– ከእስር የተፈቱት ጦማሪያንና ጋዜጠኞች ድጋሚ ትዕዛዝ ተሰጠላቸው
በሽብርተኝነት ተጠርጥረው ክስ የተመሠረተባቸው ጦማሪያን አጥናፉ ብርሃኔ፣ አቤል ዋበላ፣ ናትናኤል ፈለቀና በፍቃዱ ኃይሉ፣ ዓቃቤ ሕግ ካቀረበባቸው ክስ ነፃ ለመሆን ወይም እንዲከላከሉ ለነሐሴ 13 ቀን 2007 ዓ.ም. ለብይን ተቀጠሩ፡፡
የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ያቀረበውን ክስ እየመረመረው የሚገኘው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት ሐምሌ 22 ቀን 2007 ዓ.ም. በሰጠው ትዕዛዝ፣ በዕለቱ መዝገቡ ቀጥሮ የነበረው የዓቃቤ ሕግ ምስክሮች ቃል ከመዝገቡ ጋር መያያዝ አለመያያዙን ለመጠባበቅ እንደነበር አስታውሷል፡፡ የምስክሮቹ ቃል የተያያዘ መሆኑንም አረጋግጦ፣ ብይኑን ለመሥራት ለነሐሴ 13 ቀን 2007 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
በሌላ በኩል ሐምሌ 1 እና 2 ቀን 2007 ዓ.ም. ክሳቸው ተቋርጦ ከእስር የተፈቱት ጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስ፣ ኤዶም ካሳዬ፣ አስማማው ኃይለ ጊዮርጊስ፣ እንዲሁም ጦማሪያን ማኅሌት ፋንታሁንና ዘለዓለም ክብረት፣ ቀደም ባለው ችሎት ፍርድ ቤቱ በታሰሩበት ወቅት በፍተሻ የተወሰዱባቸው በኤግዚቢትነት የተያዙ ዕቃዎች እንዲመለሱላቸው ትዕዛዝ ቢሰጥም፣ ተግባራዊ አለመሆኑን ማመልከታቸውን ገልጿል፡፡
የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ ይዘው ታስረው ወደነበረበት ፖሊስ ጣቢያ (ማዕከላዊ) በተደጋጋሚ ሄደው የጠየቁ ቢሆንም፣ አንድ ጊዜ ከሳሽ ዓቃቤ ሕግን ጠይቀው እንደሚሰጧቸው፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ኤግዚቢቱን የተቀበለው አካል ስለሌለ ሌላ ጊዜ እንዲመለሱ በመንገር ሊፈጸምላቸው እንዳልቻለ አመልክተዋል፡፡ ፍርድ ቤቱም በድጋሚ በሰጠው ትዕዛዝ ‹‹በኤግዚቢትነት የተያዘው ዕቃ ይመለስላቸው›› ብሏል፡፡