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት)፣ ዳኛ ሙሌጌታ ኪዳኔና ዳኛ አዱኛ ነጋሳ የተሰየሙበት ቦሌ ምድብ ችሎት ባስተላለፈው የቅጣት ውሳኔ አቡበከር አህመድ፣ አህመዲን ጀበል፣ ያሲን ኑሩና ከሚል ሸምሱ፣ እያንዳንዳቸው እጃቸው ከተያዘበት ቀን አንስቶ በሚታሰብ በ22 ዓመታት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ወስኗል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ በተመሳሳይ ሁኔታ እጃቸው ከተያዘበት ቀን ጀምሮ የሚታሰብ እያንዳንዳቸው በ18 ዓመታት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ የተወሰነባቸው በድሩ ሁሴን፣ ሳቢር ይርጉ፣ መሐመድ አባተ፣ አቡበከር ዓለሙና ሙኒር ሁሴን ናቸው፡፡ ሼክ መከተ ሙሔ፣ አህመድ ሙስጠፋ፣ ሼክ ሰዒድ አሊ፣ ሙባረክ አደምና ካሊድ ኢብራሂም እያንዳንዳቸው በ15 ዓመታት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ተወስኗል፡፡ በመጨረሻም ሙራድ ሽኩር፣ ኑሩ ቱርኪ፣ ሼክ ባህሩ ዑመርና ጋዜጠኛ የሱፍ ጌታቸው እያንዳንዳቸው በሰባት ዓመታት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ በመወሰን የፌዴራል ማረሚያ ቤት እንዲያስፈጽም ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
ፍርድ ቤቱ በፍርደኞቹ ላይ የተለያዩ የቅጣት ውሳኔዎች የሰጠበትን ምክንያት አብራርቷል፡፡ ፍርደኞቹ የሽብርተኝነት ተግባር ለመፈጸም የተነሱበት ዓላማም ሆነ አንድነት ተመሳሳይ መሆኑን ገልጾ፣ እንቅስቃሴያቸውና ኃላፊነታቸው የተለያየ ስለነበር ቅጣቱም ሊለያይ መቻሉን ጠቁሟል፡፡
በ22 ዓመታት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ የተወሰነባቸው የመጀመሪያዎቹ አራቱ ፍርደኞች፣ ከ30 እስከ 40 ዓመታት ጊዜ ውስጥ እስላማዊ መንግሥት የመመሥረት ዓላማ ይዘው መንቀሳቀሳቸውን ፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡ ከ2001 ዓ.ም. ጀምሮ ባደረጉት ሕገወጥ እንቅስቃሴ መንግሥት ሙስሊሙን ኅብረተሰብ ለመነጣጠልና የሙስሊሙን እምነት ሰለፊያና ወሃቢያን በኃይል ለመተካት ሌላ አስተምህሮ መጀመሩን በመግለጽ፣ የሽብር ተልዕኮ ሲያራምዱና በመሪነት ሲንቀሳቀሱ እንደነበር ፍርድ ቤቱ አክሏል፡፡ በደምና በአጥንት የተቀረፀውን ሕገ መንግሥትና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት በኃይል ለማስወገድና ሰለፊያና ወሃቢያ ግቡን እንዲመታ ሁሉም ሙስሊም መታገል እንዳለበት፣ ለሃይማኖቱ ታግሎ ቢሞት ጀነት (ገነት) እንደሚገባ በመግለጽ ከፍተኛ ቅስቀሳ ሲያደርጉ እንደነበር ፍርድ ቤቱ በቅጣት ውሳኔው አስታውቋል፡፡
መንግሥት ከመጅሊሱ 60 ሚሊዮን ብር በመቀበል ሙስሊሙ ኅብረተሰብን ለመነጣጠል እየሠራ በመሆኑ፣ ሙስሊሙ ኅብረተሰብ የሰለፊያና የወሃቢያን አስተምህሮ መከተል እንዳለበት፣ ያ የማይሆን ከሆነ ግን የአህባሽን አስተምህሮ መቀበል እንደማይቻል በአደባባይ በመናገር፣ ሰላምና ልማት የነገሠበትን አገር የብጥብጥና የረብሻ አውድማ ለማድረግ ይንቀሳቀሱ እንደነበር ዓቃቤ ሕግ ከመሠረተው ክስና ካቀረባቸው የሰውና የሰነድ ማስረጃዎች ፍርድ ቤቱ መገንዘቡን አስረድቷል፡፡
ፍርደኞቹ የተላለፉት የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ (4)ን መሆኑን የጠቆመው ፍርድ ቤቱ፣ አንቀጹ ከ15 ዓመታት ጽኑ እስራት እስከ ሞት እንደሚያስቀጣ ጠቁሞ በአራቱም ፍርደኞች የተፈጸመውና ሊፈጸም የታሰበው በመላ አገሪቷ ሞት እንዲነግሥ የሚያደርስ የነበረ ቢሆንም፣ በሕዝብና በመንግሥት ርብርብ መታደግ መቻሉን አስረድቷል፡፡
በወንጀል ሕግ አንቀጽ 117 መሠረት የሞት ቅጣት የሚወሰነው ወንጀሉ ፍጻሜ ያገኘ ሆኖ፣ እጅግ ከባድ በመሆኑና ወንጀለኛውም በተለየ ሁኔታ አደገኛ ሆኖ ሲገኝ የሚል በመሆኑ ፍርድ ቤቱ ሞት የሚለውን ቅጣት ወደ ጎን በመተው ጽኑ እስራት የሚለውን መውሰዱን ገልጿል፡፡ የወንጀል ደረጃውን ከፍተኛ በማለት የቅጣት ውሳኔውን መወሰኑንም አብራርቷል፡፡ የወንጀል ደረጃው ከባድ የተባለውም ፍርድኞቹ ጥፋተኛ ከተባሉ በኋላ ዓቃቤ ሕግ የቅጣት ማክበጃ ያቀረበ ቢሆንም፣ ፍርደኞቹ ግን የቅጣት ማቅለያ ሐሳብ ሳያቀርቡ መቅረታቸውን አስረድቷል፡፡ ፍርደኞቹ የቅጣት ማቅለያ የሚሰጡት የዓቃቤ ሕግን የማክበጃ አስተያየት ካዩ በኋላ መሆኑን በመናገራቸው፣ የቅጣት ማክበጃው እንዲደርሳቸው ተደርጎ እንደነበርም አክሏል፡፡ ያም ሆኖ የተሰጣቸው የማቅረቢያ ጊዜ አሥር ቀናት ቢሆንም፣ ተጨማሪ ጊዜም ተሰጥቷቸው ሳያቀርቡ መቅረታቸውን አስረድቷል፡፡ ፍርደኞቹ እንቅስቃሴያቸው የማኅበረሰቡን ሕይወት ለከፍተኛ አደጋ የሚያጋልጥ፣ ተቻችሎ የመኖር እሴታቸውን የሚያሳጣና ለጦርነት የሚያነሳሳ እንደነበር ፍርድ ቤቱ ገልጾ፣ ድርጊቱ በአንድነትና በትብብር የተፈጸመ መሆኑን በመግለጽ ከላይ የተጠቀሰውን ጽኑ እስራት መወሰኑን ተናግሯል፡፡
ሌሎቹም ፍርደኞች በጋራ በመሆንና በአንድነት በመንቀሳቀስ፣ የሞት አዋጅ በማውጣትና በመቀስቀስ፣ በሕጋዊ መንገድ የተመረጠን መጅሊስ ሕገወጥ በማድረግና ሙጅሊሱን የሚከተል ሙስሊም ላይ ዕርምጃ እንደሚወስዱ በማስፈራራት፣ የሽብር ድርጊቱን ጫፍ ለማድረስ ያደረጉት እንቅስቃሴ አደገኛነቱ ሲመዘን ከፍተኛ መሆኑን ገልጿል፡፡ በመሆኑም በየደረጃቸው በመከፋፈል የጽኑ እስራቱን ቅጣት መወሰኑን አመልክቷል፡፡ ፍርደኞቹ የእስር ጊዜያቸውን ጨርሰው ሲፈቱ በወንጀል ሕግ 123 (ሀ)፣ 124 (1) እና 125 መሠረት ለአምስት ዓመታት ከመምረጥና መመረጥ፣ ለሕዝብ አገልግሎት ሥራ ከመመረጥ መብታቸው መታገዳቸውንም ፍርድ ቤቱ አስታውቋል፡፡
የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ጥቅምት 15 ቀን 2005 ዓ.ም. ክስ የመሠረተባቸው ተከሳሾች 31 ነበሩ፡፡ ጉዳያቸው በክርክር ላይ እያለ የቀድሞው የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስትር አቶ ጁነዲን ሳዶ ባለቤት ወ/ሮ ሐቢባ መሐመድ፣ ሼክ አብዱራህማን ኡስማን፣ ዶ/ር ከማል ሀጂ ገለቱ ማሜ፣ አልቢር ዴቨሎፕመንትና ኮኦፕሬሽን አሶሴሽን፣ ነማእ የበጎ አድራጎት ማኅበር፣ ሼክ ሐጂ ኢብራሂም ቱሂፋ፣ ዓሊ መኪ፣ ሐሰን አቢ ሰዒድ፣ ሼክ ጣሒር አብዱልቃድር አብዱልሀፊዝ፣ ሼክ ጀማል ያሲን፣ ሼክ ሡልጣን ሐጂ አማንና ሐሰን ዓሊ ክሳቸው ተቋርጦ ተለቀዋል፡፡
ሁሉም ተከሳሾች ተጠርጥረው የታሰሩት “የሙስሊሙ ማኅበረሰብ መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ ነን” በማለት በአወሊያ ኮሌጅ በመሰባሰብና ተማሪዎች ካነሱት ጥያቄ ጋር በማያያዝ፣ የሽብር ዓላማቸውን ለማስፈጸም በቤኒን፣ በአንዋር መስጊድና በሌሎችም መስጊዶች ብጥብጥ በማንሳት፣ ፖለቲካዊና ሃይማኖታዊ ዓላማቸውን ለማራመድ የተማሪዎችን ጥያቄ ለሚመለከተው አካል እናቀርባለን በማለት፣ ኅብረተሰቡን ለማስፈራራት፣ የአገሪቱን ፖለቲካዊና ሕገ መንግሥታዊ ተቋማትን ለማናጋት፣ የጅሃድና የአመፅ ጥሪ ለማድረግ አነሳስተዋል በሚል መሆኑ ይታወሳል፡፡
ፍርደኞቹ የተከሰሱባቸውን የወንጀል ድርጊቶች አለመፈጸማቸውን በመካድ ተከራክረዋል፡፡ በእስልምና የተለያዩ አስተምህሮዎችን መከተል የተለመደና ጤናማ አካሄድ ቢሆንም፣ መንግሥት የተወሰኑትን አስተምህሮዎች ሕጋዊ በማድረግ፣ ድጋፍ በመስጠት፣ በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ በመግባትና ሕገ መንግሥታዊ ዋስትና ያለውን የሃይማኖትና የመንግሥት መለያየት መርህ ተፃሯል በሚል መቃወማቸውም ይታወሳል፡፡ መንግሥት ከሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ጋር የማይስማማ አስተምህሮ በኢትዮጵያ ሊኖር እንደማይችል መከራከሩም ይታወሳል፡፡ በመንግሥት ግምገማ በተለይ ወሃቢ ከአስተምህሮ በላይ የወንጀል ድርጊትን የሚያስፋፋ ብሎም የሽብር ድርጊት የሚጋብዝ ነው ተብሎ መፈረጁም አይዘነጋም፡፡