Tuesday, February 7, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርት‹‹የእግር ኳሱ አስተዳደር ተለውጦ ቢሆን ኖሮ እግር ኳሱም ባደገ ነበር››

‹‹የእግር ኳሱ አስተዳደር ተለውጦ ቢሆን ኖሮ እግር ኳሱም ባደገ ነበር››

ቀን:

አቶ ግርማ መስፍን የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች

ሕይወታቸውን በእግር ኳስ ጀምረው ሙያው በፈጠረላቸው አጋጣሚ በአውሮፓ ታላላቅ አገሮች ተምረው ለትልቅ ስኬት ከበቁ ኢትዮጵያውያን የቀድሞ ተጨዋቾች ይጠቀሳሉ፡፡ ውቅሮ ተወልደው አዲስ አበባ እንዳደጉ የሚናገሩት የቀድሞ የጭማድና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ክለቦችና የኢትዮጵያ ወጣት ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች አቶ ግርማ መስፍን የሕይወታቸው መሠረት የሆነው እግር ኳስ መጫወት የጀመሩት በአዲስ አበባ ከ1973 ዓ.ም. ጀምሮ ነው፡፡ ወቅቱ ‹‹ስፖርት ለፓስፖርት›› የሚባልበት ስለነበረ፣ ለኢትዮጵያ ወጣት ብሔራዊ ቡድን የመመረጥ ዕድሉ ሲገጥማቸው ወደ እንግሊዝ ተሰደው በዲፕሎማ ደረጃ በስፖርት ኤንድ ሪክሬሽን ማኔጅመንት ትምህርታቸውን መከታተላቸውን ይናገራሉ፡፡ በዚሁ ሳያበቁ በእንግሊዝ ሲኒየር ፕሮፌሽናል ተብለው ለሚታወቁ ቡድኖች ከመጫወቻቸው በተጨማሪ እዚያው ሌሊሾ ተብሎ በሚታወው የእግር ኳስ አካዴሚ ገብተው ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የእግር ኳስ አሠልጣኝነት ላይሰንስ አግኝተዋል፡፡ ይህ ከመደበኛ የከፍተኛው ትምህርታቸው ጎን ለጎን የቀሰሙት ዕውቀት እንደሆኑም አቶ ግርማ ያስረዳሉ፡፡ ባለሙያው ከሁለት አሠርታት በላይ ከቆዩበት አገር ወደ አገራቸው ተመልሰው ኢንቨስትመንት ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ፡፡ ከኢንቨስትመንቱ ጎን ለጎን የኢትዮጵያን እግር ኳስ ባላቸው ዕውቀት ለማገዝም ፍላጎት እንዳላቸው ጭምር ይናገራሉ፡፡ ደረጀ ጠገናው አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በእንግሊዝ ወደ ኢንቨስትመንቱ ለመግባት ከወሰዱት ትምህርት በተጓዳኝ ከልጅነት እስከ ዕውቀት ባደጉበት እግር ኳስ የአሠልጣኝነትና ተዛማጅ ሥልጠናዎችን መውሰድዎን ይታወቃል፡፡ ከኢንቨስትመንቱ ጎን ለጎን በአገሪቱ የእግር ኳስ እንቅስቃሴ ውስጥ ለመግባት አስበዋል?

አቶ ግርማ፡– በኢትዮጵያ ተሰማርቼ ከምገኝበት የሥራ ዘርፍ አኳያ ከባድ ቢሆንም እግር ኳስ ለእኔ ደሜም ሙያዬም ነው፡፡ ለዚያም ነው እግር ኳስ ከሃይማኖትም በላይ ሃይማኖት በሆነባት እንግሊዝ ከሌላው የሙያ ዘርፍ ጎን ለጎን ኢንተርናሽናል ኮችንግ ላይሰንስ ለማግኘት የበቃሁት፡፡ እርግጥ ነው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ከአውሮፓ እግር ኳስ ስታንዳርድ አኳያ በጣም ወደ ኋላ የቀረ ነው፡፡ ይህም በመሆኑ ነው በትልልቆቹ አገሮች ተምረን አገራችንስ ብለን እንድንቆረቆር የሚያስገድደን፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ከአደረጃጀት ጀምሮ እጅግ በርካታ ውስብስብ ችግሮች ውስጥ እንደሚገኝ አውቃለሁ፡፡ ፈተናም አለው፡፡ ማሸነፍ የሚችል የታረመ ጠንካራ የሚባል ክለብና ቡድን በኢትዮጵያ የለም፡፡ ይህንን ስል ዝም ብዬ በጭፍን ሳይሆን በማገኘው አጋጣሚ ሁሉ አዲስ አበባ ስታዲየም እየተገኘሁ ጨዋታዎችን ተመልክቼ ከደረስኩበት ድምዳሜ ነው፡፡ እንቅስቃሴው በአጠቃላይ መጥፎ ልማድ የሚሉት ዓይነት ነው፡፡ የአገራችን እግር ኳስ ከአውሮፓ ጋር ሰፊና ሊታመን የማይችል ልዩነት እንዳለው መመልከት ይቻላል፡፡ አውሮፓውያኑ ቀርቶ ብዙ ማኅበራዊ ቀውሶች ያሉባቸው ምዕራብና ሰሜን አፍሪካውያን እንኳን በጣም ርቀውናል፡፡ ስለሆነም መለስ ብለን ከአደረጃጀቱ ጀምረን እስከ ሥልጠና ሥርዓታችን መፈተሽ ይገባናል፡፡ እርግጥ ነው በአገሪቱ አንዳንድ ክለቦች ከውጪ በመጡ አሠልጣኞች ለብዙ ዓመታት የሠለጠኑ አሉ፡፡ ሜዳ ውስጥ ግን እንቅስቃሴው ተለውጦ አናይም፡፡ መጥፎ ባህሪይ ለማለት ያስገደደኝም ይህንን አካሄድ ለመመልከት በመቻሌ ነው፡፡ እግር ኳስ ካደገበት አገር ያመጣናቸው አሠልጣኞች ናቸው ካልን የሠለጠነ ቡድን ሜዳ ውስጥ ለውጥ ማሳየት መቻል ይኖርበታል፡፡ ለምን ይመጣል? የሚል መከራከሪያ የለኝም፡፡ ቅሬታዬ ብቃቱ ላይ ነው፡፡ ፕሮፌሽናል አሠልጣኝ የሚያደርገውን የሚያውቅ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ዳር ቆሞ ከመመልከትና ከመተቸት ችግሩን በመጋፈጥ በእግር ኳሱ የድርሻዬን ለማድረግ አስቤያለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- በብዙ ባለሙያተኞች ዘንድ በተለይም አሁን አሁን እግር ኳስ ‹‹ድሮ ቀረ›› የሚሉ ወገኖች ይደመጣሉ፡፡ የእርስዎ አስተያየት ምንድን ነው፣ አባባሉስ ምክንያታዊ ነው ማለት ይቻላል?

አቶ ግርማ፡– ነውም፣ አይደለምም ለማለት ራሱን የቻለ ጥናት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ከዛ በመለስ ግን ምሳሌ አድርጌ የምወስደው ራሴን ነው፡፡ ምክንያቱም እንግሊዝ  በነበርኩበት ጊዜ ሌሊሾ የሚባለው ትልቁ የእግር ኳስ አካዳሚ ውስጥ ሠልጣኞች ተገቢውን ሥልጠና እንወስዳለን፡፡ ዳሰሳ ጥናት እናደርጋለን፣ የዳሰሳ ጥናት ውጤቶቻችን ይታያሉ፡፡ ይህንኑ መሠረት በማድረግ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ላይ የራሴን ጥናት አድርጌ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሰጥቻለሁ፡፡ ጥናቱ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ከየት ወዴት፣ የአገሪቱ  ወጣት ለእግር ኳሱ ያለው አመለካከት፣ በአጠቃይ የአገሪቱ ሕዝብ ብዛትና የእግር ኳሱ ደረጃ በሚል በብዙ በጥቂቱ ይጠቀሳል፡፡ እግር ኳስ መሥራች ከሚባሉ አገሮች ኢትዮጵያ አንዷ ለመሆኑዋ ተከራካሪ ይኖራል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ታዲያ እንዴት ወደ ኋላ ቀረን? ለሚለው እንደሙያተኛ እግር ኳስ ሙያ ቢሆንም ይኼ ግን ለዓመታት እንደ ሙያ በኅብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ያገኘ አይመስልም፡፡ ችግሩ ከጅምሩ በሁሉም አገሮች የነበረ ቢሆንም ሌሎቹ በጊዜ ሒደት ተምረው ቶሎ ወደ መስመሩ በመግባታቸው እግር ኳሳቸውም ተለወጠ፡፡ በተቃራኒው በአገራችን ግን እስካሁንም ገና ነው፡፡ እኔ ኳስ ተጨዋች የነበርኩት በደርግ ዘመን ነው፡፡ በወቅቱ ብዙ ችግሮች እንደነበሩ የሚካድ አይደለም፡፡ ያ ደግሞ በሁሉም ዘርፍ ተፅዕኖ ነበረው፣ ታይቷልም፡፡ በዘመኑ ‹‹ስፖርት ለፓስፖርት›› የሚባልበት ጊዜም ነበር፡፡ በዚያን ዘመን ታዲያ ተጨዋቾች ነበሩ ወይ? እውነት ነው እጅግ በርካታ ቁጥር ያላቸው ተጨዋቾች ነበሩ፡፡ የበዙበት መንገድ እንዴት ነበር? ብለን ስንጠይቅ ደግሞ በራሳቸው ጥረት ካልሆነ  በተቋም ደረጃ ለማለት አያስደፍርም፡፡ ሌላው ደግሞ በወቅቱ በነበረው መንግሥት የአገሪቱ የውጭ ግንኙነት ዝግ ነበር፡፡ ልክ እንደኛ ችግር የነበረባቸው የምዕራብ አፍሪካና ሰሜን አፍሪካ አገሮች በችግር ውስጥ ሆነው እንኳ የውጭ ግንኙነታቸው ክፍት ስለነበረ ወጣቶቻቸው በተለያዩ የአውሮፓ አገሮች እየሄዱ የመታየት ዕድሉ ነበራቸው፡፡ ለዚያም ነው ዛሬ እንደነ ካሜሩን፣ ናይጄሪያ፣ ጋናና የሌሎችም አገሮች እግር ኳሳቸው ለማደግ የቻለው፡፡ እዚህ አገር ግን እስካሁንም ገና ነው፡፡ የነበረው ሥርዓት ከተወገደ በኋላ አገሪቱ እያደገች ያለች አገር ከመሆኗ ጎን ለጎን ስፖርቱን በሚመለከት የወጡ ፖሊሲዎች በጣም ጥሩ ናቸው፡፡ እኛም ወደ አገራችን እንድንመለስ ያደረገን ይኼው ለውጥ ነው፡፡ ነገር ግን በእግር ኳስ አስተዳደር ለውጥ አለ ወይ? ስንል በጣም ችግር አለ፡፡ በዚህ ችግር ውስጥ የሚገኙ ኳስ ተጨዋቾች ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ ለዚያ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ማደግ እንጂ የእግር ኳስ አስተዳደር እየወሰደ ባለው የለውጥ አቅጣጫ አይደለም፡፡ የእግር ኳሱ አስተዳደር ተለውጦ ቢሆን ኖሮ እግር ኳሱም ባደገ ነበር፡፡ እንግሊዝ እያለሁም ሆነ እዚህ እያለሁ የቀድሞውንና አሁን ያለውን የእግር ኳስ አመራር ለማነጋገር ሞክሬአለሁ፣ ግን ቀና ነገር አላስተዋልኩም፡፡ ችግሩ ምን እንደሆነ አይገባኝም፡፡ ለጥቅም ነው ብለው የሚያስቡ ካሉ ተሳስተዋል፡፡ በግልጽ ለመናገር የእግር ኳስ ሙያ ባለቤት ስለሆንኩ ብቻ ለአገሬ ለወገኔ የማውቀውን ለመስጠት ካልሆነ ለጥቅም አስቤበት አላውቅም፡፡ በሙያው የተማረና አዲስ ነገር ይዞ ለሚመጣ ሰው ጆሮ የሚሰጥ አካል የለም፡፡ እንዲያውም ያልሆነ ስም ይወጣለታል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ፖሊሲ አቅምና ዕውቀት ያለው አካል እንዳይመጣ አይከለክልም፣ እግር ኳሱ ላይ ያለው ግን ከአገሪቱ ፖሊሲ በተቃራኒ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የዚህ ዘመን የእግር ኳስ ተጨዋቾች በገንዘብ ካልሆነ በብቃትና ችሎታ በእናንተ ዘመንና ከዚያ በፊት ከነበረው የተሻለ እንዳልሆነ ይነገራል?

አቶ ግርማ፡– ቀደም ሲል ለመግለጽ እንደሞከርኩት ለዚህም ጥናት ያስፈልገዋል፡፡ ባለኝ ልምድና ተሞክሮ ግን እኔ በነበርኩበት ሥርዓት እንደ አሁኑ በምርጫህ ሳይሆን በግድ ወታደር የምትሆንበት ነበር፡፡ ሌላው ደግሞ በወቅቱ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና እኔን ጨምሮ 125,000 ተማሪዎች ወስደናል፡፡ ከዚህ ውስጥ ዩኒቨርሲቲ መግባት የቻሉት 3,000 ተማሪ ብቻ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ ምክንያቱም የመግቢያ ነጥቡ ሦስት ነጥብና ከዚያም በላይ ስለነበረ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ የወጣቱ ብቸኛ አማራጭ ኳስ ተጨዋች ሆኖ ባገኘው አጋጣሚ ወደ ውጭ ለመውጣት ነበር፡፡ ይህን ዕድል ለማግኘት ደግሞ በሚሊዮን ከሚቆጠር ወጣት ጋር መፎካከር የግድ ነበር፡፡ ዛሬ ግን ወጣቱ ብዙ አማራጮች አሉት፡፡ የእግር ኳሱ አስተዳደር ካልተመቸው ሙዝዝ የሚልበት ሁኔታ የለም፡፡ ስለዚህ ኳስ ተጨዋች መሆን የግድ የሆነበት ሥርዓት አብቅቷል፡፡ አሁን ያለው ችግር ደግሞ እግር ኳስ ተጨዋቾችን ሊያማልል የሚችል መልካም የእግር ኳስ አስተዳደር መጥፋት በዋናነት ተጠቃሸ ነው፡፡ የሚገርመው በዚህ ሥርዓት ቀበሌዎችና የሃይማኖት ተቋማት ሀብታሞች ናቸው፡፡ ሕንፃ እየገነቡ ያከራያሉ፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከሰባት አሠርታት በላይ አስቆጥሯል፡፡ ዛሬም ከመንግሥት ድጎማ አልወጣም፡፡ ክለቦችም በተመሳሳይ፡፡ ነገር ግን በአገሪቱ እግር ኳስን ባህሉ ያደረገ የኅብረተሰብ ክፍል አለ፡፡ ይኼ ሥርዓት ከመጣ በኋላ መሬት ከመንግሥት ወስዶ ሕንፃ ገንብቶ ሚሊየነር የሆነ ግለሰብ አለ፡፡ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ግን አሁንም የመንግሥትን እጅ እየጠበቀ ነው፡፡ መንግሥት ለሁሉም እኩል ነው፡፡ ስለዚህ የአገሪቱ እግር እኳስ ልማት የሚሆንበት፣ ስፖርተኞች በስፖርቱ ለትልቅ ደረጃ የሚበቁበት፣ የሚያልሙበት የሙያ ዘርፍ እንዲሆን፣ የግል ባለሀብቱ የሚመርጠው እንጂ ውስጡ ባለው የተበላሸ አሠራር የሚማርበት እንዳይሆን ጠንካራ አመራር ያስፈልጋል፡፡ እግር ኳስ በእግር ኳስ ማናጀር እየተዳደረ በሚገኝበት በዚህ ዘመን እኛ አገር በኮሚቴ የሚመራበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ እግር ኳስ በተለይም በአሁኑ ወቅት ባህል ከሆኑባቸው አገሮች ያለማጋነን ኢትዮጵያ አንዷ ነች፡፡ ይህንንም ስናገር ዝም ብዬ ከመሬት ተነስቼ ሳይሆን በማስረጃ ማሳየት እፈልጋለሁ፡፡ በእንግሊዝ ቻናል ፎር የሚባል ጣቢያ አለ፡፡ ኢትዮጵያ ከ31 ዓመታት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ በበቃችበት የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ኢትዮጵያውያን ደጋፊዎችን የተመለከተው ይህ ቻናል፣ አፍሪካ ውስጥ እንዲህ ዓይነት እግር ኳስ ባህሉ የሆነ ሕዝብ መመልከቱን ሲናገር ተመልክቻለሁ፡፡ በቅርቡ በባህር ዳር ስታዲየም የታየውም ለዚህ ሌላው ማሳያ ነው፡፡ ታዲያ ይህን የመሰለ የኅብረተሰብ ክፍል ባለበት አገር አንድ ብሔራዊ ፌዴሬሽን የራሱ ነገር እንዴት አይኖረውም?

ሪፖርተር፡- ምክንያት የሚሉት ይኖርዎታል?

አቶ ግርማ፡– በጣም ግልጽ ነው፡፡ ምክንያቱም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በሙያው ሰዎች አለመመራቱ ያመጣው ችግር ነው፡፡ ወደፊትም ይሄ አካሄድ እስካልተቀየረ ድረስ በእግር ኳሱ ሕዝቡም ሆነ መንግሥት የሚፈልጉት ልማት አይመጣም፡፡ ተቋሙ ኃላፊነትና የሙያ ሥነ ምግባር በማይሰማው አካል ነው እየተዳደረ የሚገኘው፡፡ አመራሮች ይመጣሉ የተሰጣቸውን የአገልግሎት ዘመን ጨርሰው ለቀጣዩ አስተዳዳሪ ሲያስረክቡ ምን እንዳከናወኑ የሚጠየቁበት ሥርዓት የለም፡፡ ባለሙያ ቢሆኑ ግን ሙያቸው ነውና ቢያንስ የሙያው ሥነ ምግባር ስለሚያስገድዳቸው አዲስ ነገር ለማምጣት ጥረት ማድረጋቸው አይቀርም፡፡ የእግር ኳስ ሙያተኛው በሙያው የማይከበርበት፣ በኮሚቴና መሰል አደረጃጀት ወደ ሙያው የሚመጡት ግን መሪና አሠልጣኝ የሚሆኑበት፣ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ብቸኛ ተቋም እየሆነ ይመስለኛል፡፡ አገሪቱ የመጀመርያውን ትራንስፎርሜሸን ዕቅድ አጠናቃ ሁለተኛውን ለመጀመር እየተዘጋጀች ነው፡፡ ታድያ ስፖርቱስ የእዚህ ዕቅድ አካል የሚሆነው መቼ ነው? መነጋገር ያስፈልጋል፡፡ ስፖርቱ በአገሪቱ የውጭ ገጽታ ላይ የሚኖረው ድርሻ ብዙ ነው፡፡ ለእንግሊዝ ወይም ለብራዚል እግር ኳስ ለአገሮቹ የውጭ መልካም ገጽታ ግንባታ ያለው ድርሻ ምን እንደሆነ የማይገባው ይኖራል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ስለዚህ እግር ኳሱ ከአገሪቱ ዕድገት ጋር እኩል መራመድ ካልቻለ እንደ ሙያተኛ ችግር አለ ማለት ነው፡፡ ይህንን ይመለከተናል የሚሉ ወገኖች ሊያጤኑት ይገባል፡፡ አሜሪካና ጃፓን ላይ እግር ኳስ ለአንድ አገር ምን እንደሆነ ሲገባቸው እየተረባረቡ ይገኛሉ፡፡ ቀድሞ የገባን እኛ ደግሞ ተኝተናል፡፡

ሪፖርተር፡- እርሶም እንደሚሉት እግር ኳሱ ውስጥ ብዙ ችግሮች አሉ፡፡ ምን መደረግ አለበት ይላሉ?

አቶ ግርማ፡– ሙያተኞችን አሁን እንዳለው ዓይነት ሳይሆን በበቂ ሁኔታ ማፍራት ያስፈልጋል፡፡ ለሙያተኞቻችን ተገቢውን ክብርና ቦታ መስጠት ደግሞ በዚያው መጠን፡፡ ራሳችንን ማታለልና እያታለሉን ያሉትን የራሳችንን ሰዎች በመለየት ወደ ትክክለኛው አቅጣጫ መመልከት ያስፈልጋል፡፡ እዚህ አገር እግር ኳስ መጫወት የጀመርኩት በ1973 ዓ.ም. ነው፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ ያለፉትን ሰዎች አንድ በአንድ አውቃቸዋለሁ፡፡ በሙያው ያለፉትን ማለቴ ነው፡፡ ነገር ግን በፌዴሬሽኑ በተለያዩ ዲፓርትመንቶች በተለይም ደግሞ እግር ኳስ ልማት ነው ተብሎ በሚታመንበት በዚህ ዘመን ቦታውን ይዘውት የሚገኙትን አንዳቸውንም አላውቃቸውም፡፡ እርግጥ ነው እግር ኳሱን በንድፈ ሐሳብ ደረጃ ሊያውቁ የሚችሉ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በተጨባጭ ሜዳ ላይ ያለውን ሆነው ለመምራት ግን እነዚህ ሰዎች የሚቸገሩ ነው የሚመስለኝ፡፡ ምክንያቱም የእግር ኳስ አሠልጣኝ ወይም ባለሙያ ለመባል በየትኛውም አገር እንደምንመለከተው ሁሉ በኢትዮጵያም በሙያው ውስጥ ማለፍ ይጠይቃል፡፡ በእርግጥ በሙያው ውስጥ አልፎ በንድፈ ሐሳቡ ትምህርትም የገፉ ቢኖሩ ይመረጣል፡፡ የካፍ ኢንስትራክተር በሚል ሽፋን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ወደ ባሰ ነገር እንዳይሄድ እሠጋለሁ፡፡ ስለሆነም የሙያ ድርሻን መለየት ያስፈልጋል፡፡ እርግጥ ነው እግር ኳሱን ተጫውተው አሁን ደግሞ በትልልቅ ክለቦች አሠልጣኝ ሆነው እያገለገሉ ያሉ ባለሙያዎች በብዛት እንዳሉ አውቃለሁ፡፡ እነዚሁ ሰዎች የአሠልጣኝነት ደረጃቸው እስከ ‹‹ኤ›› እንዲደርስ ሥልጠናም ተሰጥቷቸዋል፡፡ ሥልጠናውን የሰጡዋቸው እነማን ናቸው? ብለን ስንጠይቅ ግን እንደባለሙያ ብቻ ሳይሆን እንደ ዜጋም ያሳስበኛል፡፡ ምክንያቱም የሙያ ባልደረቦቼ ስለሆኑ ደረጃውን የጠበቀ ሥልጠና ማግኘት ስለሚኖርባቸው ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በአዲስ አበባና ሌሎችም ዩኒቨርሲቲዎች ገብተው በእግር ኳስና ሌሎችም ስፖርቶች ሁለተኛ ዲግሪያቸውን የሠሩ ሰዎች ወደ አሠልጣኝነትና ተያያዥ ዲፓርትመንቶች ውስጥ በብዛት እየገቡ ናቸው፡፡ ሰዎቹ የስፖርቱ ዕውቀት በንድፈ ሐሳቡ ደረጃ ያላቸው ቢሆንም፣ ኳስ ተጫውተው አለማለፋቸው ደግሞ በአሉታዊ ጎኑ እየተነሳ ነው፡፡ በእርስዎ ሁለቱን አስታርቆ እንዴት ወደ ውጤት መምጣት ይቻላል፡፡

አቶ ግርማ፡- ለጥያቄው የምሰጥህ መልስ የአውሮፓን እግር ኳስ ማኅበር (ዩኤፋ) ምሳሌ አድርጌ ነው፡፡ አንድ ሰው በአውሮፓ የእግር ኳስ ባለሙያ ሊባል የሚችለው መጀመርያ በእግር ኳሱ የሙሉ ጊዜ አገልግሎትን ሰጥቶ ሲመጣ ነው፡፡ ይህ ማለት እግር ኳስ ጨዋታ ሥራው ሆኖ ማለት ነው፡፡ በእንግሊዝ ይኼ የሽግግር ጊዜ አራት ደረጃዎች አሉት፡፡ የማንችስተር ዩናይትድ አሠልጣኝ የነበሩት ፈርጉሰንና ሌሎችም ታላላቅ የዓለም አሠልጣኞች ተሞክሮዎች የሚያረጋግጡልን ይህንን ነው፡፡ በአገራችን ነባራዊ ሁኔታ እንመልከተው ከተባለ ደግሞ አንድ ተማሪ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ወስዶ በሚያመጣው ውጤት ይወሰናል፡፡ ታዲያ እግር ኳስ ተጫውቶ ያላለፈ ዩኒቨርሲቲ ገብቶ ላይሰንሱን ስላወቀው ብቻ በምን ዓይነት መመዘኛ ነው የአሠልጣኞች አሠልጣኝ መሆን የሚያስችለውን ላይሰንስ የሚወስደው፡፡ ይኼ ሆኖ ግን እየተመለከትን ነው፡፡ አሠልጣኝነት በሙያው ውስጥ ልዩ የሆነ ተሰጥኦን የሚጠይቅ ሙያ ነው፡፡ የስፖርት ሳይንስ ትምህርት ብዙ ነው፡፡ ስለዚህ የስፖርት ሳይንስ ተምረሃል ማለት የእግር ኳስ ወይም የአሠልጣኝነት ዕውቀት አለህ ማለት አይደለም፡፡ በእግር ኳስ ሁለተኛ ዲግሪ ስለሚባለው ነገር በአውሮፓ ሰምቼው አላውቀም፡፡ የእግር ኳስ ሙያውም አይፈቅድም፡፡ ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ ውስጥ እግር ኳስ ላይ ወንጀል እየተሠራ ነው፡፡ በእንግሊዝ የአሠልጣኝነት ላይሰንስ ለመውስድ ጥያቄ ሳቀርብ፣ የቀረበልኝ መጀመርያ ጥያቄ በእግር ኳስ የሙሉ ጊዜ ያገለገልኩበትን እንዳቀርብ ተደርጌ ነው ዕድሉን ያገኘሁት፡፡ በኢትዮጵያ ግን ገብረ መድኅን ኃይሌ ወይም አሥራት ኃይሌ ያላገኙትን የአሠልጣኝነት ላይሰንስ እግር ኳሱን በንድፈ ሐሳብ ደረጃ የሚያውቁት ቀድመው አግኝተውታል፡፡ ምን እየተሠራ እንደሆነ አይገባኝም፡፡

ሪፖርተር፡- ለዚህ ተጠያቂ ማን ነው? ምክንያቱም ቀደም ሲል ሙያውን ሆነው ባለሙያ የሆኑ ወገኖች መኖራቸውን ገልጸዋልና ነው፡፡

አቶ ግርማ፡– ለዚህ በዋናነት ተጠያቂው እኔን ጨምሮ በእግር ኳሱ የመጣን ባለሙያዎች ነን፡፡ ዳዊት ኃይለአብ የሚባል ድሮ የትግል ፍሬ ተጨዋች ነበረ፡፡ ዳትኮም ካሚዩን የተሰኘ ካምፓኒ አቋቁሞ ለጉግል በሚሊየን ዶላር መሸጥ የቻለ  የቢዝነስ ሰው ነው፡፡ በስሩ ብዙ ዶክተሮችና የተለያዩ የቢዝነስ ሰዎች አሉ፡፡ ምሳሌውን ያመጣሁት እግር ኳሱን ሊመሩ የሚችሉ ሙያውን ከሥር መሠረቱ የሚያውቁት አቅሙም ችሎታውም ያላቸው ሰዎች በተለያዩ ዓለማት መኖራቸውን ለመግለጽ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በሁሉም ዘርፍ የሙያተኛ ደሃ አይደለችም፡፡ እነ ዮሐንስ ሳሕሌን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በእንግሊዝ እግር ኳስ ሃይማኖት ነው፡፡ በእነዚህ አገሮች ተምረን የመጣን ባለሙያዎች ቢያንስ ልንደመጥ ይገባል፡፡ በእንግሊዝ በኳሱ ያለፉ ሙያተኞች ‹‹የሙያ ወንድማማቾች ነን›› ብለው ያምናሉ፡፡ ይህንኑ በአገራችን ማምጣት ይጠብቅብናል፡፡ የእግር ኳስ ክሕሎት ከፈጣሪ ጭምር የሚሰጥ ነው፡፡ ማንም ሰው የቱንም ያህል በአሠልጣኝነት የመጠቀ ዕውቀት ቢኖረውም፣ የሜሲን ዓይነት ተጫዋች ማፍራት ግን አይችልም፡፡ ለሜሲ ክሕሎት የፈጣሪ ገፀ በረከት አለበት፡፡ ያንን ግን ተመልክቶ የሚለይ ሙያተኛ ግን ያስፈልጋል፡፡ ለእግር ኳሳችን የሚያስፈልገው የዚህ ዓይነቱ ባለሙያ ነው፡፡ እግር ኳስ ለሳይንስ ቦታ ይኖረዋል፣ ሳይንስ ግን አይደለም፡፡ ከዚህ አኳያ ብዙኃን (ማስ) ስፖርት ተምሮ በስመ ሁለተኛ ዲግሪ ልዩ የመመልከት ተሰጥኦ የሚጠይቀውን የአሠልጣኝነት ሙያ ባለቤት ነኝ ብሎ ያዙኝ ልቀቁኝ ማለት የጤነኝነት አይመስለኝም፡፡ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ አሁን እየመጣ ያለ ትልቅ በሽታ ይኼው ነው፡፡ በእርግጥ በብዙኃን ስፖርት ትምህርት ሥነ ልቦና፣ ሥነ ምግብ፣ የአካል ብቃትና የመሳሰሉት የሙያ ዘርፎች አሉ፡፡ እነዚህ እግር ኳሱ ወደ ሚፈለገው ዕድገት እንዲመጣ በአሠልጣኞች ሥር ድርሻ አላቸው፡፡ አንድ ሰው መኪና ስለሠራ ብቻ አሽከርካሪ ሊሆን አይችልም፡፡ ሥነ ባሕሪውን ግን ያውቀዋል፡፡ ከነዚህ የሙያ ዘርፎች የሚለየው ለምንድን ነው?

ሪፖርተር፡- ሙያተኞች ለሙያቸው እንዲቆረቆሩ የሚያስችል የሙያ ማኅበር ያስፈልጋል እንበል?

አቶ ግርማ፡– አያጠያይቅም፡፡ ምንም ዓይነት የሙያ ማኅበር በሌለበት መንግሥትን ብቻ መውቀስ ውጤት አያመጣም፡፡ የሚገርመው አፍሪካ ውስጥ ፕሮፌሽናል የእግር ኳስ ተጨዋቾች ማኅበር (ፒኤፍኤ) ያላቸው አገሮች 18 ብቻ ናቸው፡፡ የተቀሩት ኢትዮጵያን ጨምሮ የዚህ ዓይነቱ ማኅበር አይታወቅም፡፡ የአገሪቱ ሕግ ይፈቅዳል፡፡ እግር ኳስ ሙያ ነው ካልን የሙያተኛው መብት እስከየት ድረስ? የሚለውን ልናውቀው ይገባል፡፡ ያን ጊዜ በሙያው ላይ የሚደረገውን ወረራ በሕግ አግባብ ማስቆም ይቻላል፡፡ የሙያ ኃላፊነቶችም በተመሳሳይ፡፡ ይኼ ካልተለወጠ የሙያተኛው መብት ቀርቶ የአገሪቱ እግር ኳስም መቼም አያድግም፡፡ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ዕድገት ወደ ኋላ መቅረት ሌላው ምሳሌ ሊሆነን የሚችለው፣ በአገሪቱ እጅግ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሚሊየነሮች እየተፈጠሩ ነው፣ አሉም፡፡ አንዳቸውም ግን እግር ኳሱን ለማልማት አይጠይቁም፡፡ ምክንያቱም ዘርፉ በተንኮልና በኔትወርክ ቢሮክራሲ የተተበተበ ስለሆነ ነው፡፡ ዓለም ላይ ባለሀብቶች ወደ እግር ኳሱ ዘርፍ እየመጡ ነው፡፡ እኛስ ብለን መጠየቅ የግድ ይለናል፡፡ በድጎማ እስከመቼ ልንቆይ ነው፡፡ በአገሪቱ ባለሀብቶች በስፖርቱ እንዳይሳተፉ የሚከለክል የፖሊሲ ችግር የለም፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ከአምስት ዓመት በኋላ እዚህ ደረጃ ላይ መድረስ አለበት ብሎ በዕቅድ የሚሠራ አመራርና ባለሙያ ያስፈልገዋል፡፡  በካፍና ፊፋ ስም የሚነግደውን ሙሰኛ የአሠራር ሥርዓት መዋጋት የግድ ይለናል፡፡ ምክንያቱም ካፍና ፊፋ ራሳቸው በአሁኑ ወቅት የገቡበትን ቅሌት እናውቃለን፡፡ ስለሆነም የእግር ኳስ ሙያተኞቻችን ደረጃውን የጠበቀ ዕውቀት የሚያገኙበት ሥልጠና ልናመቻችላቸው ይገባል፡፡ ለአሌክስ ፈርጉሰን ወይም ለሞሪኒሆ ዩኤፍ ላይሰንስ አይሰጥም፡፡ እኛ ከእነዚህ አገሮች የምንለየው ለምንድን ነው? ይኼ ግልጽ ሊሆን ይገባል፡፡ አጫጭር ኮርሶችን ይሰጣሉ እውነት ነው፡፡ ምክንያቱም በየጊዜው ሕጎችና ተዛማጅ ነገሮች ሊቀያየሩ ስለሚችሉ ማለት ነው፡፡ ከዚህ ባለፈ ትክክለኛ ዕውቀቱ ባላቸው ኢትዮጵያውያን ሙያተኞች ማመን ይገባናል፡፡ ከዮሐንስ ሳሕሌ በፊት የነበሩት ፖርቱጋላዊው አሠልጣኝ ማሪያኖ ባሬቶ ምን ዓይነት ዕውቀት አስጨብጠው ሄዱ፡፡ እርግጥ ነው ተጨዋቾቻችን በዘመናዊ የእግር ኳስ ሕይወት የመጡ ስላልሆኑ ሽንፈት ነገም ሊመጣ ይችላል፡፡ ፈረንጅ ሲሆን የማንተችበት ከውጪ ተምሮ የመጣ ኢትዮጵያዊ ከሆነ ግን መግቢያ መውጫ የምናሳጣበት አካሄድ እየተመለከትን ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቤተክህነት ባቀረበችው የይግባኝ አቤቱታ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ለዕሮብ ተቀጠረ

የኢትዮጵያ ኦሮቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሀገወጥ ነው በተባለው አዲሱ ሲኖዶስና...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና የመንግሥት ውዝግብ

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥት ባለፉት አራት ዓመታት...

የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ምሥረታ ዝግጅቶችና ከገበያው የሚጠበቁ ዕድሎች

ኢትዮጵያ ከ50 ዓመት በኋላ ዳግም የምታስጀምረውን የካፒታል ገበያ ዘመኑን...

አዲሱ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት የሚያደርጉባቸውን ቀዳሚ ጉዳዮች ይፋ አደረጉ

አዲሱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት አድርገው የሚሠሩባቸውን ቀዳሚ...