– ጠበቃቸው በመታገዳቸው ያለጠበቃ ነው የቀረቡት
በሽብርተኝነት ተጠርጥረው ክስ የተመሠረተባቸው የቀድሞ አንድነት ለፍትሕና ለዴሞክራሲ ፓርቲ (አንድነት)፣ የሰማያዊና የአረና ፓርቲዎች አመራሮችና ሌሎች ተከሳሾች ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ ያቀረበባቸው የሰነድ ማስረጃዎችን ‹‹በሕጋዊ መንገድ የተገኙ ማስረጃዎች አይደሉም›› በማለት አቅርበውት የነበረው መቃወሚያ፣ ሐምሌ 14 ቀን 2007 ዓ.ም. ውድቅ ተደረገ፡፡
የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ያቀረበውን ክስ እየመረመረው የሚገኘው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት፣ የተጠርጣሪ አቶ ዘለዓለም ወርቃአገኘሁ፣ የአንድነት አመራሮች የነበሩት አቶ ሀብታሙ አያሌው፣ አቶ ዳንኤል ሺበሺ፣ የአረና አመራር አባል አቶ አብርሃ ደስታና የሰማያዊ ፓርቲ አመራር አቶ የሺዋስ አሰፋና ባህሩ ደጉ የተባሉ ተጠርጣሪ ተከሳሾች ጠበቃ አቶ ተማም አባቡልጉ ያቀረቡት የመቃወሚያ ማመልከቻን እንዳልተቀበለው ገልጿል፡፡
ዓቃቤ ሕግ ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት እንዳገኘው ገልጾ ያቀረባቸው ማስረጃዎች፣ ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር ውለው ከታሰሩ ሦስት ወራት በኋላ የተገኙ መሆናቸውን፣ ተከሳሾቹ ለፖሊስ መረጃ የሰጡበት መንገድና ፖሊስ ማስረጃውን የያዘበት ሁኔታ አግባብነት የሌለውና ሕጋዊ ስለመሆናቸውም ያላረጋገጠ መሆኑን በመግለጽ፣ ከዓቃቤ ሕግ ማስረጃነት እንዲወጡ ወይም እንዲሰረዙ የሚል መቃወሚያ ጠበቃ ተማም ለፍርድ ቤቱ አመልክተው ነበር፡፡
ፍርድ ቤቱ የጠበቃውን መቃወሚያ ሙሉ በሙሉ ውድቅ በማድረግ፣ ተከሳሾቹ ይከላከላሉ ወይም መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነፃ ይሰናበቱ የሚለውን ብይን ለመስጠት፣ ለነሐሴ 14 ቀን 2007 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ ከላይ የተጠቀሱት ተከሳሾች በጠበቃ ተማም አባቡልጉ የተወከሉ ቢሆንም፣ ጠበቃ ተማም የዲሲፕሊን ጥፋት ፈጽመዋል ተብለው በፍትሕ ሚኒስቴር የጠበቆች ዲሲፕሊን ጉባዔ ባስተላለፈው የጥፋኝነት ውሳኔ፣ ሚኒስቴሩ አንድ ዓመት ከሰባት ወር ቅጣት ስለጣለባቸው ተከሳሾቹ ያለጠበቃ ቀርበዋል፡፡