Monday, June 17, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የዓለም ባንክ በመጪዎቹ ሦስት ዓመታት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንትና የኢኮኖሚ ዕድገት እንደሚቀንሱ ተነበየ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

–  የዕዳ ክምችት የኢኮኖሚውን 65 በመቶ ድርሻ ሊይዝ እንደሚችል ጠቆመ

የዓለም ባንክ በየዓመቱ በሚያወጣው ተከታታይ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ ባተኮረ ሪፖርት መሠረት፣ እ.ኤ.አ. ከ2015 ጀምሮ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት ይኖራል ተብሎ ከሚጠበቀው የባለሁለት አኃዝ በመውረድ ወደ 8.5 ከመቶ ዝቅ እንደሚል ባንኩ ተነበየ፡፡ የመንግሥት ባለሥልጣናት ትንበያውን ተቃውመዋል፡፡

የአገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት እንደሚቀንስና የኢንቨስትመንት ሒደቱ እንደሚቀዛቀዝ የገለጸው የዓለም ባንክ፣ የኮንስትራክሽን ዘርፍ እየቀዘቀዘ መሄድ፣ የካፒታልና የሰው ኃይል አጠቃላይ ምርታማነት መቀዛቀዝ፣ ለኢኮኖሚው ዕድገት መቀነስ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ የተባሉና በዓለም ባንክ በምክንያትነት የቀረቡ ናቸው፡፡

የዓለም ባንክ ዋና ኢኮኖሚስትና የፕሮግራም ኃላፊ ላርስ ክርስቲያን ሞለር ሪፖርቱን ባቀረቡበት ወቅት እንዳብራሩት፣ ምንም እንኳ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት እንደሚቀንስ ቢጠበቅም፣ የሚያስመዘግበው ዕድገት ግን ፈጣን ከሚባሉት መካከል ሆኖ ይዘልቃል፡፡ በመሆኑም ከሁለት ዓመት በኋላ የኢኮኖሚው ዕድገት 8.5 በመቶ ይሆናል ተብሏል፡፡ ይሁንና በመጪው ዓመት ግን የ10.5 በመቶ ዕድገት እንደሚኖር ደግሞ ባንኩ ይተነብያል፡፡

የኮንስትራክሽኑ ዘርፍ መቀዛቀዝ የሚያስከትለውን የኢኮኖሚ ዕድገት መቀነስ የሚያካክሰው የወጪ ንግድ ዘርፉ ማደግ እንደሆነ ሞለር አስታውቀዋል፡፡ በዚህ መሠረት የግብርናው ዘርፍ በዚህ ዓመት 1.9 በመቶ፣ በመጪው ዓመት 2.8 በመቶና ከሁለት ዓመት በኋላ 2.4 በመቶ ዕድገት እንደሚጠበቅበት ገልጸዋል፡፡ በአንፃሩ የኢንዱስትሪው ዘርፍ በሦስት ዓመታት ውስጥ በአማካይ የ1.9 ከመቶ ዕድገት ሲጠበቅበት፣ አገልግሎት የ5.2 በመቶ አማካይ ዕድገት እንደሚኖረው የባንኩ ሪፖርት ያሳያል፡፡

ከዚህ ባሻገር እስካሁን እየተዳከመ በመጣው የወጪ ንግድ አፈጻጸም ሳቢያ የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ክምችትና የመንግሥት ፊስካል በጀት ተፅዕኖ ውስጥ እየገቡ መሆናቸውን የባንኩ ሪፖርት ሲያመለክት፣ በተለይ በወጪና በገቢ ንግዱ መካከል በስፋት እየታየ የመጣው የንግድ ሚዛን ጉድለት የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ይበልጥ እያባባሰው መሆኑን ይጠቁማል፡፡ ላለፉት አራት ዓመታት በኢትዮጵያ የባንኩን ጽሕፈት ቤት በመምራት የቆዩት ቻይናዊው ጉዋንግ ዚ ቼን፣ የውጭ ምንዛሪ ግኝት እየሳሳ መምጣትና የመንግሥት ካፒታል ወጪ መጨመር፣ የዕዳ መጠኑን እያጎላው መምጣቱን ገልጸዋል፡፡

ሞለር ባቀረቡት ሪፖርት መሠረት የአገሪቱ የዕዳ መጠን ከነበረበት የ45 በመቶ ወደ 65 በመቶ እያሻቀበ እንደሚመጣ ይፋ ተደርጓል፡፡ የዕዳውን መጠን ያባባሰው ደግሞ በረጅም ጊዜ ከአነስተኛ የወለድ መጠን ጋር ይከፈሉ ከነበሩ ብድሮች ይልቅ፣ ከስድስት በመቶ በላይ ወለድ የሚያስከፍሉና የአጭር ጊዜ የክፍያ ዘመን ያላቸው ብድሮች መብዛት፣ በዓለም ገበያ ላይ እየተጠናከረ ከመጣው ከዶላር የመግዛት አቅምና ከብር የመግዛት አቅም መዳከም ጋር ተዳምሮ የአገሪቱን የዕዳ መጠን እያበራከተው እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡ መንግሥት ለዕዳ ክፍያ የሚያወጣውን ገንዘብ ከፍተኛ በማድረግ ኢንቨስትመንቱን እንደሚቀንስበትም ይጠበቃል ይላል ሪፖርቱ፡፡ የዶላር የመግዛት አቅም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በ25 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር ዴኤታው አቶ አህመድ ሺዴ በበኩላቸው፣ የዶላር የመግዛት አቅም እየጠነከረ መምጣቱን መንግሥት በአንክሮ እንደሚመለከተውና በቅርብ እንደሚከታተለው ገልጸው፣ ለአገሪቱ ሥጋት የመሆን ደረጃ ላይ እንዳልደረሰ ግን ተከራክረዋል፡፡ የአገሪቱ የወጪ ንግድን በማስፋፋት የዕዳ ጫናውንና የምንዛሪ ለውጡን ለመቋቋም እንደሚታሰብ ሲያስረዱም፣ ከወትሮው የሸቀጦች የወጪ ንግድ በተጓዳኝ ከኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ አንድ ቢሊዮን ዶላር እንደሚጠበቅ ገልጸዋል፡፡ ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ወደ ውጭ የሚላከው የፋብሪካ ምርትም ሌላው ተስፋ የሚደረግበት  ዘርፍ ነው ብለዋል፡፡

ይህም ቢባል ግን የአገሪቱ አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ በዝግታ እያደገ እንደሚገኝ ያረጋገጡት ሞለር፣ የኢንዱስትሪ ዘርፉ በተለይ በኮንስትራክሽን ዘርፉ ላይ ተመሥርቶ እያደገ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል፡፡ በአንፃሩ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ውስጥ በአምስት ዓመት ውስጥ ይገነባሉ ከተባሉት አምስት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስት አንዱ ብቻ እሱም በቦሌ ለሚ አካባቢ በዓም ባንክ የፋይናንስ ድጋፍ የተገነባው ነው፡፡ ቀርፋፋ የተባለው የአምራች ኢንዱስትሪ የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ከሚያስችለው ምቹ አጋጣሚ መካከል ርካሽ የጉልበት ወጪ ሲጠቀስ፣ የሠለጠነ የሰው ኃይል የማግኘት ፈተና ግን በርካቶችን ይፈታተናቸዋል ብለዋል፡፡ በብድር፣ በመሬት፣ በኃይል፣ በሎጂስቲክስና በታክስ አስተዳደር ላይ የሚታዩ ችግሮች ፈታኝ መሆናቸውን ሞለር አስታውቀዋል፡፡ ሆኖም በሁለተኛው የአምስት ዓመት ዕቅድ ውስጥ መሠረታዊ የመዋቅር ለውጥ በኢኮኖሚው ላይ ሊታይ እንደሚችል ሞለር ጠቁመዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታው ዶ/ር መብራህቱ መለስ፣ የብሔራዊ ባንክ ተወካዮች፣ የጠቅላይ ሚኒስትር የኢኮኖሚ ጉዳዮች አማካሪ አቶ ነዋይ ገብረአብና ሌሎችም ባለሥልጣናት በዓለም ባንክ የጥናት ሪፖርት ውስጥ የተካተቱ ግኝቶችን ተችተው ተከራክረዋል፡፡  በብድር አቅርቦት፣ በሠለጠነ የሰው ኃይልና በመሬት አቅርቦት ላይ የመንግሥት ድጋፍ መኖሩን ተናግረዋል፡፡ የሎጂስቲክስና የታክስ ጉዳዮችን በተመለከተ መሠረታዊ ለውጥ እየተደረገ እንደሆነ በመግለጽ፣ ዕድገቱና የወጪ ንግዱ እየጨመረ እንደሚሄድ አስረድተዋል፡፡ የዓለም ባንክን ትንበያም አልተቀበሉም፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች