– የተቀጡበት ደንብ ለትርጉም ለፌዴሬሽንና ምክር ቤት እንዲላክ ጠይቀው ነበር
ጠበቃ ተማም አባቡልጉ በባልና ሚስት መካከል የተፈጠረ አለመግባባትን ለመፍታት ሽምግልና የተቀመጡበትን ጉዳይ በጥብቅና ይዘዋል ተብለው በቀረበባቸው የዲሲፕሊን ክስ፣ ለአንድ ዓመት ከሰባት ወራት ከጥብቅና አገልግሎታቸው የሚያግድ ቅጣት ተጣለባቸው፡፡
የጠበቆች የዲሲፕሊን ጉባዔ ከሰኔ 5 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ ቅጣቱ እንዲጣልባቸው ያቀረበው የቅጣት ውሳኔ ሐሳብ በፍትሕ ሚኒስትሩ ፀድቆ፣ ሰኔ 29 ቀን 2007 ዓ.ም. የጥብቅና ፈቃድና አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ፍቃዱ ደምሴ ቅጣቱን ለ13 ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ይፋ አድርገዋል፡፡
ጉባዔው የሰጠው የውሳኔ ሐሳብ እንደሚያብራራው፣ ወ/ሮ ፈትያ የተባሉ ግለሰብና ባለቤታቸው መሀል በተፈጠረ አለመግባባት ጠበቃ ተማም ሽምግልና ይቀመጣሉ፡፡ ሽምግልናው ውጤታማ ባለመሆኑ ባልና ሚስት በፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ቦሌ ምድብ ችሎት ክስ ሲመሠርቱ ጠበቃ ተማም አባቡልጉ የወ/ሮ ፈትያ ጠበቃ ሆነው በመቆማቸው፣ የወ/ሮ ፈትያ ባለቤት ጠበቃውን በመቃወም ለፍትሕ ሚኒስቴር የጠበቆች ዲሲፒሊን ጉባዔ አቤቱታ ማቅረባቸውን የውሳኔ ሰነዱ ያስረዳል፡፡
ሐምሌ 25 ቀን 2006 ዓ.ም. ለቀረበባቸው አቤቱታ ነሐሴ 1 ቀን 2006 ዓ.ም. ምላሽ የሰጡት ጠበቃ ተማም እንዳስረዱት፣ ፍትሕ ሚኒስቴር ተከራካሪ ወገን በመሆኑ ጉዳዩን ተቀብሎ ማየቱ የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 25 (የእኩልነት መብት) እና 79 የዳኝነት መብትን የሚጥስ ነው፡፡ በመሆኑም ጉባዔው ጉዳዩን ተቀብሎ ማየት እንደሌለበት አስረድተዋል፡፡ ሙሉ አድራሻ እንዳላቸው እየታወቀ ጉባዔው መጥሪያውን ጠቅላይ ፍርድ ቤት እንዲለጠፍ በማድረግ መድልኦ እንደፈጸመባቸው ጠቁመዋል፡፡ ይኼም ጉባዔው ገለልተኛ ሆኖ የማይሠራ መሆኑን ስለሚያሳይ መዝገቡ ተዘግቶ እንዲሰናበቱ ጠይቀዋል፡፡ አመልካቹ በፍርድ ቤት እሳቸው ጉዳዩን በሽምግልና ያዩት መሆኑን አንስቶ ሳይቃወም፣ ለዲሲፕሊን ክስ ሊያቀርብ እንደማይችልም ጠበቃ ተማም አስረድተዋል፡፡
ጉባዔው የተከሰሰን ጠበቃ ሁሉ ጥፋተኛ እንደሚል በመልሳቸው የጠቆሙት አቶ ተማም፣ ፍትሕ ሚኒስቴርም ጠበቆችን በባለድርሻ አካላት ዝርዝር ሥር እንደ አንድ ባለድርሻ ስለማይቆጥርና ጉባዔው በሥሩ የተደራጀ በመሆኑ ገለልተኛ እንደማይሆንም ገልጸው፣ ሥልጣንን ለፍትሕ ሚኒስቴር የሰጠው ደንብ ኢ-ሞራላዊ ስለሆነ ለትርጉም ለፌዴሬሽን ምክር ቤት እንዲላክላቸው መጠየቃቸውን ውሳኔው ያብራራል፡፡
ጠበቃ ተማም ዘርዝር ባለው ምላሻቸው በሽምግልና እንዳልተቀመጡ የሚያስረዱላቸውን ሰባት የሰው ማስረጃዎች ማቅረባቸውም ተገልጿል፡፡
ጉባዔው የአመልካችን ምስክሮች ከመስማቱ በፊት ጠበቃ ተማም ባነሱዋቸው መቃወሚያ ላይ ብይን ሰጥቷል፡፡ በብይኑ እንደገለጸው፣ ጉባዔው ሥልጣን እንደሌለውና ሥልጣኑን የሰጠው ሕግ ኢ-ሕገመንግሥታዊ መሆንን በሚመለከት ጠበቃው የገለጹት፣ ፍትሕ ሚኒስቴር ከጠበቆች ጋር ተከራካሪ መሆኑን ለመግለጽ እንደሆነ አስፍሯል፡፡ ነገር ግን ጠበቃው ይኼንን ያነሱት የመሥሪያ ቤቱን ሰፊ ሥልጣን ካለመረዳትና የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 25 እና 79 በሚገባ ባለመረዳታቸው መሆኑን ገልጿል፡፡
ጠበቃው ጉባዔው ገለልተኛ እንዳልሆነ መግለጻቸው የጉባዔውን ስም የሚያጠፋና ክብሩንም ዝቅ የሚያደርግ መሆኑን ጠቁሞ፣ ይህም ለመከራከር ዝግጁ አለመሆናቸውን የሚያሳይ መሆኑን በማስታወቅ መቃወሚያቸውን ውድቅ ማድረጉን ገልጿል፡፡
አመልካች በመከራከርያ ያላነሳውን ነጥብ የዲሲፕሊን ክስ መመሥረቻ ማድረግ እንደማይችል ጠበቃው ያነሱትን ክርክር በሚመለከት፣ ጉባዔው ‹‹ውኃ የሚያነሳ ሐሳብ አይደለም›› ብሏል፡፡
ጠበቃ ተማም ሥልጣኑን ለጉባዔው የሰጠው ሕግ ኢ-ሕገመንግሥታዊ መሆኑን ቢናገሩም፣ ሕጉ ግልጽና ሕገ-መንግሥታዊ በመሆኑ ለትርጉም ለፌዴሬሽን ምክር ቤት መላክ እንደማያስፈልግ በውሳኔው ገልጿል፡፡
የአመልካች ምስክሮች በሰጡት ምስክርነት ጠበቃ ተማም በሽምግልናው ወቅት መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡ የጠበቃ ተማም ምስክሮች ሽምግልና መደረጉን የገለጹ ቢሆንም፣ ጠበቃው ስለመገኘታቸው ግን ምንም ያሉት ነገር እንደሌለም ጠቁሟል፡፡
ጉባዔው ማስረጃው ሲመዘን የአመልካች ምስክሮች አመሰካከር ዕምነት የሚጣልበት ሆኖ መገኘቱን ጠቁሞ፣ ጠበቃው በሽምግልና ያዩትን ጉዳይ በጥብቅና ይዘዋል ማለት የሚችልበት ድምዳሜ ላይ መድረሱን ገልጿል፡፡
በመሆኑም ጠበቃ ተማም የፌዴራል ፍርድ ቤቶች የሥነ ምግባር ደንብን በመተላለፋቸው ጥፋተኛ ብሏቸዋል፡፡ በፌዴራል ፍርድ ቤቶች በጠበቆች ምዝገባና ፈቃድ አዋጅ መሠረት አንድ ዓመት ከሰባት ወራት ከጥብቅና ሥራቸው እንዲታገዱ ቅጣት ጥሎባቸዋል፡፡