Monday, June 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ከአገሪቱ ባሻገር ኩባንያዎችም በካፒታል ገበያው ውስጥ ብዙ መሥራት የሚችሉበት ጊዜ ይመጣል››

አቶ አድማሱ ይልማ ታደሰ፣ የፒቲኤ ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚና ፕሬዚዳንት

በጥቂት ዓመታት ውስጥ የምሥራቅና የደቡባዊ አፍሪካ የንግድና ኢንቨስትመንት ባንክን (ፒቲኤ) በመለወጥና የውስጥና የውጭ አሠራሮቹን በማሻሻል፣ በአመራራቸው ምክንያት በመጣው ለውጥ ሳቢያ ባንኩ በአፍሪካ ተፈላጊ እየሆነ መምጣቱ ይነገራል፡፡ በርካታ የምሥራቅና የደቡባዊ አፍሪካ አገሮችን ያቀፈው ፒቲኤ ባንክ፣ የኮሜሳ ባንክ እየተባለም ይጠራል፡፡ በኢትዮጵያም የባንኩ ዕውቅና እየጎላ መጥቷል፡፡ በተለይ ባለፈው ዓመት ለኢትዮጵያ አየር መንገድና ለሐባሻ ሲሚንቶ በጠቅላላው የ90 ሚሊዮን ዶላር ብድር መስጠቱ ጎልቶ ይታወሳል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ግማሽ ቢሊዮን ዶላር ለኢትዮጵያ ኩባንያዎችና የመንግሥት የልማት ድርጅቶች በማቅረብ ብድር አመቻችቷል፡፡ ከጥቂት ቀናት በፊት በአዲስ አበባ የፋይናንስ ለልማት ጉባዔ ላይ የተገኙት አቶ አድማሱ ይልማ ታደሰ፣ የፒቲኤ ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚና ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡ ፕሬዚዳንቱ እንዳብራሩት፣ ባንካቸው በኢትዮጵያ በቱሪዝምና በአምራች ኢንዱስትሪው ላይ፣ በቱሪዝም መስክ በተለይ ደግሞ በሆቴል ግንባታ ፕሮጀክቶች ፋይናንስ የማቅረብ ፍላጎት አለው፡፡ ባንኩ በዳያስፖራው ማኅበረሰብና በሌላውም አፍሪካ ሕዝብ ዘንድ ከውጭ ሊገኝ የሚችል የኃዋላ ገንዘብን ወደ ኢንቨስትመንት ማምጣት የሚቻልበትን ሥልት በመቀየስ እንደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ካሉ የአገር ውስጥ ተቋማት ጋር የመሥራት ዓላማ እንዳለውም አቶ አድማሱ ገልጸዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር በባለቤታቸው ሱፐር ሞዴልና ዲዛይነር አና ጌታነህ የተቋቋመው ‹‹ኢትዮጵያን ችልድረንስ ፈንድ›› የተባለው ፋውንዴሽን እስከ 900 የሚጠጉ ሕፃናትን በነፃ የሚያተምርበት ትምህርት ቤት ከፍቶ ሲሠራ 15 ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ አንዳንዶቹም የውጭ ነፃ የትምህርት ዕድል እያገኙ በመሄድ የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ እንደሚገኙም ከአቶ አድማሱ ጋር ከተደረገው ቆይታ ለመረዳት ተችሏል፡፡ በቅርቡ አዲስ የውጭ ብድር ያገኛሉ ተብለው ከሚጠበቁት ባሻገር የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ስለሚለቀቅላቸው የብድር መጠንና ሌሎች ጉዳዮችን በሚመለከት አቶ አድማሱን ብርሃኑ ፈቃደ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ዓምና ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቆይታ ፒቲኤ ባንክ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጨምሮ የተወሰኑ ድርጅቶች ብድር ማግኘታቸውን ገልጸው ነበር፡፡ ዘንድሮ ደግሞ ፋይናንስ ለልማት ጉባዔ ላይ ከትልልቅ ባለሥልጣናት ጋር ሲነጋገሩ  ነበር፡፡ ዘንድሮ ምን ይፋ የሚደረግ ነገር ይኖራል?

አቶ አድማሱ፡- ፋይናንስ ለልማት ጉባዔ ዘንድሮ ሲካሄድ በተለየ ወቅት ነው፡፡ የሚሊኒየሙ መባቻ ወቅት በሜክሲኮ የተደረገው የመጀመሪያው ጉባዔ ላይ ውይይቶቹ በሀብታም ለጋሽ አገሮችና በደሃ በአገሮች መካከል የተደረጉ በመሆናቸው የፋይናንስ ውይይቱ ትኩረት በአንድ ነገር ላይ ብቻ ያጠነጠነ ነበር፡፡ መካከለኛ ገቢ ያላቸው አገሮች አስፈላጊነት፣ ከአገር ውስጥ የገቢ ምንጮች ተፈላጊውን ገንዘብ ማሰባሰብ፣ በደቡባዊ ንፍቀ ክበብና በአፍሪካ የሚገኙ የፋይናንስ ተቋማት አስፈላጊነት ከ15 ዓመታት በፊት የውይይት ተካፋይና የውይይት ነጥቦች አልነበሩም፡፡ ስለዚህ በዚህ ፋይናንስ ለልማት ጉባዔ ላይ መገኘት ለእኔ አዲስ ልምድ ከመሆኑም በላይ፣ ልማትን እንዴት ፋይናንስ ማድረግ ይቻላል በሚለው የዓለም ውይይት ላይ መሳተፍ በተለይ ፒቲኤ ባንክ ባለድርሻ የሆነበት አጋጣሚ ነው፡፡ በአፍሪካ ኢንቨስተሮች ፈንድ የምንደረግ ተቋም ብንሆንም፣ በተወሰነ ደረጃ እንደ ቻይና ያሉ መካከለኛ ገቢ ያላቸው አገሮችም በባንኩ ኢንቨስት አድርገዋል፡፡ የቡድን ሰባት አገሮች የዓለም ባንክን ወይም የአፍሪካ ልማት ባንክን ፋይናንስ እንደሚያደርጉት ፒቲኤን ፋይናንስ አያደርጉትም ነበር፡፡ በአፍሪካ ካፒታል እንዲስፋፋና የአፍሪካ ተቋማትም በተለይ በፋይናንስ መስክ የተሰማሩት በዲስፕሊን የታነፁና በሥራ በሚተገበሩ ስታንዳርዶች የሚሠሩ መሆናቸውን ለማሳየት እኛ ጥሩ ታሪክ አለን፡፡ በአሁኑ ወቅት ይህ መሆኑ በዓለም የውይይት መድረክ ላይ የመሳተፍና ሚናውን መወጣት የሚችል አካል እንድትሆን ያበቃሃል፡፡ የዓለም ወሳኝ ተዋናዮች ዘላቂ የልማት ግቦች በአፍሪካ እንዲሳኩ ከአፍሪካ የፋይናንስ ተቋማት ጋር መሥራት እንደሚቻል፣ ለዚህ ተግባር እንደ አገናኝ ሆነው ሊሠሩ የሚችሉ ተዓማኒና ምስጉን የፋይናንስ ተቋማት መኖራቸውም እየተነገረ ነው፡፡ ስለዚህ በተለያዩ ስብሰባዎች ታድመን ጥሩ ውይይቶችን አካሂደናል፡፡

ሪፖርተር፡- ፋይናንስ ለልማት ጉባዔን ካነሱ አይቀር ከስብሰባዎቹ መካከል የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ ለኢትዮጵያ ብድር የሰጠበት መድረክ አንዱ ነው፡፡ ፒቲኤ ከአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ ጋር ያለው ግንኙነት ምንድነው?

አቶ አድማሱ፡- የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ በዓለም ላይ ካሉ የበዙ ባለድርሻ ተቋማት መካከል አንዱ ሲሆን፣ በአውሮፓ ሀብታም አገሮች ባቤትነት የሚተዳደርና ደህና ፈንድ የሚመደብለት ተቋም ነው፡፡ ደረጃውም ‹‹ትሪፕል ኤ›› የሚባለው ከፍተኛው እርከን ነው፡፡ እርግጥ አፍሪካና አውሮፓ ጠንካራ ታሪካዊ ትስስር አላቸው፡፡ ከዚህ ቀደም የባንኩን ፈንድ ለማግኘት የሚያስችል አቋም አልነበረንም፡፡ ባለፈው ዓመት ግን ለባንኩ ስኬታማ የሆንበትን ጉዳይ አቅርበናል፡፡ በአፍሪካ ከእኛ ጋር አብረው ቢሠሩ በምሥራውና በደቡባዊ አፍሪካ ምስጉን አጋር እንደምንሆናቸው በማሳየታችን አብረውን ለመሥራት ተስማምተዋል፡፡ 80 ሚሊዮን ዩሮ አቅርበዋል፡፡ በአፍሪካ ትልቁን የአነስተኛና የመካከለኛ ዘርፍ የብድር ፕሮግራም ይፋ አድርገናል፡፡ ለእኛ ከአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ ጋር ያደረግነው የፋይናንስ ትብብር የመጀመሪያው ሲሆን፣ ትልቅ ገንዘብም ይዘው የመጡበት አጋጣሚ ነው፡፡ ፒቲኤ ባንክ ከጀርባው የየትኛውም አገር ዋስትና ሳይጠየቅ ነው የመቶ ሚሊዮን ዶላር ፋይናንስ እያገኘ ያለው፡፡ አገራዊ የልማት ባንክ ስትሆን የትኛውም የምትወስደው ነገር በሙሉ በአገሪቱ ላይ የሚታሰብ ነው፡፡ በመሆኑም ፈንድ የሚያደርጉ አካላት የተቋማቱን ጥንካሬ ሳይሆን የመንግሥቱን ጥንካሬ ይመለከታሉ፡፡ እኛ ግን በራሳችን በኩል ባደረግነው ጥረትና በራሳችን አቅም ያገኘነው ነው፡፡

ከአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ ጋር ባድረግነው ግንኙነት ደስተኞች ብንሆንም፣ ነገር ግን ከዚህ  ባንክ ባሻገር ከሌሎችም ጋር ግንኙነታችንን እያሰፋን ነው፡፡ ይህ የሆነውም ባደረግነው ሪፎርም፣ ባሻሻልነው የባንኩ አስተዳደር ጭምር ነው፡፡ ከጀርመኑ ኬኤፍደብሊው ጋር ፈንድ እንዲያደርጉን ወደ አጋርነቱ ገብተናል፡፡ ከብራዚሎች ጋር ስምምነት ፈርመናል፡፡ ቻይኖቹ ከዚህ ቀደም ከሰጡት በተለይ ፈንዳቸውን አሳድገዋል፡፡ በፒቲኤ ባንክ ያላቸውን የአክሲዮን ድርሻ በእጥፍ ጨምረዋል፡፡  በርካታ እየተከናወኑ ያሉ ነገሮች አሉ፡፡ ሁልጊዜ የምንለው ነገር አለ፡፡ እነሱ እንደሚሉት ሥራው እንጂ መምጣታቸው አይቀርም፡፡ ከሦስትና ከአራት ዓመት በፊት ለባንኩ አዲስ ስትራቴጂ ይዘን መጣን፡፡ በአፍሪካ ተዓማኒነት ያለው፣ በዲሲፕሊንና በስታንዳርዶች የሚመራ የአፍሪካ ፋይናንስ ተቋም መፍጠር የምችልበት ዕድል እንዳለ አሳወቅን፡፡ ዲሲፕሊን ማለት ትክክለኛውን የብድር ውሳኔ መወሰን፣ ባንኩን ችግር ውስጥ ሊጥሉ በሚችሉ ነገሮች አለመዋጥ ወይም ዕይታ ቢስ አለመሆን ለማለት ነው፡፡ ባንኩን ዘመናዊ በማድረጋችን የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ ከዋናዎቹ አንዱ አጋር ሆኖ አብሮ ለመሥራት ብቅ አለ፡፡ ይህ የመጀመሪያው ቢሆንም ግንኙነታችን እያደገና እየጠነከረ እንደሚመጣ ተስፋ እናደርጋለን፡፡ የምዕራቡ ዓለም የፋይናንስ ተቋማት ከአፍሪካ ተቋማት ጋር አብረው ለመሥራት ሲመጡ ትልቅ በራስ መተማመንን የሚፈጥር ነው፡፡ በራሱ ብዙ የሚናገረው አለው፡፡ ገንዘቡም ቢሆን ትንሽ አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ ሁሉ መሆኑ በባንኩ የማበደር አቅም ላይ የሚጨምረው ነገር ምንድነው?

አቶ አድማሱ፡- ባንኩ ባለፉት ሦስትና አራት ዓመታት ውስጥ በሦስት እጥፍ አድጓል፡፡ እ.ኤ.አ. እስካለፈው ጁን 30 ድረስ የሒሳብ መዝገባችን አራት ቢሊዮን ዶላር መድረሱን ያሳያል፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት አንድ ቢሊዮን ዶላር ላይ የተገታ ነበር፡፡ ጠንካራ ዕድገት አሳይተናል፡፡ ዕድገቱም በበርካታ መስኮች የተገኘ ነው፡፡ በከፍተኛ መጠን ከሚያድጉ እንደ ኢትዮጵያ ካሉ አገሮች ጋር እየሠራን ነው፡፡ ሩዋንዳ፣ ታንዛንያ፣ ዛምቢያ ጠንካራ ኢኮኖሚያ ያላቸውና አብረን እየሠራን የመጣንባቸው አገሮች ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት ወደ ሞዛምቢክ ለመስፋፋት እየሠራን ነው፡፡ ደቡብ ሱዳን እንድትቀላቀለን እንጠብቃለን፡፡ ማዳጋስካርም በቅርብ ጊዜ ውስጥ ትቀላቀለናለች፡፡ በጥቂት ጊዜ ውስጥ ከ20 በላይ አገሮች በባለድርሻነት የሚገኙበት ባንክ በመሆን የአፍሪካ ልማት ባንክን ግማሽ ያህል ግዝፈት ይኖረናል፡፡ ዋናው ጠንካራ ትኩረታችን በምሥራቃዊና በደቡባዊ አፍሪካ አገሮች ላይ ነው፡፡ ላለፉት አምስት ዓመታት ከ25 እስከ 30 በመቶ በዓመት ዕድገት አስመዝግበናል፡፡ ይህ በአፍሪካ ካለው የዕድገት መጠን አራት ዕጥፍ የሚበልጥ ነው፡፡ ምሥራቃዊና ደቡባዊ አፍሪካ በኢኮኖሚ ስድስት በመቶ በዓመት እያደገ ነው፡፡ ምሥራቅ አፍሪካ እንዲያውም በፍጥነት በማደግ የተሻለ አካባቢ ነው፡፡ እኛ ግን በ25 በመቶና ከዚያ በላይ እያደግን በመሆኑ ጠንካራ አቅም አለን፡፡ ለአንድ የፋይናንስ ተቋም ከአማካይ የኢኮኖሚ ዕድገት በላይ በብዙ እጥፍ በልጦ ማደጉ ጤናማ ነው፡፡ ይህንን ለማሳካት ፈንድ ማሰባሰብ ችለናል፡፡

የልማት ባንኮች አብዛኛውን ጊዜ ከመንግሥት በሚያገኙት ፈንድ ላይ ጥገኛ ይሆናሉ፡፡ የአክሲዮን ባለድርሻነቱም መቶ በመቶ የመንግሥታት ብቻ ሆኖ ይታያል፡፡ የልማት ባንኮች የረጅም ጊዜ ፋይናንስ የሚያቀርቡ በመሆናቸው የገንዘብ ምንጫቸው የግድ የግብር ከፋዮች ገንዘብ ብቻ መሆን የለበትም ብለን ተነሳን፡፡ ከአፍሪካ ተቋማት የቁጠባ ተቀማጭ ገንዘብ ማግኘት እንችላለን ብለን ተነሳን፡፡ በመሆኑም የጡረታ ፈንድ፣ የኮርፖሬት ገንዘቦችን፣ የኢንሹራንስ ኩባንያዎችንና የአገሮችን ሀብት የሚያስተዳድሩ ተቋማትን ወይም ‹‹ሶቨሪን ዌልዝ ፈንድ›› ከመሳሰሉት ተቋማት ገንዘብ ማመንጨት ይቻላል፡፡ እነዚህ ተቋማት የረጅም ጊዜ ገንዘብ በእጃቸው ይዘው የተቀመጡ ናቸው፡፡ እንዲህ ያሉትን ተቋማት ሆነ ብለን አተኮርንባቸው፡፡ ይህን ማድረጋችን ባለድርሻ አገሮች ተጨማሪ ገንዘብ እንዲያዋጡ ላለማስጨነቅ ስንልም ነው፡፡ ባለአክሲዮን መንግሥታቱ ስትራቴጂያቸንን ወዲያውኑ ተረድተው ሲፈቅዱ፣ በአንፃሩ በባንኩ ኢንቨስት የሚያደርጉ ተቋማት እምነት እንዲጥሉበት የሚያስችሉ ስታዳርዶችን ማሟላት እንደሚገባው አሳስበውናል፡፡ ወደ ቁጠባ ፋይናንስ ሲመጣ ሥነ ምኅዳሩ ከተለመደው የባለአድርሻ አገሮች መዋጮ የተለየ አካሄድ አለው፡፡ የጡረታ ፈንድ ወይም የኢንሹራስ ኩባንያ በባንክ ኢንቨስት ሲያድርጉ ለሚኖርህ ቁርጠኝነትና ‘ሪስክ ማኔጅ’ የምታደርግበትን ተዓማኒ አሠራር ዘርግተህ ማየት ይፈልጋሉ፡፡ ምክንያቱም የሚሰጡህ ገንዘብ የግብር ከፋይ ገንዘብ አይደለም፡፡ የጡረተኞች ገንዘብ ነው፡፡ በቀላሉ የሚጠፋ ካፒታል አይደለም ብዬ ብገልጸው ጥሩ ይመስለኛል፡፡

እርግጥ ነው የታክስ ከፋዮች ገንዘብ በቀላሉ ይጠፋል ማለት ሳይሆን፣ በዓለም ላይ ያለው ተሞክሮ እንደሚሳየው ከተቋማት ካፒታል ወይም ከተቋም ኢንቨስመንት ጋር አብረህ ስትሠራ ትክክለኛነቱና ኃላፊነቶቹ የተለዩ ይሆናሉ ለማለት ነው፡፡ በአንድ በተወሰነ ወቅት ትርፍ መስጠት አለብህ፡፡ ባለፉት ሦስት ዓመታት ያንን ማድረግ ችለናል፡፡ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ስምንት ተቋማትን አክሲዮን እንዲገቡ አድርገናል፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ የአክሲዮን ባለድርሻዎች ቁጥር ከ19 ወደ 30 እንዲያድግ ማድረግ ችለናል፡፡ በርካቶች የአፍሪካ የጡረታ ፈንድ ተቋማትና የአፍሪካ ኢንሹራንስ ኩባንያዎች በባንካችን ኢንቨስት ያደርጋሉ የሚል ዕምነት አልነበራቸውም፡፡ ጉዳያችንን አቅርበን፣ ያለንን የአፈጻጸም ብቃት አሳይተን የምናወራቸው በእጃችን ስለሌለው ነገ ሳይሆን አሁን ስላለው ተጨባጭ ነገር፣ ነገ ዛሬ መሆኑን በትክክል ለማሳየት ችለናል፡፡ እነዚህ እንግዲህ ለማሳካት የቻልናቸውና የቁርጠኝነታችንን ጥልቀት የሚያሳዩልን ነጥቦች ናቸው፡፡ በሪፎርም፣ በፈጠራ፣ በሠራተኞች ጥራት፣ ሰዎችን በአፈጻጸማቸው ልክ ተጠያቂ እንዲሆኑ የማድረግ ሥራዎችን በመሥራት ያገኘናቸው ውጤቶቸ ናቸው፡፡ በመሆኑም ለባንኩ ውጤታማነት ምስክር እየሆኑ መጥተዋል፡፡ መንግሥታቱም ባሳየነው ውጤት ደስተኞች ናቸው፡፡ ምክንያቱም በየጊዜው በራቸውን እያንኳኳን ገንዘብ እንዲያዋጡ ከመጠየቅ አሳርፈናቸዋል፡፡ መንግሥታቱ በርካታ ቀዳዳዎችን መድፈን አለባቸው፡፡ ገቢ በሚያስገኙ መስኮች ላይ ኢንቨስት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ለምሳሌ እንደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ወይም እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ያሉት ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህ ተቋማት በኢትዮጵያ ቁልፍ ተብለው የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በመንግሥት የሚተዳደሩ ቢሆንም እንኳ አፈጻጸማቸው ከሚገባው በላይ ጥሩ ደረጃ ያለው ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ፒቲኤ ባንክ ዓምና ለኢትዮጵያ አየር መንገድና ለሐበሻ ሲሚንቶ ማበደሩ ይታወሳል፡፡ እርስዎ ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቆይታ ግማሽ ቢሊዮን ዶላር ለኢትዮጵያ ኩባንያዎች የሚውል ብድር መመደቡን ገልጸው ነበር፡፡ ከዚያ ወዲህ ምን አዲስ ነገር አለ ሊባል ይችላል?

አቶ አድማሱ፡- በርካታ ብድር ልንሰጥባቸው የምንችላቸው ጥያቄዎች ቀርበዋል፡፡ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ አዲስ 100 ሚሊዮን ዶላር ብድር ከሁለት ወር በፊት አፅድቀናል፡፡ ለንግድ ባንክም አዲስ 200 ሚሊዮን ዶላር አፅድቀናል፡፡ ትልቅ እንቅስቃሴ አለ፡፡ እንደ ኢነርጂ፣ አግሪ ቢዝነስ እንዲሁም ቱሪዝም የመሳሰሉት ፐሮጀክቶችን ፋይናንስ ለማድረግ እየተለመለከትን ነው፡፡ ብድር ልንሰጥባቸው የምንችልባቸው መስኮች ብዙ አሉ፡፡ ፕሮጀክቶችን ወደ መመዘኑ እየገባን ነው፡፡ ነገሮች እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡ ሆኖም አፈጻጸም ዋናው በመሆኑ ሁሉም አካል የተቀመጡ ስታንዳርዶችን ለማሟላት በሚችልበት አቅም መነሳት ይጠበቅበታል፡፡ እኛ ቢዝነስ ለመሥራት ክፍት ነን፡፡ ነገር ግን ሁሉም የባንኩን መመዘኛዎች ማሟላት ይጠበቅበታል፡፡ ያንን ማድረግ እንደሚችሉ ያሳዩና ያስመሰከሩ በርካቶች  አሉ፡፡ ለምሳሌ የኢትጵያ ንግድ ባንክ፣ ኢትዮ ቴሌኮም እንዲሁም የባህር ትራንስፖርትና የማሪታይም አገልግሎት ድርጅት አብረናቸው ለመሥራት ክፍት ከሆኑት ተቋማት መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ የምንወክለው ዓለም አቀፍ ድንበር ተሸጋሪ ካፒታል በመሆኑ፣ ዕምነት ከሚጣልባቸው አጋሮች ጋር መሥራት ይጠበቅብናል፡፡ በምንወስደው ‘ሪስክም’ ጠንቃቃ መሆን ይኖርብናል፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ ካበደራችኋቸው የመንግሥት ተቋማት ባሻገር ከግሉ ዘርፍ አክሲዮን ማኅበራትና ከሌሎች ኩባንዎች ጋር ያላችሁ ግንኙነት እንዴት ይታያል?

አቶ አድማሱ፡- ለግሉ ዘርፍ በራችን ክፍት ነው፡፡ ነገር ግን መታየት ያለባቸው እውነታዎች አሉ፡፡ በዶላር የሚሰጡ ብድሮችን በሚመለከት አገሪቱ የምትከተለው የፖሊሲ ማዕቀፍ አለ፡፡ ስለዚህ ብድሮቻችንን ኤክስፖርት ላይ ለሚያተኩሩ ኩባንያዎች ማቅረብ ይኖርብናል፡፡ ለዚህም ነው በቱሪዝም ዘርፍ ለምሳሌ ሆቴሎች ላይ የምናተኩረው፡፡ የአግሪ ቢዝነስ ፕሮጀክቶችን እያየን ነው፡፡ አምርተው ለውጭ መላክ የሚችሉ የተመረጡ የአምራች ኢንዱስትሪ ፕሮጀክቶችን እያየን ነው፡፡  እንዲህ ያሉትን በርካታ ፕሮጀክቶች ፋይናንስ ለማድረግ ሕጋዊ ስምምነቶችን ገና አልፈረምንም፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ፕሮጀክቶች ወደ ፍፃሜ ተቃርበዋል፡፡ በቦርድ በኩል ያፀደቅናቸው ነገር ግን ሕጋዊ ስምምነት ያልፈጸምንባቸው ፕሮጀክቶች አሉ፡፡ ስምምነቱ ሳይፈጸም ስለነሱ አሁን መናገር አልችልም፡፡ አንድ በቅርቡ የፀደቀ የአምራች ኢንዱስትሪ ፕሮጅክት አለ፡፡ በቅርቡ ይፋ ይደረጋል፡፡ እነዚህ በሙሉ በግሉ ዘርፍ የሚተዳደሩ ፕሮጀክቶች ናቸው፡፡ ፒቲኤ ባንክ ዓለም አቀፍ ፋይናንስ አቅራቢ እንደመሆኑ መጠን፣ ፕሮጀክቶቹ ዓለም አቀፍ ፋይናንስ ለማግኘት የሚያስችላቸውን ስታንዳርዶችን በማሟላት ብድር ለማግኘት ብቁ ሆነው የተገኙ ፕሮጀክቶች ናቸው፡፡

አለመታደል ሆኖ እንዲህ ያለውን ፋይናንስ ለማግኘት ዝግጁ ላልሆኑ ድርጅቶች የማደበር አቅም የለንም፡፡ ድንበር ዘለል ፋይናንስ ውስብስብና በርካታ ቅድመ ሁኔታዎችን ማሟላት የሚጠይቅ በመሆኑ ለመበደር የሚያበቃ አቅም ሊኖርህ ይገባል፡፡ ባንኩ ሲመሠረት እንደ አፍሪካ ልማት ባንክና እንደ ሌሎቹ ሁሉ አገር ዓቀፍ የመንግሥት ተቋማትን ለማገዝ ነው፡፡ አነስተኛ የቢዝነስ ሥራዎችን ለመሥራት አንሻም፡፡ ምክንያቱም ያንን ለማድረግ የሚችሉ የአገር ውስጥ ተቋማት ስላሉ ማለት ነው፡፡ በበርካታ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ የምናደርገው ምንድነው ከተባለ በርካታ ብድሮችን ለአገር አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት በማቅረብ እንደ አገሮቻቸው የፖሊሲ ማዕቀፍ ማደበር እንዲችሉ እናግዛለን፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ከንግድ ባንክ ጋር የምናደርገው ይህነኑ ነው፡፡ ወደፊት የአገሪቱ ፖሊሲዎችና ድንጋጌዎች ሲለወጡ ከሌሎች ንግድ ባንኮች ጋር አብረን በመሆን የግሉን ዘርፍ ለመደገፍ እንሠራለን፡፡

ሪፖርተር፡- ስለ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እየጠቀሱ ከሆነ ከፍላጎቶቻችሁ ጋር ምን ያህል እየተጓዘ ነው ማለት ይቻላል?

አቶ አድማሱ፡- ብሔራዊ ባንክ የአገሪቱን የክፍያ ሚዛን ማስጠበቅና የውጭ ምንዛሪ ጉዳዮችን መቆጣጠር ይጠበቅበታል፡፡ አለመጣጣሞች እንዳይፈጠሩ መሥራት አለባቸው፡፡ ዶላር የማያመነጩ ፕሮጀክቶች በዶላር ብድር እንዳያገኙ ይፈልጋሉ፡፡ ይህ ቢሆን አለመጣጣም ይፈጥራል፡፡ በትክክልም በአገሪቱ ክፍያ ሚዛን ላይ የሚያስከትለው ተፅዕኖ ያሳስባቸዋል፡፡ ሁላችንም እንደምናውቀው አገሪቱ የዶላር እጥረት አለባት፡፡ በመሆኑም መንግሥት የውጭ ፋይናንሶች ወደ ኤክስፖርት ዘርፍ እንዲያመሩ አተኩሮ እየሠራ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አገሪቱ ወደ ካፒታል ገበያ ስለመግባቷ ወይም ዩሮ ቦንድን መቀላቀሏን በሚመለከት ምን ይላሉ?

አቶ አድማሱ፡- በመንግሥት በኩል የተወሰደው ዕርምጃ በጣም ጥሩ ነው፡፡ አገሪቱ የንግድ  ቦንድ ስታቀርብ የመጀመሪያዋ ነው፡፡ የመንግሥትን ብቻም ሳይሆን እንደ አንድ ሉዓላዊ አገር ለበርካታ አበዳሪዎች ያቀረበችበትና አበዳሪዎችም የአገሪቱን ብድር ሁኔታ መመልከት የጀመሩበት ጊዜ ነው፡፡ የውጭ ካፒታልን በማፈላለግ ረገድ ይህ የመጀመሪያው ዕርምጃ ነው፡፡ ሆኖም ወደፊት ከአገሪቱ ባሻገር ኩባንያዎችም በካፒታል ገበያው ውስጥ ብዙ መሥራት የሚችሉበት ጊዜ ይመጣል፡፡ የአገሪቱ ታሪክ በካፒታል ገበያው ላይ አወንታዊ ተቀባይነትን በማስገኘት ትልቅ ፍላጎት ሊፈጥር እንደሚችል ይታመናል፡፡ እንደማስበው ኢትዮጵያ በውጭው ዓለም ዲሲፕሊን በመጠበቅ ረገድ ጥሩ ስም አላት፡፡ ዲሲፕሊን ሲባል የውጭ ገንዘብ የሚተዳደርበትን መንገድ በተመለከተ ማለት ነው፡፡ ዕዳችንን በወቅቱ እንከፍላለን፡፡ ይህም ከውጭ ጥሩ መተማመን ገንብቷል፡፡ በርካታ የአፍሪካ አገሮች የካፒታል እጥረት፣ በተለይም የውጭ ካፒታል እጥረት እንዳለባቸው ግልጽ ነው፡፡ የአገር ውስጥ ገንዘብ በቀላሉ ማፍራት ይቻላል፡፡ ትልቁ ፈተና ግን የውጭ ምንዛሪን ማፍራትና የክፍያ ሚዛንን ማስጠበቅ ሲሆን፣ ይህንን ተንተርሰው የሚመጡ ፈተናዎችም አሉ፡፡ የኢኮኖሚያችንን ሚዛን ማስጠበቅ ተገቢ ነው፡፡ ሁልጊዜ ከዓለም እየተቀበልን መኖር አንችልም፡፡ ለዚህም ነው በኢንዱስትሪ ዘርፍ ለመመራት ትልቅ ግፊት የሚደረገው፡፡ በቱሪዝም መስክ፣ በኃይልና በማዕድን መስክም ትልቅ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ ችግሩን ለመፍታት የሚረዱ ወሳኝ መስኮች ናቸው፡፡ ሆኖም ጊዜ መውሰዱ ግድ ነው፡፡

በሌላ በኩል ለኢትዮጵያ በጣም ጠቃሚው ነገር የውጭ ኃዋላ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በውጭ የሚኖር በርካታ ቁጥር ያለው ሕዝብ ስላላት ለውጭ ምንዛሪ ትልቅ ምንጭ ሆኖ እየጠቀመ ነው፡፡ ከውጭ ኃዋላ የሚገኘው ምንዛሪ ከኤክስፖርት ከሚገኘው በላይ ነው፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ ሕዝቧን ኤክስፖርት ታደርጋለች ቢባል ሊያስኬድ ይችላል፡፡ በርካታ በውጭ የሚኖሩ የዳያስፖራው ማኅበረሰብ አባላት በጥሩ ሁኔታ እየሠሩ ነው፡፡ በርካቶች ወደ አገር ቤት ገንዘብ በመላክ ድጋፍ ሲያደርጉ በትጋት ነው፡፡ ሆኖም አብዛኛው ገንዘብ ለቤተሰብ መገልገያ ወይም ለፍጆታ የሚውል ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር ግን የዳያስፖራው ኢንቨስትመንት ወደ ትልልቅ ከተሞች በመምጣት ላይ ነው፡፡ አዲስ አበባ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ናት፡፡ ሐዋሳም በጣም ጥሩ እያገኘች ነው፡፡ ባህር ዳር፣ ጎንደር፣ መቀሌና ሌሎችም ከተሞች ቀላል የማይባል ኢንቨስትመንት እያገኙ በመሆናቸው ኢትዮጵያ በዚህ ኢንቨስትመንት በብዛት የመጠቀም ዕድል ይኖራታል፡፡ ከጥቂት ጊዜ በፊት ከዚምባብዌ መንግሥት ጋር የዳያስፖራ ቦንድ መሸጥ ጀምረን ነበር፡፡ እርግጥ እዚህ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ጥሩ ስኬት እንደተገኘ ይታወቃል፡፡ ሆኖም ጥያቄው ግን የቦንዱን ‘ሪስክ’ መጋራት ላይ ነው፡፡ በዚምባብዌ ጉዳይ ላይ ከሌሎች አጋሮቻችን ጋር በመሆን የቦንዱን የብድር አቅም በማሳደግ በውጭ የሚኖሩ ዚምባቤያውያን ልበ ሙሉነት እንዲሰማቸውና ኢንቨስት እንዲያደርጉ አስችለናል፡፡ ምክንያቱም በአንድ በኩል ከቦንዱ በሌላ በኩል ዋስትና ከሰጠው አካል ጋር እንደሚገናኙ ስለሚያውቁ ነው፡፡ ይህ የሆነውም ፒቲኤ ባንክ ለቦንዱ ዋስትና በመስጠቱ ነው፡፡ እንደማስበው ይህንን በኢትጵያም ማድረግ እንችላለን፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ ልትጠቀምበት የምትችለው ብዙ ካፒታል በውጭ ስለሚገኝ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ስለዚህ ፒቲኤ ባንክ በኢትዮጵያ ተመሳሳይ የዳያስፖራ ቦንድ ሽያጭ ይጀምራል ማለት ነው?

አቶ አድማሱ፡- እዚህ ካሉ አጋሮቻችንና ባለድርሻዎቻችን ጋር በመሆን በመስኩ አዳዲስ ነገሮችን መፍጠር እንችላለን፡፡ ብሔራዊ ባንክ እንደ ተቆጣጣሪ አካል ቁልፍ የመሪነት ሚና በፋይናንስ መስክ ላይ እንደሚኖረው ግልጽ ነው፡፡ እርግጥ እንደ ንግድ ባንክ ካሉ አገር አቀፍ ተቋማት ጋር በመሆን ወደ አገሪቱ ካፒታል በሚፈልስበት መንገድ ላይ በጋራ ልንሠራ እንችላለን፡፡ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ብቻም ሳይሆን የኢትዮጵያን ቦንድ ለመግዛት የሚፈልጉ በርካታ አፍሪካያውን ይኖራሉ፡፡ በርካታ የአፍሪካ ካፒታል በውጭው ዓለም በብዛት ይገኛል፡፡ ዋናው ግን ልበ ሙሉ ሆነው እንዴት ኢንቨስት ሊያደርጉ ይችላሉ የሚለውን ጥያቄ መመለስ ነው፡፡ ይህ ጉዳይ በአፍሪካ መሪዎች ዘንድ ውይይት እየተደረገበት የሚገኝ ይመስለኛል፡፡ የአፍሪካ መሪዎችን የአፍሪካን ካፒታል ለአፍሪካ ጥቅም እንዴት ማዋል እንችላለን እያሉ ነው፡፡ በውጭ የሚኖሩ አፍሪካውያን እንዴት ብንሠራ ነው ልበ ሙሉነት ተሰምቷቸው ኢንቨስት የሚያደርጉት እያሉ በመምከር ላይ ይገኛሉ፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያም ሁለተኛውን ዩሮ ቦንድ ወደፊት ለሽያጭ አቅርባ ቢያንስ አንድ ሦስተኛውን በውጭ የሚኖረው ዳያስፖራ ሲገዛ ይታየኛል፡፡

ሪፖርተር፡- ከዩሮ ቦንድ አኳያ በሌላ በኩል ሊነሳ የሚችለው ጥያቄ በቅርቡ የዓለም ባንክ ካወጣው ሪፖርት ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ ባንኩ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ያወጣው ሪፖርት የአገሪቱ የዕዳ ጫና እየጨመረ በመምጣት ከሦስት ዓመት በኋላ የኢኮኖሚውን 65 በመቶ ድረስ ሊይዝ ይችላል የሚል ነው፡፡

አቶ አድማሱ፡- የቅርብ ጊዜ አኃዙ ምን እንደሆነ አላውቅም፡፡ ሆኖም ዩሮ ቦንድ ለገበያ በቀረበበት ወቅት የአገሪቱ ብድር ከኢኮኖሚው አኳያ የነበረው ድርሻ 60 በመቶ አልደረሰም ነበር፡፡ ያኔ 40 በመቶ ገደማ ላይ ስለነበር ያን ያህል ትልቅ አልነበረም፡፡ የኢኮኖሚው ዕድገት አሁን ባለው የስምንት በመቶ ገደማ የዕድገት ፍጥነት ከቀጠለና አዲስ የሚመጣው ብድርም ከኢኮኖሚው ዕድገት ጋር በተመሳሳይ ካላደገ የብድር ዕዳ ጫናው የሚያሰጋ አይሆንም፡፡ ጠቃሚው ነገር ኢትዮጵያ ጠንካራ ዕድገቷን ማስጠበቋ ነው፡፡ የግሪክን ጉዳይ መመልከት እንችላለን፡፡ ግሪክ አሁን ለምትገኝበት ሁኔታ የተዳረገችው ኢኪኖሚዋ ማደግ ስላልቻለ ነው፡፡ ዕድገት በሌለበት ኢኮኖሚያዊ ጠባይ ውስጥ ዕዳን መሸከም ቀላል አይሆንም፡፡

ሪፖርተር፡- ወደ ግል ጉዳይ እንመለስና እርስዎና ባለቤትዎ (የቀድሞዋ ሱፐር ሞዴልና ዲዛይነርና አና ጌታነህ) እዚህ ፋውንዴሽን አቋቁማችሁ ሕፃናትን እየረዳችሁ ነው፡፡ እንዴት እየሄደላችሁ ነው?

አቶ አድማሱ፡- እንግዲህ እኔ እንዲሁ አጋዥ ሆኜ ነው የምደግፈው፡፡ ከ15 ዓመት በፊት የመሠረተችው ፋውንዴሽን በቀድሞ ሥራዋ ከነበራት መልካም ስኬት ተነስታ ለአገሯ መልሳ መስጠትና ማበርከት የቻለችበት ነው፡፡ በመሆኑም ትምህርት ቤት ገንብታለች፡፡ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ጥሩ ኑሮ መኖር ያልቻሉ፣ ወላጆቻቸውን ያጡና ከማጣት እኩል በሆነ ደረጃ ላይ የሚገኙ ከ800 እስከ 900 ያህል ሕፃናት በትምህርት ቤቱ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ምስኪን ሕፃናት ለትምህርት ቤት አይከፍሉም፡፡ ትምህርት ቤቱም ጥሩ ደረጃ ያለው ነው፡፡ ምንም እንኳ ለልጆቹ ያን ያህል ባናደርግላቸውም የመምህራኑ ሥነ ሥርዓት፣ የአስተዳደር ሥርዓቱ፣ የእንክብካቤውና የፋውንዴሽኑ ትጋት በትክክለኛው ደረጃ ላይ የሚገኝ ነው፡፡ በትምህርት ቤቱ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ሕፃናት የሚኖሩ በመሆናቸው ከሚጠበቀው በላይ ውጤታማ ሆነው አኩርተውናል፡፡ ይህም በትምህርት ላይ ኢንቨስት ማድረግ ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ አሳይቶናል፡፡ ሁሉም ሕፃናት ግን መልካም ዕድሎችን ማግኘት ይገባቸዋል፡፡ 

ሪፖርተር፡- ባለፈው ጊዜ በነበረን ቆይታ አንዳንድ ታዳጊዎች ለዩኒቨርሲቲ የሚያበቃቸውን ውጤት እንዳመጡ ገልጸው ነበር፡፡

አቶ አድማሱ፡- አዎ፡፡ በርካቶቹ ሁለተኛ ደረጃና አሥረኛ ክፍልን አጠናቀው በዩኒቨርሲቲዎች ተመድበዋል፡፡ አንዱ እንዲያውም በአውሮፓ ትልቅ የትምህርት ተቋም ውስጥ የነፃ ትምህርት ዕድል አግኝቷል፡፡ ይህ በጣም አኩርቶናል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች


ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹ከ400 ዓመት በፊት በአውሮፓ የኢትዮጵያ ጥናት እንዲመሠረት ምክንያት ለሆኑት ለአባ ጎርጎርዮስ ምን አደረግንላቸው?›› ሰብስቤ ደምሰው (ፕሮፌሰር)፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ የዕፀዋት...

ዘንድሮ ጀርመን በኢትዮጵያዊው አባ ጎርጎርዮስ ግእዝና አማርኛ፣ የኢትዮጵያን ታሪክና መልክዓ ምድር ጠንቅቆ የተማረው የታላቁን ምሁር ሂዮብ ሉዶልፍ 400ኛ የልደት በዓልን እያከበረች ትገኛለች፡፡ በ1616 ዓ.ም....

‹‹ፍትሕና ዳኝነትን በግልጽ መሸቀጫ ያደረጉ ጠበቆችም ሆኑ ደላሎች መፍትሔ ሊፈለግላቸው ይገባል›› አቶ አበባው አበበ፣ የሕግ ባለሙያ

በሙያቸው ጠበቃ የሆኑት አቶ አበባው አበበ በሕግ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር ሕጉ ምን ይላል የሚል የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅ ናቸው፡፡ በሕግ መምህርነት፣ በዓቃቤ ሕግነት፣ እንዲሁም ከ2005...

‹‹በሁለት ጦር መካከል ተቀስፎ ያለ ተቋም ቢኖር አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ነው›› አቶ ዘገየ አስፋው፣ የአገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር

በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል የተነሳው ግጭት በተጋጋለበት ወቅት በ2014 ዓ.ም. በአገሪቱ መሠረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ለተፈጠሩ ልዩነቶችና አለመግባባቶች ወሳኝ ምክንያቶችን በጥናትና በሕዝባዊ ውይይቶች በመሰብሰብ፣ በተለዩ...