Tuesday, March 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበሽብርተኝነት የተከሰሱ እስረኞችን ለማስለቀቅ በህቡዕ ሲንቀሳቀሱ ተደርሶባቸዋል የተባሉ ተጠርጣሪዎች ተከሰሱ

በሽብርተኝነት የተከሰሱ እስረኞችን ለማስለቀቅ በህቡዕ ሲንቀሳቀሱ ተደርሶባቸዋል የተባሉ ተጠርጣሪዎች ተከሰሱ

ቀን:

የሽብርተኝነት ክስ ተመሥርቶባቸው ጥፋተኛ የተባሉትን እነ አቡበከር አህመድንና ክሳቸው በመታየት ላይ የሚገኙትን እነ ኤልያስ ከድርን ከእስር ለማስፈታት በአዲስ አበባ፣ በወልቂጤ፣ በወራቤ በጅማና በአዳማ ከተሞች በህቡዕ ተደራጅተው የአመጽ ድርጊት ለመፈጸም ሲንቀሳቀሱ ተደርሶባቸዋል የተባሉ 20 ተጠርጣሪዎች ላይ፣ ሐምሌ 15 ቀን 2007 ዓ.ም. የሽብርተኝነት ክስ ተመሠረተባቸው፡፡

ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ ሐምሌ 13 ቀን 2007 ዓ.ም. ጽፎ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት ያቀረበው ክስ እንደሚገልጸው፣ አመፅ ለመፈጸም በህቡዕ ተደራጅተው ሲንቀሳቀሱ ተደርሶባቸዋል የተባሉት ተጠርጣሪዎች ከድር መሐመድ፣ ነዚፍ ተማም፣ ካሊድ መሐመድ፣ ፉአድ አብዱልቃድር፣ ኢብራሂም ከማል፣ አብዱ ጀባር፣ ሁሴን አህመድ፣ ሀሚድ መሐመድ፣ ቶፊቅ ሚስባህ፣ ዑስማን አብዱ፣ መሐመድ ኑሪ፣ አብዱልሀፊዝ ሺፋ፣ ዳርሰማ ሶሪ፣ ፍፁም ቸርነት፣ ሀሮን ሀይረዲን፣ ሸህቡዱን ነስረዲን፣ አያትል ኩበራ፣ ሐሺም አብደላ፣ ሙዳብ አሚኖና መሐመድ ከማል ናቸው፡፡

ተጠርጣሪዎቹ የወንጀል ሕግ 32(1/ሀ)ንና 38(1)ን እንዲሁም የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 7(1)ን በመተላለፍ፣ ሕዝበ ሙስሊሙን ወደ አመፅ በማስገባትና የሽብር ተግባር በመፈጸም፣ በመንግሥት ላይ ጫና በመፍጠርና አማራጭ በማሳጣት በሽብርተኝነት ተከሰው ጥፋተኛ የተባሉትንና ክሳቸው በመታየት ላይ ያሉትን ተከሳሾች፣ ከእስር ለማስለቀቅ ሲንቀሳቀሱ እንደነበር ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡

የሙስሊሙ ማኅበረሰብ መፍትሔ አፈላላጊ ናቸው የሚባሉትን ኮሚቴዎች መንግሥት በግፍ እንዳሰራቸው በመግለጽ፣ እንዲሁም የመጅሊስ አመራሮችን ለማስቀየር ሕዝብ ሙስሊሙን ወደ አመፅ ሊያስገቡ የሚችሉ የቅስቀሳ በራሪ ወረቀቶችንና ስቲከሮችን በማዘጋጀት፣ በአዲስ አበባ፣ በጅማና በወልቂጤ ከተሞች መበተናቸውን ክሱ ያብራራል፡፡ ሕገወጥ ሠልፎችን በማዘጋጀትና የቅስቀሳ ጥሪ ማድረጋቸውንም ያክላል፡፡

አንደኛ ተከሳሽ ከድር መሐመድ ከ2004 ዓ.ም. መጨረሻ ጀምሮ በአዲስ አበባ አንዋር፣ ቤኒንና አወሊያ መስጊዶች በተካሄዱ አመፆች ላይ መሳተፉን ክሱ ጠቁሞ፣ ‹‹ድምፃችን ይሰማ፣ የታሠሩ ኮሚቴዎቻችን ይፈቱ፣ የሀበሽ አስተምህሮን መንግሥት በኃይል ሊጭንብን አይገባም›› በማለት በዓመፁ መሳተፉን ገልጿል፡፡ ተጠርጣሪው በቁጥጥር ሥር እስከዋለበት የካቲት 10 ቀን 2007 ዓ.ም. ድረስ በአንዋር መስጊድ ተመሳሳይ መፈክሮችን ሲያሰማ እንደነበርና ‹‹መጅሊሱ አይወክለንም፣ መንግሥት ከሃይማኖታችን ላይ እጁን ያንሳ›› የሚሉ ኅብረተሰቡን ወደ አመፅ የሚያስገቡ ጽሑፎችን ሲበትን እንደነበር በክሱ በዝርዝር ተገልጿል፡፡

በሸሪያ ሕግ የሚመራ እስላማዊ መንግሥት ለመመሥረት የሽብር እንቅስቃሴ በመላ አገሪቱ በማካሄድ መንግሥትን ከሥልጣን ለማውረድ፣ በ2006 ዓ.ም. የካቲት ወር ላይ ከጅማ ከተማ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ከሌሎቹ ግብረ አበሮቹ ጋር ሆኖ ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ታስረው ከሚገኙትና በተከሰሱበት የሽብርተኝነት ድርጊት ወንጀል ጥፋተኛ ከተባሉት ውስጥ አህመዲ ጀማልን ማነጋገሩን ክሱ ያስረዳል፡፡

በጅማ ከተማ የቀዘቀዘውን አመፅ ለማስቀጠል ቀስቃሽ በራሪ ወረቀቶችን በማዘጋጀትና ፎቶ ኮፒ በማድረግ፣ ለጅማው ቡድን አመፅ መሪ ‹አሚር› ነዚፍ ተማም መላኩንም ያክላል፡፡

ተጠርጣሪዎች በአጠቃላይ በአዲስ አበባ፣ በወልቂጤ፣ በወራቤ፣ በጅማና አዳማ ከተማ በህቡዕ በመደራጀት፣ አመፅ ቀስቃሽ ወረቀቶች በመበተን፣ በሽብርተኝነት ተከሰውና ጥፋተኛ ተብለው ቅጣታቸውን በመጠባበቅ ላይ ያሉት እስረኞችን ለማስፈታት፣ በስልክ ግንኙነት በማድረግ፣ በመገናኘትና አባላትን በመመልመል፣ በህቡዕ በመደራጀት በመሳተፋቸው፣ በዋና ወንጀል አድራጊነት የሽብርተኝነት ክስ እንደተመሠረተባቸው የዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹ከኦነግ ሸኔ ጋር ያለውን ግጭት በሰላም ለመፍታት ከፍተኛ ፍላጎት አለን›› ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ

መንግሥት ከ‹‹ኦነግ ሸኔ››ጋር ያለውን ግጭት በሰላም ለመፍታት ከፍተኛ ፍላጎት...

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...