Thursday, April 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ተስፋና ትዝታ ይወዘውዙናል!

ሰላም! ሰላም! በኑሮ ውጣ ውረድ፣ የአልሞት ባይ ተጋዳይ ዳገት ላይ ለምትወራጩ … በመጀመሪያ የደላላነት ማዕረጌን ሳልሽር ወታደራዊ ሰላምታ አቀርባለሁ። እያደር በሚብሰን ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ ጫና ወገቤን ስንል እያዩ አሁን አሁን አህዮች ሳይቀሩ ‘ሙድ’ መያዝ ጀምረዋል አሉኝ። አሉ ነው ያልኩት ግን አደራ። ጋሽ ማኦ፣ በእባብ ሾርባና በአህያ አሮስቶ ያስመረቋቸው መንገድ ቀያሾቻችን፣ አህዮቻችን ገፈው የጨረሱብን አንድም በአንተ የአስተርጓሚነት ሚና ነው የሚለኝ አይጠፋም ብዬ እኮ ነው። አዎ! ነገሮች ግልጽ እየሆኑ ስንጓዝ ጥሩ ነው። አይደል እንዴ? ምነው ግን አካል እርቃኑን ሲመናቀር የሚጨበጨብለትን ያህል ነገርና ሸር ግልጥልጥ ሲል የማንወድ? ምነው ግን?

 ‘ባይዘዌ’ (ማወቅ በእንግሊዝኛ ቃላት ጥቅስ ‘ሃይዌ’ ላይ መንጠላጠል ነው ካልን ስለከረምን ነው መራቀቅ ባልገባን መጠን የምራቀቅባችሁ) ወዳጆቻችን ቻይናዎች፣ የባህልና የማንነት መንገዳችንን መቀየስ ላይ ችላ ብለው (ወይ እኛ ችላ በሉት ብለናቸው) በቀየሱት ‘ቀለበት መንገድ’ ላይ በጭንቅ ዘርተን በጭንቅ የምንሰፍረውን እህል ተሸክመው ሲሮጡ መቼስ ታዝባችኋል። ኧረ እንዲያውም የባሻዬ ልጅ እንዳስታወሰኝ ከሆነ ለቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሳይቀር ፓርላማ ላይ ነገሩ ተነስቶላቸው ነበር አሉ። ነፍሳቸውን ይማርና ከአርሶ አደሩ ድህነትና ከማጓጓዣ አቅርቦት ማነስ ጋር አነፃፅረው (“ንፅፅር የሚገባን ቅን ልቦና ሲኖር ነው፤” ይላሉ ባሻዬ) ‘አህያ የትራፊክ ፍሰቱን አወከች። ቀለበት መንገዱንም የሥልጣኔ ማሳያና የዕድገታችን ነፀብራቅ ከማድረግ ይልቅ የኋላ ቀርነታችን ጥቅስ አደረገችው’ ሲባሉ፣ “በ80 ከበረረች መብቷ ነው፤” ብለው ነበር አሉ። በክፉም በደግም፣ በሳቅም ሆነ በመሳቀቅ፣ ቶሎ መፍረስ ከሚቀናን ከእኛ የተውጣጡ የፓርላማ አባላት በሳቅ ፈረሱ። እኛም ሥርጭቱ ተቆራርጦም ሆነ ተለጣጥፎ ሲደርሰን (ኋላ እንደመጣልኝ) ቀድመናቸው በሳቅ ፈርሰን ነበር። ነበር መቼም እያደር ቀረበን።

ምን ነበር? አዎ! ስለኑሮ ሸክም አወራለሁ ብዬ ሌላ ሸክም ቁለላ ውስጥ ተደነጎርኩ። መቼስ ወግ አይደል? ወግ ደግሞ በዓይን ይገባል። አሁን እንኳ በቴክስት፣ በቫይበር፣ በፌስቡክና በትዊተርም እየገባ ነው። ማን ዓይን ለዓይን ይተያያል? እውነቴን ነው። ስንተያይም የራሳችንን ምሰሶ ሳንነቅል የሰው ጉድፍ ካላወጣን እያልን አገር ይያዝልን ሆኗል ሙያችን። ይኼው ያልነው አልቀረልንም እማማ ኢትዮጵያ፡፡ ይህቺ የሆሜር ድርሰት አድማቂ፣ የሦስት ሺሕ ዓመት ተጀምረው ያልተጨረሱ ሥልጣኔዎች ባለቤት፣ እርስ በርስ በመነቋቆርና በመጠዛጠዝ ግርግር ተይዛልን አረፍነው። እሰየው አይባል አገር፣ እንቢየው አይባል ፍቅር ነስቶን በ‘ምን አባህ! የት አባሽ! ምን ታመጣለህ?! ምን ታመጫለሽ?!’ ግልምጫ ማን አለብኝነታችን ፋፋ። “ምነው ግን በልጅነታችን የበላነው ፋፋ ደግ ደጉ ባህላችን ላይ አላፋፋን አለ?” ብዬ የባሻዬን ልጅ ስጠይቀው፣ “ከጥያቄህ በፊት የሚቀድመው ‘ስንት ፐርሰንቷ ኢትዮጵያ ናት ይኼን ምግብ እኩል ተመግባ የፋፋችው?’ የሚል ጥያቄ አለ፤” ብሎኝ አረፈው። እሱ ደግሞ እንዴትም እንዴትም ብሎ ‘ፐርሰንት’ እና ‘ዕድገት’ የሚባሉ ቃላት ንግግሩ መሀል መደንጎር ይወዳል። ኤድያ!

እኔም ቆርጦ አይቆርጥልኝ ዞሬ ዞሬ ለእሱን ነው የሆዴን የማጫውተው። ሆዴ ከሞላና ጨዋታ ‘ኤክስፖርት’ የማድረግ አቅም ካለው ነው ታዲያ። ለነገሩ ተመስገን ነው! እኛ እኛ ምንም አንልም። ለእነሱ ለእነሱም በልማታዊ ብልፅግና ጎርፍ በሥልትና በጥበብ (ጥበብ የሚለው የፀደቀ ስለመሰለኝ አቋራጭ ማለቱን ትቻለሁ) ተሽለው ለሚታዩትም አገሩ አማን ነው። ግን ደግሞ አሉ ወዲያ። ከአደባባዩ ባሻገር፣ ፍሳሽ እያስመለሰ ከተማችንን ከፊል ጎርፋማ ከሚያደርገው ፉካ ሥር የሚያድሩ። መጠለያና ንፁህ ምግብ ማግኘት፣ መንግሥተ ሰማይ ‘ቪአይፒ’ ቦታ ከማግኘት እኩል የሆነባቸው ደግሞ አሉ። ‘እንዴት ይረሳል?’ እንዳለው የትዝታው ንጉሥ!

ታዲያ በቁሜ የማየው የዚህች ዓለም ትዕይንት በሐዘን እያፈዘዘኝ በቁሜ ላንኮራፋ ‘ሲንግል ዲጂት’ የሮሮ ዕድገት ሲቀረኝ፣ እባንንና እጄ ላይ ያሉትን ሥራዎች ለመጨራረስ እቃብዛለሁ። እዚያ የሚከራይ ቤት አለኝ። ወዲህ ወደ 12.8 ሚሊዮን ብር የሚገመት የተንጣለለ ቪላ ቤት፣ ተከራይና ገዢ የሚፈልጉ ከባድና ቀላል ተሽከርካሪዎችማ አልቆጥርላችሁም። ግን መምረጥ ይከብደኛል። ‘የቱን ቅድሚያ ልስጥ? ማን ደውሎልኝ ነበር? ምን ፈልጎ?’ ስል የሚታዘበኝ አንድ የሙያ ባልደረባዬ፣ “አይ አንበርብር አንተም ብለህ ብለህ እንደ ሰፊው ሕዝብ ግራ ተጋባህ?” ይለኛል። እንደምታውቁት ባልተጻፈው የጠቅ ጠቅ ፎርሙላችን እገዛ መናገር የምንፈልገውን ቀጥታ ተናግረን አናውቅም። መናገሩን ትታችሁት መንገዱንም ቀጥ ብለን አንራመድም። ለምሳሌ ከቤት ወጥተን ጎረቤት ቤት ገብተን፣ ከጎረቤት አውርተን ደግሞ ዕቃ ረሳን ብለን ቤታችን ተመልሰን ገብተን ከዚያ ተመልሰን የሠፈራችን ሱቅ ወይም ከአንድ ባለሻይ ቤት ወዳጅን ጋር አቶክቱከን፣ ከዚያ ነው ሊመሽ አካባቢ ሠፈር የምንለቀው እንጂ፣ ከፈረንጅ እኩል 24 ሰዓት ተሰጥቶን ይኼን ያህል የኑሮና የአስተሳሰብ ልዩነት እንዴት ይመጣል? ደግሞ ይኼን ልናጣራ ነው ብላችሁ ዙሩን አክርሩት አሉዋችሁ። ሆሆ!

 እንግዲህ ይኼ በእኛ ጊዜ ነው። መብራትና ስልክ ከተግባር በጽንሰ ሐሳብ ደረጃ በምናውቅበት ዘመን ነው ያወራሁት። ምናልባት አሁን በ‘ቻት’ መረብ ተለክፈን፣ በ‘ቴክኖሎጂ’ አጥር ታጥረን ስለምንገኝ ጎረቤታችንን ሳናውቀው ባህር ተሻግረን አሜሪካና አውሮፓ ነው ቤተስኪያን ሳይቀር የምንሳለመው። ግነት አይደለም። ኑሯችን ነው። እና ባልደረባዬ ‘አንተም እንደ ሰፊው ሕዝብ’ ሲለኝ ወዲያው የገባኝ ከዚያ በፊት ‘ጠባቡ ሕዝብ’ ከሚባለው የእሱን መደላደል፣ መብላት፣ መጠጣት እንጂ የሌላው ደንታ ከማይሰጠው መሀል መድቦኝ እንደኖረ ገባኝ። ምናልባትም እንዲያ እንዲገባኝ ፈልጌ ይሆን? እውነቱን ሳይሆን ደስ ያለንን እያመንን መሰለኝ ግን የሚባባስብን እየተባባሰብን ያለው። ሲሪየስ!

ወዲያው ግን ነገር ማንሸዋረሩን ትቼ “እንዴት?” ስለው “ጊዜው የነጥብ ሆና። ይኼ የ‘ዴሲማል ኑሮ’ እኮ አንጎላችንን እንዳወዛገበው ሌላ ምን አወዛገበው?” አለኝ። ገረመኝ። ትኩር ብዬ ሳስበውማ የዘመኑ የኑሮ ትግል ከአንግሎ ሳክሶኖች በተሻለ የምናብድለትን የእግር ኳስ ሊግ አስከንድቶታል። ስንት ተሸጠ? 1.5 ሚለዮን። ስንት ያወጣል? 2.4 ሚሊዮን። አኮኖሚያችን በስንት አደገ በምናምን ነጥብ ምናምን (ነጥቡ ላይ ብቻ ስለምንስማማ ብዬ ነው እ)፣ በቃ ምን አለፋችሁ ሁሉ ነገራችን ነጥብ ሆኗል። እኛም እያደር ነጥብ ያከልነው ለዚያ ሳይሆን አይቀርም። አንዳንዴማ የምፈራው ወደፊት ስማችንን ስናስተዋውቅ ሁሉ በነጥብ እንዳናደርገው ነው። ‘ላይክ’ … ‘አንበርብር ነጥብ ምንተስኖት’ አይነት። የምሬን ነው! ያን ጊዜ አዳሜ ኪሱ በነጥብ ሥሌት ሰውነቱን ከፍ ዝቅ እንዳደረገው ወደ ስሙም ይተላለፍለትና ያበቃለታል። ከሁሉ ከሁሉ ይኼ ወዳጄ ‘የዴሲማል ኑሮ’ ያላት አገላለጽ መጀመሪያ አፅኖት ሰጥቼ ላወራችሁ ከነበረው የኑሮ ጫናና የእኛ አፍሶ መበተን ጋር ተመሳስሎብኛል። እንዴት ካላችሁ ነገሩ ‘ማቲማቲካል’ ስለሚሆን ‘አቴንሽን’ እ? መቼም ገቢ ለማሥላት ከሚጠቅሙን አራቱ የሒሳብ መደብ ሥሌቶች ሌላ ብዙዎቻችን በ‘ማትስ’ ክፍለ ጊዜ ‘ሮማንስ’ እንዳነበብን አስታውሳለሁ። ዛሬ እሱም ተስቶ፣ ኑሮ ቀልብ ነስቶን ሳንጣመድ ስንፋታ ብንውልም። ጉዳችን መቼስ አያልቅም! ለምን ተብሎ?

እንግዲህ በ‘ዴሲማል’ ወግ ወይም በክፍልፋይ የሒሳብ ሥሌት፣ ከነጥብ በኋላ የሚመጡት ቁጥሮች ምን እልፍ አላፍ ቢሆኑ በጋራ አይቆጠሩም። ከነጥቡ በኋላ የሚመጡት ቁጥሮች አንድ በአንድ እንጂ በጅምላ አይጠሩም ነው ባጭሩ። የሒሳብ መምህር ክፍተት ያለባቸው ትምህርት ቤቶች ካወቃችሁ ግድየለም ጠቁሙኝ አላሳፍራችሁም። ይኼን ወደ ኑሯችን ስትገለብጡት ታዲያ ከላይ እንዳወራነው የነጥብ ኑሮ ነውና የምንኖረው የምንደረድረው ትርፍ፣ የምናግበሰብሰው፣ እኔ ብቻ በልቼው ልሙት እያልን የምንሰቃይበት ኮተት ሁሉ ከንቱ ነው ለማለት ነው። ገባችሁ? እንግዲህ ይኼ ከገባችሁ ክፍልፋዩ የዚህ ዓለም ኑሮ 0.000 … ስለሆነባቸው ወገኖቻችን ለማብራራት ብዙ አታደክሙኝም። በዚህ ከቀጠላችሁ ‘የትምህርት ጥራትን በተመለከተ ከፍተኛ ሥራ መሠራቱን ትምህርት ሚኒስቴር ገለጸ’ የሚል መግለጫ ማመን እጀምራለሁ ማለት ነው። ወይ እናንተ፣ የማታስለፈልፉኝ የለም?

በሉ እንሰነባበት። መሀል ላይ ጨዋታውና ፍልስፍናው ተቀዣብሮብኝ ምኑን ከምን አድርጌ ጠቀም ያለ ኮሚሽን መሰለቄን አልነገርኳችሁም። እጄ ላይ የነበረውን 12.8 ሚሊየን ብር የሚገመት ቪላ 11.6 ሚሊየን ብር አሻሻጥኩት። ይኼ በየት በኩል እንደተሰማ አላውቅም። ለነገሩ እንኳን ገበና አወጣሹ ቴክኖሎጂ እንዲህ ሕፃን አዋቂው እጅ ገብቶ፣ ያኔም በገመና ከታቹ ደግ ጊዜ ወሬን ተራራ አይጋርደውም ነበር የሚባል። እህ? ያም እየደወለ ‘ዛሬ እከሌ ጋ ቦትል ዊስኪ ካላወረድክ’ ሲለኝ፣ ያም እየደወለ ‘በስካር ብራና ላይ ሽርፍራፊ ህልውናችንን በነጥብ እንድንስል ዕድል ካላመቻቸህልን’ ሲለኝ ልቤን ፍርኃት ፍርኃት አለው። ወዲያው ወደ ውዷ ባለቤቴ ማንጠግቦሽ ደውዬ፣ “ዛሬ በጊዜ ነው የምመጣው፤” አልኳት። እንደ ዘመኑ ፊልም የተመልካችን ፍላጎት ለማርካት ‘ሟች ከመሞቱ በፊት ይንቀዠቀዥ ነበር’ የሚል ፊልም የምሠራው እብድ ነኝ ታዲያ? እሱን እኮ ነው የማወራው!

ቤት ስደርስ ምን የመሰለ ጎመን ትክትክ ብላ ከበሰለች ሽሮ ወጥ ጋር ቀርቦ ደረስኩ። ውዷ ማንጠግቦሽ ረከቦት ዘርግታ በሰከነና ሥርዓት ባለው የሴት ወግ ጎጆዬን አድምቃ ስትጠብቀኝ ባያት “ሁከት በሞላበት ሠፈር ከመዋል የጣፈጠ ጎመን ወጥ በሰላም በልቶ ማደር ይበልጣል፤” እያሉ ባሻዬ ዘወትር ከሰለሞን ምሳሌዎች የሚጠቅሷት ጥቅስ ውልብ አለችብኝ። አትርፈን በማናተርፍበት የአኗኗር ዘዬ፣ ስክነትና መረጋጋት ርቆን በገንዘብ ኃይል የምንሆነው የጠፋንን እያሰብኩ፣ በዚህ ዓለም ገንዘብ የሚገዛቸው ነገሮች እጅግ ርካሽ ሆነው ታዩኝ። የተፈጥሮ ሚዛን አጠባበቅ የራሴን ሚዛን አሳተኝ። ‘የሚዛን አጠባበቅ ኮርስ እንሰጣለን’ ብለው ሳይመጡብን ቀድመን ከተፈጥሮ ብንማር አይበጅም ታዲያ? ያኔ “ደቁና ስትመጣ ቄስ ሆንኩባት እኔ፤” የሚለውን ጋብዞ ከወጪ መዳን ይቻላል። ይኼንንና የመሳሰለውን ሳወጣና ሳወርድ የትናንቱ በርቀት እየታየኝ፣ የነገው በቅርበት እየመጣብኝ ራሴን መሀል ላይ አገኘሁት፡፡ የገዛ ሕይወቴ ከፊት ተስፋን ከኋላ ትዝታን አስከትላ ሳያት ወደድኳት፡፡ ስንቶቻችን እንሆን በተስፋና በትዝታ የምንወዛወዘው? ይመቻችሁ። መልካም ሰንበት!            

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት