Friday, June 21, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የሁለት ትሪሊዮን ዶላሮች ጥያቄ የሚያስተናግደው የአዲስ አበባ ጉባዔ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የአዲስ አበባ ድርጊት አጀንዳ›› የሚል መጠሪያ የተሰጠውና ከትናንት በስቲያ የተከፈተው ሦስተኛው ፋይናንስ ለልማት ዓለም አቀፍ ጉባዔ፣ ለኢትዮጵያም ለአፍሪካም ትልቅ ድል ተደርጎ ይቆጠራል፡፡ ከአምስት ሺሕ በላይ ተሳታፊዎች፣ በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ ከሚካሄደው የመሪዎች ጉባዔ ባሻገር፣ የአዲስ አበባን ዋና ዋና ሆቴሎች አጨናንቀው ከ200 በላይ ተጓዳኝ ስብሰባዎችን እያካሄዱ ይገኛሉ፡፡ 

ጉባዔው በመጪው ታኅሣሥ ወር መጨረሻ የሚካተቱትን የመጀመሪያዎቹ የሚሊኒየሙ የልማት ግቦች መጠናቀቅን መነሻ አድርጎ ቀጣዮቹንና ለመጪዎቹ አሥራ አምስት ዓመታት የሚተገበሩትን ዘላቂ የልማት ግቦች በጥር ወር ለማስጀመር የሚያስችሉ የመንደርደርያ ሐሳቦችና የፋይናንስ ምንጮች ይፋ የሚደረጉበት ወሳኝ ጉባዔ መሆኑ ይነገርለታል፡፡ በዚህ ዓመት ዓለም የምታስተናግዳቸው ሦስት ቁልፍ ጉባዔዎች አሉ፡፡ አንደኛው በአዲስ አበባ የሚካሄደው ፋይናንስ ለልማት ሦስተኛው ጉባዔ ነው፡፡ ሁለተኛው በፓሪስ የሚካሄው የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ሲሆን፣ ሦስተኛውና ትልቁ ደግሞ በኒውዮርክ በጥር ወር እንዲካሄድ ቀን የተቆረጠለትና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሚጠራው የዘላቂ ልማት ግቦች ጉባዔ ነው፡፡

አዲስ አበባው የድርጊት አጀንዳ ጉባዔ፣ ከሚመክርባቸው መስኮች መካከል ፋይናንስ ይጎላል፡፡ በመጪዎቹ አሥራ አምስት ዓመታት ውስጥ ይተገበራሉ ተብለው የሚታሰቡት ዘላቂ የልማት ግቦች 17 ያህል ናቸው፡፡ በሚሊኒየሙ የልማት ግቦች ውስጥ በዋና ዋና መስክ የተካተቱት ስምንት እንደነበሩ ይታወሳል፡፡ በዘላቂ የልማት ግቦች ውስጥ ትልቅ ቦታ ይሰጣቸዋል ከሚባሉት አንዱ ደግሞ ድህነትና ረሃብን ከዓለም ማጥፋት ነው፡፡ ይህም ማለት በመጪዎች 15 ዓመታት ውስጥ በቀን 1.25 ዶላር እያገኙ ኑሯቸውን የሚገፉ ሚሊዮኖች ከዚህ የድህነት መገለጫ ይወጣሉ ማለት ነው፡፡

17ቱ ዘላቂ ግቦች 

 1. በየትኛውም የዓለም ክፍል በየትኛውም ዓይነት መንገድ የሚገኘውን ድህነት ማጥፋት፤
 2. ረሃብን ማስቀረት፣ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥና ሥርዓተ ምግብ ይዘትን ማሻሻልና ዘላቂ ግብርናን ማስፋፋት፤
 3. በየትኛውም የዕድሜ ክልል ለሚገኙ ሰዎች ጤናን ማረጋገጥና የሁሉንም ደኅንነት ማስጠበቅ፤
 4. ሁሉን የሚያካትትና ጥራት ያለው ትህምርት ማረጋገጥና የዕድሜ ልክ ትምህርት ዕድሎችን ለሁሉም ማስፋፋት፤
 5. የጾታ እኩልነትን ማረጋገጥና ሁሉንም ሴቶችና ልጃገረዶች ማብቃት፤
 6. ዘላቂ የውኃ አቅርቦትና ሳኒቴሽን አስተዳደርን ለሁሉም ማረጋገጥ፤
 7. ሁሉም በአቅሙ የሚያገኘው አስተማማኝ፣ ዘላቂና ዘመናዊ የኃይል አቅርቦትን ለሁሉም ማረጋገጥ፤
 8. ዘላቂነት ያለውና አካታች የኢኮኖሚ ዕድገትን ማበረታታት፣ ሙሉና ውጤታማ እንዲሁም ተስማሚ የሥራ ዕድል ለሁሉም ማረጋገጥ፤
 9. የማይበገር መሠረተ ልማት መገንባት፣ አሳታፊና ዘላቂ የኢንዱስትሪ ዘርፍ መፍጠርና ፈጠራን ማካተት፤
 10.  በአገር ውስጥና በአገሮች መካከል ያለውን የእኩልነት ልዩነት መቀነስ፤
 11. ከተሞችና ሰዎች የሰፈሩባቸውን አካባቢዎች ለሁሉም የሚሆኑ፣ ጤናማ፣ የማይበገሩና ዘላቂ እንዲሆኑ ማድረግ፤
 12. ዘላቂ ፍጆታና የምርት ሒደቶችን ማረጋገጥ፤
 13. የአየር ንብረት ለውጥንና ተፅዕኖዎቹን ለመዋጋት አስቸኳይ ዕርምጃ መውሰድ፤
 14.  ውቅያኖሶችን፣ ባህሮችንና የባህር ሀብቶችን ለዘላቂ ልማት መንከባከብ ማስቀጠል፤
 15. ዘላቂ የዓለም ሥነ ምኅዳር አጠባበቅ፣ መልሶ ማምጣት፣ ደኖችን በዘላቂነት ማስተዳደር፣ የደን ጭፍጨፋን መዋጋት እንዲሁም የመሬት መከላትና የሥነ ምኅዳር ጥፋትን ማስቆም፤
 16. ሰላማዊና ቀጣይ ማኅበረሰቦችን ለዘላቂ ልማት ማበርታት፣ ፍትሕን ለሁሉም ማዳረስና ውጤታማ፣ ተጠያቂነት ያለበት እንዲሁም አካታች ተቋማትን በሁሉም ደረጃ መገንባት፤
 17. ለዘላቂ ልማት የዓለም አጋርነትን የማጠናከሪያና የትግበራ ዘዴዎችን መቀየስና ማስፋፋት፣

ዘላቂ የልማት ግቦችን በድሃ አገሮች ውስጥ ለማስፈጸም የዓለም ሀብታም አገሮች ከኢኮኖሚ ድርሻው ለማዋጣት ቃል የገቡት ከ15 ዓመት በፊት ሲሆን፣ በተለይ ከ‹‹ሚሊኒየሙ ውሳኔዎች›› በኋላ ማለትም እ.ኤ.አ. በ2000 የፀደቁትን የልማት ግቦች ለማስተግበር ሀብታሞቹ ከዓመታዊ ብሔራዊ ገቢያቸው ውስጥ 0.7 በመቶ ለማዋጣት ቃል ገብተው ነበር፡፡ በዚህ መሠረት የሚሊኒየሙ የልማት ግቦችን ለማስፈጸም 200 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ያስፈልጋል ተብሎ ነበር፡፡

ለ17ቱ ዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ ስልቶች ከሆኑት መካከል ትልቁን ድርሻ የሚይዙት አሁንም ሀብታሞቹ አገሮች ናቸው፡፡ ኦፊሴላዊ የልማት ትብብሮችን በማቅረብ ሚናቸውን እንዲወጡ አሁንም እየወተወቱ ይገኛል፡፡ በመጪዎቹ አሥራ አምስት ዓመታት ውስጥ ይተገበራሉ የተባሉት ከእንግዲህ የሚጠይቁት ቢሊዮን ዶላሮች ብቻ አይሆንም ተብሏል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ፕሬዚዳንት ሆነው በተመረጡበት ፋይናንስ ለልማት ጉባዔ ላይ የተባበሩት መንግሥታት የልማት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ባን ኪ ሙን እንዳስታወቁት፣ ከቢሊዮኖች ወደ ትሪሊዮኖች የመሸጋገሪያው ጊዜ ነው፡፡ ታዳጊና በልማት ወደ ኋላ የቀሩ እየተባሉ የሚታወቁት አገሮች ከ1.5 እስከ ሁለት ትሪሊዮን ዶላር ይፈልጋሉ፡፡ ይህ ግን ከሀብታም አገሮች ብቻ የሚመጣና የሚዋጣ አይሆንም፡፡

ድሆቹ አገሮች ታክስ የማሰባሰቢያ ስልቶቻቸውን በማሻሻል አገር ውስጥ ገቢያቸውን ማሳደግ ትልቅ የቤት ሥራቸው ይሆናል፡፡ እርግጥ ከ15 ዓመት በፊትም ቢሆን ከአገር ውስጥ የፋይናንስ ምንጮች በመጠቀም የሚሊኒየሙን የልማት ግቦች ለመደገፍ ስምምነት ተደርጎ ነበር፡፡ ይሁንና ግን ታዳጊ አገሮች የታክስ ማጭበርበር፣ ወጪን ሆነ ብሎ በማናር ትርፍን የማሳነስና ገቢን የመሰወር፣ በባንኮች ጥላ ሥር በመሆን በሚፈጸም የካፒታል ማጭበርበርና ማሸሽ ተግባር ከፍተኛ ደባ ሲፈጸምባቸው ኖረዋል፡፡ የአፍሪካ አገሮች ብቻ በዓመት ከ50 እስከ 80 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት የካፒታል ማሸሽ ወይም የትርፍ ማጭበርበር ሰለባ ሆነዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ የኢትዮጵያ ድርሻ ከአሥር ቢሊዮን ዶላር በላይ ተገምቷል፡፡ በጠቅላላው በየዓመቱ ከዓለም ድሃ አገሮች የሚዘረፈው ገንዘብ ግን ግማሽ ትሪሊዮን ዶላር አሻቅቧል፡፡ 

የታክስ ማጭበርበርና የገቢ ስወራዎችን የሚያፋጥኑ፣ የሚያማክሩ ኩባንያዎች ከግማሽ በላይ መገኛቸው በሀብታሞቹ አገሮች ውስጥ መሆኑን በአዲስ አበባ እየተካሄዱ ከሚገኙት ስብሰባዎች የሚወጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ይህንን ለመከላከል የዓለም አገሮች በጋራ ለመሥራት እየተስማሙ ይመስላል፡፡

ታዳጊ አገሮች በታክስና በሌሎች የአገር ውስጥ የፋይናንስ ምንጮች የራሳቸውን የልማት አጀንዳ እንዲደጉሙ ግፊት እየተደረገባቸው መሆኑ ጎልቶ መውጣቱም በአዲስ አበባው ጉባዔ እየታየ ነው፡፡ አክሽን ኤድ ያወጣውን የተቃውሞ መግለጫ አሜሪካንና በአሜሪካ ጎራ የተሰለፉ ሀብታም አገሮችን የሚቃወም ነበር፡፡ ከዚህ ባሻገር ግን ትርጉም ያለው የፋይናንስ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን በመግለጽ የአውሮፓ አገሮች እ.ኤ.አ. እስከ 2020 ባለው ጊዜ ውስጥ ያዋጣሉ ተብሎ የሚጠበቀውን የገንዘብ መጠን ይፋ በማድረግ የአውሮፓ ኅብረትን የቀደመው የለም፡፡ ማክሰኞ ሐምሌ 6 ቀን 2007 ዓ.ም. ማምሻውን የአውሮፓ ኅብረት ይፋ ባደረገው መሠረት በአምስት ዓመት ውስጥ ተጨማሪ 100 ቢሊዮን ዩሮ በጋራ ለማቅረብ ቃል ገብቷል፡፡

የአዲስ አበባው የድርጊት አጀንዳ ስምምነት ተደርጎበት ወደ ኒውዮርክ ሰነዱ በተመድ አገሮች ዘንድ እንዲፀድቅ ይደረጋል ተብሎ ቢጠበቅም፣ በአውሮፓ ኅብረት ከታየው የፋይናንስ ድጋፍ አኳያ ሲታይ፣ ሁለት ትሪሊዮን ዶላር ላይ ስምምነት ይደረጋል ተብሎ መጠበቅ ከባድ እንደሚሆን ፍንጭ ሰጥቷል፡፡ ከወዲሁ ወገቤን እያሉ ያሉ አገሮች መታየታቸውም ስምምነቱን በሚፈለገው የገንዘብ መጠን ልክ እንዲፀድቅ መጠበቅን ፈታኝ ያደርገዋል፡፡ ይህም ሆኖ አዲስ አበባ የብዙዎችን መጻዒ ዕድል ሊወስን በሚችል ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ትገኛለች፡፡ የዓለም ዓይንና ጆሮም አዲስ አበባ ላይ ተተክሏል፡፡ ባን ኪ ሙን ይህንን ተንተርሰው እንዲህ ብለዋል፡፡ ‹‹የዓለም ሕዝቦች በጉጉት እየተለመከቱን ነው፡፡ አናሳዝናቸው፡፡›› ይህንን የተናገሩት ዋና ጸሐፊው የሚመሩት ተመድ 70 ዓመቱ ላይ በሚገኝበት ወቅት፣ የዓለም ድሃ ሕዝቦች ግን አሁንም ድህነትንና ረሃብን ለማጥፋት በየዓመቱ 66 ቢሊዮን ዶላሮች ያስፈልጋቸዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች