በኪሳራ የተዘጋውን ሆላንድ ካር የመኪና መገጣጠሚያ ኩባንያቸውን ለመታደግ፣ ከሦስት ዓመታት ቆይታ በኋላ ግንቦት 4 ቀን 2007 ዓ.ም. ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱት ኢንጂነር ታደሰ ተሰማ፣ ኩባንያውን እንዴት ሊታደጉት እንደሚችሉ ያቀረቡትን ሐሳብ 201 የሚሆኑ ገንዘብ ጠያቂዎች ውድቅ አደረጉት፡፡
ኩባንያውን ከጨረታ ሽያጭ ያድናል ያሉትን ዕቅድ ነድፈውና ለመንግሥት አቅርበው ተቀባይነት በማግኘታቸው ወደ አገር ቤት የተመለሱት ኢንጂነር ታደሰ፣ ስድስት ሚሊዮን ብር ይዘው መምጣታቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
201 የሚሆኑት የኩባንያው ደንበኞች መኪና ለመግዛት ከ62 ሚሊዮን ብር በላይ ክፍያ የፈጸሙ ቢሆንም፣ ኩባንያው በገባው ቃል መሠረት ሊፈጽም ባለመቻሉ ኪሳራ አሳውጆ ነበር፡፡
ቁጥራቸው 201 መሆናቸው የተጠቀሰው ገንዘብ ጠያቂዎች፣ ሰኔ 14 ቀን 2007 ዓ.ም. የኩባንያው ባለቤት፣ የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ሬጅስትራርና የተለያዩ ኮሚቴዎች ተሰብስበው በኩባንያው ባለቤት ሐሳብ ላይ ውሳኔ አስተላልፈዋል፡፡
በጠበቃቸው አቶ ጥላሁን ምትኩ አማካይነት የኩባንያው ባለቤት ሐሳብ ተገልጿል፡፡ በዚህም መሠረት ኩባንያው ከኪሳራ ወጥቶ የባለገንዘቦቹን መብት እንደሚያስጠብቅ፣ በመገጣጠሚያ ፋብሪካው ውስጥ ያሉ 174 መኪኖችን ገጣጥሞ ለገበያ ለማቅረብ ስድስት ሚሊዮን ብር እንደተዘጋጀ፣ ተሽከርካሪዎቹ ተገጣጥመው እስከሚሸጡ ድረስ ንብረቶቹ በሙሉ በንብረት ጠባቂና መርማሪ ዳኛ ሥር እንደሚቆዩ ተናግረው፣ በሐራጅ ቢሸጡ ግን የሚገኘው ገንዘብ ከመንግሥት ግብር፣ ከባንክ ዕዳ፣ ከሠራተኞች ክፍያና ከንብረት ዕዳ ማጣሪያ ክፍያ እንደማይተርፍ በመግለጽ፣ በኢንጂነሩ ሐሳብ መስማማት ምርጫ የሌለው መሆኑን ጠበቃው አብራርተዋል፡፡
ገንዘብ ጠያቂዎቹ በበኩላቸው በሰጡት ምላሽ እንዳብራሩት፣ ኢንጂነር ታደሰ ያቀረቡት ሐሳብ ቀደም ብሎ በእንግሊዝኛ ካቀረቡላቸው የሚለየው በአማርኛ መቅረቡ ነው፡፡ የቀረበው የአፈጻጸም ዕቅድ ተዓማኒ እንዳልሆነና ለገንዘብ ጠያቂዎቹ ገንዘባቸው እንዴት እንደሚመለስና ምን ያህል ወለድ እንደሚያካትት አይገልጽም፡፡ ለ174 መኪናዎች መገጣጠሚያ ብለው ያቀረቡት ገንዘብ፣ ባለአንድ ፎቅ የሆነ ቤት እንኳን መግዛት አይችልም ብለዋል፡፡ ኩባንያው ሐሳብ ሲያቀርብ ስለዕዳው አከፋፈል በቅድሚያ የገንዘብ ዋስትና ማቅረብ ቢኖርበትም አለማቅረቡን፣ የከሰረው ኩባንያ ከፍተኛ ዕዳ ቢኖርበትም ከባንክና ከገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ከፍተኛ ግብር ከፋዮች መሥሪያ ቤቶች ጋር ምን ዓይነት ስምምነት ላይ እንደደረሰ ባለማሳወቁ፣ ሐሳቡን ለመቀበል እንደማይችሉ አስረድተዋል፡፡
የከሰረው ኩባንያ ንብረት ጥበቃ ሹም አቶ ግርማ ዓለሙ የሚባሉት ግለሰብ ደግሞ፣ የኢንጂነር ታደሰን ሐሳብ ሌላ ጊዜ ጽፈው ከሚያቀርቡት የተለየ አለመሆኑን ተናግረው፣ የመክሰር ሥርዓት ሒደቱን ለማቋረጥና በስምምነት ሐሳቡ ለመቀጠል የሚያስችል፣ በንግድ ሕጉ ያሉ አስገዳጅ ሁኔታዎችን አሟልተው አለመቅረባቸውን ተናግረዋል፡፡ ስድስት ሚሊዮን ብር እንዳቀረቡ ኢንጂነሩ ቢናገሩም፣ በቅድሚያ መፍትሔ ማግኘት ያለባቸው የቀድሞ ሠራተኞች ክፍያ፣ የፎርክሎዠር (በሐራጅ የመሸጥ) መብት ያለው ዘመን ባንክ ብድር ጉዳይና ለሌሎች የመንግሥት ክፍያዎች የሚበቃ ገንዘብ ስለመኖሩ ተጨባጭ ማረጋገጫ እንደሌለ ገልጸዋል፡፡
በንግድ ሕግ ቁጥር 1064(3) መሠረት የስምምነት ሐሳቡ በኩባንያው ሥልጣኑ በተሰጠው አስተዳዳሪ የፈረመበት ሆኖ ባለመገኘቱ፣ የኢንጂነር ታደሰ ውክልና ሥልጣን የተሰጣቸው ስለመሆኑ ማስረጃ ማቅረብ ስላልቻሉ፣ ሐሳቡ ተቀባይነት እንደሌለውም ተናግረዋል፡፡
በሕግ መሟላት የሚገባቸው ነገሮች ሳይሟሉ ስምምነት ላይ ቢደረስና ሥራ ቢጀመር፣ ንብረቶች ሊሸሹና ሊጠፉ ስለሚችሉ ሊመለስ የማይችል ጉዳት ሊደርስ እንደሚችልም አክለዋል፡፡
በመጨረሻም በውይይቱ ላይ የተለያዩ አስተያየቶች በመቅረባቸው ድምፅ እንዲሰጥበት ተደርጐ፣ በዕለቱ የተመዘገቡ 201 ግለሰቦች ወይም 62,516,068 ብር ካላቸው ገንዘብ ጠያቂዎች ውስጥ 54,982,120 ብር ያላቸው 134 ሰዎች ሐሳቡን ውድቅ አድርገውታል፡፡ በመሆኑም በንግድ ሕግ ቁጥር 1084 (1) መሠረት የስምምነት ሐሳቡ ተቀባይነት አለማግኘቱን፣ የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዋና ሬጅስትራር አቶ መሠረት አያሌው በፊርማቸው አረጋግጠዋል፡፡