Monday, June 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የፋይናንስ ለልማት ጉባዔ የጫረው የታክስ ጭማሪ ሥጋት

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለሳምንት ያህል የዓለም ዓይንና ጆሮ ማረፊያ ሆና የሰነበተችው አዲስ አበባ፣ እንግዶቿን አሰናብታ እፎይ ማለት ጀምራለች፡፡ በሦስተኛው ፋይናንስ ለልማት ጉባዔ ላይ የታደሙ እንግዶች ወደየመጡበት ተመልሰው፣ የሰሞኑ ሽርጉድም ተረስቶ የአዘቦት ሕይወት ቀጥሏል፡፡ ነገር ግን ከስብሰባው የቤት ሥራ ሆነው ያለፉ፣ በገርባባው የታዩ የወደፊት ሥጋት ምንጭ የሚሆኑ ክስተቶች ታይተዋል፡፡

የጉባዔው ዕድምተኞች ካነሷቸውና ከተወያዩባቸው በርካታ ርዕሰ ወሬዎች መካከል የታክስ ጉዳይ አንዱ ነበር፡፡ የተባበሩት መንግሥታት በጠራው በሦስተኛው ፋይናንስ ለልማት ጉባዔ ላይ የታደሙ አገሮች፣ በአዲስ አበባ የተግባር አጀንዳ ሰነድ ከተስማሙባቸው 134 አንቀጾች ውስጥ የታክስ ይዘቶችንም አካቷል፡፡ ጉባዔው ለመጪዎቹ 15 ዓመታት የሚተገበሩት የዘላቂ ልማት ግቦች ወይም ድኅረ የሚሊኒየሙ የልማት ግቦች ተብለው የተመዘገቡትን ለማስፈጸም ያስችላሉ የተባሉ የፋይናንስ ምንጮች ተለይተዋል፡፡ ምንም እንኳ ሁሉንም ባያስማሙም የፋይናንስ ምንጮች ተብለው ከተለዩት መካከል፣ የኦፊሴል ዕርዳታዎች፣ የግሉ ዘርፍና የመንግሥታት የጋራ ትብብር፣ ከበጎ አድራጊዎች የሚደረግ ልግስና እንዲሁም ትልቅ ትኩረት በመሳብ መነጋገሪያ የሆነው የአገር ውስጥ የፋይናንስ ምንጮችን ማጎልበትና የታክስ አሰባሰብ ሪፎርም ማካሄድ የሚሉት ይገኛሉ፡፡

በታክስ ላይ በርካታ ክርክሮች ተስናግደዋል፡፡ በርካታ ትችቶችም ተደምጠዋል፡፡ የበለፀጉ አገሮች በታዳጊ አገሮች ውስጥ የአገር ውስጥ የፋይናንስ ምንጮችን ለማጎልበት መሠረት የሚያደርጉት የታክስ ሥርዓትን ማሻሻል ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር የታክስ ኦዲት አሠራሮችን በማዘመንና የታክስ ባለሙያዎችን ክህሎት ከሙያቸው ብቃት በማዳበር ውጤታማ የታክስ አሰባሰብ ሥራዎች መሠራት እንደሚገባቸው ይመክራሉ፡፡ በዚህም ሳይገደቡ ከታዳጊ አገሮች በዓለም አቀፍ ኩባንያዎች የሚደረገውን ዝርፊያና የታክስ ስወራ ተግባር ለመከላከል ያስቻላል ያሉትን ድንበር የለሽ የታክስ ኢንስፔክተሮች ቡድን እንዲቋቋምና በዚህ ቡድን አማካይነት የታክስ ማጭበርበርና የስወራ ተግባራትን ለመግታት ይታሰባል፡፡ ፕሮጀክቱም በሦስት አገሮች ላይ እየተሞከረ ውጤት ማስገኘቱን የኢኮኖሚ ትብብርና የልማት ድርጅት ሥር የተሰባሰቡበት የ34 አገሮች ተቋም እያስተጋባ ይገኛል፡፡ ጥያቄው ግን ከዚህም በላይ ነው፡፡

የቡድን 77 አባል አገሮች የሚባሉት ወይም በጅምላው ታዳጊ አገሮች እየተባሉ የሚጠሩት የአፍሪካ፣ የካሪቢያን፣ የላቲን አሜሪካና የትንንሽ ደሴቶች አገሮች ለመጪዎቹ 15 ዓመታት በድህነት የሚላቀቁባቸው የተባሉትን የልማት ግቦች ለመተግበር ያስችሏቸዋል ከተባሉት ስልቶች ውስጥ አገር ውስጥ የታክስ መረባቸውን ማስፋት ወይም የታክስ አሰባሰብ ስልታቸውን እንዲያዘምኑ እየተጠየቁ ይገኛል፡፡ እርግጥ ይህንን ለማድረግ ይረዳሉ ከሚባሉት መካከል የታክስ ስወራና ማጭበርበርን ለመግታት ለሚሠሩ ሥራዎች ትኩረት እንደሚሰጥ ቢገለጽም፣ ይህንን ተግባር በተሻለ ደረጃ ይወጣል የተባለው ዓለም አቀፍ የታክስ ተቋም ይቋቋም የሚለውን የታዳጊ አገሮችና የዓለም ሲቪል ተቋማት ውትወታ የሰማው የለም፡፡ ይልቁንም የአገር ውስጥ የታክስ ምንጮችን ማስፋፋቱ ላይ ትኩረት እንዲደረግ፣ በአራቱ ቀናት የፋይናንስ ለልማት ጉባዔ ወቅት በተዘዋዋሪ ሲነገር ሰንብቷል፡፡

ይህንን የታክስ ጭማሪ በሚመለከት ተቃውሟቸውን ካሰሙት መካከል የዓለም የሲቪክ ማኅበራትን የቀደመ የለም ማለት ይቻላል፡፡ የዓለም የሲቪክ ማኅበራትን የወከሉት ተቋማት፣ የዓለም ታዳጊ አገሮችን በመወከል ተቃውሞ ሲያሰሙበት ከነበረው ጭብጥ አንዱ የሆነው የአገር ውስጥ የታክስ አሰባሰብን የሚቃወም ነው፡፡ ይህም ታክስ በታዳጊ አገሮች እንዲጨምር ማድረግ ተቀባይነት እንዳይኖረው የሚጠይቁት ሲቪክ ማኅበራቱ፣ በተመድ የፋይናንስ ለልማት አጀንዳዎች ላይ ከጠቀሷቸው መካከል በተለይ ከበጎ አድራጊ ለጋሾች ዘንድ እንዲመነጭና የልማት ግቦችን ፋይናንስ እንዲያደርጉ ያቀረበውን ውጥን ኮንነዋል፡፡

ጂዬኬ ታኖህ የአፍሪካ ሲቪል ማኅበራትን በመወከል በሦስተኛው ፋይናንስ ለልማት ጉባዔ ላይ ከታደሙት የዓለም ሲቪክ ማኅበራት መካከል አንዱ ናቸው፡፡ በሦስተኛው ዓለም አገሮች የፖለቲካ ኢኮኖሚ አፍሪካ ጥምረት ኃላፊ የሆኑት ጂዮኬ ታኖህ፣ በአፍሪካ የሚታየው ኢኮኖሚ ዕድገት በተለይ በኤክስፖርት ዘርፍ የተሰማሩ የውጭ ኩባንያዎችን ኪስ ከማደለብ ባሻገር ያልተመጣጠነ ነው ይሉታል፡፡ 134 አንቀጾችን አንግቦ በ193 አገሮች የፀደቀው የአዲስ አበባ የድርጊት አጀንዳ ሰነድ ‹‹ለአፍሪካ ምንም ያልፈየደ›› በማለት አጣጥለውታል፡፡

አፍሪካ የንግድ ሚዛን ጉድልትና የዕዳ መጠን እያሻቀበ በመምጣት አገሮችን ሥጋት ላይ መጣል እንደጀመረ ያብራሩት ታኖህ፣ በከፍተኛ የውጭ ንግድ ዘርፍ ላይ ተሰማርተው ከአፍሪካ ሸቀጦችን በገፍ እየጫኑ የሚገኙ የውጭ ኩባንያዎች፣ በነዳጅና በማዕድን ማውጣት ተግባር የተሠማሩ ኩባንያዎች በአንፃሩ ተገቢውን ታክስ አይከፍሉም፡፡ አይከፍሉም ብቻም ሳይሆን የሚከፍሉበት የታክስ ሥርዓትና የሚዋዋሉበት መንገድ አፍሪካን ለጉዳት የሚዳርግ ሆኖ እንደሚገኝ ታኖህ ያስረዳሉ፡፡ በአንዳንዶቹ ከነጭራሹም ታክስና ግብር ሳይከፍሉ በሚያገኙት የታክስ እፎይታና የታክስ ነፃ ዕድል በመጠቀም በርካታ ቢሊዮን ዶላሮችን አካብተው እብስ የሚሉ እንደሆኑ ሞግተዋል፡፡

ምንም እንኳ የሲቪል ማኅበራቱ ዋነኛ መከራከሪያ ነጥብ ዓለም አቀፍ የታክስ ተቋም መቋቋም እንዳለበት በመወትወት የዓለም መንግሥታት እንዲያቋቁሙት ጫና መፍጠር ቢሆንም፣ ከመነሻው ሁሉም መንግሥታት ያልመከሩበት ረቂቅ ሰነድ በደፈናው እንዲፀድቅ ለድርድር መቅረቡንም ሲቪል ማኅበራቱ ሲኮንኑ ከርመዋል፡፡ በታዳጊ አገሮች ላይ ይደረግ የነበረው የቀጥታና ተዘዋዋሪ ጫና ተገቢውን ድርድር እንዳያካሂዱ አስገድዷቸዋል፤ በዚህም የዓለም የታክስ ተቋም እንዳይቋቋም ብቻም ሳይሆን፣ በራሳቸው ዜጎች ላይ የታክስ ጫና በማብዛት ድሆች በሕወይታቸው ላይ ለውጥ እንዳያመጡ የሚያስገድድ እንደሆነም አበክረው ሲሞግቱ ተደምጠዋል፡፡

ይህ ሁሉ ሳይበቃ የሠረታኞችን የጡረታ መዋጮ የልማት ተግባሮችን ፋይናንስ ለማድረግ እንዲውሉ ጥሪ እየቀረበ እንደሚገኝ የገለጹት ታኖህ፣ ከአፍሪካ 360 ቢሊዮን ዶላር የሠራተኞችን የጡረታ ፈንድ ለዚህ ዓላማ ለመሰብሰብ ምክክር እየተደረገ መሆኑን ተቃውመዋል፡፡ በዚህ አያበቃም፡፡ በምዕራቡ ዓለም የተስፋፋው የተጨማሪ እሴት ታክስ ክፍያ፣ በአፍሪካ ሲተገበር ድሃውን ክፍል ጫና ውስጥ ከቶታል የሚለው መከራከሪያም ተነስቷል፡፡ ታኖህና አጋሮቻቸው እንደሚያስረዱት አፍሪካውያን በየዓመቱ ከግማሽ ቢሊዮን ዶላር በላይ ታክስ ለመንግሥቶቻቸው ይከፍላሉ፡፡ በአንፃሩ አፍሪካውያን መንግሥታት ይህንን ያህል ገንዘብ በውጭ መጠባበቂያ በውጭ ባንኮች እንዲያከማቹ የሚገደዱ ሲሆን፣ ይህም የፋይናንስ ቀውስ ቢያጋጥማቸውና የገቢ ንግዳቸውን ወጪ መሸፈን ቢያቅታቸው እንደ ዋስትና የሚቀመጥ ገንዘብ ነው፡፡

በመሆኑም አፍሪካ ባለፉት ሠላሳ ዓመታት ውስጥ የምትሰበስበው ታክስ በአብዛኛው ለዕዳ መክፈያነት እየዋለ መቆየቱ ሲነገር፣ ለዚህ ተግባር በአብዛኛው ከታች ወደ ላይ እየጨመረ የሚሄድ የገቢ ግብር አከፋፈል ሥርዓት ሲተገበር ቆይቶ ነበር፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ወደታች እየጨመረና እየሰፋ የሚሄድ፣ የሰዎች ፍጆታ በጨመረ ቁጥር በዚያው ልክ እየጨመረ የሚመጣ የተጨማሪ እሴት ታክስ ሥርዓት መተግበር በመጀመሩ፣ በርካታ ዜጎች ኑሯቸው እንዳይሻሻል ጫና እየፈጠረ እንደሚገኝ ታኖህ ተከራክረዋል፡፡

እርግጥ በተጨማሪ እሴት ታክስ አወንታዊና አሉታዊ ጎኖች ላይ ከተሰነዘሩ አስተያየቶች መካከል ዋሽንግተን ፖስት ከጥቂት ዓመታት በፊት ያወጣው ጽሑፍ አስረጅ ነው፡፡ በግርድፉ ለመመልከት ይህችን አንቀጽ መጥቀሱ ይጠቅማል፡፡ ተጨማሪ እሴት ታክስ በዕቃዎችና አገልግሎቶች ላይ የሚጣልና ሙሉ ለሙሉ በሸማቹ የሚከፈል የፍጆታ ታክስ ሊባል የሚችል ነው፡፡ በመሆኑም በእያንዳንዱ የፍጆታ ግብይት ላይ ሸማቾች ታክስ እንዲከፍሉ ይጠየቃሉ፡፡ ዋጋ ይጨምርባቸዋል፡፡ ደካማ ጎኑ ወይም ጉዳቱ ይህ ሲሆን፣ መንግሥት በጤና ክብካቤ፣ በመንገድና በትምህርት ቤት ግንባታ በመሳሰሉት ላይ ወጪ በማድረግ ለሕዝቡ ተደራሽ ያደርግበታል ተብሎ የሚታሰበው ገንዘብ የሚመነጭበት የታክስ ዓይነት ተደርጎ ይታሰባል፡፡ ጉዳቱም በዚህ ይካካሳል የሚል ክርክር ከአሜሪካውያኑ ዘንድ ሲስተጋባ ኖሯል፡፡

ኢትዮጵያ በዚህ መነጽር ስትታይ

በኢትዮጵያ የመንግሥትና የግል ሠራተኞች የጡረታ ፈንድ ለመንግሥት የልማት ሥራዎች ፋይናንስ እንደሚውል ይታወቃል፡፡ ተጨማሪ እሴት ታክስም እንዲሁ ከሸማቹ ሕዝብ እየተሰበሰበ የመንግሥትን የግብር ገቢ ከግማሽ እጅ ያላነሰ እየሸፈነ ይገኛል፡፡ በፈረንሳይ እ.ኤ.አ. በ1950ዎቹ እንደተጀመረ የሚነገርለት ተጨማሪ እሴት ታክስ፣ በኢትዮጵያ ከአሥር ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ የመንግሥት የገቢ ምንጭ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል፡፡

መንግሥት የገቢ ግብር አዋጁን ለማሻሻል ከተነሳ ሰንበትበት ብሏል፡፡ ያሰባቸው ፕሮጀክቶች መጠነ ሰፊ ናቸው፡፡ ቢሊዮኖችን የሚፈልጉና የሚጠይቁ ናቸው፡፡ ከፍተኛ የታክስ ገቢ ለመሰብሰብ የሚያስችሉ ዕቅዶች እንደሚወጡ እየተነገረ ነው፡፡ የታክስ ማሻሻያ ይደረጋል የተባለው በሠራተኞች ላይ የተጫነውን የታክስ መጠን ለመቀነስ ነው ቢባልም፣ ከመንግሥት ዕቅዶች እንደሚታየው ይህንን ለማድረግ ጊዜው አይመስልም፡፡

ተመድ ይፋ ያደረጋቸው 17ቱን የልማት ግቦች ለማሳካት ያስፈልጋል የተባለው ሁለት ትሪሊዮን ዶላር ገንዘብ ከብድር፣ ከዕርዳታና ከበጎ ፈቃደኛ ለጋሾች የሚጠበቀውን ያህል ባይገኝ ታዳጊ አገሮች በአገር ውስጥ የፋይናንስ ምንጮቻቸው ተጠቅመው እንዲያሳኩ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህንን ለማድረግ ደግሞ የታክስ ጭማሪ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በፋናንስ ለልማት ከተነሱ ጉዳዮችም ይኸው የአገር ውስጥ የፋይናንስ ምንጮችን ማስፋፋት የተባለው ነው፡፡

ይህንን ጉዳይ በሚመለከት፣ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒኒስትሩ አቶ ሱፊያን አህመድና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም የፋይናንስ ለልማት ጉባዔ በስኬት መጠናቀቅን በማስመልከት አርብ፣ ሐምሌ 10 ቀን 2007 ዓ.ም መግለጫ በሰጡት ወቅት ከጋዜጠኖች ተጠይቀው ነበር፡፡ አቶ ሱፊያን እንዳብራሩት፣ የታክስ ጭማሪን በሚመለከት በኢትዮጵያ አሁን እየተሰበሰበ የሚገኘው የታክስ መጠን ከኢኮኖሚው አኳያ (ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት አንፃር ሲታይ)  በሚቀጥሉት አራት ዓመታት 13 ከመቶ መሆኑንና ይህንን መጠን ወደ 17 ከመቶ ማድረስ የመንግሥት ዕቅድ ነው፡፡

‹‹ይህ የሚሆነው ግን ሰዎች ላይ ታክስ በመጫንና በመጨር አይደለም፡፡ ታክስ መክፈል ያለበት ሁሉ የታክስ መረብ ውስጥ እንዲገባ፣ እንዲከፍል በማድረግ ነው፡፡ የታክስ አሰባሰቡን ግልጽ በማድረግ ነው፤›› ብለዋል፡፡ በአንፃሩ በአገሪቱ ከፍተኛ ግብር ከፋዮች ተብለው የሚታወቁት ትልልቅ ኩባያዎች ከአንድ ሺሕ ያነሰ ቁጥር እንዳላቸው በመግለጽ እነዚህ ግብር ከፋዮች ተገቢውን ታክስ እየከፈሉ አይደለም፣ ለዚህ ደግሞ የመንግሥት ባለሥልጣናት በሙስና ተባብረዋል በማለት ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ መናገራቸው አይዘነጋም፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች