መንግሥት በጠራው ሰላማዊ ሠልፍ ላይ ሁከት ፈጥረዋል ተብሎ ክስ የተመሠረተባቸው የሰማያዊ ፓርቲ አባላት፣ በሁለት ወራት እስራት እንዲቀጡ የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ቂርቆስ ምብድ ችሎት ሰኔ 15 ቀን 2007 ዓ.ም. ፍርድ ሰጠ፡፡
በሊቢያ አይኤስ የተባለው ቡድን በኢትዮጵያውያን ላይ የፈጸመውን አሰቃቂ ግድያ ለማውገዝ፣ መንግሥት ሚያዝያ 14 ቀን 2007 ዓ.ም. በመስቀል አደባባይ በጠራው ሰላማዊ ሠልፍ ላይ ረብሻ በመፍጠር፣ በመሳደብና ድንጋይ በመወርወር ሰላማዊ ሠልፉን አውከዋል ተብለው የተከሰሱት የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ወይንሸት ሞላ፣ ኤርሚያስ ፀጋዬ፣ ዳንኤል ተስፋዬና ቤተልሔም አካለወርቅ መሆናቸው ይታወሳል፡፡
ፍርድ ቤቱ ተከሳሾቹ የቀረበባቸውን ክስ ሊከላከሉ እንዳልቻሉ ገልጾ ጥፋተኛ ካላቸው በኋላ፣ የቅጣት አስተያየት ጠይቋል፡፡ ዓቃቤ ሕግ ቅጣቱ ከብዶ እንዲቀጡ አመልክቷል፡፡ ተከሳሾቹም የቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆናቸውን፣ በተለይ ወይንሸት ሞላ ረብሻ ተፈጠረ በተባለበት ዕለት ጠዋት የታሰረች መሆኗንና የታሰረችበትን ፖሊስ ጣቢያ ገልጻ ቅጣቱ እንዲቀልላት ጠይቃለች፡፡
ፍርድ ቤት በሰጠው ፍርድ ቅጣቱ ከብዶ እንዲቀጡ የሚለው የዓቃቤ ሕግን የቅጣት ማክበጃ አስተያየት የተቀበለ ቢሆንም፣ በቡድን ስለመረበሻቸው ያቀረበው ማስረጃ እንደሌለ ገልጿል፡፡ በመሆኑም እያንዳንዳቸው እጃቸው ከተያዘበት ጀምሮ ያለው ጊዜ ተቆጥሮ፣ በሁለት ወራት እስራት እንዲቀጡ ፍርድ ሰጥቷል፡፡ ተከሳሾቹ ሁለት ወራት ከአንድ ቀን የታሰሩ በመሆናቸው በዕለቱ እንዲፈቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ ፍርደኞቹ የማስፈቻ ትዕዛዝ ተዘጋጅቶላቸው ከማረሚያ ቤት የተፈቱት ሰኔ 16 ቀን 2007 ዓ.ም. ቢሆንም፣ ከማረሚያ ቤት ሲወጡ ተይዘው በፀጥታ ኃይሎች ወደ ፖሊስ ጣቢያ መወሰዳቸውን ሰማያዊ ፓርቲ አስታውቋል፡፡