– ባለቤቱ የተጠረጠሩበትን ከ143 ሚሊዮን ብር በላይ የወንጀል ክስ ተቃወሙ
በመንገድ ግንባታ የሚታወቀው የእስራኤሉ ትድሃር ኤክስካቬሺን ኤንድ ኧርዝ ሙቪንግ ሊሚትድ ኩባንያ ባለቤትና ዋና ሥራ አስኪያጅ ሚስተር ሚናሼ ሌቭ ዮሴፍ ንብረቶችና ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ ክፍያ ታገደ፡፡
የኩባንያው ባለቤት ሚስተር ሚናሼ ሌቭ ዮሴፍ በሙስናና በጉቦ ወንጀል ተጠርጥረው፣ ከሐምሌ 9 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ በቁጥጥር ሥር በመዋል ሐምሌ 23 ቀን 2007 ዓ.ም. በፌዴራል ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ክስ ተመሥርቶባቸዋል፡፡
ክሱን እየመረመረው የሚገኘው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 18ኛ ወንጀል ችሎት፣ የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ባቀረበው ማመልከቻ መሠረት የኩባንያው ባለቤት ንብረት የሆኑና በድርጅቱ ስም ተመዝግበው የሚገኙ 16 የተለያዩ ተሽከርካሪዎች፣ 21 የተለያዩ የግንባታ ማሽነሪዎች፣ ኩባንያው ለሠራው ሥራ የሚከፈል ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ እንዲታገድ ትዕዛዝ አስተላልፏል፡፡
የኩባንያው ባለቤት ለመንግሥት መክፈል የሚገባቸውን ከ52.7 ሚሊዮን ብር በላይ ላለመክፈል፣ ከኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ሦስት ኦዲተሮች ጋር በመመሳጠርና ለእያንዳንዳቸው 500 ሺሕ ብር በድምሩ 1.5 ሚሊዮን ብር ጉቦ በመስጠት ወንጀል መጠርጠራቸውን የተመሠረተባቸው ክስ ያስረዳል፡፡ ኦዲተሮቹ 46,683,008 ብር ተቀናሽ በማድረግ፣ ሚስተር ዮሴፍ 6,114,770 ብር ብቻ እንዲከፍሉ ማድረጋቸው ታውቆ፣ ክስ ተመሥርቶባቸው በሒደት ላይ መሆኑንም ክሱ ይገልጻል፡፡
ትድሃር ኤክስካቬሺን ኤንድ ኧርዝ ሙቪንግ ሊሚትድ በግብር ከፋይነት የሚታወቅ ድርጅት ሆኖ ሳለ፣ ከታኅሳስ 23 ቀን 2002 ዓ.ም. እስከ ታኅሳስ 21 ቀን 2005 ዓ.ም. ድረስ ለሦስት ተከታታይ ዓመታት ካገኘው ገቢ ውስጥ ለመንግሥት መክፈል የሚገባውን ግብር ላለመክፈል ትክክለኛ ገቢውን መደበቁን ክሱ ይጠቁማል፡፡
ድርጅቱ በሦስት ተከታታይ የግብር ዓመታት መክፈል የነበረበት በድምሩ 61,444,033 ብር እንደነበር ክሱ ይገልጻል፡፡ ግብሩን ባለመክፈሉ 13,947,207 ብር ወለድ፣ ግብር አሳንሶ በማሳወቁ የሚጣል መቀጮ 30,722,016 ብር፣ ግብር በማዘግየት መቀጮ 18,318,422 ብር፣ ለባለቤቱ የተከፈለ ክፍያ ግብር፣ ወለድና ቅጣትን ጨምሮ 5,887,185 ብር በድምሩ 130,318,864 ብር አሳውቆ መክፈል ሲገባው፣ ባለመክፈሉና ሕግን በመጣስ ግብርን ባለመክፈል ወንጀል መከሰሱን የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡ ድርጅቱ ሕግን ጥሶ ግብርን ባለመክፈሉ ወካዩ ባለቤቱ ሚስተር ዮሴፍ በመሆናቸው እሳቸውም ሕግን በመጣስ ግብርን ባለመክፈል ወንጀል ተከሰዋል፡፡
ድርጅቱና ባለቤቱ ግብር አሳውቀው መክፈል ሲገባቸው፣ እንዳይከፍሉ የሚያደርግ አሳሳች መረጃ (መግለጫ) በመስጠታቸው በፈጸሙት የሐሰት መረጃ ማቅረብ ወንጀል ተከሰዋል፡፡
ድርጅቱ ለሦስት ተከታታይ ዓመታት ካደረጋቸው የንግድ እንቅስቃሴዎች ከሰበሰበው ገቢ ላይ፣ ለመንግሥት አሳውቆ መክፈል የነበረበትን የተጨማሪ እሴት ታክስ ፍሬ ግብር 2,132,817 ብር አለመክፈሉን፣ የተጨማሪ እሴት ታክስ ፍሬ ግብር ወለድ 4,141,387 ብር፣ መቀጫ 7,497,249 ብር በድምሩ 13,771,455 ብር ለመንግሥት አሳውቆ ባለመክፈሉና ባለቤቱም የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ በመሆናቸው፣ በፈጸሙት ሕግን በመጣስ ታክስ ያለመክፈል ወንጀል መከሰሳቸውን ክሱ ይገልጻል፡፡ በአጠቃላይ የተከሰሱበት ከ143 ሚሊዮን ብር በላይ ነው፡፡
ሚስተር ዮሴፍ የትድሃር ሥራ አስኪያጅ ሆነው ሲሠሩ ከ2002 ዓ.ም. እስከ 2005 ዓ.ም. ድረስ በትድሃር አማካይነት ካገኙት ገቢ ለመንግሥት መክፈል የሚገባቸውን ሳይከፍሉ፣ ከፍተኛ ገንዘብ ደብቀው ማስቀረታቸውን ክሱ ጠቁሟል፡፡
ተከሳሹ የከፍተኛ ገንዘብ ሕገወጥ አመጣጥን ለመሰወርና ሕጋዊ አስመስሎ ለማቅረብ በማሰብ፣ ከሰኔ 10 ቀን 2004 ዓ.ም. እስከ ጥቅምት 8 ቀን 2006 ዓ.ም. ድረስ በተለያዩ 17 ቼኮች በድምሩ 8,681,500 ብር በለጠ ደጀኔ በተባለ ግለሰብና የድርጅቱ ሠራተኛ ባልሆነ ሰው አማካይነት፣ በውጭ ምንዛሪ በጥቁር ገበያ ተቀይሮ እንዲቀርብላቸው በማድረግ መጠቀማቸውን ክሱ ያስረዳል፡፡ በመሆኑም በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ መጠቀም ወንጀል መከሰሳቸውም በክሱ ተገልጿል፡፡
ፍርድ ቤቱ ክሱን ካነበበላቸው በኋላ ተጠርጣሪ ተከሳሾቹ የክስ መቃሚያ አቅርበዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ የክስ መቃወሚያውን መርምሮ ብይን ለመስጠት ለጥቅምት 25 ቀን 2008 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡