Wednesday, June 7, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የገቢዎች ባለሥልጣን ለአዲስ አበባ ገቢ መቀነስ አስመጪዎችንና አከፋፋዮችን ወቀሰ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ከፍተኛ ግብር ከፋዮችን ሐሙስ ሐምሌ 16 ቀን 2007 ዓ.ም. ለመሸለም በጠራው ስብሰባ እንዳስታወቀው፣ በአዲስ አበባ በ2007 በጀት ዓመት ለታየው ከዕቅድ በታች የግብር አሰባሰብ በመርካቶ የሚሠሩ አስመጪዎችንና አከፋፋዮችን ወቀሰ፡፡

‹‹የመርካቶ ሕገወጥነት ትርምስ አላበቃም፤›› ያሉት የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ በከር ሻሌ፣ ባለፈው በጀት ዓመት የአዲስ አበባ ገቢ አፈጻጸም አጥጋቢ አልነበረም በማለት፣ ለገቢው ማነስ የመርካቶ አስመጪዎችን፣ አከፋፋዮችንና ቸርቻሪዎችን ተጠያቂ አድርገዋል፡፡

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ፣ በ2007 ዓ.ም. ከመርካቶ ይሰበሰባል ተብሎ የነበረው የታክስ መጠን 22 ቢሊዮን ብር ቢሆንም፣ ከዚህ ውስጥ መሰብሰብ የተቻለው ግን 17 ቢሊዮን ብር ብቻ ነበር፡፡ በመሆኑም ‹‹አዲስ አበባን ለመደጎም አልቻልንም፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹የአከፋፋዮች ትልቅ እጅ ስላለበትና የችግሩ ምንጭም ስለሆኑ ያለደረሰኝ ለከተማውና ለክልሎች የሚያከፋፍሉት ተደርሶባቸዋል፤›› ካሉ በኋላ በዚህ ዓመት ትኩረት እንደሚደረግባቸው አስጠንቅቀዋል፡፡

በ2008 ዓ.ም. 142 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ መታቀዱን የገለጹት አቶ በከር፣ ከዚህ ውስጥ 60 ቢሊዮን ብር ከከፍተኛ ግብር ከፋዮች የሚሰበሰብ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በአገሪቱ ካለው ግብር ከፋይ ውስጥ አምስት በመቶውን የሚሸፍኑት ከፍተኛ ግብር ከፋዮች 70 በመቶውን የታክስ ገቢ እንደሚያመነጩ ባለሥልጣኑ አስታውቋል፡፡ በአንፃሩ የፌደራል የታክስ አሰባሰብ አጥጋቢ ነበር ያሉት አቶ በከር፣ 116 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 117 ቢሊዮን ብር መገኘቱን ገልጸዋል፡፡

እንደ አቶ በከር ማብራሪያ፣ በአገሪቱ የታክስ ማጭበርበርና ሙስና ምንጮች ከሆኑት መካከል ኮንትሮባንድ፣ የታክስ ኦዲት፣ የዋጋ ትመና፣ ያለደረሰኝ መሸጥ እንዲሁም አድበስብሶ ታክስ መክፈል በግብር ከፋዩና በአስከፋዩ መካከል ትልቅ ክፍተቶች እንዲፈጠሩ ምክንያት መሆናቸው ተመልክቷል፡፡

ከወትሮው የተለሳለሰ የግብር ከፋዮች ስሞታ በተስተናገደበት መድረክ፣ ሆን ብለው የሒሳብ አሠራሮችን በማጭበርበር ከታክስ ባለሥልጣኑ ጥቅም ለማግኘት ሲሉ ሆን ተብሎ የተፈጸመ ማጭበርበር እንዳለ በማስመሰል የሚሠሩ ባለሙያዎችን ባለሥልጣኑ እንዲከታተል የጠየቁት የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር አረጋ ይርዳው፣ በባለሥልኑና በማዘጋጃ ቤት አካባቢ በሚያጋጥም ቢሮክራሲ ሳቢያ ጉቦኝነት መስፋፋቱን ተናግረዋል፡፡ ይህንን ተከትሎም ‹‹ጉቦን ሰፕሊመንታሪ ሳላሪ ብለን መጥራት ጀምረናል፤›› በማለት ለባለሥልጣኑ ሠራተኞች የሚከፈለውን ጉቦ ‹ደመወዝ ደጓሚ› እየተባለ እስከመጥራት መደረሱን ገልጸዋል፡፡ ‹‹ፋሲሊቴቲንግ ፊ›› ወይም ‹‹የማስፈጸሚያ ክፍያ›› እየተባለ እንደሚጠራ የገለጹ ነጋዴዎችም በስብሰባው ተገኝተዋል፡፡ 

የተጨማሪ እሴት ታክስ ተመላሽ ሒሳብ እስከ ስድስት ዓመታት ለድርጅቶች ሳይመለስ መቆየቱን የተቹት ዶ/ር አረጋ፣ መንግሥት መመለስ ያለበትን እንዲመልስ ጠይቀዋል፡፡ በኮንትሮባንድ እየደረሰ ያለው ኪሳራ አሥር ቢሊዮን ብር እንደሚገመት የገለጹት ነጋዴዎች፣ መንግሥት መፍትሔ ካልሰጠው ህልውናቸው እንደሚያከትምለት አሳስበዋል፡፡ ከቀረጥ ነፃ በገቡ ተሽከርካሪዎች፣ በትርፍ ድርሻ አከፋፈል (ዴቪደንድ)፣ በዊዝሆልዲንግ ታክስ፣ በጉምሩክ ዋጋ ትመናና በመሳሰሉት ላይ ጥያቄዎች ተነስተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በሙስና ወንጀል ተጠርጠረው ወደ እስር ቤት ከተላኩት ከፍተኛ ባለሥልጣናት በኋላ ለከፍተኛ ግብር ከፋዮች የዕውቅና ሽልማት በተሰጠበት ሥነ ሥርዓት ላይ 48 ኩባንያዎች የዋንጫና የምስክር ወረቀት በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ ከፋይናንስና ኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪና የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ሚኒስትር ዶ/ር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል እጅ ተቀብለዋል፡፡ ከእነዚህ ድርጅቶች ውስጥ ሰባቱን የሚድሮክ ግሩፕ እህት ኩባንያዎችና አጋሮቹ ሽልማቱን አግኝተዋል፡፡

 

 

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች