Thursday, March 23, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል በተለያዩ ንብረቶች ላይ ውድመት አደረሰ

ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል በተለያዩ ንብረቶች ላይ ውድመት አደረሰ

ቀን:

–  ንብረት የወደመባቸው በ24 ሰዓታት ውስጥ ማስመዝገብ አለባቸው

በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ክፍላተ ከተሞችና በተለያዩ ወረዳዎች ያሉ ነዋሪዎች፣ በመኖሪያ ቤታቸውና በሚሠሩበት አነስተኛ ድርጅቶች ላይ ድንገት የተለቀቀ የኤሌክትሪክ ኃይል ንብረታቸው እንዳቃጠለባቸው ለሪፖርተር ገለጹ፡፡

ነዋሪዎቹ እንደገለጹት፣ በተለይ በኮልፌ ቀራኒዮ አካባቢ በድንገት የተለቀቀው የኤሌክትሪክ ኃይል ከ24 ሰዓታት በላይ በመቆየቱ ያለመብራት ለመቆየት ተገደዋል፡፡ በሥራ ላይ እያሉ በድንገት ይቋረጥና ወዲያው የሚመጣው ኃይል እጅግ ከፍተኛ በመሆኑ በሥራ ላይ ያሉ ኮምፒዩተሮች፣ ቴሌቪዥኖች፣ የሞባይል ቻርጀሮች፣ አምፖሎች፣ የተለያዩ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎችና አነስተኛ ማሽኖች መቃጠላቸውን የሚናገሩት ተጎጂዎቹ፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልም ሆነ የአገልግሎት ድርጅት ኃላፊነቱን ሊወስዱ ይገባል ብለዋል፡፡

የደረሰባቸውን ችግር አስረድተው አፋጣኝ መፍትሔ ለማግኘት ወደ ዲስትሪክት መሥሪያ ቤቶች ሲሄዱ፣ ተገቢ መስተንግዶ ካለማግኘታቸውም በተጨማሪ፣ ሊያናግራቸው የሚፈልግ እንደሌለም ገልጸዋል፡፡ መሥሪያ ቤቱ በውጭ ድርጅቶች ታግዞ የተሻለ የኃይል አቅርቦትና አገልግሎት ይሰጣል የሚል እምነት እንደነበራቸው የሚናገሩት ተጎጂዎቹ የኃይል መቆራረጥ፣ ድንገተኛ የኃይል መለቀቅና ሲያስፈልግም ከሳምንት በላይ ኃይል አጥቶ መቆየት የዘወትር ተግባር መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የኤሌክትሪክ መሥሪያ ቤቶቹ የሆነውን ሁሉ እንደሚያውቁና የደረሰውን ችግር ተመልክተው አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጧቸው የጠየቁት ጉዳት የደረሰባቸው ነዋሪዎች፣ አሁንም ችግሩ በቀላሉ ስለማይፈታ የሚመለከታቸው አካላት ዘላቂ መፍትሔ መስጠት እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡

ድንገት በተለቀቀ የኤሌክትሪክ ኃይል ንብረታቸው እንደወደመ የገለጹትን ነዋሪዎች አስመልክቶ ማብራሪያ እንዲሰጡ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎትና የኤሌክትሪክ ኃይል ኃላፊዎችን ለማነጋገር ሪፖርተር ያደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡ ነገር ግን አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አገልግሎት የሥራ ባልደረባ እንደገለጹት፣ በአጠቃላይ በብሔራዊ የኃይል ማሠራጫ ሥርዓቱ የቮልቴጅ መጨመርና መቀነስ ሊኖር ይችላል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ቮልቴጁ ከፍ ሲል በንብረቶች ላይ ጉዳት ያስከትላል፡፡ በአሁኑ ወቅት በኃይል ማመንጨት በኩል በቂ አቅም ቢኖርም፣ በሁለቱም መሥሪያ ቤቶች ማለትም በህንዱ ፓወር ግሪድ ኮርፖሬሽን ኦፍ ኢንዲያ የሚመራው የአገልግሎቱ ዘርፍም ሆነ፣ በኢንጂነር አዜብ አስናቀ የሚመራው ኤሌክትሪክ ኃይል ሁለቱም በጥራት ላይ ችግር እንዳለባቸው አስረድተዋል፡፡

መሥሪያ ቤቶቹ ኃይል አቅራቢውም ሆነ ኃይሉን ተቀብሎ የሚያሠራጨው፣ ከብሔራዊ የኃይል ማሠራጫ ቋት (National Grid) ተመጣጣኝ ኃይል እንዲሠራጭ የሚያደርግ ሥርዓት ማበጀት እንደሚገባቸውም የመሥሪያ ቤቱ ባልደረባ ገልጸዋል፡፡ ብዙ ዋጋ ስለሚጠይቅ በጥራት ማሻሻል ላይ ብዙ መሥራት እንደሚቀር የገለጹት ሠራተኛው፣ ሁለቱም መሥሪያ ቤቶች ለሚደርሱ ችግሮች ኃላፊነት በመውሰድ አፋጣኝ ምላሽ መስጠትና ዘላቂ መፍትሔ ማምጣት እንዳለባቸው አስረድተዋል፡፡

ሌላው ደንበኞች በሚፈጥሩት የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ ችግር በርካታ ጥፋቶች እንደሚከሰቱ ሠራተኛው ጠቁመው፣ በአንድ ቤት ውስጥ የተደራረበ የኤሌክትሪክ ገመድ በመዘርጋትና ከሙያው ውጪ ያለ ሰው በማሠራት ችግሩን እያባባሱት መሆኑን በመጠቆም፣ ለኤሌክትሪክ አደጋ መድረስ ተጠያቂ መሆን ያለባቸው ደንበኞችም ጭምር መሆናቸውን አክለዋል፡፡ የመሥሪያ ቤቱ ባለሙያዎችም በተለይ ቆጣሪ ሲያስገቡ የመስመር ዝርጋታውን በመመርመርና የመቆጣጠሪያ ማሽን ቆጣሪያቸው ላይ እንዲያስገጥሙ ማስጠንቀቅና ማስገደድ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

ሰሞኑን በተወሰኑ የአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ ወረዳዎች ውስጥ ችግሩ መከሰቱን ያመኑት የመሥሪያ ቤቱ ባልደረባ፣ ችግሩ ያጋጠማቸው ደንበኞች ወዲያው በ905 እና ለሕዝብ በሚነገሩ ስልኮች በመደወል ማስመዝገብ እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡ በ24 ሰዓታት ውስጥ በመሥሪያ ቤቱ ባለሙያዎች እንዲታይላቸው ማድረግ እንዳለባቸውም ተናግረዋል፡፡ ጉዳቱ በባለሙያ ተለክቶና ተመርምሮ እውነት ሆኖ ከተገኘ የጥገናና የካሳ ክፍያ እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡ ጉዳቱ ከባድ ከሆነ ጉዳቱ የደረሰበት አካል ከሦስት ታዋቂ ድርጅቶች የዋጋ ማነፃፀሪያ ፕሮፎርማ በማቅረብ በመሥሪያ ቤቱ የግዢ ዲፓርትመንት ተረጋግጦ የተተኪ ዕቃ ግዢ እንደሚፈጸም ባልደረባው ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...