Monday, June 17, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ፒቲኤ ባንክ ለንግድ ባንክና ለአየር መንገድ የ300 ሚሊዮን ዶላር ብድር ማፅደቁን አስታወቀ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

–  የዳያስፖራ ቦንድ አሠራርን ለመተግበር እንደሚፈልግ ገለጸ

የምሥራቅና የደቡባዊ አፍሪካ አገሮች የንግድና የልማት ባንክ (ፒቲኤ) በኢትዮጵያ ትኩረት ካደረገባቸውና ብድር ሊያፀድቅላቸው ከሚያስባቸው ኩባንያዎች መካከል፣ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ለኢትዮጵያ አየር መንገድ የ300 ሚሊዮን ዶላር ወይም የስድስት ቢሊዮን ብር ብድር ማፅደቁን፣ የባንኩ ፕሬዚዳንትና ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አድማሱ ይልማ ታደሰ ለሪፖርተር ገለጹ፡፡

አቶ አድማሱ በተለይ ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ ፒቲኤ ባንክ ለሁለቱ መንግሥታዊ ተቋማት ካፀደቀው ብድር በተጨማሪ በኃይል ዘርፍ፣ በማዕድን ዘርፍ፣ በቱሪዝም ዘርፍ በተለይ በሆቴል ቢዝነስና በአግሪቢዝነስ ዘርፎች ላይ ተጨማሪ ብድሮችን ለማቅረብ ፍላጎት እንዳለው ገልጸዋል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባለፈው ዓመት 50 ሚሊዮን ዶላር ብድር ማግኘቱ ሲታወስ፣ ሐበሻ ሲሚንቶ 40 ሚሊዮን ዶላር ከፒቲኤ ባንክ በብድር ማግኘቱ አይዘነጋም፡፡ ‹‹እንደ ኢነርጂ፣ አግሪ ቢዝነስ እንዲሁም ቱሪዝም የመሳሰሉት ፕሮጀክቶችን ፋይናንስ ለማድረግ እየተመለከትን ነው፡፡ ብድር ልንሰጥባቸው የሚችሉ መስኮች ብዙ አሉ፡፡ ፕሮጀክቶችን ወደ መመዘኑ እየገባን ነው፤›› ያሉት አቶ አድማሱ፣ ምንም እንኳ ሕጋዊ ስምምነት ሳይደረግ ፋይናንስ የሚደረጉ ፕሮጀክቶችን ከመግለጽ እንደሚቆጠቡ ቢገልጹም፣ በቅርቡ ይፋ የሚደረጉ እንዳሉ ተናግረዋል፡፡

ባንኩ ከግሉ ዘርፍ ጋር አብሮ ለመሥራት ዝግጁ መሆኑን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፣ ነገር ግን ሁሉም የባንኩን መመዘኛዎች ማሟላት እንደሚጠቅባቸው አሳስበዋል፡፡ ‹‹ያንን ማድረግ እንደሚችሉ ያሳዩና ያስመሰከሩ በርካቶች  አሉ፡፡ ለምሳሌ የኢትጵያ ንግድ ባንክ፣ ኢትዮ ቴሌኮም እንዲሁም የባህር ትራንስፖርትና የማሪታይም አገልግሎት ድርጅት አብረናቸው ለመሥራት ክፍት ከሆኑት ተቋማት መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፤›› በማለት ጠቅሰው፣ ብድር የሚሰጣቸው ተቋማት በአብዛኛው በኤክስፖርት መስክ የተሠማሩት እንደሚሆኑ ይፋ አድርገዋል፡፡ ወደፊት የብሔራዊ ባንክ ሕጎች ሲፈቅዱም ለግል ባንኮች ለማደበር ፒቲኤ ፍላጎት አለው ብለዋል፡፡

ከዚህ ባሻገር በውጭ ከሚኖሩ ዜጎችና ከሌሎች አፍሪካውያን ካፒታል በቀላሉ ለማሰባሰብ የሚያስችል የዳያስፖራ ቦንድ ሽያጭ የመጀመር ዕቅድ እንዳለው አስታውቀው፣ ከዚህ ቀደም በዚምባብዌ ተመሳሳይ የቦንድ ሽያጭ በባንኩ ዋስትና መሠረት መከናወኑን አስታውሰዋል፡፡ በኢትዮጵያም ከውጭ ሊገኝ የሚችል ትልቅ ካፒታል በዳያስፖራ ቦንድ አማካይነት ለማሰባሰብ ከንግድ ባንክና ከሌሎች ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር ለመሥራት እየተዘጋጀ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡

አቶ አድማሱ የፒቲኤ ባንክ አመራርነቱን ሲረከቡ ባንኩ አንድ ቢሊዮን ዶላር ሀብት እንደነበር ገልጸው፣ በአሁኑ ወቅት ግን አራት ቢሊዮን ዶላር ሊደርስ መቻሉን፣ በባንኩ ባለድርሻ እንዲሆኑ ከሚፈልጉት መካከል ደቡብ ሱዳን፣ ማዳጋስካርና ሞዛምቢክ እንደሚጠቀሱ አስታውቀዋል፡፡ በባንኩ ድርሻ ያላቸው አገሮች ብዛት ከ20 በላይ መድረሱን፣ ከዚህ በተጨማሪ በተቋም ደረጃ በባንኩ ኢንቨስት የሚያደርጉትን ባለድርሻዎች ጭምሮ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከ19 ወደ 30 ማደጋቸውን ፕሬዚዳንቱ አስታውሰዋል፡፡ ከጡረታ ፈንድ፣ ከአገሮች የሚዋጣ ተቀማጭ ፈንድ፣ እንዲሁም ከኢንሹራንስ ኩባንዎች ተቀማጭ ሒሳብ ራሱን ፋይናንስ በማድረግ በባንኩ አባል አገሮች ላይ ይደርስ የነበረውን የመዋጮ ጫና መቀነሱን አቶ አድማሱ አስረድተዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች