Thursday, October 6, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ማኅበራዊየሽልማት ቴአትር በብሔራዊ ቴአትር

  የሽልማት ቴአትር በብሔራዊ ቴአትር

  ቀን:

  –  ሁለት ሚኒስትሮችም ተሸልመዋል

  የኤሚሪባስክ ኢንፎ ኮሙኒኬሽን ኤንድ ኤቨንትስ ከእህት ኩባንያው ኤፍ ስቶፕ ፕሮዳክሽን ጋር በመተባበር ‹‹ቅድሚያ ለኢትዮጵያውያን›› በሚል ርዕስ ግለሰቦችንና ተቋማትን ሸልሟል፡፡ ሸላሚ ድርጅቱ ‹‹ድንቅ ኢትዮጵያዊ ለውጥ አምጪ›› ያላቸውን ስድስት ሴቶች፣ 25 ወንዶች፣ 11 የግልና የመንግሥት ተቋማትን እንዲሁም ዘጠኝ የሚዲያ ተቋማትን ጨምሮ ሦስት ልዩ ተሸላሚዎችን አካትቶ፣ በአጠቃላይ 54 ሽልማቶችን ሰኔ 30 ቀን 2007 ዓ.ም. ለተሸላሚዎች አበርክቷል፡፡

  የሽልማቱ ሥነ ሥርዓቱ የተካሄደው በዋናው የብሔራዊ ቴአትር አዳራሽ ሳይሆን፣ አዳራሹ ከመገባቱ በፊት ባለው በስተግራ በረንዳ ላይ ነው፡፡ በስፍራው በተለጠፈው ፖስተር ላይ ‹‹ሰኔ 30 የተማሪ አበሳ x ሰኔ 30 የጀግኖች ውደሳ›› የሚል መሪ ቃል ተጽፏል፡፡ በሽልማት ሥነ ሥርዓቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ሲሆኑ፣ አብረዋቸውም የቀድሞ አማካሪያቸው አቶ አሰፋ ከሲቶም ነበሩ፡፡

  የሥነ ሥርዓቱ የፕሮግራም መሪ የነበረው አርቲስት ችሮታው ከልካይ የሽልማት ድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ታምራት ፈቃደ ንግግር እንዲያደርጉ ወደ መድረክ ጋብዞአቸዋል፡፡ አቶ ታምራትም የዚሁ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ እሳቸው ሳይሆኑ ሕዝቡ መሆኑን ገልጸው፣ የሽልማቱ ሥነ ሥርዓት ዘግይቶ በመጀመሩ ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡ አቶ ታምራት አክለውም በዝግጅቱ ‹‹የበግ ነጋዴ›› (በወቅቱ ቡርትካናማ ሸሚዝና ቡናማ ሱሪ አድርገዋል) መስለው በመቅረባቸው ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡ አቶ ታምራትም በዚሁ ሽልማት ሥነ ሥርዓት ላይ የተመረጡት ሰዎች በምን መሥፈርት ለሽልማት እንደበቁ ማብራሪያ ሳይሰጡ፣ በሊቢያ ለተሰዉ ኢትዮጵያውያን የህሊና ፀሎት ተደርጐ ሥነ ሥርዓቱ ተጀምሯል፡፡

  ከህሊና ፀሎቱ ቀጥሎ የፕሮግራሙ መሪ አርቲስት ችሮታው የተሸላሚዎቹን ግለሰብ ስም በመጥራት ከታዳሚያን ጭብጨባ እንዲቀበሉ ተደርጓል፡፡ በወቅቱ ስማቸው ከሚጠሩት ግለሰቦች ውስጥ በርካቶቹ በሥፍራው አልተገኙም ነበር፡፡ ተሸላሚ ናቸው የተባሉት ግለሰቦችም በምን መሥፈርት እንደተሸለሙ ሳይገለጽም፣ እንዲሁ በደፈናው ለአገራቸው ጠቃሚ ሥራዎችን መሥራታቸው ተገልጿል፡፡

  አቶ ታምራት በድርጅታቸው የተሸለሙት ተቋማትና ግለሰቦች በምን መሥፈርት እንደተመረጡ ሪፖርተር ሲጠይቃቸው የሚከተለውን ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ‹‹የሽልማቱ መሥፈርቶች ሁለት ናቸው፡፡ አንደኛው ተሸላሚዎቹ ለማኅበረሰቡ ችግር ፈቺ ሆነው የራሳቸውን ዕቅድ ነድፈውና ጊዜያቸውን ሰውተው ኃላፊነት በመውሰድ ውጤት ማምጣታቸው ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ መረጃ የመስጠትና የመቀበል አቅማቸው ምን ድረስ ነው? የሚል ነው፡፡ ከዚህም ባለፈ እርስ በእርስ የመፈላለጋቸው ስሜት ምን ይመስላል? የሚለውም ተካቷል፤›› ብለዋል፡፡

  አቶ ታምራት 54 ተሸላሚዎቹ የተመረጡት በእነዚህ ሁለት መሥፈርቶች መሆናቸውን ገልጸው ተሸላሚዎቹን ግለሰቦች፣ የመንግሥት ተቋማት፣ የግል ተቋማትና የሚዲያ ተቋማትን ቢያካትቱም ሁለቱ መሥፈርቶች ለሁሉም ተሸላሚዎች እንደ መሥፈርት መጠቀማቸውን ተናግረዋል፡፡

  አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ግን ተሸላሚዎቹ የተሸለሙበት መሥፈርት ግልጽ ካለመሆኑ ባሻገር እጅግ ሰፊ ጉዳዮችን የሚነኩ መሥፈርቶች ናቸው ብለዋል፡፡ በተለይም መረጃ የመስጠትና የመቀበል አቅም በምን እንደሚለካ ግራ ተጋብተው ይጠይቃሉ፡፡ ይህም ለአገር ጠቃሚ ሥራ የሠሩ ግለሰቦችና ተቋማት እንዴት ሊሸለሙበት እንደቻለ አስገርሟቸዋል፡፡ ከዚያም ባለፈ ተቋማትና ግለሰቦች በአንድ ዓይነት መሥፈርት መገምገማቸውም ሌላ ጥያቄ ጭሮባቸዋል፡፡

  ለሽልማቱ የበቁት 54 ተሸላሚዎች ከ128 ተሸላሚዎች ተመልምለው መሆኑን የሚገልጹት አቶ ታምራት፣ የዳኝነቱ ውሳኔ የተሰጠው በራሳቸው ድርጅት ሠራተኞች መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በምልመላውም ወቅት የምርመራ ጋዜጠኝነት (Investigative Journalism) በመጠቀም ግለሰቦቹና ተቋማቱ ቢያውቁትም ባያውቁትም የሠሯቸውን ሥራዎች ሲመረምሩ እንደቆዩ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ በዚህም መሠረት ከ128 ተሸላሚዎች መካከል ሚዛን የደፉባቸውን 54ቱን ለመሸለም በመጨረሻ መወሰናቸውን ገልጸዋል፡፡ የሽልማቱንም ዓላማ ሲገልጹ፣ ‹‹ተሸላሚዎቹ የሚሠሯቸው ሥራዎች ቢታወቁም፣ እነሱ ግን ስለማይታወቁ ለማወደስ ነው፡፡››

  ከተሸላሚዎቹ መካከል በርካታ ታዋቂ ግለሰቦች ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል አትሌት ኃይሌ ገብረ ሥላሴ፣ አትሌት መሠረት ደፋር፣ አትሌት ደራርቱ ቱሉ፣ አርቲስት ሙላቱ አስታጥቄ፣ አርቲስት ተስፋዬ አበበ (ፋዘር)፣ አርቲስት ኤሊያስ መልካ፣ አርቲስት ስለሺ ደምሴ፣ አርቲስት አሊ ቢራ፣ አቶ ውብሸት ወርቃለማሁ፣ የቅዱስ ጊዮርጊስ የስፖርት ማኅበር ቦርድ ሰብሳቢ አቶ አብነት ገብረ መስቀል ይጠቀሳሉ፡፡ እንዲሁም ልዩ ተሸላሚዎቹ ደግሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም፣ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የኢኮኖሚና ፋይናንስ ክላስተር አስተባባሪና የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶ/ር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል፣ የሚድሮክ ኢትዮጵያ ባለቤትና ሊቀመንበር ሼክ ሙሐመድ አሊ አል አሙዲ ይገኙበታል፡፡ በሽልማት ሥነ ሥርዓቱ ላይ አብዛኞቹ ተሸላሚዎች ያልተገኙ ሲሆን፣ ከላይ ከተዘረዘሩት ተሸላሚዎች መካከል እንኳን የተገኙት ሦስቱ (አርቲስት ሙላቱ፣ አርቲስት ተስፋዬና አቶ ውብሸት) ብቻ ናቸው፡፡

  በሥፍራው ተገኝተው ሽልማቱን የተቀበሉት አቶ ውብሸት፣ ‹‹ሽልማቱ ቆንጆ ነበር፡፡ ያለፈው ሽልማት ክትፎና ዓይብ ነበረው፡፡ የአሁኑ ግን ውኃ ብቻ ነው፡፡ የተሸለምነው ሜዳሊያ ልዩ ነው (አርቲስቱ ሜዳሊያ ያሉት በቢጫ ጨርቅ የተሠራ ኮርዶን ነው)፡፡ ስማችን (በኮርዶኑ ላይ) ተጽፏል፡፡ አርቲፊሻል ሳይሆን በእጅ የተጻፈ ነው፤›› ብለዋል፡፡ አቶ ውብሸት በሌሎች ሥራዎች ላይ የተወጠሩ ቢሆኑም፣ ሌሎች ታዋቂ ግለሰቦች በሥነ ሥርዓቱ ላይ እንደሚገኙ ሸላሚው ስለገለጸላቸው መገኘታቸውን ተናግረዋል፡፡ ለሽልማቱ ዕጩ መሆናቸውን ከስምንት ቀናት በፊት መስማታቸውን የገለጹት አቶ ውብሸት፣ ሸላሚው ከየቦታው ለአገራቸው ሠሩ የተባሉ ግለሰቦችን መርጦ በመሸለሙ ክብር ይገባዋል ብለዋል፡፡

  ሽልማቱን ከተቋደሱ ተቋማት መካከልም አንበሳ የከተማ አውቶቡስ፣ የመከላከያ ሚኒስቴር፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን፣ የወደቁትን አንሱ የነዳያን ማኅበር፣ እናት ባንክ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ብሔራዊ ቴአትር፣ የፖስታ አገልግሎት ድርጅት፣ ብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት ኤጀንሲና ቢጂአይ ኢትዮጵያ ይገኙበታል፡፡ በተመሳሳይ ከእነዚሁ ተቋማት መካከል በሽልማቱ ተገኝተው የተቀበሉት የአንበሳ የከተማ አውቶብስ ሥራ አስኪያጅ ብቻ ነበሩ፡፡ ከሚዲያም ሸገር 102.1 ኤፍኤም ሬዲዮ፣ አዲስ ዘመንና ኢትዮጵያን ሔራልድ ጋዜጣ፣ ኢቢኤስ ቴሌቪዥን፣ አዲስ አድማስ ጋዜጣ፣ ሜዲካል መጽሔት፣ ኦሮሚያ ቲቪ፣ ድሬ ቲዩብ፣ ፎርቹን ጋዜጣና ሪፖርተር ጋዜጣ ናቸው፡፡ ከእነዚህም ተሸላሚዎች መካከል የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ አቶ ነቢይ መኮንን ብቻ ሽልማቱን ወስደዋል፡፡

  በወቅቱ የተገኙት ተሸላሚዎች ሽልማቶቻቸውን ከክብር እንግዳው አቶ ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ እጅ ተቀብለዋል፡፡ በሽልማቱ ሥነ ሥርዓት ወቅት ተሸላሚዎቹ የተሸለሙበት መሥፈርት በግልጽ ባይነገርም፣ ሁሉም ተሸላሚዎች ሽልማታቸውን በደስታ ተቀብለዋል፡፡ ሥነ ሥርዓቱ ካለቀ በኋላም ተሸላሚዎች ከቤተሰቦቻቸው ጋር ፎቶግራፍ በመነሳት ደስታቸውን ሲገልጹ ታይተዋል፡፡

  ምንም እንኳን የሪፖርተር ጋዜጣም ከተሸላሚዎቹ አንዱ ቢሆንም፣ በምን ዓይነት መሥፈርት ለሽልማት መብቃቱ ባለመታወቁ በሥፍራው የተገኙት ተወካይ ሽልማቱን አልተቀበሉም፡፡     

  የሽልማት ሥነ ሥርዓቱን ስፖንሰር ያደረገ ድርጅት አለመኖሩን የገለጹት አቶ ታምራት፣ ለሥነ ሥርዓቱ የወጣውን ወጪ ግን ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡

   

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img