– ፌዴሬሽን ምክር ቤት የሥራ ዘመኑን ጨርሶ ተበትኗል
በከባድ የሙስና ወንጀል ክስ ተመሥርቶባቸው ፌዴራል ማረሚያ ቤት ሆነው በመከራከር ላይ የሚገኙት የቀድሞ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋናና ምክትል ዋና ዳይሬክቶች አቶ መላኩ ፈንታና አቶ ገብረዋህድ ወልደ ጊዮርጊስን ጨምሮ፣ ነጋዴዎች፣ ግለሰቦችና የንግድ ድርጅቶች ባነሱት ተቃውሞ ምክንያት ለትርጉም ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ተልኮ የነበረው ጉዳይ ባለመድረሱ ተጨማሪ ጊዜ ተሰጥቶ ተቀጠረ፡፡
ተከሳሾቹ ባቀረቡት አቤቱታ መሠረት ጉዳዩ ለትርጉም ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት የተላከው፣ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ኅዳር 30 ቀን 2007 ዓ.ም. አሻሽሎ ባወጣው አዋጅ ቁጥር 859/2006 አንቀጽ 182 ምክንያት ነው፡፡
አዲስ ተሻሽሎ የፀደቀው የጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 859/2006 የጉምሩክ ማጭበርበርና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን ከወንጀል ነፃ በማድረጉ በአስተዳደራዊ ቅጣት እንዲታለፉ አድርጓል፡፡ ተከሳሾቹ ከተመሠረቱባቸው በርካታ ክሶች አብዛኛዎቹ በአዲሱ አዋጅ ተሽረውና ወንጀል መሆናቸው ቀርቶ፣ በአስተዳደራዊ ቅጣት እንዲታለፉ በመደረጉ ክሱ እንዲቋረጥላቸው ጠይቀዋል፡፡
ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ በበኩሉ፣ ባለሥልጣኑ ባሻሻለው አዲሱ አዋጅ ቁጥር 859/2006 አንቀጽ 182 መሠረት አዲሱ አዋጅ ከፀናበት ቀን በፊት የተጀመሩ ጉዳዮች ቀድሞ በነበረው ሕግ መሠረት ተፈጻሚ እንደሚሆኑ እንደሚገልጽ፣ የወንጀል ሕግ 411 (1) ደግሞ (የመንግሥት ሥራን በማያመች ሁኔታ መምራት) ዋስትናን ስለሚከለክል የተከሳሾች አቤቱታ ውድቅ እንዲደረግለት ተቃውሞ ነበር፡፡
ተከሳሾቹ ባነሱት መከራከሪያ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 22(2) ድርጊቱ ከተፈጸመ በኋላ የወጣ ሕግ ለተከሳሹ ወይም ለተቀጣው ሰው ጠቃሚ ሆኖ ከተገኘ፣ ከድርጊቱ በኋላ የወጣው ሕግ ተፈጻሚነት እንደሚኖረው በመደንገጉ የዓቃቤ ሕግ መከራከሪያ ነጥብ ከሕገ መንግሥቱ ጋር እንደሚጣረስ በመግለጽ ተከራክረው ነበር፡፡ ፍርድ ቤቱም ትርጉም እንዲሰጥበት ሥልጣን ወዳላቸው የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔና ፌዴሬሽን ምክር ቤት መርቶት ነበር፡፡
ፍርድ ቤቱ ለትርጉም ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት የላከበት ወቅት ፌዴሬሽኑ የሥራ ዘመኑን ለማጠናቀቅ አንድ ወር ሲቀረው የነበረ ቢሆንም፣ ፌዴሬሽኑ እስከ ሐምሌ 13 ቀን 2007 ዓ.ም. ድረስ ምላሽ እንዳልሰጠ ፍርድ ቤቱ አስታውቆ፣ ለአንድ ሳምንት በማራዘም ለሐምሌ 22 ቀን 2007 ዓ.ም. ቀጥሯል፡፡ ነገር ግን ፌዴሬሽኑ የሥራ ዘመኑን ጨርሶ ተበትኗል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ከሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ አሥራ አንድ አባላት መካከል ስድስቱ የሥራ ዘመናቸውን የጨረሱ ሲሆን፣ ሦስቱ ደግሞ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ተወካይ በመሆናቸው ከምክር ቤቱ የሥልጣን ዘመን ማብቃት ጋር ተያይዞ ውክልናቸው አብቅቷል፡፡ ይሁን እንጂ ፓርላማው ሰኔ 30 ቀን 2007 ዓ.ም. የሥልጣን ዘመኑ ከማብቃቱ ቀደም ብሎ የሥልጣን ዘመናቸው በተጠናቀቀ ስድስት የጉባዔው አባላት ምትክ ዕጩ ተሿሚዎችን በማፅደቅ ለአገሪቱ ርዕሰ ብሔር ለሹመት መርቶታል፡፡