Monday, April 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየኦሕዴድ አባላት የተቃውሞ ድምፅ የሰጡበት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ፀደቀ

የኦሕዴድ አባላት የተቃውሞ ድምፅ የሰጡበት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ፀደቀ

ቀን:

  • የኦሕዴድ ሊቀመንበር በስብሰባው አልተገኙም

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ዓርብ የካቲት 23 ቀን 2010 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ395 የድጋፍ ድምፅ ሲፀድቅ፣ 88 የኦሕዴድ አባላት የተቃውሞ ድምፅ ሰ፡፡ በድምፅ አሰጣጡ ወቅት ሰባት ድምፀ ተዓቅቦ ነበር፡፡

ፓርላማው ከየካቲት 2 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ለአንድ ወር ዕረፍት ከተበተነ በኋላ፣ የካቲት 9 ቀን 2010 ዓ.ም. በሚኒስትሮች ምክር ቤት የፀደቀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲያፀድቅ ነበር የተጠራው፡፡

በዚህ ስብሰባ 490 የምክር ቤቱ አባላት የተገኙ ሲሆን፣ የኮማንድ ፖስቱ ሰብሳቢና የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አልተገኙም ነበር፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የብአዴን ሊቀመንበርና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ በቅርቡ የተሾሙት የደኢሕዴን ሊቀመንበር አቶ ሽፈራው ሽጉጤ፣ የሕወሓት ሊቀመንበርና የትግራይ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) ሲገኙ፣ የኦሕዴድ ሊቀመንበር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ግን የፓርላማ አባል ቢሆኑም አልተገኙም፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አስፈላጊነት በተመለከተ ከፓርላማው አባላት ለቀረቡ ጥያቄዎች ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ አቶ ጌታቸው አምባዬ ምላሽ ሲሰጡ፣ በአገሪቱ መንግሥትና ሕግ የሌለ የሚያስመስል ሁኔታ መፈጠሩን አስረድተዋል፡፡

ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ እየተጣሰ ብሔርን መሠረት ባደረገ ጥቃት ምክንያት በሰላም ወጥቶ መግባት አስቸጋሪ እየሆነ መምጣቱን፣ በመደበኛው የሕግ ማስከበር ሥርዓት ሁኔታዎችን ለማስተካከል አዳጋች በመሆኑ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መታወጁን ገልጸዋል፡፡

ከማብራሪያው በመቀጠል በአዋጅ ድንጋጌዎች ላይ አስተያየቶች እንዲቀርቡ አፈ ጉባዔ አባዱላ ገመዳ ዕድል የሰጡ ሲሆን፣ አብዛኛዎቹን አስተያየቶች የሰጡት የኦሕዴድ አባላት ነበሩ፡፡

የዞን አስተዳዳሪዎች በኮማንድ ፖስቱ አደረጃጀት ውስጥ አለመካተታቸውን፣ እንዲያውም በኦሮሚያ ክልል የምሥራቅ ወለጋ ዞን አስተዳዳሪ በኮማንድ ፖስቱ መታሰራቸው አግባብነት የለውም ሲሉ ተቃውመዋል፡፡ በድብቅ ቅስቀሳ ማድረግ የሚለው ሐረግ በማስረጃ ማረጋገጥ የማይቻል በመሆኑ መውጣት ይገባዋል ብለዋል፡፡ ሕገ መንግሥቱ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚታወጀው እስከ ስድስት ወራት የሚል በመሆኑ ጊዜው ወደ ሦስት ወራት ዝቅ እንዲደረግ፣ እንዲሁም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስቱ በአዋጅ የተሰጠው ከመጠን ያለፈ ኃይል ነው፣ በመሬት ጉዳይ ላይ ለምን ይሳተፋል? ይኼ የአስተዳደር ጉዳይ ነው በማለት ማሻሻያ ጠይቀዋል፡፡

ለቀረቡት ጥያቄዎች ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ኮማንድ ፖስት በጀት የሚወጣው ከፌዴራል መንግሥት እንደሆነ፣ የወረዳ አመራሮችን በኮማንድ ፖስቱ ማሳተፍ መደበኛ የአስተዳደር ሥራን የሚጎዳ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ኮማንድ ፖስቱ በመሬት ጉዳይ ላይ እንዲገባ የተገደደው ሕገወጥ የመሬት ወረራ በስፋት በመስተዋሉ ነው ብለዋል፡፡ ከስድስት ወራት ዝቅ ሊል ይገባል የሚለውንም አቶ ጌታቸው አልተቀበሉትም፡፡

አቶ ጌታቸው ማብራሪያ ከሰጡ በኋላ አፈ ጉባዔ አባዱላ፣ ‹‹አዋጁን በተባበረ ድምፅ እናፅድቀው?›› በማለት ሲጠይቁ በጩኸት ተቃውሞ ስለገጠማቸው ወደ ድምፅ አሰጣጥ ተገብቷል፡፡

የድምፅ አሰጣጡን ውጤት 346 ድጋፍ፣ 88 ተቃውሞና ሰባት ድምፀ ተዓቅቦ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ከምክር ቤቱ አባላት ሁለት ሦስተኛ የሚሆነው ድምፅ ከ339 በላይ በመሆኑ፣ የተሰጠው የድጋፍ ድምፅ ከሁለት ሦስተኛ በላይ ስለሆነ መፅደቁን አስታውቀዋል፡፡ በመቀጠልም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ ተሰይሞ ምክር ቤቱ ስብሰባ ተጠናቆ አባላቱ ወደ ዕረፍታቸው ተመልሰዋል፡፡

ይህ ከሆነ በኋላ ግን የፓርላማው ጽሕፈት ቤት ኮሙዩኒኬሽን ተጠባባቂ ዳይሬክተር አቶ ያዕቆብ ወልደ ሰማያት ለሪፖርተርና ለሌሎችም ሚዲያዎች እንደገለጹት የምክር ቤቱ ቆጠራ የተሳሳተ ነበር፡፡ በመሆኑም አዋጁ በ395 ድጋፍ፣ በ88 ተቃውሞና በሰባት ተዓቅቦ እንደፀደቀ በማስታወቅ ማስተካከያ እንዲደረግበት አሳስበዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...