Monday, June 17, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኢትዮጵያ የአሜሪካ ኢንቨስተሮችን ለማስተናገድ ምን ያህል ዝግጁ ናት?

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኧርነስት ኤንድ ያንግ ማኔጂንግ ፓርትነር አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ ስለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ግዙፍነትና የወደፊት ትልልቅ ተስፋዎች በተለያዩ መድረኮች በተደጋጋሚ ሲናገሩ ይደመጣሉ፡፡ በቅርቡም በአዲስ አበባ በተስተናገደው ሦስተኛው ፋይናንስ ለልማት የተባበሩት መንግሥታት ጉባዔ ላይ በተካሄደ የጎንዮሽ መድረክም ይህንኑ አስተጋብተዋል፡፡

ስለኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት አማራጮችና የወደፊት ተስፋዎች በተናገሩበት፣ ‹‹ኢትዮጵያ ራይዚንግ›› የሚል ስያሜ በተሰጠው የኢትዮጵያ ጉባዔ ወቅት፣ የአገሪቱ የኢንቨስትመንት ዕድሎችን ከማስተዋወቅ ባሻገር የውጭ ኢንቨስትሮች መጥተው ኢንቨስት እንዲደርጉ አቶ ዘመዴነህና የሶልሪ ቤልስ ጫማ ማምረቻ ኩባንያ ባለቤት ወ/ሮ ቤተልሔም ጥላሁን ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በመንግሥት የተመረጡት ሁለቱ የንግድ ሰዎች፣ ስለአገሪቱ ተስፋዎች በመዘርዘር በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝና በአማካሪያቸው ዶክተር አርከበ እቁባይ በተመራው መድረክ ላይ ለማስተዋወቅ ሞክረዋል፡፡

አቶ ዘመዴነህ ‹‹ኢንቨስቲንግ ኢን ኢመርጂንግ ኢትዮጵያ›› ወይም እያደገች ባለችው ኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት ስለማድረግ በሚያመለክተው ጥራዛቸው ውስጥ በኢትዮጵያ ኢንቨስት ስላደረጉ የውጭ ኩባንያዎች ያሰፈሩበት ክፍል አንዱ ነው፡፡ ከ13 የውጭ ኩባንያዎች ውስጥ የአሜሪካ ኩባንያዎችም ተካተዋል፡፡ ኬኬአር የተሰኘው አበባ አምራች፣ ለቦይንግ አውሮፕላኖች ልዩ ልዩ የኤሌክትሪክ ኬብሎችን የሚያመርተው ‹‹ዋየር ኪት ሃርነስ›› ፋብሪካ፣ የኢትጵዮያ አየር መንገድ ንብረት የሆኑ አውሮፕላን ሞተሮች ላይ በመሥራት ሲንቀሳቀስ የቆየ ሲሆን፣ አሁን ደግሞ በጤና ክብካቤ መስክ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው ጄነራል ሞተርስ (ጂኢ) እንዲሁም ከሃምሳ ዓመታት በላይ በኢትዮጵያ ለስላሳ መጠጦችን በማምረት ላይ የሚገኘው ኮካ ኮላ ከአሜሪካ ኩባንያዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ እነዚህን ኩባንያዎች ጨምሮ ከቻይና፣ ከቱርክ እንዲሁም ከደቡብ ኮሪያ የመጡ ኩባንዎች በአገሪቱ እያደረጉ ስላለው ኢንቨስትመንት አቶ ዘመዴነህ በጥራቸው አስተዋውቀዋል፡፡

ይህም ቢባል ግን መንግሥት ለበርካታ ዓመታት ከውጭ በተለይም በምዕራቡ ዓለም የሚመጣው ኢንቨስትመንት ከሚፈልገውና ከሚጠብቀው መጠን በታች ሆኖበት እንደሚገኝ ሲገልጽ መቆየቱ ይታወሳል፡፡ በአገሪቱ የሚገኘው የኢንቨስትመንት ሕግ፣ የጉምሩክ ሥነ ሥርዓት አፈጻጸም ሕግ፣ የወጪና ገቢ ዕቃዎች አያያዝ፣ እንዲሁም አገሪቱ የትራንስፖርትና የሎጂስቲክስ አሠራሮች ላይ መንግሥት ደጋግሞ ማሻሻያ እያደረገ እንደሚገኝ ቢገልጽም የምዕራብ ኢንቨስተሮችን እንደሚፈልገው መጠን ለመሳብ አላስቻለውም፡፡

ከአውሮፓና ከአሜሪካ የሚመጡ የንግድ ልዑካን ደጋግመው የሚገልጹት አገሪቱ በእነሱ ደረጃ ወይም ስታንዳርድ የሚመጥኑ መሠረተልማቶችና የሚመጡትን ኢንቨስትመቶች ማስተናገድ የሚችሉ ተቋማት ብቃት እንዲሁም የተማረ የሰው ኃይልና የመሳሰሉትን ችግሮች ዘወትር በመጥቀስ እነዚህ ችግሮች እንዲቀረፉ መንግሥትን ሲጠይቁ ይደመጣሉ፡፡ የቢሮክራሲና የጉዳይ ማስፈጸም ችግሮች ሰፊ ቦታ እየያዙ እንደሚገኙ ስሞታዎች ቢኖሩም፣ ከፍ ባለደረጃ ከሚሰነዘሩት ውስጥ የውጭ ባንኮች አገር ውስጥ መሥራት እንዲችሉ፣ የቴሌኮምና ሌሎች ስትራቴጂካዊ ተቋማት ከመንግሥት ይዞታ በመውጣት ወደ ግል እንዲዛወሩ ቅድመ ሁኔታዎችን ማስቀመጥም ከምዕራቡ ዓለም የሚዘነዘሩ ጥያቄዎች ናቸው፡፡    

በአሜሪካ መንግሥት ከተቋቋመውና መቀመጫውን በአዲስ አበባ አሜሪካ ኤምባሲ ያደረገው የአሜሪካ የንግድ ጽሕፈት ቤት በባንክና በመሰል መንግሥታዊ ተቋማት ፕራይቬታይዜሽን እርምጃዎች ላይ በመሥራት መንግሥት ዘርፎቹን ክፍት እንዲደርግ እንደሚሠሩ የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ ታንያ ኮል ከጥቂት ሳምታት በፊት ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቆይታ መግለጻቸው አይዘነጋም፡፡ በአንጻሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በበኩላቸው ባንኮችም ሆኑ ሌሎች መንግሥታዊ ተቋማት ቢያንስ  በቅርብ ጊዜ ውስጥ ለውጭ ኩባንዎች ክፍት እንደማይደረጉ ያረጋገጡት በዚሁ አቶ ዘመዴነህ ስለአገሪቱ ኢንቨስትመንት ባስተዋወቁበት መድረክ ነበር፡፡

ከዚህ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ሐሳብ ጋር የሚቀረነው ደግሞ አንዳንድ የግል ባንኮች ስትራቴጂካዊ ጥናት መጀመራቸው ሲታይ ነው፡፡ አዋሽ ባንክን ጨምሮ ጥቂት አገሪቱ ባንኮች ለመጪዎቹ ዓመታት ስለሚጓዙበትና ኢንዱስትሪውን የውጭ ባንኮች ቢቀላቀሉ የሚኖራቸውን ተፎካካሪነት መሠረት ያደረገ የሚሊዮን ዶላሮች ፕሮጀክት ማስጠናት ጀምረዋል፡፡

የሰሞኑ የኦባማ ጉብኝት በኢትዮጵያ የሚቋመጥለትን የአሜሪካ ኩባንያዎች መምጣት በግርድፍ ያመላከተ እንጂ እንደ ቻይኖቹ፣ እንደ ህንዶቹና እንደ ቱርኮቹ ከፕሬዚዳንቱ ጉብኝት ጎን ለጎን ስምምነት ሲደረግ አልተስተዋለም፡፡ በአንድ ወቅት ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስለምዕራባውያን ኩባንያዎች አለመምጣት ይልቁንም ስለቻይኖችና ህንዶች መብዛት ተጠይቀው ነበር፡፡ በምላሻቸው እንዳስታወቁት፣ ምንም እንኳ የምዕራብ ኩባንያዎችን መምጣት ቢፈልጉም ሊሳካላቸው እንዳልቻለ ገልጸዋል፡፡

ከአአሜሪካ ባሻገር በኢትዮጵያ ኢንቨስት ያደረጉ የአውሮፓ ኩባንያዎች በሚያካሂዷቸው ፎረሞች፣ አገሪቱ እንድታሻሽልላቸው የሚፈልጓቸውን የቢሮክራሲና የኢንቨስትመንት መሰናክሎች ደጋግመው ሲያቀርቡ ይደመጣል፡፡ የመሬት አሰጣጥ፣ የጉምሩክና የግብር አሠራሮች፣ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ቅልጥፍናና ወጪ፣ እየቀነሱም ቢሆን የመሠረተ ልማት አለመሟላት ጥያቄዎች፣ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት፣ የቴሌኮም አገልግሎት አቅርቦትና ጥራት፣ የተማረ የሰው ኃይል፣  የውሳኔ አሰጣጥ ወዘተ ተደጋግመው ከሚሰሙ ችግሮች መካከል ይገኙባቸዋል፡፡

እነዚህ ሁሉ ጥያቄዎች ተመልሰውም እንኳ የአሜሪካም ሆነ የአውሮፓ ኩባንዎችን በብዛት በኢትዮጵያ ለማየት የማያስችሉ ቢያንስ ሁለት መሠረታዊ ሳንካዎች እንደሚታዩ የሚናገሩ አሉ፡፡ አንደኛው የቻይናም ሆነ ሌሎች የእስያ ኩባንያዎች በትልልቅ ፕሮጀክቶች ላይ ለመሳተፍ ሲመጡ ከመንግሥቶቻቸው የረጀምም ይሁን የአጭር ጊዜ ብድር ይዘው ይመጣሉ፡፡ ለሚከናወኑት ግንባታዎችም ቅድሚያ ያገኛሉ፡፡

በኢትዮጵያም ሆነ በአፍሪካ የሚታየውን የቻይኖች ተጽዕኖ ምዕራባውያኑ የወደዱት አይመስሉም፡፡ ከአንዳንድ ግለሰቦች ጋር በሚደረጉ ከአፍ መለስ ክርክሮች ይኸው ስሜት ይስተጋባል፡፡ በአንድ ወቅት የአውሮፓ የንግድ ልዑካንን አጅበው የመጡ ጋዜጠኞች፣ በኢትዮጵያ የሚታዩትን ዋና ዋና አውራ ጐዳናዎች፣ ትልልቅ የግድብ ግንባታዎችና የባቡር መስመሮች የሚገነቡት ቻይኖቹ መሆናቸውን እየጠቀሱ ‹‹እኛ ብድር ዕርዳታ እንሰጣለን፡፡ በእኛ እርዳታ ግን ቻይኖቹን እየከፈላችሁ ታሠራላችሁ፤›› የሚሉ ስሞታዎችን ቀልድ በሚመስሉ ምጸቶች ሲገልጹ ማድመጥ እየተለመደ ይመስላል፡፡

ይህም ቢባል ግን ጥቂት በጥቂትም ቢሆን የምዕራብ ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ የሚመላለሱበት የኢንቨስትመንት ሰበብ አላጡም፡፡ በፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ለአፍሪካ ከተዘረጉት ጅምሮች መካከል ‹‹ፓወር አፍሪካ›› የተሰኘው ፕሮጀክት ይጠቀሳል፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ ስድስት ከሰሃራ በታች ያሉ አገሮችን የሚያካትተው የሰባት ቢሊዮን ዶላር ፕሮጀክት ላይ የሚሳተፉ ኩባንያዎች ከአገር ውስጥም ከውጭም ብቅ ብቅ ማለት ጀምረዋል፡፡ ድ’ቬንተስ የተባለውን ልዩ ልዩ የኤሌክትሪክ መሣሪያዎች አምራቹ ኩባንያ ‹‹ስማርት›› ቆጣሪዎችን በማምረት የሬዚዳንት ኦባማን ፓወር አፍሪካ ፕሮጀክት ከተቀላቀሉ መካከል ይጠቀሳል፡፡

በጠቅላላው ሲታይ፣ ኢትዮጵያ አሜሪካውያን ኩባንያዎችን ለመሳብ ብዙ መጓዝና መሥራት እንደሚጠበቅባት መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ የአገሪቱ የገንዘብ ፖሊሲና የመንግሥት የውጭ ባንኮች አይከፈቱም አቋም ለዚህ ዋናዎቹ ምክንያቶች መሆናቸው ይጠቀሳል፡፡ ከዚህ ባሻገር ግን አገሪቱ ለአምራች ኢንዱስትሪዎች እየዘረጋቻቸው የሚገኙ መሠረተ ልማቶች መስፋፋትም ቀላል ኢንዱስትሪዎችን ከአሜሪካ ለመሳብ እንደሚረዱ ይታመናል፡፡  

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች