Tuesday, March 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየሲኤምሲ አካባቢ ነዋሪዎች ከድጋሚ መፈናቀል እንዲታደጉዋቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩን ተማፀኑ

የሲኤምሲ አካባቢ ነዋሪዎች ከድጋሚ መፈናቀል እንዲታደጉዋቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩን ተማፀኑ

ቀን:

‹‹ሕገወጥ ግንባታ ነው ስለተባለ መፍረስ የሌለበትን አናፈርስም›› የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን

በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 08 ሲኤምሲ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ፊት ለፊት የሚኖሩ 43 አባወራዎች (ከ200 በላይ ቤተሰቦች)፣ ቀደም ብለው ይኖሩበት የነበረውን ቀያቸውን በልማት ምክንያት ለቀው በተጠቀሰው ወረዳ እየኖሩ ቢሆንም፣ በመንገድ ግንባታ ምክንያት ሕገወጥ ገንቢዎችን ለማዳን ተብሎ እነሱ በድጋሚ ሊፈናቀሉ መሆኑን በመጥቀስ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲታደጓቸው በደብዳቤ ተማፀኑ፡፡

ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ ለአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ፣ ለአፈ ጉባዔ አባዱላ ገመዳ፣ ለትራንስፖርት ሚኒስቴር፣ ለኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤትና ለሌሎችም ይመለከታቸዋል ላሏቸው ተቋማት የድረሱልን ጥሪ በማድረግ ላይ የሚገኙት ዳግም የመፈናቀል አደጋ ውስጥ መሆናቸውን የሚገልጹት ነዋሪዎች፣ ከ1985 ዓ.ም. ጀምሮ በተለያዩ ጊዜያት የተፈናቀሉ ናቸው፡፡ በ1985 ዓ.ም. በሸራተን ሆቴል ግንባታ ምክንያት የተነሱ የፍል ውኃ አካባቢ ነዋሪዎች፣ ከ1996 ዓ.ም. ጀምሮ በመልሶ ማልማት ምክንያት ከካዛንቺስ የቀድሞ ቀበሌ 30 እና 31 (ኢንተርኮንቴኔንታል ሆቴልና በአካባቢው የነበሩ)፣ ከመገናኛ ዲያስፖራ አደባባይና በሸራተን ማስፋፊያ ምክንያት የተፈናቀሉ ናቸው፡፡

ነዋሪዎቹ ከልጅነት እስከ ዕውቀት የኖሩበትን ቀያቸውን በልማት ምክንያት ሲለቁ፣ ያለምንም ተቃውሞ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አሁን እየኖሩበት ያለው አካባቢ እንዳሁኑ የለማም ባይሆን፣ በአካባቢው መንገድ እንደሚወጣ ተነግሯቸውና የመንገዱም ስፋት ምን ያህል እንደሆነ ተለክቶ ቤታቸውን መገንባታቸውን ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን አሥር ዓመት ሳይሞላው “ለመንገድ ማስፋፊያ” በማለት የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ያለምንም ማስታወቂያና ማስጠንቀቂያ ልኬት መጀመሩ እንዳስደነገጣቸው ተናግረዋል፡፡ ተቃውሟቸውን ለአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ያቀረቡ ቢሆንም፣ የባለሥልጣኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀበሏቸው ስላልቻሉ ለአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አሳውቀዋል፡፡ በድጋሚ ለከንቲባ ድሪባ ኩማ በቅርቡ የተቃውሞ አቤቱታ ደብዳቤ ማስገባታቸውንም ነዋሪዎቹ ይናገራሉ፡፡

ቀድሞ የተሠራው የመንገድ ዲዛይን ማለትም ኮተቤ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ መዳረሻ ከሚገኘው ከወንድይራድ ትምህርት ቤት አንስቶ፣ ሲኤምሲ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ፊት ለፊት የባቡር ሐዲዱን አቋርጦ የረር ጐሮ ድረስ የሚገነባው መንገድ በ20 ሜትር ስፋት እንደሚሠራ የሚገልጽ ቢሆንም፣ የቀድሞ ልኬት (ዲዛይን) ከተሠራ በኋላ በሕገወጥ መንገድ የተሠሩ ሕንፃዎች እንዳይፈርሱ፣ ሌላ ዲዛይንና ልኬቱም በድጋሚ እንዲሠራ መደረጉ ተገቢ አለመሆኑን ነዋሪዎቹ ይገልጻሉ፡፡ የመንገድ ግንባታው ተገቢ ቢሆንም ድጋሚ ዲዛይን ተሠርቶ እነሱ እንዲፈናቀሉ መደረጉ አግባብ አለመሆኑን ሲቃወሙ፣ ነዋሪዎቹ ልማቱን የሚቃወሙ በማስመሰል ከመንግሥት ጋር ለማጋጨት ሆን ተብሎ እየተፈጸመ ያለ ድርጊት መሆኑን በመጥቀስ፣ መንግሥት እንዲደርስላቸው እየለመኑ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከንቲባ ድሪባ ኩማ የነዋሪዎቹ አካባቢ በመሄድ ሁኔታውን ከተመለከቱ በኋላ፣ አዲስ የተሠራው የመንገድ ዲዛይንና አግባብ ያልሆነው ልኬት ተሻሽሎ እንደገና እንዲሠራና ቤት እንዳይፈርስ ትዕዛዝ በመስጠት ለነዋሪዎች ቃል ገብተው እንደነበር ነዋሪዎቹ ገልጸዋል፡፡ ከንቲባው የሰጧቸው ተስፋ ቀርቶ ግንቦት 28 ቀን 2007 ዓ.ም. በድጋሚ በመለካት፣ ከ2.5 ሜትር እስከ 13 ሜትር ወደ ቤታቸው በመግባት አዲስ ምልክት በማድረግ፣ መውጫ መግቢያቸው ላይ ቁፋሮ መጀመሩንና ከስድስት ወራት በላይ ችግር ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ነዋሪዎቹ ከወጣት እስከ 100 ዓመት ዕድሜ ያላቸው አዛውንቶች ሲሆኑ፣ አንዳንዶቹ እስከ አሥር ሚሊዮን ብር ድረስ ወጪ በማውጣት የገነቡት ሆቴል ሙሉ በሙሉ እንደሚፈርስ እንደተነገራቸው ገልጸዋል፡፡ ከአሥር ዓመታት በላይ የኖሩበት ቤትና ድርጅት ያለምንም ማስጠንቀቂያ በ15 እና በሦስት ቀናት ውስጥ እንደሚፈርስ በድንገት መናገር ተገቢ ካለመሆኑም በተጨማሪ፣ ከ20 በላይ ሠራተኞችን የሚያስተዳድርን ሆቴል በድንገት ማፍረስ ዜጎችን ሥራ አጥ ከማድረጉም በላይ፣ ምን ያህል ቤተሰቦችን ሊጎዳ እንደሚችልም ሊታሰብበት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ባለሥልጣናት የሰጡት ትዕዛዝ ችላ እየተባለና ሕገወጥ ግንባታዎችን ለማትረፍ ሁለትና ሦስት ዲዛይኖች እየተቀየሩ፣ በልማት ምክንያት የተፈናቀሉ አባወራና እማ ወራዎችን በድጋሚ ለማፈናቀል መሯሯጡ ስለበዛባቸው፣ ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያምና ለሌሎች ለሚመለከታቸው የፌደራል መንግሥት ተቋማት መሪዎች በማመልከት እንዲታደጓቸው እየለመኑ መሆኑን በድጋሚ ተናግረዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም የነዋሪዎቹን አቤቱታ ተቀብለው፣ ነዋሪዎቹ ሁለት ጊዜ እንዲነሱ የሚደረግበትን ምክንያት አስተዳደሩ እንዲገልጽ በመዝገብ ቁጥር 14/910/6 አዘዋል፡፡ አስተዳደሩ ደግሞ በመዝገብ ቁጥር 799 ለአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ማሳወቁን ነዋሪዎቹ ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን ይኼ ሁሉ ሁኔታ ታልፎ ቤቶቻቸው እንዲፈርሱና መግቢያ መውጫ የሚያሳጣቸው የመንገድ ፕላን ተግባራዊ እየተደረገ ስለሚገኝ፣ መንግሥትም ሆነ የሚመለከታቸው የአስተዳደሩ ባለሥልጣናት ተገቢ ትኩረት ሰጥተው እንዲታደጓቸው ጠይቀዋል፡፡ የቦሌ መንገድ ሲገነባ የሩዋንዳ ኤምባሲ አካባቢዎች ባቀረቡት አቤቱታ ምክንያት መኖሪያቸው እንዲተርፍላቸው መደረጉን አስታውሰው፣ እነሱንም መንግሥት እንዲታደጋቸው ጠይቀዋል፡፡

የ100 ዓመት የልደት በዓላቸውን በቅርቡ ማክበራቸውን የሚናገሩት አቶ በዛብህ ባህሩ፣ ከቀበሌ 30 እና 31 ካዛንቺስ ኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል ከተገነባበት አካባቢ ተፈናቅለው ወደ ሲኤምሲ መሄዳቸውን ይናገራሉ፡፡ የዘጠኝ ልጆች አባት መሆናቸውንና ከ50 ዓመታት በላይ ከኖሩበት ቀያቸው የተፈናቀሉት፣ ከተማ ማደግ ካለበት የዕድገቱ ደጋፊ መሆን እንዳለባቸው በማመናቸው መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ አሁን ግን አሥር ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በድጋሚ እንዲፈናቀሉ ወይም መንግሥት የሰጣቸውን ሕጋዊ ይዞታ፣ ዲዛይን በማጣመምና የሌሎችን ግንባታ ለማዳን ተብሎ የእሳቸውና የመሰሎቻቸው ቤት እንዲፈርስ መደረጉ አግባብ አለመሆኑንና የመንግሥትም ዓላማ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡ ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ጀምሮ ጡረታ እስከወጡበት ድረስ ለአገራቸው ብዙ ማገልገላቸውን የሚናገሩት አቶ በዛብህ፣ በዚህ ዕድሜያቸው እንደመጦር “ቤት ይፈርሳል” የሚለውን መስማታቸው እንዳሳዘናቸው አስረድተዋል፡፡ ወግ ማዕረግ ያዩበት፣ ልጆች ያፈሩበትንና የትዳር አጋራቸውን ያጡበትን ቀያቸውን ለልማት ብለው እንደለቀቁ ሁሉ፣ መንግሥትም አረጋውያንን እየሰበሰበና እየጦረ ባለበት በአሁኑ ጊዜ የ100 ዓመታት የዕድሜ ባለፀጋ በድጋሚ ተፈናቀሉ ማለት ተገቢ ባለመሆኑ፣ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ ሊያስተካክል እንደሚገባ ጠይቀዋል፡፡ አቤቱታ ለማቅረብ ብዙ ቦታዎች ሄደው አክብሮት የተሞላበት ምላሽ ያገኙ ቢሆንም፣ ለምን ተፈጻሚ ሊሆን እንዳልቻለ ግራ መጋባታቸውንና አሁንም መማፀናቸውን እንደማይተው ገልጸዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሌላ አማራጭ ይታይላቸው በማለት የሰጡት ማሳሰቢያ መታለፉ ተገቢ አለመሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ሌላው የመፈናቀል ሥጋት አድሮባቸው አቅም ቢያንሳቸውም በልጆቻቸው አማካይነት አቤት እያሉ የሚገኙት 96 ዓመት ዕድሜ እንዳላቸው የሚናገሩት አቶ ሙሀባ ነጠረ ናቸው፡፡ እሳቸው በልማት ምክንያት የተፈናቀሉት መገናኛ ዳያስፖራ አደባባይ ከሚባለው አካባቢ ሲሆን፣ አሁን በመንገድ ምክንያት በድጋሚ እንደሚፈናቀሉ መነገሩ ተገቢ አለመሆኑን ይገልጻሉ፡፡ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ከሁለት ጊዜ በላይ የፓርላማ ተመራጭ እንደነበሩ የሚናገሩት አቶ ሙሀባ፣ ለአገራቸው መልካም ነገርን መሥራታቸውን በመግለጽ መንግሥት ሊጦራቸው ሲገባ እንዲፈናቀሉ መታሰቡ እንዳሳዘናቸው ገልጸዋል፡፡ ቀሪ ሕይወታቸውን በቤታቸው እንዲያሳልፉ መንግሥት በጉዳዩ ላይ ትኩረት እንዲሰጥበት እሳቸውም እንደ አቶ በዛብህ አሳስበዋል፡፡ የመልካም አስተዳደር እጦት በግልጽ እየታየና እየጎዳቸው መሆኑንም አክለዋል፡፡ ሸራተን አዲስ ከተገነባበት ቦታ (ፍል ውኃ አካባቢ) የተነሱና በሼክ መሐመድ አል አሙዲ ቤት ተገንብቶላቸው (አልታድ ሠፈር) ከ20 ዓመታት በላይ የኖሩ እናቶችም፣ በዲዛይን ምክንያት ቤታቸው ሳይቀር እንደሚፈርስ መለካቱን ገልጸዋል፡፡ ድርጊቱም ተገቢ ያልሆነና መንግሥት ያላወቀው ሕገወጥ ግንባታን የማትረፍ ዘዴ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አንዳንዶቹ ጧሪ ቀባሪ ስለሌላቸው መንግሥት የማይታደጋቸው ከሆነና ቤታቸው ከፈረሰ፣ ወደ ጎዳና እንደሚወጡም አስረድተዋል፡፡ ነገር ግን መንግሥት እንዲታደጋቸው ለምነዋል፡፡ የከንቲባው ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሰግድ በቦታው ተገኝተው ሲጠይቁ መሐንዲሱ 15 ሜትር ወደ ነዋሪዎቹ ቤት እንደሚገባ ገልጾ ሳለ የባለሥልጣኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ፍቃዱ ኃይሌ ግን ሦስት ሜትር ነው ማለታቸው እንዳሳዘናቸው ገልጸዋል፡፡ ነዋሪዎቹ በዋናነት እየኮነኑት ወይም እየተቃወሙት ያሉት የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣንን በመሆኑ፣ ኢንጂነር ፍቃዱን ሪፖርተር አነጋግሯቸዋል፡፡

ኮተቤ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ መዳረሻ ከሚገኘው ወንድይራድ ትምህርት ቤት እስከ የረር ጎሮ የሚደርስ መንገድ በመገንባት ላይ እንደሚገኝ የገለጹት ኢንጂነር ፍቃዱ፣ መንገዱ ጠቅላላ ርዝመቱ 5.3 ኪሎ ሜትር መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ስፋቱ ከትምህርት ቤቱ እስከ ሲኤምሲ ሚካኤል ድረስ 20 ሜትር፣ ከሚካኤል የባቡር ሐዲዱን አቋርጦ እስከ ፋውንቴን ትምህርት ቤት ድረስ መንገዱ በድልድይ ስለሚሠራ 35 ሜትር ስፋት እንደሚኖረው አስረድተዋል፡፡ የመንገዱን ግንባታ ሳትኮን ኮንስትራክሽንና ማክሮ ኮንስትራክሽን የተባሉ ኩባንያዎች የሚገነቡት ሲሆን፣ ከ140 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚፈጅም ጠቁመዋል፡፡ ከመንገዱ መገንባት ጋር በተያያዘ በ20 ሜትር ስፋት በሚሠራው መንገድ ዳርና ዳር የተገነቡ መኖሪያ ቤቶች የማይነኩ ቢሆንም፣ በተለይ 35 ሜትር ስፋት ያለው ድልድይ በሚሠራበት ግራና ቀኝ ያሉ ነዋሪዎች ቤት እስከ ሦስት ሜትር ድረስ ሊፈርስባቸው እንደሚችል ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል፡፡ ሰማንታ የሚባለው ሆቴል ግን ሙሉ በሙሉ ሊፈርስ እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡

መንገዱ እየተጠመዘዘ የሚሄድ በመሆኑ ከየረር ጐሮ ወደ ሲኤምሲ በሚመጣው መንገድ ግራ በኩል የሚኖሩት ባለይዞታዎች እንደሚነኩ የገለጹት ኢንጂነር ፍቃዱ፣ ይህ የተደረገው ዝም ተብሎ ሳይሆን ከአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ጋር በሥፍራው ተገኝተው ሁኔታውን ከተመለከቱና በሰጡት ትዕዛዝ መሠረት፣ ቀደም ተብሎ የተሠራው ዲዛይን ተሻሽሎና ነዋሪዎችንም በማይጎዳ ሁኔታ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ቀድሞ የተሠራው ዲዛይን ግራና ቀኝ የመከላከያ ግንብ (Retaining Wall) የነበረው ሲሆን፣ ግራና ቀኝ ያሉትን ነዋሪዎች የማያገናኝና የሚሸፍን በመሆኑ እንዲቀር ተደርጎ በመስተካከሉ፣ ግራና ቀኝ ያሉ ነዋሪዎች በቀላሉ የሚተላለፉበትና የሚገናኙበት አሠራር ተግባራዊ መደረጉን ሥራ አስኪያጁ አስረድተዋል፡፡ ይህ በመደረጉም የአንዳንዶቹን ይዞታ ከ2.5 ሜትር እስከ ሦስት ሜትር ሊነካ መቻሉን አክለዋል፡፡

‹‹እኛ ዕድሜ እየለካን አፍርሰን አናውቅም፣ አናፈርስምም፤›› የሚሉት ኢንጂነር ፍቃዱ፣ ለልማት አስፈላጊ ከሆነና ዲዛይን ከወጣበት ማንኛውም ዓይነት ግንባታ ሊፈርስ እንደሚችል ገልጸው፣ በዚህ መንገድም መፍረስ ያለበት ካለ እንደሚፈርስ ገልጸዋል፡፡ በድጋሚ ዲዛይን ተቀይሮ ሲለካ፣ ምልክት የተደረገው በቤቶቹ አጥር ላይ መሆኑን ጠቁመው፣ ነዋሪዎቹ ሆን ብለው ቤታቸው ግቢ ውስጥ ምልክት ማድረጋቸውን ከአማካሪ መሐንዲስ መረዳታቸውን ገልጸዋል፡፡ የከንቲባው ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሰግድ ጌታቸውም በቦታው ተገኝተው መመልከታቸውን አስረድተዋል፡፡ ሥራው መጠናቀቅ ካለበት በዓመት መዘግየቱን የጠቆሙት ሥራ አስኪያጁ፣ ነዋሪዎቹ እንቅፋት ሆነው መቆየታቸውን አስረድተዋል፡፡ ነዋሪዎቹ በማያመችና መስመሩ በማይገናኝ ቦታ ዲዛይኑ እንዲቀየር ሐሳብ እያቀረቡ ቢሆንም፣ መሠራት ያለበት በአግባቡና በትክክለኛው ዲዛይን በመሆኑ፣ መሠራቱ የማይቀር መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ‹‹ነዋሪዎቹ ሕገወጥ ግንባታ እንዳለ ገልጸው መፍረስ አለበት ስላሉ፣ ከዲዛይን ውጪ ነው ብለን አናፈርስም፤” ብለዋል፡፡   

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...