Thursday, April 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

በአረጀ ሶፍትዌር አትጨቃጨቁን!

ሰላም! ሰላም! “በዚህ ጊዜ ባወጡት ዕቅድ ሲመሩ የምናየው መሪዎችን ብቻ ሆኗል፤” ይለኛል አንዱ ተሰብስበን በቆምንበት። ያው በየሄድንበት መቆም አይደል ሥራችን? ለነገሩ የዛሬው አቋቋማችን ለየት ያለ ነው። ‘አቋቋምሽማ’ን ጋብዙኝማ አደራ! እና አለ አይደል ቄጤማ በአቅሙ ተወዶብን በገላጣ ወለል፣ ለነፈሰበት የቡና ‘ሴሬሞኒ’ እየተሰበሰብን (ከአንድ ሲኒ በላይ መጠጣት የፈለገ የቡና ዱቄት ይዞ ይምጣ በቅርቡ መባላችን አይቀርም የሚል ፍርኃት አለኝ) እንግዳ ግን ሳሩም ሸሩም ሳይጎልበት መሸኘት አለብን። በስውር፣ ‘ገመናችንንማ አናሳይም’ የምንላት ትንቅንቅ እንዳትዘለል። ለነገሩ ነገር መዝለል ብሎ ነገር አናውቅም። “ስፖርቱስ ላይ መቼ እናውቅና?” እንዳትሉኝ ብቻ? ግድ የለም በቅርቡ ኦባማ ተጣጣፊ ምርኩዝ ይልኩልንና እንደ ሩጫው በምርኩዝ ዝላይ ባንዲራችን ይውለበለባል። አይዟችሁ ብቻ። ዋናው ቡና መጠራራታችን መቀጠል ነው። ቡና አምጡ ባንላቸውም ስኳሩን እንዲቸገሩበት እያሳሰብን ነው ታዲያ። ያለዚያማ በተወደደ ስኳር በአሜሪካውያን የቡና ሱስ እንዴት እንችላለን? በነገራችን ላይ ‘አገራችን ከዘራ ጠፍቶ፣ ሸንበቆ ሳይቸግረን፣ እንዴት ካሜሪካ በመጣ ከዘራ ባንዲራችን ይውለበለባል?’ የሚል ከገጠማችሁ ድምፅን በድምፅ የመሻር ልማታዊ መብታችሁን ተጠቅማችሁ ‘ፀረ ልማት’ ወይም ‘ፀረ ዲፕሎማሲ’ ብላችሁ አፉን ማዘጋት አለባችሁ። አዎ! አንዳንዴማ አፍ ማዘጋት እንልመድ እንጂ። ሲም ካርድ ይመስል ደስ ያለው ሲዘጋን ደስ ያለው ሲከፍተንማ እስከ መቼ? ‘አም አይ ራይት?’

“እንደ እኔማ ቢሆን እንዳስተሳሰቤ . . .”  ግጣም በማጣት እንጂ ስንኝ በመጨረስ ስለማንታማ እንድትጨርሱት ትቼላችሁ ማልጄ ወጥቼ የሚሸጥ ‘ሲኖትራክ’ አደራድሬ ያስማማኋቸውን ደንበኞቼን ጉዳይ ከሰዓት በኋላ ለመቋጨጥ ሳስብ የገጠመኝን ላጫውታችሁን። አጉል ወጪ ቆጣቢ ልሁን ስል ቤት ገባሁና ማንጠግቦሽ ክሽን አድርጋ የሠራችውን ወጥ በሠርገኛ ጤፍ እንጀራ ሰልቅጬ፣ ሁለት ስኒ ቡናዬን ልፌ ለመመለስ ነበር አገባቤ። በነገራችን ላይ ለወትሮው የሥራው ባህሪ ሆነና ምሳ ሰዓት ሲደርስ ‘የተገኘው ሬስቶራንት’ ገብቼ ነበር የምመገበው። አሁን አሁን ግን ሁለት ስህተት እንደ ድር ደጋግሜ ሳደራ መኖሬ ገባኝ። አንደኛው ‘የተገኘ’ የሚባል (እኔ እንደማስበው ዓይነት ምስኪንና ለትርፍ ያልቆመ ምግብ ቤት ማለቴ ነው) እንደሌለ የምሳ ወጪዬ የሳምንት አስቤዛዬን ሲያስከነዳው ሳይ የተረዳሁት ነው። ሁለት እስከ ዛሬ በየካፌና በየሬስቶራንቱ ለምግብና ለመጠጥ ያወጣሁት ወጪ ቆጥቤው ቢሆን የደርሶ መልስ የአውሮፕላን ትኬቴን ሸፍኖልኝ አሜሪካ ደርሼ እመለስ ነበር። ማን ነው ‹መምጣቱንስ ተመልሰህ አትመጣም› ሲለኝ የሰማሁት? ኧረ ልኑርበት እባካችሁ!

 እና በስህተቴ በጣም አፈርኩ። አይበለውና ኦባማ መኪናቸው ተበላሽቶ (ታክሲ መሰለህ መኪናቸው ያለኝ ማን ነበር?) ወይ አገሬ ታድላው በነበረው ኃያላን አገሮች በሚለቁት የተበከለ አየር ምክንያት ተረት ለመሆን የተቃረበውን የ13 ወራት ፀጋ ለመገምገም ወክ ሲያደርጉ መንገድ ብንገናኝ፣ ስለአገራቸው በዓይኔ አይቼ የምመሰክረው ምንም የለኝም። ኃፍረቴ ባሰ። ጨነቀኝ። ከላሊበላ ወይ ከአክሱም የመጣ ለማኝ ባይ ግን ላሊበላና አክሱምን አለማየቴ አሜሪካንን ያለማየቴን ያህል እንደማያስደነግጠኝ ውልብ ቢለኝ፣ ከወቀሳ ለመሸሽ ‘ያን የሚያህል ድንጋይ እግር አውጥቶ አይሄድ ቀስ ብሎ ይደርሳል’ እያልኩ ራሴን አረጋጋ ጀመር። ‘ራሴን በራሴ ካላረጋጋሁ ማን ያረጋጋልኛል?’ በማለቷ አይደል እንዴ ኢትዮጵያችን የተጎበኘችው? እና ታዲያ!

እናማ ቡናዬን ጠጥቼ ትንሽ ጋደም ብዬ ዕረፍት ወሰድኩና ደንበኞቼ የሚጨራረሰውን ጨራርሰው ‘ኮሚሽኔ’ ሳያድር ቢሰጡኝ በማለት ተስፋ አድርጌ እየሮጥኩ ስወጣ፣ ወደ ዋናው አውራ ጎዳና ገባር የሆነው ሰፊው የሠፈራችን ኮብልስቶን መንገድ የእጅ ፍሬን ይዘው በተጠንቀቅ በቆሙ የመንደሬ ነዋሪዎች ተዘጋግቷል። ጠጋ ብዬ ተናግሬ ላናግር፣ “መንግሥት ዳገቱ ላይ ማረፍ ብሎ ነገር የለም’ እያለ እናንተ ያውም ሜዳ ላይ ሞተር ነከሰባችሁ?” ማለት። ይኼን ብዬ ዘወር ስል በተክለ ሰውነት ሦስት ጊዜ የሚደርበኝ መለሎ ወታደር አጠገቤ ቆሟል። ከኋላዬ እንደ እኔ ምኑም ያልገባው ቀልቃላ፣ “አልሸባብ ፈርጥጦ እኛ ሠፈር መሸገ እንዴ?” ብሎ እሱም የእጅ ፍሬኑን መያዝ። “ኧረ እባክህ ዝም በል አንተ ሰውዬ! እንኳን ለክፉ ቀን መደበቂያችን፣ ለስንቱ ጧሪ ቀባሪ ሠርቶ መኖሪያ መለወጫ ለሆነችው ውዷ አሜሪካችን መሪ ቀርቶ ‘ህልሜን ጨርሱልኝ’ ብሎን ለሚሄደው ሳይቀር በተጠንቀቅ ቆመን አልተቀበልንም እንዴ?” ብሎ አንዱ እገታው የጨዋ እንግዳ ተቃባይነት ባህላችን አንዱ ምዕራፍ መሆኑን ጠቆመን።

ይኼን ጊዜ ነው ታዲያ ያ ያልኳችሁ ሰው ስለዕቅድ ያነሳው። እኔም መቆሜ ካልቀረ አቋቋሜን ላሳምር ብዬ፣ “አቅደው ተነስተው አቅደው ሲያርፉ የምናየው መሪዎችን ብቻ ሆነ እኮ ስትል?” ስለው፣ “እህ እኛማ መድረሻችን አይታወቅ፣ መነሻችን አይታወቅ። እዚያ እናርፋለን ስንል እዚህ ስንቆም፣ ዛሬ ያልቃል ያልከው ጉዳይ ወር ሲያጉላላህ፣ ለዓመት ያልከው ሱሪ በሳምንቱ ታጥቦ ሲቀደድ፣ ለዕለት ያልከው ጉርስ ቁርስ ላይ አመድ ሲሆን ምን ያቀድነው ይሳካልናል እኛማ?” አለኝ። ብዙ ልሰማው ፈልጌ ነበር። ወዲያው ግን ኦባማ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ መድረሳቸውን አንዱ በሬዲዮ የቀጥታ ሥርጭት እየተከታተለ ኖሮ፣ “ገቡ! ገቡ!” ብሎ ማጨብጨብ ጀመረ። ጀማው ተከተለው። ወይ ጀማው! ገቡ! ገቡ! ሲባል ማጨብጨቡ የሚገርመው፣ አላምጦና አድቅቆ ሳይረዳ በአንጀኛው ንግግር አኩርፎ በሌላኛው ንግግር መፈንደቁ ነው የሚል ትችት ሰማን ልበል? ምን የማይሰማ አለ?

ፈዝዤ አይኔ ሲቅበዘበዝ ያ ከእኔ ዘግይቶ የመጣው አፉ የማያርፍ ሰው፣ “እስኪ እኛም እናጨብጭብ። መቼም ከዚህ በኋላ አጨብጭበህ እንጂ ‘አሳይለም’ ጠይቀህ አሜሪካ ‘ቪዛ’ አትሰጥህም፤” አለኝ ወደ ጆሮዬ ሹክክ ብሎ። በተራው እሱን ላስወራው፣ “አልገባኝም?” ስለው ሁለት ዕርምጃ ቀድመው ከፊት ለፊቴ የቆሙት የባሻዬ ጥሩ ጎረቤት ዕልልታቸውን አቀለጡት። “አይገርሙም? ‘ሴት ልጄ ሃይማኖቷን ቀይራ አሰደበችኝ’ ብለው ሠርጓን ቀርተው ለኦባማ ዕልል ሲሉ?” ሲሏቸው ወዲያ ማዶ ጆሮዬ ጥልቅ። አይ እኛ! የማናይ እንመስላለን እንጂ ለካ እናያለን? እያልኩ በውስጤ ስገረም በስተግራ በኩል የፍሳሽ ቱቦው ውኃ ልክ ላይ ወጥተው የማንጠግቦሽ ቡና አጣጭ ‘ጉሮ ወሸባዬ ወሸባ’ እያሉ ማስተባበር ጀመሩ። ዓይን ዓይናቸውን ሳይ አተኩረው አንድ ሰው ብቻ ነው የሚመለከቱት። ማንን እየታዘቡ ነው ብዬ የዕይታ ማዕዘኔን አስተካክዬ ሳጤን በቅርብ ሁለት ወንዶች ልጆቻቸውን በማዕረግ ያስመረቁትን ወይዘሮ አየኋቸው። ኬሚስትሪውን ስሠራው ‘ጉሮ ወሸባዬ’ን የሚያስነኩት የማንጠግቦሽ ወዳጅ ልጆች በሰፈሩ የታወቁ ቃሚና አቃቃሚዎች መሆናቸው መጣልኝ። እንዲያውም በምርቃና የተዋጣላቸው ከመሆናቸው የተነሳ ‘ኢሕአዴግ ደርግን ለመጣል የፈጀበትን 17 መራራ የትግል ዘመን ለማሳጠር በተደጋጋሚ ዕቅድ ሲያወጡ ታይተዋል’ ይባላል። ኧረ እንዲያውም፣ “የአገራችን ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት አስተማማኝ እንዲሆን ምርቃና ወሳኝ ድርሻ አለው፤” እያሉ ልማታዊ ለመሆን ሲሞክሩ በሕግ አስከባሪ ተይዘው ሲመከሩ በዓይኔ በብረቱ አይቻለሁ። ምን ሩቅ እሄዳለሁ። ሸክላ ሆነንበት እንጂ ብረቱ ዓይናችንማ መቼ ማየት ሰለቸው ብላችሁ ነው?!

አወጣጤ እንደተደናቀፈ አቋቋሜ የኅብረተሰቡን ድብቅ የልቡና አጀንዳ ሳጠና ሰዓቱ ሸመጠጠ። መንገዶች ሁሉ ወሬዎች ሁሉ ኦባማ ኦባማ ይላሉ። ባሻዬ መቼ ዕለት የተናገሯት ነገር ጆሮዬ ላይ ትደውላለች። “መሲሁ እንኳ ተመልሶ ቢመጣ እየሩሳሌም የመጎብኘቷን ወራት አስባ ይኼን ያህል አትንጫጫም፤” ነበር ያሉት። እሳቸው ውሏቸውና አዳራቸው ከቅዱሱ መጽሐፍ ጋር እንደመሆኑ መጠን ሲናገሩም ልቡናቸው ካለበት ሥፍራ ቃል እየመዘዘ ነው። ዳሩ አይተነው የማናውቀው ዕድገት መምጫና መጥፊያው በማይታወቅ ገንዘብ ላይ የሚሯሯጠው እንደኔ ዓይነቱ ከአዛውንቶች ጥበብ ይልቅ የባንክ ሒሳቡ መጉደልና መሙላት እያሳሰበው በሁለቱም ጆሮው አያዳምጣቸውም። የጀመርነውን ከማጥራት የማንጨርሰው መጀመር ስለሚቀናንም ይሆናል። ኧረ ምኑን አውቀነው እናንተ? ‘ኢንተርኔት’ ላይ አፍጥጠን እየዋልን ‘የመናገር ነፃነታችን ታፍኗል’ እያልን ፖስት ስናደርግ እኮ ነው የምንውለው። ለቀባሪው አረዳሁ መሰል!

በሉ እንሰነባበት። ‘እንቅስቃሴዎች ሁሉ ኦባማን ይመለከታሉ’ ሲሆንብኝ ጊዜ ሥራዬ እንደ ‘ኔትወርኩ’ እና ንቃተ ህሊናችን ተጓተተብኝ። ደስ የሚለው የሲኖትራኩ ገዢ ኮሚሽኔን በባንክ አካውንቴ ገቢ እንዳደረገልኝ ደውሎ ነግሮኛል። እዚህም እዚያም የተሳኩልኝ ቤት የማሻሻጥና የማከራየት ሥራዎችም ነበሩ። ታዲያ ምኔ ሞኝ ነው አልኩና በተገኘው አጋጣሚ ለውዷ ባለቤቴ ‘አቴንሽን’ ለመስጠት አሰብኩ። ሰው እንደ ሞባይሉ የ‘አቴንሽኑ ኔትወርክ’ እየተቆራረጠ አይደል ድል ባለ ሠርግ ተጋብቶ መንፈቅ አልቆይ ያለው? እውነቴን እኮ ነው። “በጀመርንበትና ባስለመድነው ፍጥነት ልክ ለምን እንደማንፋቀር አይገባኝም?” ስለው ቤቴ በተከተትኩበት በአንዱ ቀን ቡና ሊጠጣ የመጣውን የባሻዬ ልጅ፣ “ከእውነተኛ የወንድማማችነትና የተቃራኒ ፆታ ፍቅር ወደ ፖለቲካዊ ፍቅር ‘አፕግሬድ’ ስላደረግን ነዋ። ዘመኑ የ‘አፕዴት’ እና የ‘አፕግሬድ’ አይደል? በአረጀ ‘ሶፍትዌር’ አይምሰልህ ‘ማይክሮሶፍት’ ገበያውን እየመራ ያለው፤” ብሎ ወጋጋኝ። “ደግሞ ፖለቲካዊ ፍቅር ምንድነው? አያልቅብህ?” ስለው ለኦባማ የተዘፈነላቸው ዘፈን ድምፅ አላደማምጠን ብሎ በርቀት መቆጣጠሪያዬ ቀነስ እያደረኩ “የጥቅም ፍቅር ነዋ! የእከክልኝ ልከክልህ። እንደ ሸንኮራ አገዳ አኝኮ፣ መረቁን መጦ የመተፋፋት ፍቅር፤” አለኝ ኮስተር ብሎ። ዝም ስለው መልሶ፣ “የገለባ እሳትን እውነት እሳት ብለሽ፣ ማገር አትወርውሪ እፍ እፍሺን አምነሽ’ ሲባል አልሰማህም? በወረት ፍቅር፣ በፖለቲካዊ ፍቅር፣ በእፍ እፍ ፍቅር ያብድ ያብድና አዳሜ የጎረቤቱ፣ የወንድሙ፣ የሩቅ የቅርቡ ሰው ታሪክ ራሱን ሲደግም መያዣ መጨበጫ ማጣት። ከዚህ ሁሉ ከአስብቶ አራጅ መራቅ እያለ? በመሳም አሳልፎ ከሚሰጥ መጠበቅ እየተቻለ? ማስተዋል እያለ? ቆይ እንደ ርግብ የዋህ፣ እንደ እባብ ብልህ መሆን ማንን ገደለ?” እያለ ብዙ ስንጫወት አመሸን። የገለባ እሳት ከማመን ይሰውረን ነው። ቢቻል ደግሞ በማስተዋል መፋቀር። ያረጀ ሶፍትዌር ጭነን አንጨቃጨቅ፣ አትጨቅጭቁን! መልካም ሰንበት!     

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት