Monday, April 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ኢትዮጵያ የኢንዱስትሪዎች መጠለያ እንደምትሆን እጠብቃለሁ››

አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ፣ የኧርነስት ኤንድ ያንግ ኢትዮጵያ ማኔጂንግ ፓርትነር

አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ የኧርነስት ኤንድ ያንግ ኢትዮጵያ ማኔጂንግ ፓርትነር ሲሆኑ፣ የትራንሳክሽን አድቫይዘሪ ሰርቪስስ ኃላፊም ናቸው፡፡ ከአፍሪካና ከመካከለኛው ምሥራቅ የመጡትን ጨምሮ በርካታ ኢንቨስተር ደንበኞች አሉዋቸው፡፡ አቶ ዘመዴነህ የእንግሊዙ ዲያጆ ሜታ ቢራን እንዲገዛ ቁልፍ ሚና ተጫውተዋል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የልማት ፍኖተ ካርታ የሆነው ራዕይ 2020 እንዲቀረፅም ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል፡፡ ለተለያዩ ደንበኞቻቸው በፋይናነስ አገልግልቶች፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በቴሌኮምና በአየር መንገዶች ዘርፍ በማማከር ዓለም አቀፋዊ ልምድ አላቸው፡፡ አሥራት ሥዩም በመጀመርያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሸን ዕቅድ አፈጻጸም ላይ፣ በሁለተኛው ዕቅድ በማኑፋክቸሪንግ ላይ ትኩረት ስለተደረገበት ምክንያትና በኢትዮጵያ መደበኛ የሆነ የኢኩቲ ገበያ አስፈላጊ መሆን አለመሆኑን በተመለከተ አቶ ዘመዴነህን አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የመጀመርያውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ እንዴት ይገመግሙታል? ምንስ አሳክቷል?

አቶ ዘመዴነህ፡- በመጀመርያ ደረጃ ዕቅዱ ወደ ሥራ የገባው በትክክለኛ ጊዜ ላይ ነው፡፡ ዕቅዱ አገሪቱ በቀጣይ አምስት፣ አሥርና አሥራ አምስት ዓመታት የት መድረስ እንዳለባት ትኩረት የሚያደርግና ቁርጠኝነት የታየበት ምልከታ ያለው ነበር፡፡ ኢትዮጵያ በፍጥነት ማደግ ትችላለች፡፡ ከዚህ በፊት እንደነበረው ሁሉ አሁንም ትልቅ ነገር ማሳካት እንችላለን የሚል ከባቢያዊ ሁኔታን ለመፍጠር ጠንካራ ቁርጠኝነት የታየበት ዕቅድ ነበር፡፡ መዋቅራዊ ማዕቀፍ ለአገሪቱ የሰጠ ዕቅድ ነበር፡፡ በዕቅዱ ላይ የተቀመጡ ሁሉም ነገሮች ባይሳኩም በርካታ ነገሮች ግን አሳክቷል፡፡ በእኔ ዕይታ ከመጀመርያውም የዕቅዱን መቶ በመቶ ለማሳካት ይቻላል በሚል አልተነሳንም፡፡ ለምሳሌ የግዙፍ መሠረተ ልማት ግንባታዎችን በተመለከተ ብዙዎቹ ተሳክተዋል ወይም በሒደት ላይ ይገኛሉ፡፡ የተቀሩትም በቅርቡ እንደሚሳኩ አምናለሁ፡፡

ዕቅዱ በፈጠረው ማዕቀፍ የተነሳ ባለፉት አምስት ዓመታት ምን ለመሥራት እንደታቀደና ምን እንደተሳካ የምንለካባቸው መሣሪያዎች አሉ፡፡ ምናልባት በታቀደውና በተሳካው መካከል መመጣጠን ያልታየባቸው ዘርፎች ማኑፋክቸሪንግና ወጪ ንግድ ናቸው፡፡ በቀጣዩ ዕቅድ የማኑፋክቸሪንግ ግቦች የሚሳኩ ይመስለኛል፡፡ የወጪ ንግድ ላይ ግን ብዙ መሥራት አለብን፡፡ ማኑፋክቸሪንግና ወጪ ንግድ እርስ በርስ እንደሚመጋገቡ እጠብቃለሁ፡፡ ጥሬ ዕቃዎችን ብቻ ወደ ውጭ በመላክ ወጪ ንግድን ማሳደግ አይቻልም፡፡ እሴት መጨመር መቻል አለብን፡፡ የምሥራቅ እስያ አገሮች ዕድገት ያስመዘገቡት በማኑፋክቸሪንግና እሴት በመጨመር ወደ ውጭ በሚልኳቸው ዕቃዎች አማካይነት ነው፡፡ በነገራችን ላይ ማኑፋክቸሪንግ የግብርና ምርቶች ላይ እሴት መጨመርን ያጠቃልላል፡፡ ቀጣዩ ዕቅድ እነዚህን ነገሮች እንደሚያስተካክል አስባለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ለማቀድ ግንዛቤ ውስጥ ሊገቡ ይገባሉ የሚሏቸው ነገሮች ምንድን ናቸው? መሠረታዊ የሚባሉትስ ክፍተቶች የትኞቹ ናቸው?

አቶ ዘመዴነህ፡- በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ኢትዮጵያ ለተለያዩ ኢንዱስትሪዎች መጠለያ እንደምትሆን እጠብቃለሁ፡፡ በግብርና ላይ በከፍተኛ ሁኔታ ጥገኛ የሆነው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ወደ ማኑፋክቸሪንግ እንደሚጓዝ አስባለሁ፡፡ ረቂቁ ዕቅድ ለውይይት በቀረበበት ወቅት ለመረዳት እንደሚቻለው በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ላይ ትረኩት ተደርጓል፡፡ ሁለተኛ በግዙፍ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች ላይ የሚደረገው ኢንቨስትመንት አሁንም ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶበታል፡፡ ኢትዮጵያ ባለሁለት አኃዝ ጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት ዕድገት ማስመዝገቧን ለመቀጠል በመሠረተ ልማቶች ላይ ኢንቨስት ማድረግ አለባት፡፡ ይህ ደግሞ የወጪ ንግድን ያጠናክራል፡፡ ይኼ ለኢትዮጵያ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ የእስያ አገሮች በተለይ የቻይናና የደቡብ ኮሪያ ምሳሌም የሚያሳየው ዕድገታቸው የመጣው በማኑፋክቸሪንግና ተያይዞ በሚጠናከረው የወጪ ንግድ ነው፡፡ በሁለተኛው ዕቅድ በመሠረተ ልማትና በማፋክቸሪንግ ላይ የተደረገው ትኩረት የኢትዮጵያን ተወዳዳሪነትና የወጪ ንግድ አፈጻጸም እንደሚያሳድገው አምናለሁ፡፡ በሁለተኛው ዕቅድ የካፒታል ገበያ ቢኖር እመርጣለሁ፡፡ በተለይ የስቶክ ገበያ ለኢትዮጵያ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ስለካፒታል ገበያ በኋላ እንመለስበታለን፡፡ እርስዎ እንደሚሉት ዕቅዱ በማኑፋክቸሪንግ ላይ ማተኮር አለበት፡፡ ፖሊሲ አፍላቂዎችም በዚህ ይስማማሉ፡፡ ይሁንና ከረቂቁ ዕቅድና ከሕዝባዊ ውይይቶች ለማየት እንደሚቻለው ከመጀመርያው ዕቅድ የሚለየው ነገር የለም፡፡

አቶ ዘመዴነህ፡- አንድ መታወስ ያለበት ነገር የመጀመርያው ዕቅድ በጣም ጥሩ የሆነ የፖሊሲ ሰነድ እንደሆነና ኢትዮጵያ ምላሽ ልትሰጥባቸው የሚገቡ ቁልፍ ጉዳዮችን በሙሉ ያካተተ እንደነበር ነው፡፡ ሁለተኛው ዕቅድ ይኼን ማጠናከር ያለበት ይመስለኛል፡፡ የመጀመርያው ዕቅድ ብዙ ነገር ቢያሳካም አሁንም ያልተጠናቀቁ ነገሮች አሉ፡፡ ስለዚህ ሁለተኛው ዕቅድ በመሠረቱ በማኑፋክቸሪንግ ላይ ትኩረት አድርጎ ያለፈውን የሚቀጥል ነው፡፡ ልክ እንደ ዱላ ቅብብል ቡድን አንዱ የጀመረውን ለቀጣዩ የሚያስረክብ ነው፡፡ በመጀመርያው ያልተሳኩ በዚህኛው ይሳካሉ፡፡ የሁለተኛው ዕቅድ የማስፈጸም አቅም የተሻለ እንደሚሆንም አምናለሁ፡፡ ለውይይት ከቀረበው ውጪ ሙሉውን ሰነድ ገና አላየሁትም፡፡

ሪፖርተር፡- የመጀመርያው ዕቅድ መዋቅራዊ ሽግግር ያመጣል ተብሎ ነበር፡፡ ያለፉት አምስት ዓመታት የሽግግር ዓመታት ነበሩ ማለት ይቻላል?

አቶ ዘመዴነህ፡- በሚገባ! የመጀመርያውን ዕቅድ ባንቀርፅ ኖኖ ዕድገቱን አሥር በመቶና ከዚያ በላይ ሆኖ እንዲቀጥል ለማድረግ አይቻልም ነበር፡፡ ይኼን ከፍተኛ የኢኮኖሚ ዕድገት ማሳካት የተቻለው ለተወሰኑ ጉዳዮች ቅድሚያ የሚሰጥና በትክክለኛ መንገድ መዋቅር የፈጠረ ዕቅድ ሥራ ላይ በመዋሉ ነው፡፡ አንዱ የትኩረት አቅጣጫ በመሠረተ ልማት ላይ ኢንቨስት መደረጉ ነው፡፡ በመጀመርያው ዕቅድ የታላቁ የህዳሴ ግድብን መገንባት ጀምረናል፡፡ ይኼ ግዙፍ ፕሮጀክት ነው፡፡ ያለ ዕቅዱ ይኼን ማሳካት እንችል ነበር? ምናልባትም ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ዕቅዱ ማዕቀፍ በመፍጠር ከቀረው ኢኮኖሚ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንዲኖረው አድርጓል፡፡ የተገኘው ስኬት በጣም አበረታች ነው፡፡ ነገር ግን መንግሥት ራሱ በወጪ ንግድ በኩል የታቀደው እንዳልተፈጸመ የሚቀበለው ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በማምረትና ወደ ውጭ በመላክ የሚጠበቅበትን ያላሳካው በምን ምክንያት ነው?

አቶ ዘመዴነህ፡- መጀመርያ ላይ አቅም የማሳደጉ ነገር ከተጠቀበው በላይ ጊዜ ፈጅቷል፡፡ ለምሳሌ የኢንዱስትሪ ፓርኮች በሙሉ ኃይላቸው ወደ ሥራ የገቡት በዕቅዱ የመጨረሻ ሁለት ዓመታት ነው፡፡ ለኢንዱስትሪ ፓርኮች የመሠረተ ልማት መሠረት ከአምስት ዓመታት በፊት ቢኖረን ኖሮ የተሻለ ስኬት እናስመዘግብ ነበር፡፡ ሁለተኛ የኢትዮጵያ ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነት አሁንም ዝቅተኛ ነው፡፡ እነዚህ ነገሮች ጊዜ ይወስዳሉ፡፡ እውነቱን ለመናገር ለዚህ አምስት ዓመት በጣም አጭር ጊዜ ነው፡፡ ወጪ ንግድ ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ነው የምትወዳደረው፡፡ የወርልድ ኢኮኖሚክ ፎረም የተወዳዳሪነት ጠቋሚን ብናይ ኢትዮጵያ በጣም ዝቅተኛ ቦታ ላይ ነው ያለችው፡፡ ሦስተኛ ኢትዮጵያ ጥሬ ዕቃን ነው በአብዛኛው ወደ ውጭ የምትልከው፡፡ የእነዚህ ዕቃዎች ዋጋ የሚወሰነው በሌሎች አገሮች በመሆኑ ሒደቱ ከቁጥጥራችን ውጪ ነው፡፡

ከዓመታት በፊት የቡና ዋጋ በጣም አድጎ ስለነበር ዕድለኛ ነበርን፡፡ ባለፉት አምስት ዓመታት ደግሞ የቡና ዋጋ ላይ መሠረታዊ ማሽቆልቆል ታይቷል፡፡ ይኼ አሉታዊ ተፅዕኖ ነበረው፡፡ ስለዚህ ነው እሴት በመጨመር ወደ ውጭ ለመላክ ወደ ማኑፋክቸሪንግ መሄድ አለብን የምንለው፡፡ ለዚህ ቡናና ሰሊጥን በምሳሌነት መውሰድ እንችላለን፡፡ በሁለቱም ላይ እሴት ጨምረን ብንልክ ገበያችን ላይ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት ይቻላል፡፡ በዚህ ረገድ በቀጣዩ ዕቅድ መሠረታዊ ለውጥ የምናይ ይመስለኛል፡፡ በመጀመርያው ዕቅድ ስኬት የተመዘገበበትና ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ያስገኘው የአገልግሎት ዘርፍ ነው፡፡ ምን ያህል ሰዎች እንደሚያውቁ አላውቅም፡፡ ግን በወጪ ንግድ ዘርፍ ትልቁን ገቢ የሚያስገኘው ብቸኛ ዘርፍ ማለት ይቻላል አቪዬሽን ነው፡፡ ከአቪዬሽን የሚገኘው ገቢ ከቡና ከሚገኘው በአምስት እጥፍ ይበልጣል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2012/13 ኢትዮጵያ ከአቪዬሽን አገልግሎት 3.2 ቢሊዮን ዶላር አግኝታለች፡፡ በጊዜው ከቡና የተገኘው ገቢ 750 ሚሊዮን ዶላር ነበር፡፡ ይኼ በኢኮኖሚው ላይ ለውጥ እየተከናወነ እንደሆነ ያሳያል፡፡ ጥሬ ዕቃ በመላክ ለምትታወቀው አገር ይኼ ተቃርኖ ነው፡፡ ይኼ በመጀመርያው ዕቅድ ተከስቷል፡፡ በሁለተኛው ማደጉ አይቀርም፡፡

ሪፖርተር፡- ወደ አገልግሎት ዘርፍ የተደረገው ሽግግር በግልጽ የሚታይ ቢሆንም የሚያወሳው የለም፡፡ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ድርሻው 45 በመቶ ደርሷል፡፡ አስተያየት ሰጪዎች የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ወደ ኢንዱስትሪ ከማምራት ይልቅ ወደ አገልግሎት መሸጋገሩ በተሳሳተ አቅጣጫ ላይ ነው እንዲሉም አስችሏል፡፡ የእርስዎ ዕይታ ምንድነው?

አቶ ዘመዴነህ፡- በአምስት ዓመት ውስጥ ሁሉም ነገር ሙሉ በሙሉ እንዲሸጋገር መጠበቅ የለብንም፡፡ ኢኮኖሚው ወይ በግብርና ወይም በአገልግሎት ላይ ጥገኛ ነው፡፡ አሁን ቀስ በቀስ ከግብርና ወደ አግሮ ፕሮሰሲንግ፣ ከአገልግሎትና ከንግድ ወደ ማኑፋክቸሪንግ እየተሸጋገረ ነው፡፡ ይኼ ጊዜ ይወስዳል፡፡ ቻይናን ብንወስድ 30 ዓመታት ፈጅቶባቸዋል፡፡ እ.ኤ.አ. በ1979 ጀምረው ከ1990ዎቹ አጋማሽ እስከ 2000ዎቹ መጀመርያ ላይ ነው ማኑፋክቸሪንግ ላይ የተመሠረተ ኢኮኖሚ የፈጠሩት፡፡ ለዚህ ነው ሁለተኛው ዕቅድ የሽግግሩ አቅጣጫ ላይ በድጋሚ ያነጣጠረው፡፡ ነገር ግን የአገልግሎት ዘርፍ በየትኛውም ዓለም ቢሆን ወሳኝ የኢኮኖሚ አካል ነው፡፡ የሚገባውን ዋጋ ልንሰጠው ይገባል፡፡ እኔና ድርጅቴ የምንሰጠውን ሙያዊ አገልግሎት ጨምሮ ንግድ፣ ወጪ ንግድና ገቢ ንግድ እንዲሁም ሌሎች የአገልግሎት ዓይነቶች ኢኮኖሚን የማነቃቃት ሚና ይጫወታሉ፡፡ በአገልግሎት ዘርፍ ላይ አሉታዊ ዕይታ የለኝም፡፡ በጣም ባደጉት እንደ አሜሪካ ባሉ ኢኮኖሚዎች ውስጥ የአገልግሎት ዘርፍ 75 በመቶ ድርሻ አለው፡፡ ነገር ግን እያደጉ ባሉ እንደ ቻይናና ደቡብ ኮሪያ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው ድርሻ ከፍ ያለ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ወደ ማኑፋክቸሪንግ የሚደረገው ሽግግር በሁለተኛው ዕቅድ በሚገባ የሚታይ ይመስለኛል፡፡

ሪፖርተር፡- በመጀመርያው ዕቅድ የአገልግሎት ዘርፍ ከግብርናው ዘርፍ ተጠቃሚ ነበር፡፡ በሁለተኛው ዕቅድ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ከአገልግሎት ዘርፍ ጋር የሚወዳደርና የሰው ኃይልና ሌሎች ሀብቶችን የሚወስድ ይመስልዎታል?

አቶ ዘመዴነህ፡- የማኑፋክቸሪንግና የአገልግሎት ዘርፎች ተመጋጋቢ ናቸው፡፡ ምናልባት የተሻለ ክህሎት ያለውን ለመቅጠር ሊወዳደሩ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ በፋይናንስና በማርኬቲንግ መስኮች በሚሠሩ ሰዎች ላይ ይፎካከራሉ፡፡ ነገር ግን በአብዛኛው ይደጋገፋሉ፡፡ የአገልግሎት ዘርፍ ባንክና ቴሌኮሙዩኒኬሽንን ጨምሮ በጣም ሰፊ ነው፡፡ ያለ አገልግሎት ዘርፍ ማኑፋክቸሪንግ ሊኖር አይችልም፡፡ የዚያኑ ያህል ያለ ጠንካራ ማኑፋክቸሪንግ እነዚህ የአገልግሎት ዘርፎች ሊያድጉ አይችሉም፡፡ በተለይ የጨርቃ ጨርቅና የአልባሳት ኢንዱስትሪ ከግብርና ዘርፍ እንደ ጥጥ ያለ ጥሬ ዕቃ ስለሚፈልግ ተደጋጋፊ መሆኑ አይቀርም፡፡

ሪፖርተር፡- በሁለተኛው ዕቅድ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ‹‹ፕሮዳክሽን ፖሲቢሊቲ ፍሮንቲየርን›› ማረጋገጥ እንደ ራዕይ ተቀምጧል፡፡ ይኼ ምንን ያሳያል?

አቶ ዘመዴነህ፡- የእዚህ ትርጉም ምንም ሆነ ምን የማኑፋክቸሪንግን ዘርፍን ተወዳዳሪ ለማድረግ መሥራታችን አይቀርም፡፡ ዘርፉ በአገር ውስጥም ጭምር ተወዳዳሪ መሆን አለበት፡፡ አለበለዚያ ከውጭ አስገብተው የሚሸጡ ይኖራሉ፡፡ ይህን ለማድረግ ዘርፉ ፈጣሪ፣ ለውጥ ተቀባይ፣ በዋጋና በጥራት ተወዳዳሪ መሆን አለበት፡፡ ምንም እንኳን መሠረታዊ ቁሶችን በማምረት ላይ ያተኮረ ቢሆንም ወሳኝ መሆን አለበት፡፡ የኢትዮጵያ ማኑፋክቸረርስ ይኼን የሚያደርጉ ይመስለኛል፡፡ ጥሩ አዝማሚያዎችን እያየን ነው፡፡ የተለያዩ ድንበር ዘለል ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ እየመጡ ነው፡፡ የኢንዱስትሪ ፓርኮቻችን አሁን ሞልተዋል፡፡ የእኛ ደንበኛ የሆኑ ድንበር ዘለል ኩባንያዎች የቦሌ ለሚ ምዕራፍ ሁለት ኢንዱስትሪ ፓርክ ሲጀመር ለመግባት እየተጠባበቁ እንደሚገኙ አውቃለሁ፡፡ የመጀመርያው ምዕራፍ ሞልቷል፡፡ እነዚህ ኩባንያዎች የሥራ ዕውቀታቸውንና ከዓለም አቀፍ የገበያ ሰንሰለት ጋር ያላቸውን ግንኙነት ይዘው ነው የሚመጡት፡፡ ይኼ ኢትዮጵያን ተወዳዳሪ ለማድረግ ወሳኝ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በጣም ሰፊ የሆነ ክህሎት ያለው፣ ወጣት የሆነ፣ በቀላሉ ወደ ሥራ የሚሰማራና በተመጣጣኝ ዋጋ የምትቀጥረውና ለመሥራት ጉጉት ያለው የሰው ኃይል አለን፡፡ የገበያ ተደራሽነትም አለን፡፡ በድርጅታችን ኧርነስት ኤንድ ያንግ የተጠና አንድ ጥናት ከአዲስ አበባ የዓለምን ግማሽ ሕዝብ ማለትም 3.5 ቢሊዮን ሕዝብ ለመድረስ የስምንት ሰዓታት የአየር ጉዞ ብቻ ነው የሚያስፈልገው፡፡ ስለዚህ ስትራቴጂካዊ የሆነ አቀማመጥ አለን፡፡ እነዚህ ሁሉ ኢትዮጵያን የተሻለ ተጠቃሚ ያደርጋሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ትኩረት ያደረገችበትን የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ እንዴት ማልማት ይቻላል የሚለው አከራካሪ ነው፡፡ በውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ወይስ በአገር ውስጥ ማኑፋክቸረርስ መተማመን ያለበት?

አቶ ዘመዴነህ፡- እኔ እንደማስበውና እየሆነም እንዳለው የውጭ ኢንቨስተሮች ያስፈልጉናል፡፡ ምክንያቱም አስቀድሜ እንደገለጽኩት ዕውቀት፣ የሥራ ክህሎት፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርና እንዲሁም የገበያ ተደራሽነት ይዘው ይመጣሉ፡፡ ለምሳሌ ያህል የቻይናውን የጫማ ፋብሪካ ሑጂያንን ብንወስድ ከቻይና ወደ አሜሪካ ከ20 ዓመታት በላይ ምርቶቹን በመላክ የካበተ ልምድ አለው፡፡ ስለዚህ የደንበኛ መሠረቱ አለው፡፡ ከኢትዮጵያ የሚልካቸው ምርቶቹ በአሜሪካ ገበያ ደንበኛ አላቸው፡፡ ኢትዮጵያዊው ኩባንያ ይህን ገበያ ለመድረስ መቸገሩ አይቀርም ነበር፡፡ ነገር ግን በዓለም አቀፍ ማኑፋክቸረርስና በኢትዮጵያ የግል ዘርፍ መካከል ግንኙነት እንዲፈጠር ማድረግ አለብን፡፡ ሸሚዝ የሚያመርተውን የውጭ ድርጅት ቁልፍ ከሚያመርተው አገር በቀል ኩባንያ ጋር ማጣመር ያስፈልጋል፡፡ የኢኩቲ ሼር በመግዛትም ሊጣመሩ ይችላሉ፡፡ የውጭ ዜጎችና የአገር በቀል ድርጅቶች የተለያዩ መጠን ያላቸው ሼሮችን ሊገዙ ይችላሉ፡፡ ይኼ በኢትዮጵያ እየተከናወነ ነው ወይ? ከእኛ ጋር አብረው የሚሠሩ ሰዎች ይህን ለማድረግ ስምምነት መፈራረማቸውን እናውቃለን፡፡ ሕጉ ይህንን እንደ መሥፈርት አያስቀምጥም፡፡ ይኼ ጥሩ ሕግ ነው፡፡ የውጭ ድርጅቶችን ከአገር በቀል ኩባንያዎች ጋር እንዲሠሩ በሕግ ማስገደድ ጥሩ አይደለም፡፡ ነገር ግን ይበልጥ የውጭ ድርጅቶች ከአገር በቀል ድርጅቶች ጋር በፍላጎታቸው ተጣምረው እየሠሩ ነው፡፡ ቻይናም የተለወጠችው በዚህ መንገድ ነው፡፡ አሁን ያሉት የቻይና ግዙፍ ኩባንያዎች በ1980ዎቹና በ1990ዎቹ ከድንበር ዘለል ኩባንያዎች ጋር ተጣምረው በመሥራት ነው የጀመሩት፡፡ ስለዚህ እነዚህ ነገሮች እየተስፋፉ የሚመጡ ይመስለኛል፡፡

ሪፖርተር፡- በመጭዎቹ አምስት ዓመታት በርካታ የውጭ ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጡ ይጠብቃሉ?

አቶ ዘመዴነህ፡- ኧርነስት ኤንድ ያንግ በቅርቡ ዓመታዊውን ሪፖርታችንን የአፍሪካ መስህብነት ሰርቬይ (Africa Attractiveness Survey) አውጥቷል፡፡ በጣም ግሩም የሆነ ሪፖርት ነው፡፡ በዚህ ዓመት ምርጥ አፈጻጸም በውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት አንፃር ያሳየችው ኢትዮጵያ ነች፡፡ ይህም በተለያዩ ምክንያቶች ነው፡፡ አንደኛ በአፍሪካ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመትን በመሳብ ቅድሚያ ካላቸው አሥር አገሮች አንዷ ኢትዮጵያ ነች፡፡ እ.ኤ.አ. በ2013 ኢትዮጵያ 14ኛ ነበረች፡፡ በዚህ ዓመት ስምንተኛ ሆናለች፡፡ ሁለተኛውም በጣም ቁልፍ የሆነው ግኝት የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት እ.ኤ.አ. በ2014 በአፍሪካ ከሚፈጥራቸው አምስት የሥራ ዕድሎች አንዱ (18.5 በመቶ) በኢትዮጵያ ውስጥ ይገኛል፡፡ ይኼ የኢትዮጵያ ፖሊሲ ትኩረት ማኑፋክቸሪንግ ብቻ ሳይሆን የሥራ ዕድል መፍጠር መሆኑንም ያሳያል፡፡ በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ስለመግባቱ ዜናዎች ቢያሳዩም፣ በእነዚህ አገሮች ኩባንያዎቹ በርካታ የሥራ ዕድሎችን አይፈጥሩም፡፡

ለምሳሌ በአንዳንድ አገሮች በአምስት ቢሊዮን ዶላር ነዳጅ ለማውጣት ስምምነት ሊደረግ ይችላል፡፡ ገንዘቡ በአብዛኛው የነዳጅ ማጣሪያና ማስተላለፊያ ለመገንባት ይውላል፡፡ ምናልባትም ከ100 ሰዎች በላይ ላይቀጥር ይችላል፡፡ ሦስተኛ በዚህ ዓመት የኢትዮጵያ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት 1.5 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2008 የነበረው መጠን 100 ሚሊዮን ዶላር ነበር፡፡ ለሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት የሚኖረው አማካይ መጠን 1.5 ቢሊዮን ዶላር ይሆናል ተብሎ ይገመታል፡፡ ይህም በስድስት ዓመት ውስጥ 15 እጥፍ ዕድገት መመዝገቡን ያሳያል፡፡ ስለዚህ ቁጥሮቹ በጣም አበረታች ናቸው፡፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ወራት ይፋ የሚሆኑ በርካታ አዳዲስ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ስምምነቶች በሥራ ላይ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ይህን ቀጣይ ለማድረግ መሥራት አለባት፡፡

ሪፖርተር፡- ባለፉት አሥር ዓመታት ወደ ኢትዮጵያ የመጡት የውጭ ድርጀቶች በቅርቡ ኢንዱስትሪያላይዝድ ከሆኑት እንደ ቻይና፣ ህንድና ቱርክ ነው፡፡ አንዳንዶቹ ከቴክኖሎጂ ሽግግር አኳያ እነዚህ አገሮች ራሳቸው ከሌላው ኮፒ ያደረጉ በመሆኑ ኢትዮጵያ ከእነሱ ኮፒ ማድረጓ ተጎጂ ያደርጋታል ይላሉ፡፡ በዚህ ላይ እርስዎ ምን ይላሉ?

አቶ ዘመዴነህ፡- መጀመርያ አካባቢ ከሰባት ዓመት በፊት ብዙዎቹ ድርጅቶች ከአዳዲስ ኢኮኖሚዎች ነው የመጡት፡፡ ባለፉት ሦስትና አራት ዓመታት ግን ከአዳዲሶቹና ከምዕራባውያን ኢኮኖሚዎች የሚመጡት ኢንቨስተሮች የተመጣጠኑ ናቸው፡፡ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነን ባለፈው ክረምት የአሜሪካው ግዙፍ የኢኩቲ ፈንድ ኩባንያ ኬኬአር ዝዋይ በሚገኘው አፍሮ ፍሎራ በተሰኘ የአበባ ኩባንያ ላይ 200 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስት አድርጓል፡፡ ኬኬአርን የገዛው ኩባንያ በአሜሪካ ፕራይቬት ኢኩቲን የፈጠረው ኩባንያ ነው፡፡ ይኼ የአሜሪካ ገንዘብ ነው፡፡ እንደ ኔጄራል ኤሌክትሪክ ያሉ ኩባንያዎችም በኢትዮጵያ ቢሮ በመክፈት የማኑፋክቸሪንግ አገልግሎት ላይ ለመሥራት እየተዘጋጁ ነው፡፡ በሌላ በኩል ከአውሮፓ የመጡት እነ ዲያጆ፣ ሐይኒከን፣ ሳብሚለርና ዩኒሊቨር አሉ፡፡ ስለዚህ ቀድመው የገቡት እንደተባለው በቅርቡ ካደጉ አገሮች የመጡ ቢሆንም፣ አሁን ከበለፀገው አሜሪካና አውሮፓም የሚገኙ ኩባንያዎች እየመጡ ነው፡፡ በቅርቡ ይፋ የሚደረጉትም ኢንቨስተሮች ምዕራባውያን በተለይ አሜሪካውያን ናቸው፡፡ ነገር ግን በቅርቡ ካደጉ አገሮች የሚመጡ ኢንቨስተሮችም ሊበረታቱ ይገባል፡፡ በማደግ ላይ ላለ ኢኮኖሚ ምን መደረግ እንዳለበት የበለጠ ተስማሚ ናቸው፡፡ እርግጥ እንደ አሜሪካው ኔጄራል ኤሌክትሪክ ያሉ ኩባንያዎችም ለታዳጊ ኢኮኖሚ ተስማሚ እየሆኑ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከላይ ስለተውነው ስቶክ ማርኬት እናንሳ፡፡ በቅርቡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሁለተኛ ደረጃ የቦንድ ገበያ ለመፍጠር እየተዘጋጀ መሆኑ ተገልጿል፡፡ ከስቶክ ማርኬት ይልቅ ለሁለተኛ ደረጃ ቦንድ ማርኬት ቅድሚያ መስጠቱ ተገቢ ነው ይላሉ?

አቶ ዘመዴነህ፡- ሁለቱም ጎን ለጎን መሄድ የሚችሉ ናቸው፡፡ የቦንድ ገበያ መጀመሩ በጣም ጥሩ ነገር ነው፡፡ የጊዜ ጉዳይ ነው፡፡ በተለይ አሁን የኢትዮጵያ ቦንድ ለዓለም ገበያ የቀረበ መሆኑ (ዩሮ ቦንድ) ለአገር ውስጥ ገበያ መቅረቡ የሚጠበቅ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ የተደራጀ ኢኩቲ ማርኬት መጀመር አለባት፡፡ ኢትዮጵያ በአፍሪካ አራተኛው ትልቅ ኢኮኖሚ ቢኖራትም የስቶክ ማርኬት የላትም፡፡ ከእኛ ያነሳ ኢኮኖሚ ይዘው የኢኩቲ ገበያ ያላቸው አገሮች አሉ፡፡ በኢትዮጵያ የኢኩቲ ገበያ የሌለበት ምክንያት አሳማኝ አይደለም፡፡ ለሁሉም ነገር መፍትሔ ይሆናል ወይ? አይሆንም፡፡ ነገር ግን የገበያ አማራጮች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ ኢኮኖሚያችን እየዘመነ ነው፡፡ በአፍሪካ ደረጃ ትልቅ የሚባል ነው፡፡ ከመግዛት አቅም መመዘኛ (Purchasing Power Parity) አንፃር የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የ139 ቢሊዮን ዶላር ኢኮኖሚ ሲሆን፣ በጥሬ አኃዝ የ55 ቢሊዮን ዶላር ኢኮኖሚ ነው፡፡ ኢንቨስተሮች አማራጭ የካፒታል ምንጭ ያስፈልጋቸዋል፡፡ እኔ የማገኛቸው ወጣት ኢትዮጵያውያን ኢንተርፕረነር መሆን ይፈልጋሉ፡፡ ይኼ ባፉት 15 ዓመታት ያልነበረ የሚገርም የአመለካከት ለውጥ ነው፡፡ ነገር ግን ሥራቸውን ለመጀመር ካፒታል ያስፈልጋቸዋል፡፡ ሁሌም ዕቁብ በመግባትና ከጓደኞችህ በመጠየቅ ካፒታል ማግኘት አይኖርብህም፡፡ በተወሰነ መልኩ የኢኩቲ ማርኬት የመሰለ ነገር ኢትዮጵያ ውስጥ አለ፡፡ የባንክ ሼር ያላቸው ሰዎች ይነግዱበታል፡፡ ነገር ግን ይኼ የተደራጀና መደበኛ አሠራር አይደለም፡፡

ስለዚህ ግልጽነት ባለው ሁኔታ የሼሮችን ዋጋ ማወቅ አይቻልም፡፡ አሁን ብዙ ሰዎች የሼር ካምፓኒ እየፈጠሩ ነው፡፡ ነገር ግን ይህን የሚገዛ ገበያ የለም፡፡ ስለዚህ መንግሥት የስቶክ ኤክስቼንጅ በማደራጀት፣ ደንብ በማውጣት፣ የፋይናንስ ሪፖርት ግዴታ በመጣልና ኮርፖሬት ገቨርናንስ በመቅረጽ ግልጽ የሆነ አሠራር ቢጀምር ጥሩ ነው፡፡ ሰዎች ምን እንደሚነግዱና በምን ሁኔታ እንደሚነግዱ ማወቅ አለባቸው፡፡ እንደኛ ያለ ኢኮኖሚ ካለው አገር ጋር ሲተያይ ስቶክ ማርኬት የሌላት ኢትዮጵያ ብቻ ናት፡፡ በሁለተኛው ዕቅድ ይህን ለማካተት መንግሥት ቢያስብበት ጥሩ ነው፡፡ ከ1993 ዓ.ም. ጀምሮ በዚህ ጉዳይ ላይ ስለምሠራ ነው ይህን አቋም የሚያንፀባርቁ እነዚህ ነገሮች አለመጀመራቸው ችግር የሚሆነው፡፡ በኢትዮጵያ ፕራይቬት ኢኩቲም ሆነ ቬንቸር ካፒታል ፈርም የሌለን በመሆኑ ነው፡፡ እነዚህ ነገሮች የቢዝነስ ሐሳብ ላላቸው ሰዎች የፋይናንስ ምንጭ ሆነው ሊያገለግሉ ይችላሉ፡፡ ለፌስቡክና ለአፕል ጨምሮ ፋይናንስ የተገኘው ከእነዚህ አሠራሮች ነበር፡፡ ኢትዮጵያ እንደ ሞዴል የምትወስዳቸው አገሮች ካፒታል ማርኬት አላቸው፡፡ በነገራችን ላይ በ1960ዎቹ በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ኢትዮጵያ የስቶክ ማርኬት ነበራት፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የሥራ አጦች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመርና መከማቸት ለትግራይ ክልል ሰላምና ደኅንነት ትልቅ ሥጋት ይፈጥራል›› አትክልቲ ኪሮስ (ዶ/ር)፣ የፋይናንስ ባለሙያ

በሰሜን ኢትዮጵያ የተደረገው ጦርነት ከፍተኛ ውድመት አስከትሏል፡፡ ለማኅበራዊ ቀውስ ምክንያትም ሆኗል፡፡ በጦርነቱ ሕይወታቸውን ያጡ፣ ለአካል ጉዳት የተዳረጉና ሀብት ንብረታቸው የወደመባቸው ዜጎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ ...

‹‹በሌሎች ክልሎች ያለው የሰብዓዊ ዕርዳታ ፍላጎት ከትግራይ አንፃር አነስተኛ ነው ብዬ ለመግለጽ አልችልም›› ራሚዝ አላክባሮቭ (ዶ/ር)፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይና የሰብዓዊ ዕርዳታ...

በኢትዮጵያ የሰብዓዊ ዕርዳታ የሚያቀርቡ ዓለም አቀፍ የረድዔት ድርጅቶችና ሠራተኞች በአገሪቱ በሚከሰቱ የበሽታ ወረርሽኞች፣ ድርቅ፣ ጎርፍና ጦርነት ምክንያት ባለፉት ጥቂት ዓመታት በእጅጉ ተፈትነው ነበር። በኮቪድ-19...

‹‹የውጭ ዜጎች ንብረት እንዲያፈሩ መፍቀድ ከፍተኛ ጥቅም አለው›› ቆስጠንጢኖስ በርሃ (ዶ/ር)፣ የኢኮኖሚ ባለሙያ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ተከታታይ ውይይት እያደረጉ ነው፡፡ ከእነዚህ የውይይት መድረኮች መካከል ከከፍተኛ የግብር ከፋዮች ወይም ታማኝ ግብር ከፋዮች...