Tuesday, March 28, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ላይ ሙስና በመፈጸም ተጠርጥረው የተከሰሱ ዋስትና ተከለከሉ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

–  ከ17.7 ሚሊዮን ብር በላይ መመዝበሩ ተጠቅሷል

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የደቡብ ሱዳን ሊሚትድ ጁባ ቅርንጫፍ ከ17.7 ሚሊዮን ብር በላይ በተጭበረበረ መንገድ ለግለሰቦች እንዲውል አድርገዋል ተብለው የሙስና ክስ የተመሠረተባቸው አምስት የባንኩ ሠራተኞች፣ ዋስትና ተከልክለው ወደ ማረሚያ ቤት ወረዱ፡፡ አንዲት የቅርንጫፍ ባንኩ ከፍተኛ ኦዲተር በዋስ ተለቀቁ፡፡

የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ዓቃቤ ሕግ ክስ የመሠረተባቸው የባንኩ ሠራተኞች፣ የሒሳብ ሹም አቶ ረሚላ ለወይ ኡስማን፣ የደንበኞች ሥራ አስኪያጅ አቶ ፍፁም ብርሃን ዓለም ስምኦን፣ ሥራ አስኪያጅ የነበሩት አቶ ሀብታሙ ዮሴፍ ማርዬ፣ ማኔጂንግ ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ሚካኤል ተክለ እግዚ ገብረ ማርያም፣ የንግድ አገልግሎት መኰንን አቶ ደስታው ፈንታሁን መንበር (ያልተያዙ)፣ ዋና ኦዲተር ወ/ሮ ሙሉሸዋ ክብረት፣ እንዲሁም አቶ መሐመድ ሁሴን ጣቢር (ያልተያዙ) እና አቶ ሁሴን ለወይ ኡስማን የተባሉ ግለሰቦች ናቸው፡፡

የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አንደኛ ወንጀል ችሎት ያቀረበው ክስ እንደሚያስረዳው፣ ሲቴፕ ፎር ትሬድ ኤንድ ኢንቨስትመንት ካምፓኒ ሊሚትድ የተባለ ድርጅት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጁባ ቅርንጫፍ ደንበኛ ነው፡፡ በባንኩ በኩል 4,360,000 ዶላር ኤልሲ በደቡብ ሱዳን ማዕከላዊ ባንክ ይፈቀድለታል፡፡ ዶላሩ የሚለቀቅለት በሦስት ጊዜ ክፍያዎች ነው፡፡ ክፍያው የሚፈጸመው ገንዘቡ ኬንያ ወደሚገኘው ስታንቢክ ባንክ ከተላለፈ በኋላ ነው፡፡ የመጀመርያው 1,453,33 ዶላር ተልኮለታል፡፡ ለድርጅቱ የሚላከው ዶላር ከደቡብ ሱዳን ፓውንድ ጋር ተመጣጣኝ የሆነና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በደቡብ ሱዳን ማዕከላዊ ባንክ ካለው ሒሳብ ተቀንሶ መሆኑን ክሱ ያስረዳል፡፡

ነገር ግን አንደኛ ተከሳሽ አቶ ረሚላ ለድርጅቱ የተላከውን የገንዘብ መጠን መቀነስ ሲገባው ሳይቀንስ መቅረቱን ክሱ ያክላል፡፡ አንደኛ ተከሳሽ ሒሳብ ሲሠራ (Reconciliation) ሳይቀነስ የቀረው ገንዘብ ተንጠልጣይ ሆኖ ሲያየው ማዕከላዊ ባንኩ እንዲቀንስ ማድረግ ቢገባውም አለማድረጉ ክሱ ጠቅሷል፡፡ አንደኛ ተከሳሽ በሌሉበት ክሱ በተመሠረተባቸው አቶ መሐመድ ሁሴን ጣቢር ስም በ200 የደቡብ ሱዳን ፓውድ አካውንት እንዲከፍቱ ማድረጋቸውም ተጠቅሷል፡፡ በመቀጠልም በተለያዩ ጊዜያት በድምሩ 3,008,813 የደቡብ ሱዳን ፖውንድ የያዙ አራት ቼኮች ወደ  ኬንያ ንግድ ባንክ ለቼክ ማጣራት በማዕከላዊ ባንኩ በኩል ሲላኩ፣ የኬንያ ባንክ በግለሰቡ ገንዘብ እንደሌለው የገለጸ ቢሆንም አንደኛው ተከሳሽ ቼኮቹንና ተያያዥ ቅጾችን በማጥናት ግለሰቡ ገንዘብ ያለው ማስመሰሉ ክሱ ያብራራል፡፡ አንደኛ ተከሳሽ የዴቢት ትኬት በማዘጋጀትና ከሁለተኛ ተከሳሽ ጋር አቶ ፍፁም ብርሃን ጋር በጣምራ ፈርመው የተንጠለጠለው ገንዘብ መሐመድ ሁሴን በተባለ ተከሳሽ ስም ወደ ተከፈተው ሒሳብ እንዲገባ በማድረግ በባንኩ ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን ክሱ ይገልጻል፡፡ በአጠቃላይ ገንዘቡ በኢትዮጵያ ብር ሲሰላ 17,768,589 ብር መሆኑን፣ ተከሳሾቹ በሥልጣን ያላግባብ መጠቀም የሙስና ወንጀል ክስ እንደተመሠረተባቸው የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡

ተጠርጣሪ ተከሳሾቹ ከላይ የተገለጸውን ገንዘብ በሕገወጥ መንገድ የተገኘ መሆኑን እያወቁ፣ በሐሰተኛ መንገድ በስድስተኛ ተከሳሽ አቶ መሐመድ ስም በተከፈተ ሒሳብ የተቀመጠውን ገንዘብ ከተለያዩ አካውንቶች የተላኩ በማስመሰልና ወደተለያዩ የባንክ ሒሳቦች አዘዋውረናል፡፡ የተለያዩ ተሽከርካሪዎችን፣ አንድ ባለሁለት መኝታ የኮንዶሚኒየም ቤት በመግዛት፣ በአጠቃላይ አንደኛ ተከሳሽና ስድስተኛ ተከሳሽ የአንደኛ ተከሳሽን ወንድም ሰባተኛ ተከሳሽ አቶ ሁሴን ለወይንን በመጠቀም፣ ገንዘቡን ማቀናነሳቸውንና በሕገወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ አስመስለው በማቅረብ የሙስና ወንጀል መከሰሳቸውን ክሱ ይገልጻል፡፡

ሁለተኛ ተከሳሹ አቶ ፍፁም ብርሃን ዓለም የወንጀል ሕግ አንቀጽ 411 (2)ን በመተላለፍ የመንግሥትን ሥራ በማያመች አኳኋን በመምራት በሕጋዊ መንገድ ማግኘት ከሚገባቸው በላይ 6,620,600 ብር ይዘው መገኘታቸውንና ይኼም የሙስና ወንጀል መሆኑን ክሱ ይገልጻል፡፡ ሦስተኛ ተከሳሽ አቶ ሀብታሙ ዮሴፍም ማግኘት ከሚገባቸው በላይ 8,298,880 ብር ከሕጋዊ ገቢያቸው በላይ ይዘው በመገኘታቸውን፣ አራተኛም ተከሳሽ አቶ ሚካኤል ተክለ እግዚም 27,930,429 ብር ከሕጋዊ ገቢያቸው በላይ ይዘው በመገኘታቸው፣ አቶ ደስታው ፋንታሁንም 2,684,876 ብር ከሕጋዊ ገበያቸው በላይ ይዘው በመገኘታቸው፣ በፈጸሙት ምንጩ ያልታወቀ ንብረትና ገንዘብ ይዞ መገኘት የሙስና ወንጀል መከሰሳቸውን ክሱ ያብራራል፡፡

በቅርንጫፉ ዋና ኦዲተር የነበሩት ወ/ሮ ሙሉሸዋ ክብረት ሒሳቦችን በአግባቡ ባለመቆጣጠራቸውና የሥራ ኃላፊነትን ባለመወጣት የሚፈጸም የወንጀል ክስ ተመሥርቶባቸዋል፡፡ ተጠርጣሪ ተከሳሾቹ ችሎት ቀርበው ክሱ ከተነበበላቸው በኋላ በጠበቆቻቸው አማካይነት ክሱ ዋስትና እንደማያስከለክል፣ ምክንያቱ ደግሞ አዲስ በወጣው የኮሚሽኑ አዋጅ መሠረት ዋስትና የሚከለክል አንቀጽ መሻሩን ጠቅሰው በዋስ እንዲለቀቁ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡

ዓቃቤ ሕግ የተጠቀሰው አንቀጽ ዋስትና እንደሚከለክልና በአዲሱ አዋጅ ዋስትናን የሚመለከተው አንቀጽ እንዳልተሰረዘ በመግለጽ ጥያቄውን ተቃውሟል፡፡ ፍርድ ቤቱ የደቂቃዎች ረፍት ወስዶ በሁለቱ ወገኖች ክርክር ላይ ከተወያየ በኋላ፣ በድጋሚ በመሰየም ከኦዲተር በስተቀር ሌሎቹን ተከሳሾች ዋስትና ከልክሏቸዋል፡፡ ኦዲተሯም ዋስትና ተፈቅዶላቸዋል፡፡ የክስ መቃወሚያ ለመስማት ለሐምሌ 21 ቀን 2007 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች