Wednesday, June 7, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በተወዳዳሪነትና በመዋቅራዊ ለውጥ ሲቃኝ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በየሁለት ዓመቱ ብቅ የሚለው የአፍሪካ የተወዳዳሪነት ሪፖርት፣ በዓለም የኢኮኖሚ ፎረም በኩል እየተዘጋጀ የሚወጣ ነው፡፡ በዚህ ዓመት ለንባብ የበቃው ሪፖርት የአፍሪካን ተወዳደሪነትና ፈታኝ ገጽታዎችን ዘክሯል፡፡ የዓለም ባንክ በየዓመቱ ከሚያወጣቸው ሪፖርቶች መካከልም ዘንድሮ ለአራተኛ ጊዜ ይፋ የተደረገውና የአገሪቱን የተወዳዳሪነት፣ የመዋቅራዊ ለውጥና መሰል ጉዳዮች የቃኘው ሪፖርትም ይጠቀሳል፡፡

በአፍሪካ አገሮች ዘንድ እየታየ ያለውን የኢኮኖሚ ዕድገት ከዓለም ንፍቀ ክበብ የሚገዳደሩት የእስያና የላቲን አገሮች ናቸው፡፡ በተቀረው ግን ላለፉት 15 ዓመታት አፍሪካ ሳታቋርጥ የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገቧን ቀጥላለች፡፡ ሁሉም ፈጣን ዕድገት ማስመዝገብ ብቻም ሳይሆን ያደጉ አገሮች በበርካታ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በሚናጡበትና ዓመታዊ የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብ ባልቻሉበት በዚህ ዘመን እንኳ፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ አገሮች የዓለምን ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ይዘውራሉ፡፡

በዓለም የኢኮኖሚ ፎረም ሪፖርት መሠረት ባለፉት 40 ዓመታት የአፍሪካን ኢኮኖሚ ዘርፎች ተቆጣጥሮ የነበረው ግብርናም የበላይነት ይዞታውን እያስረከበ ይገኛል፡፡ እጅ ሰጥቷል፡፡ በአርባ ዓመታት ውስጥ የግብርና ኢኮኖሚያዊ ድርሻ በአማካይ ከ30 ከመቶ ወደ 15 ከመቶ ቀንሷል፡፡ ሆኖም የግብርናው ወደኋላ መሸሽ መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት አላስቻለም፡፡ ኢንዱስትሪና የኢንዱስትሪ ውጤቶችን የሚያመርቱ ፋብሪካዎች በአፍሪካ እንግዳ ናቸው፡፡ ከዚህ ይልቅ የአገልግሎት ዘርፍ ከአራት አሠርት በፊት 35 ከመቶ የነበረው ድርሻ አሁን ላይ 55 ከመቶ ደርሷል፡፡ የግብርናውን የበላይነት የተቆጣጠረው ይኸው ዘርፍ ሆኖ ይገኛል፡፡

በዓለም የኢኮኖሚ ፎረም ዘንድሮ ይፋ የተደረገው ሪፖርት አብዛኛው ይዘቱ ከዚህ ቀደም የዓለም ባንክ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ በየዓመቱ ከሚያወጣቸው የጥናት ውጤቶች ጋር ተመሳሳይነት ያለው ነው፡፡ በአፍሪካ ደረጃ እየታየ ያለው ዕድገት ልክ ኢትዮጵያ ላይ እንደሚሰነዘሩት ዓይነት መዋቅራዊ ለውጥ ከማምጣት ይልቅ፣ የአገልግሎት ዘርፍ ላይ የተመረኮዙ ሆነው ተገኝተዋል፡፡ መዋቅራዊ ለውጥ ማለት በሪፖርቱ ማብራሪያ መሠረት፣ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎችንና ወይም የምርት ኃይሎችን ምርታማነታቸው ዝቅተኛ ከሆኑ ዘርፎች ይበልጥ ምርታማና ውጤታማ ወደሆኑ ኢኮኖሚ ክፍሎች ማሸጋገር መቻል ሲሆን፣ በአፍሪካ ይህንን ለማድረግ የሚያስችል ለውጥ አልመጣም፡፡

ይብሱን ከሰሐራ በታች በሚገኙ አገሮች ውስጥ የኢኮኖሚ ኃይሎች ከሆኑት መካከል የሰው ኃይል ከግማሽ በላይ ተሰማርቶ የሚገኘው በግብርና ሲሆን፣ ከዚህ ዘርፍ እየተሰደደ በብዛት ወደ አገልግሎት ዘርፍ የሚገባው ማለትም ወደ ንግድና ወደ ሌሎች ንዑስ ዘርፎች እየገባ ያለው የሰው ኃይል ቁጥር ወደ አምራች ኢንዱስትሪው ከሚገባው በከፍተኛ መጠን በልጦ ይታያል፡፡ በአፍሪካ እያደገ መሆኑ የሚነገርለት መካከለኛ ገቢ ያለው የሕዝብ ቁጥር የአኅጉሪቱን የኢኮኖሚ ዕድገት ወደ ላይ ከሚመነድጉት ዋናው ምክንያት መሆኑን ከጥቂት ወራት በፊት በተባበሩት መንግሥታት ይፋ የተደረገው የዓለም ኢኮኖሚ ሁኔታ ማሳያ ሪፖርት ይጠቀሳል፡፡ ከዚህም ባሻገር የንግድ እንቅስቃሴ መሻሻሎችና ቢዝነስ ለማካሄድ እንቅፋት የነበሩ እንቅፋቶች መሻሻል የአፍሪካ አማካይ ዕድገት በአምስት ከመቶ እያደገ እንዲቀጥል ለማስቻል አግዘዋል ተብለዋል፡፡

በአፍሪካ በፍጥነት ከሚያድገው ኢኮኖሚ ጎን ለጎን የአኅጉሪቱ የሕዝብ ቁጥር ዕድገትም አብሮ ይነሳል፡፡ ኢኮኖሚያዊ ዕድገቱ ለሕዝቡ ኑሮ መሻሻል የሚያበረክተው አቻዊ አስተዋጽኦ ጥያቄ አጭሯል፡፡ ሪፖርቱም ይህንን መከራከሪያ ያቀርባል፡፡ የዓለም ባንክ በበኩሉ በቅርቡ ይፋ ያደረገውና ኢትዮጵያ ላይ ብቻ ያተኮረው ዓመታዊ ሪፖርት እንደሚያትተው ኢትዮጵያ ከግብርና ዘርፍ ይልቅ በአምራች ኢንዱስትሪ የሚመራ፣ ኢንዱስትሪ ተኮር ኢኮኖሚ ለመገንባት የምታደርገውን እንቅስቃሴና የመንግሥትን የአምስት ዓመት የልማት ዕቅድ ቃኝቷል፡፡

በዚህ መሠረት ቅኝቱ እንደሚያመለክተው አገሪቱ አሁንም በግብርና ዘርፍ የበላይነትም የምትመራ መሆኗን ሲሆን፣ ሦስት አራተኛውን የሰው ኃይል የሚቀጥረውም ይኼው የግብርናው መስክ ነው፡፡ በመሆኑም የአገሪቱ መዋቅራዊ ለውጥ ደካማ ከመሆን በላይ ገና ምልክቱ እየታየ የሚገኝበት ምዕራፍ ላይ ይገኛል፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያ ወደ ኢንዱስትሪው ዘርፍ የሰው ኃይል ለማጉረፍ ያልተሳካላት አገር ተብላ ተፈርጃለች፡፡ ግብርና 78 ከመቶ የሚሆነውን ሕዝብ አሰማርቶ እንደሚገኝ የዓለም ባንክ ይፋ አድርጓል፡፡ ማዕድን ዘርፍ 0.5 ከመቶ፣ አምራች ኢንዱስትሪ አስምት ከመቶ፣ ኮንስትራክሽን ሁለት ከመቶ፣ ንግድ ሰባት ከመቶ፣ ትራንስፖርት 0.9 ከመቶ፣ ፋይናንስ 0.3 ከመቶ፣ የሕዝብ አገልግሎት ሦስት ከመቶ እያለ በንዑስ ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ውስጥ የተሰማራውን የሰው ኃይል ቁጥር ባንኩ አስፍሯል፡፡

የኮንስትራክሽን ዘርፉ በፍጥነትና በከፍተኛ መጠን በማደግ ትልቁን ድርሻ ቢይዝም በሰው ኃይል ረገድ የያዘው ድርሻ ያን ያህል ሆኖ ይታያል፡፡ በአንፃሩ መንግሥት በጥቃቅንና አነስተኛ ድርጅቶች አማካይነት ሚሊዮኖች የሥራ ዕድል እንዲያገኙ እያደረገ እንደሚገኝ፣ የራሳቸውን ገቢ ከመፈጠር ባሻገር መካከለኛ ኢንዱስትሪዎችን እንዲፈጥሩ ጭምር እየረዳ እንደሆነም ደጋግሞ ሲገለጽ ይደመጣል፡፡ የዓለም ባንክ በበኩሉ መንግሥት በጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፍም ሆነ በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ አሠልጥኖ ለአምራች ኢንዱስትሪው ግብዓት እንዲሆኑ የሚያወጣቸው ዜጎች አብዛኞቹ የሥራ ዕድል እያገኙ አለመሆኑን በሪፖርቱ ማቅረቡም አይዘነጋም፡፡

የምርታማነት ውጤት ከሚወስኑ ተግባር መካከል አንዱ የሆነው ውጤታማ የሰለጠ የሰው ኃይል ሲሆን፣ ኢትዮጵያ በተለይ በአዲስ አበባ ከሚገኙ ተቋሞቿ ውስጥ ከሌሎች አቻ አገሮች ጋር ተነጻጽራ የተገኘው ውጤት የተሻለ ከሆነባቸው መስኮች መካከል አንዱ ለጉልበት የሚከፈል ዝቅተኛ ወጪ ነው፡፡ በዚህ መሠረት እንደ ዛምቢያና ቬትናም ከመሳሰሉ አገሮች ጋር ሲነጻጸር ኢትዮጵያ ውስጥ የሚሠራ አንድ ድርጅት ከአንድ ሠራተኛ በአማካይ 4900 ዶላር ግምት ያላቸውን ምርቶችን ያመርታል፡፡ በአንጻሩ ከቻይናና ከደቡብ አፍሪካ ጋር ስንነጻጸር ግን ኢትዮጵያ ያላት የሰው ኃይል ምርታማነት ዝቅተኛውን ደረጃ ይዞ ይገኛል፡፡ ለምሳሌ አንድ የእንጨት ወንበር ኢትዮጵያ ውስጥ ለማምረት 2592 ዶላር ያስወጣል፡፡ በአንጻሩ በቻይና 100 ዶላር፣ በቬትናም 888 ዶላር እንዲሁም በታንዛንያ 1884 ዶላር ያስወጣል፡፡ በአንጻሩ ፖሎ ቲሸርቶችን ለማምረት በኢትዮጵያ 50 ዶላር ሲያስወጣ፣ በቻይና 100፣ በቬትናም 101፣ በታንዛንያ 102 ዶላር ወጪ ያስከትላል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የቆዳ ውጤቶችን ለማምረት በኢትዮጵያ የሚጠይቀው የሠራተኛ ወጪም ከሌሎቹ አገሮች አኳያ ሲነጻጸር ዝቅተኛ ሆኖ ይታያል፡፡ በኢትዮጵያ 15 ዶላር የሚጠይቀው የቆዳ ውጤቶች መስክ በቻይና 100 ዶላር፣ በቬትናም 29 ዶላር እንዲሁም በታንዛንያ 37 ዶላር ይጠይቃል፡፡ 

ይህም ሆኖ በአገሪቱ የሚታየው የምርታማነትና የክህሎት ችግር የአገሪቱን አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ የሚፈታተን ክስተት እንደሆነ የዓለም ባንክ አካቷል፡፡ ከዚህም ባሻገር ድርጅቶችና የቴክኒክና ሙያ ተቋማት የቴክኒክ ዕውቀት ያላቸውን ሙያተኞች ለመቅጠር የሚያስችል ተግባቦት የሌላቸው መሆኑን ያመለከተው ባንኩ፣ ጥናት ካደረገባቸው 60 ድርጅቶች ውስጥ 14 ብቻ ከቴክኒክና ሙያ ተቋማት ጋር ግንኙነት እንዳላቸው አስታውቀዋል፡፡ በመሆኑም ከቴክኒክና ሙያ ተመርቀው ከሚወጡት ውስጥ ሥራ ማግኘት ያልቻሉትን በሚመለከት በዝርዝር አስቀምጧል፡፡  ለአብነትም ከስፌት ማሰልጠኛዎች ከሚመረቁት ውስጥ 36 ከመቶው ሥራ የማያገኙ ናቸው፡፡ በኤሌክትሪክ ሥራዎች ከሚመረቁት 36፣ በኮምፒውተር አፕሊኬሽንሽና በአጠቃቀም 42 ከመቶ፣ በብረታ ብረት ቴክኖሎጂ 43 ከመቶ፣ በግምበኝነት 49 ከመቶ፣ በእንጨት ሥራ ወይም በአናጢነት 53 ከመቶ፣ በሽመና 54 ከመቶ፣ በጨርቃ ጨርቅ ምህንድስና 60 ከመቶ እንዲሁም በቧንቧ ሥራ 71 ከመቶ ሥራ የማያገኙ ነግር ግን ከቴክኒክና ሙያ ተመርቀው የሚወጡ መሆናቸውን የዓለም ባንክ ይፋ አድርጓል፡፡

በጠቅላላው በአገሪቱም ሆነ በአፍሪካ የሚታየው ከፍተኛ ኢኮኖሚ ዕድገት ተወዳዳሪነት ለማምጣት ብዙ ከሚቀረው መሆኑን ሁለቱም ሪፖርቶች ሲጠቁሙ፣ በአብዛኛው በግብርና ሸቀጦች ላይ የተመሠረተው የወጪ  ንግዳቸው፣ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው አምራች ኢንዱስትሪያቸው፣ በሰለጠነ የሰው ኃይል አለመኖርና በክህሎት ችግሮቻቸው ሳቢያ አፍሪካውያኑ የሚያስመዘግቡት ኢኮኖሚያዊ ዕድገት መሠረታዊ ለውጥ በማምታት ሕዝቦቻቸውን ተጠቃሚ ከማድረግና የኑሮ መሻሻሎችን ከማስዝገብ አኳያ የሚኖራቸው ሚና ጥያቄ ውስጥ ይገኛል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች