Monday, December 5, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ማኅበራዊየኢትዮጵያ የበካይ ጋዞች ልቀት ወደ 147 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን እንዲቀንስ ይደረጋል ተባለ

  የኢትዮጵያ የበካይ ጋዞች ልቀት ወደ 147 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን እንዲቀንስ ይደረጋል ተባለ

  ቀን:

  የአካባቢና የደን ሚኒስቴር ይፋ ያደረገው ጠቋሚ ዕቅድ የሙቀት አማቂ ወይም በካይ ጋዞች (ግሪን ሐውስ ጋዝ) ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቁበትን መጠን በመቀነስ፣ በመጪዎቹ አምስት ዓመታት ውስጥ 147 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ላይ እንዲገደቡ ለማድረግ ማቀዱን አስታወቀ፡፡

  ሚኒስቴሩ ባለፈው ሐሙስ ሰኔ 25 ቀን 2007 ዓ.ም. ለውይይት ባቀረበው የአምስት ዓመት ሰነድ ላይ በአገሪቱ ለበካይ ጋዞች ወይም ለሙቀት አማቂ ጋዞች መለቀቅ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ዘርፎች ላይ የሚሠሩ ሥራዎች፣ የልቀት መጠኑን ለመቀነስ እንደሚያስችሉ አመላክቷል፡፡ የአካባቢና ደን ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኑርመደድ ጀማል ባቀረቡት የአምስት ዓመት መነሻ ዕቅድ መሠረት፣ በአገሪቱ ለሙቀት አማቂ ጋዞች ልቀት አስተዋጽኦ ከሚያደርጉት መካከል የደን መጨፍጨፍ፣ የአፈር መከላትና መሸርሸር፣ የጋማ ከብቶች ሲያመሰኩና እበት ሲጥሉ የሚመነጩ ጋዞች፣ የኢነርጂ ዘርፍና የመጓጓዣ ዘርፍ የሚያመነጩት፣ የኢንዱስትሪና የከተሞች መስፋፋት ከሚጠቀሱት መካከል ናቸው፡፡

  በመሆኑም እንስሳት ያመነጩታል ተብሎ የሚጠበቀውን የ88 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ልቀት ወደ 44 ሚሊዮን መቀነስ ከታቀዱት መካከል ይገኝበታል፡፡ በአፈር መከላትና መሸርሸር ምክንያት 40 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ጋዝ ይለቀቃል ተብሎ የሚጠበቅ በመሆኑ፣ ሚኒስቴሩ ይህንን መጠን ወደ 12 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ዝቅ የማድረግ ዕቅድ አስቀምጧል፡፡

  መንግሥት ከአራት ዓመት በፊት በደቡብ አፍሪካ ይፋ ያደረገው የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት የተነሳው ስትራቴጂ አካል የሆነው የመጪዎቹ አምስት ዓመታት ዕቅድ፣ በጠቅላላው በ147 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የበካይ ጋዞችን ልቀት ለመቀነስ ተነስቷል፡፡ የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂው እንዳሰፈረው ከሆነ፣ እ.ኤ.አ. እስከ 2030 ባለው ጊዜ ውስጥ ሊመነጭ ይችላል ተብሎ የሚታሰበው ሙቀት አማቂ ጋዝ መጠን 400 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ነው፡፡ ሆኖም ካለፉት አምስት ዓመታት ጀምሮ በየዓመቱ እየመነጨ የሚገኘው በካይ ጋዝ መጠን 150 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን እንደሚገመት አስፍሯል፡፡

  አቶ ኑርመደድ እንዳስታወቁት፣ በኢትዮጵያ የሚመነጨው የሙቀት አማቂ ጋዝ መጠን 0.3 በመቶ በመሆኑ ከዓለም አኳያ ያለው ድርሻ ዝቅተኛ ነው፡፡ ይህም ቢባል ግን የአገሪቱን የልቀት መጠን በታቀደው ዝቅተኛ መጠን ለማቆየትና በመጨረሻም ወደ ዜሮ ለማውረድ መንግሥት ያለፉት አምስት ዓመታትን ጨምሮ፣ በሃያ ዓመት ውስጥ 150 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልገው በአረንጓዴ ስትራቴጂው ማስፈሩ አይዘነጋም፡፡

   በሌላ በኩል መንግሥት ለመሠረተ ልማት ግንባታ ብቻ ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ 50 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልገው እንደነበር በአረንጓዴ ስትራቴጂ ሰነድ ላይ ያሰፈረ ሲሆን፣ በተጠናቀቀው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱም ጠቅላላ ዕቅዱን ለማስፈጸም ከ75 እስከ 79 ቢሊዮን ዶላር በጅቶ እንደነበርም አይዘነጋም፡፡ በተጠናቀቀው የአምስት ዓመት ዕቅድ ዘመን ውስጥ  ከዚህን ያህል ገንዘብ ውስጥ ምን ያህሉ እንደተገኘና ሥራ ላይ እንደዋለ መንግሥት ማብራሪያ እንደሚሰጥ ይጠበቃል፡፡ 

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  ዳግም ነፍስ የዘራው የተማሪዎች ማርች ባንድ

  የሙያው ፍቅር ያደረባቸው ገና በልጅነታቸው ነው፡፡ በ1970ዎቹ መጀመርያ፣ ለቀለም...

  በስንደዶና ሰበዝ የተቃኘው ጥበብ

  በአንዋር አባቢ ተወልዳ ያደገችው መሀል አዲስ አበባ አራት ኪሎ ነው፡፡...

  አዲስ ጥረት የሚጠይቀው  ኤችአይቪ  ኤድስን  የመግታት  ንቅናቄ

  ‹‹ኤችአይቪ በመላው ዓለም  በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን የሚያጠቃ ዋነኛ የሕዝብ...

  የኅትመት ብርሃን ያየው ‹‹የቃቄ ወርድዎት›› ቴአትር

  ከአራት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር መድረክ ላይ ይታይ...