Friday, March 31, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበድንገት ክሳቸው ተቋርጦ ከእስር የተለቀቁ ጦማርያንና ጋዜጠኞች ጉዳይ እያነጋገረ ነው

በድንገት ክሳቸው ተቋርጦ ከእስር የተለቀቁ ጦማርያንና ጋዜጠኞች ጉዳይ እያነጋገረ ነው

ቀን:

–  መንግሥት ‹‹ክሴን አቋርጫለሁ›› ከማለት ባለፈ ምክንያቱን ከመናገር ተቆጥቧል

ከአንድ ዓመት በፊት ሚያዝያ 26 እና 27 ቀን 2006 ዓ.ም. በድንገት ተይዘው ከታሰሩ በኋላ፣ በፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ክስ ተመሥርቶባቸውና የሰነድና የሰው ማስረጃ ቀርቦባቸው፣ ለብይን የተቀጠሩበትን ቀን እየተጠባበቁ ከነበሩት አሥር ተከሳሾች መካከል አምስቱ በድንገት ሐምሌ 1 እና 2 ቀን 2007 ዓ.ም. መፈታታቸው እያነገጋገረ ነው፡፡

ለተከሳሾቹም ሆነ ወክለዋቸው ለሚከራከሩላቸው ጠበቆቻቸው ምንም ዓይነት መረጃ ሳይደርሳቸው በድንገት፣ ‹‹ዓቃቤ ሕግ ክሱን አቋርጣል፡፡ በመሆኑም ከዛሬ ጀምሮ ከእስር ተለቃችኋል፤›› የተባሉት ተከሳሾች ጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስ፣ አስማማው ኃይለ ጊዮርጊስ፣ ኤዶም ካሳዬና ጦማሪያን ዘለዓለም ክብረትና ማህሌት ፋንታሁን ናቸው፡፡ ክሱ እንደተቋረጠ በማረሚያ ቤት ኃላፊዎች ከማወቃቸው በስተቀር፣ ከክሱ ሙሉ በሙሉ ነፃ ስለመሆናቸው ወይም በተፈለገ ጊዜ በዚሁ ክስ የሚከሰሱ ስለመሆኑ የሚያውቁት  ነገር እንደሌለ ተገልጿል፡፡

ተከሳሾቹ የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 3(2) ማለትም የኅብረተሰቡን ወይም የኅብረተሰቡን ክፍል ደኅንነት ወይም ጤና ለከፍተኛ አደጋ ማጋለጥ፣ በንዑስ አንቀጽ 4 ማለትም የሽብርተኝነት ድርጊት ለመፈጸም በማቀድ፣ በመዘጋጀት፣ በማሴርና በማነሳሳት ሙከራ፣ እንዲሁም የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32(1) ሀ እና ለን በመተላለፍ፣ በቀጥታ ወይም በእጅ አዙር፣ በመላ ሐሳባቸውና አድራጎታቸው በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን መጠርጠራቸውን ጠቅሶ ዓቃቤ ሕግ ክስ አቅርቧል፡፡ ጉዳይዋ በሌለችበት እየታየ ካለችው ጦማሪ ሶልያና ሽመልስ በስተቀር በሁሉም ተከሳሾች ላይ 18 የሰዎች ምስክሮች፣ የሰነድ፣ የሲዲና ቪሲዲ ማስረጃዎችንም አቅርቦ ጨርሷል፡፡ ፍርድ ቤቱ መዝገቡን መርምሮ ብይን ለመስጠት ለሐምሌ 13 ቀን 2007 ዓ.ም. ቀጠሮ ይዟል፡፡ ነገር ግን በፌዴራል ማረሚያ ቤት ሆነው ክሳቸውን በመከታተል ላይ ካሉት ዘጠኝ ተከሳሾች ውስጥ፣ ከላይ የተጠቀሱት አምስቱ ተከሳሾች ሐምሌ 1 እና 2 ቀን 2007 ዓ.ም. ከእስር ተፈተዋል፡፡

ተከሳሾቹ ከእስር የተፈቱት የኢፌዴሪ አስፈጻሚ አካላት ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 691/2003 አንቀጽ 16(6) መሠረት፣ ፍትሕ ሚኒስቴር በቂ ምክንያት ሲኖረው በሕግ መሠረት ክሱን ማቋረጥ እንደሚችል የሚገልጸውን ድንጋጌ ተጠቅሞ ክሱን በማቋረጡ ነው፡፡

ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ ለፍትሕ ሚኒስቴር በተሰጠው ሥልጣን መሠረት በተከሳሾቹ ላይ የመሠረተውን ክስ ያቋረጠ ቢሆንም፣ አዋጁ ‹‹በቂ ምክንያት ሲኖረው በሕግ መሠረት ክሱን ያነሳል›› ለሚለው በየትኛው ሕግ እንደሆነ ዝርዝር ማብራሪያ አለመስጠቱ የሕግ ባለሙያዎችም ግልጽ እንዳልሆነላቸውና ግራ እንዳጋባቸው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ‹‹በቂ ምክንያት ማለት ምን ማለት ነው?›› የሚል ጥያቄ የሚያነሱም አሉ፡፡

የተከሳሾቹ ክስ የተቋረጠው ከፍትሕ ሚኒስቴር መዝገቡን እየመረመረ ለሚገኘው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት በተጻፈ ደብዳቤ መሆኑን፣ ፍርድ ቤቱም የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ተከሳሾቹን እንዲፈታ በሰጠው ትዕዛዝ መሠረት እንደሆነ በመገለጹ፣ ሪፖርተር ማብራሪያ ለማግኘት ፍትሕ ሚኒስቴር በመሄድ ጠይቋል፡፡ የፍትሕ ሚኒስትሩም ሆኑ ሚኒስትር ዴኤታዎች በተለያዩ ስብሰባዎች ላይ መሆናቸው በመገለጹ ምላሽ ማግኘት አልተቻለም፡፡ የኮሙዩኒኬሽን ማስተባበሪያ ኃላፊው አቶ ደሳለኝ ተሬሳ የተከሳሾቹ ክስ በአዋጅ ቁጥር 691/2003 አንቀጽ 16(6) መሠረት መቋረጡን ከመግለጽ ባለፈ ተጨማሪ ማብራሪያ መስጠት አልቻሉም፡፡

መንግሥት በተከሳሾቹ ላይ የጀመረውን ክስ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ማቋረጡን ከመናገር ባለፈ፣ ተጨማሪ ማብራሪያ ከመስጠት መቆጠቡ ተፈቺዎችም ሆኑ ሌሎች አስተያየት ሰጪዎች ውዥንብር ውስጥ መግባታቸውን እየተናገሩ ነው፡፡ ተከሳሾቹ በድንገት ክሳቸው ተቋርጦ በመፈታታቸው ደስተኛ ቢሆንም፣ ክሱ ሲቋረጥ ሙሉ በሙሉ ነፃ ስለመሆናቸው ወይም በድጋሚ የሚከሰሱበት ስለመሆኑ አለመገለጹ ግራ የሚያጋባ በመሆኑ፣ የሚመለከተው አካል ግልጽ ማድረግ እንዳለበት አስተያየት ሰጪዎች ተናግረዋል፡፡ ተፈቺዎቹ ‹‹በነፃ ተፈትተናል ብለው ያለምንም ሰቀቀን መኖር ይችላሉ? ተፈቺዎቹና ጠበቆቻቸው ክሱ ስለተቋረጠበት ምክንያት ማወቅ የለባቸውም? ያለምንም ማብራሪያ ብድግ ብሎ ክሴን አንስቻለሁ ማለት ምን ማለት ነው? ሕጉ በቂ ምክንያት ወይም ጥሩ ምክንያት (Good Cause) ሲል ምን ማለቱ ነው?›› የሚሉ ጥያቄዎች ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ የሕግ ባለሙያ አንስተው፣ በቂ ማብራሪያ እንደሚያስፈልገው አሳስበዋል፡፡

ከእስር ከተፈቱት መካከል ጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስ እንዴት እንደተለቀቁና ስለመለቀቃቸው ቅድመ መረጃ እንደነበራቸው ወይም እንደሌላቸው ሪፖርተር ላቀረበለት ጥያቄ በሰጠው ምላሽ፣ እሱና ሌሎቹ ታሳሪዎች እስከተለቀቁበት ሐምሌ 1 ቀን 2007 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ 10፡30 ሰዓት ድረስ፣ ምንም የሚያውቁት ነገር አልነበረም፡፡ ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ ባቀረበባቸው የሰነድ ማስረጃዎች ላይ የትችት ማብራሪያ ማቅረብ እንደሚችሉ ፍርድ ቤቱ በሰጠው ትዕዛዝ መሠረት የመጀመሪያ የትችት ጽሑፋቸውን ለጠበቆቻቸው ሰጥተው፣ የመጨረሻውን (በጠበቆች ተጽፎ ለፍርድ ቤቱ የሚሰጠውን ትችት) ለማየት ጠበቆቻቸውን እየተጠባበቁ እንደነበሩ ተናግሯል፡፡ በተጠቀሰው ሰዓት በእስር ላይ የሚገኘው አጥናፍ ብርሃኔና እሱ ባሉበት ዞን መዝናኛ አዳራሽ ውስጥ ሆነው፣ በኢቢሲ-3 የሚተላለፍ ፊልም እያዩ እንደነበር የገለጸው ጋዜጠኛ ተስፋለም፣ በጠባቂዎች ዘወትር እንደሚደረገው ከእስር የሚለቀቁ ሰዎች ስም በድምፅ ማጉያ ሲጠራ፣ የአባቱ ስም ትክክል ባይሆንም ‹‹ተስፋለም›› የሚል ስም መስማቱን ገልጿል፡፡

የእሱን ስም የሚጠራው ተሳስቶ እንደሆነ በመገመት ፊልሙን በማየት ላይ እያሉ በተደጋጋሚ በመጠራቱ፣ ወደሚጠራው ሰው ጠጋ ብለው ስም ዝርዝር ሲመለከቱ፣ የዘለዓለምንና የአስማማውን ስም በማየቱ ‹‹የሆነ ነገር አለ›› በማለት፣ ወደ አስተዳደር ሄደው ሲጠይቁ ‹‹ስምህ እየተጠራ አልቀርብ ያልከው አንተ ነህ?›› ተብሎ ሲገባ፣ የሞላው ቅጽ ተረጋግጦ ‹‹ውጣ›› መባሉን ተናግሯል፡፡

‹‹አንድ ዓመት ከሦስት ወራት ታስሬ እንዴት በድንገት ውጣ እባላለሁ? በምን ምክንያት?›› የሚል ጥያቄ ማንሳቱን የገለጸው ጋዜጠኛ ተስፋለም፣ ‹‹ዓቃቤ ሕግ ክሱን አቋርጦ ነው›› መባሉንና የመፈቻ ካርኒ (እንደ ሰርተፊኬት የምታገለግል) ሲሰጠው በካርኒውም ላይ ‹‹ክሱ ተቋርጧል›› ከሚል ውጪ ምንም የተገለጸ ነገር እንደሌለ አስረድቷል፡፡ የማረሚያ ቤቱ የውጭ በር ላይ ሲደርስ ማመን አቅቶት ቆም ብሎ ግራና ቀኝ ሲመለከት ምንም ነገር ማጣቱን የተናገረው ጋዜጠኛ ተስፋለም፣ ማረሚያ ቤት የሚለብሰውን ፒጃማ እንደለበሰ ባጃጅ ውስጥ ገብቶ ልብሱን እንደቀየረና ከባለባጃጁ ስልክ ጠይቆ መፈታቱን መጀመሪያ ያበሰረው ለእህቱ መሆኑን ገልጿል፡፡ እስከ ሐምሌ 3 ቀን 2007 ዓ.ም. ድረስ እሱም ሆነ ጓደኞቹ ጠበቃቸውን አቶ አመሐ መኰንን አግኝተው ሲያነጋገሩ፣ ጠበቃውም ቢሆኑ እንዴትና በምን ሁኔታ እንደተለቀቁ እንደማያውቁ መናገራቸውን ጋዜጠኛ ተስፋለም ለሪፖርተር አስረድቷል፡፡         

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተወግዘው የነበሩ ሦስቱ ሊቀጳጳሳትና 20 ተሿሚ ኤጲስ ቆጶሳት ውግዘት ተነሳ

_ቀሪዎቹ ሦስት ህገወጥ ተሿሚዎች የመጨረሻ እድል ተሰጥቷቸዋል ​ ጥር 14...

በሕወሓት አመራሮች ላይ ተመስርቶና በሂደት ላይ የነበረው የወንጀል ክስ ተቋረጠ

በቀድሞ የትግራይ ክልል ፕሬዚደንት ደብረጽዮን ገብረሚካኤ,(ዶ/ር)ና ባለፈው ሳምንት በተሾሙት...

[የምክር ቤቱ አባል ላቀረቡት ጥያቄ በተሰጣቸው ምላሽ አቤቱታቸውን ለክቡር ሚኒስትሩ እያቀረቡ ነው]

ክቡር ሚኒስትር እየሆነ ያለው ነገር ትክክል ነው? ምነው? ምክር ቤቱም ሆነ...

የጉራጌ የክልልነት ጥያቄ ትኩሳት

ቅዳሜ መጋቢት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. በጉራጌ ዞን ወልቂጤ...