Thursday, November 30, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ ከ200 ቢሊዮን ዶላር በላይ ቃል ተገባ

ተዛማጅ ፅሁፎች

–  ሁለት ትሪሊዮን ዶላር ይጠበቃል

የአውሮፓ አገሮች እ.ኤ.አ. እስከ 2020 ባለው ጊዜ ውስጥ ያዋጣሉ ተብሎ የሚጠበቀውን የገንዘብ መጠን ይፋ በማድረግ ሰኞ ሐምሌ 6 ቀን 2007 ዓ.ም. ማምሻውን የአውሮፓ ኅብረት ይፋ ባደረገው መሠረት፣ በአምስት ዓመት ውስጥ ተጨማሪ 100 ቢሊዮን ዩሮ በጋራ ለማቅረብ ቃል ገባ፡፡ የዓለም ኢኮኖሚክ ፎረምና የኢኮኖሚ ትብብርና የልማት ማኅበር (ኦኢሲዲ) በጋራ 100 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብተዋል፡፡

በአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን የዓለም አቀፍ ትብብርና ልማት ኮሚሽነር ኔቨን ሚሚካ፣ እንዲሁም የሉክዘምበርግ የልማት ትብብርና የሰብዓዊ ጉዳዮች ሚኒስትር ሮሜይን ሽናይደር በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ መሠረት፣ ለታዳጊ አገሮች የልማት ትብብር ድጋፍ እንዲውል ቃል ከተገባው 100 ቢሊዮን ዩሮ ውስጥ 20 በመቶው ለአየር ንብረት ለውጥ ሥራዎች የሚውል ነው፡፡ ለታዳጊ አገሮች ተመራማሪዎች የሚውል የ77 ቢሊዮን ዩሮ ድጋፍ በኅብረቱ እንደሚቀርብ ይፋ ተደርጓል፡፡ በገንዘብ ምን ያህል ሊያዋጣ እንዳሰበ ባይገለጽም፣ 500 ሚሊዮን ሰዎችን ከረሃብና ከተመጣጠነ ምግብ እጥረት፣ እንዲሁም 500 ሚሊዮኖችን ደግሞ ከኃይል እጦት ለመታደግ በሚደረገው ትብብር ላይ የአውሮፓ ኅብረት አጋር እንደሚሆን ቃል ገብቷል፡፡

ከአውሮፓ ኅብረት በተጓዳኝ 100 ቢሊዮን ዶላር በመጪዎቹ አምስት ዓመታት ውስጥ ለታዳጊ አገሮች የዘላቂ ልማት ድጋፍ ለማድረግ ቃል የገቡት የኦኢሲዲ አባል አገሮች፣ ረቡዕ ሐምሌ 8 ቀን 2007 ዓ.ም. በአዲስ አበባ እየተካሄደ በሚገኘው ሦስተኛው ፋይናንስ ለልማት ጉባዔ ጎን ይፋ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በመጪዎቹ 15 ዓመታት ለታዳጊ አገሮች የዘላቂ ልማት ማስፈጸሚያነት ይውላል ተብሎ የሚታሰበው የገንዘብ መጠን ሁለት ትሪሊዮን ዶላር ሲሆን፣ እስካሁን ከአውሮፓ ኅብረትና ከኦኢሲዲ አገሮች ከተገኘው ውጪ ከሌሎች ያደጉ አገሮች ዘንድ የፋይናንስ ድጋፍ እስከ ጉባዔው መጠናቀቂያ ቀን ድረስ ቃል ኪዳኖች ይፋ ይደረጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ባለፉት 15 ዓመታት ለታዳጊ አገሮች የልማት ግቦች ድጋፍ ለማድረግ ያስፈልጋል ተብሎ የተገመተው የገንዘብ መጠን 200 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ሲሆን፣ በአዲስ አበባው ጉባዔ ሁለት ቀናት ውስጥ ግን ለሚሊኒየሙ የልማት ግቦች ይጠበቅ የነበረው የገንዘብ መጠን እንደሚለቀቅ ተነግሯል፡፡  

አዲስ አበባ የምታስተናግደው ሦስተኛው ፋይናንስ ለልማት ጉባዔ፣ ስምምነት ይደረግባቸዋል ተብለው ከሚጠበቁ መካከል ያደጉ አገሮች ከ15 ዓመታት በፊት ቃል የገቡትን ከጠቅላላ ብሔራዊ ገቢያቸው ውስጥ የ0.7 በመቶ መዋጮ በማድረግ የልማት ግቦችን ፋይናንስ ማድረግ ነው፡፡ በርካታ አገሮች ይህንን ማድረግ እንዳልቻሉ ሲታወቅ፣ ቃላቸውን በመጠበቅ በኦፊሴል የልማት ትብብር አማካይነት ልገሳውን በማድረግ ከሚጠቀሱት ውስጥ እንግሊዝ፣ ሉክዘምበርግና ስዊድን ይገኙበታል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች