Monday, April 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዝንቅማዘጋጃ ቤት ዱሮ እና ዘንድሮ

ማዘጋጃ ቤት ዱሮ እና ዘንድሮ

ቀን:

በዳግማዊ ምኒልክ ዘመን 130 ዓመት ግድም የተቆረቆረችው አዲስ አበባ ከተማ ማዘጋጃ ቤቷ የተቋቋመው በ1901 ዓ.ም. እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ አራዳ ጊዮርጊስ አካባቢ የተሠራው የመጀመርያው ሕንፃ ላይ (በፎቶው የሚታየው) የከተማው አስተዳደር መጠርያ የተገለጸው በአማርኛና በፈረንሳይኛ ‹‹የአዲስ አበባ ከተማ ማዘጋጃ ቤት Muncipalite Addis Abeba›› በሚል ነበር፡፡ ከፈረንሳይኛ ወደ እንግሊዝኛ ሽግግር ሲደረግ ግን በእንግሊዝኛ ፊደል አዲስ አበባ የተገለጸችው      “Addis Ababa” (አዲስ አባባ) ሆኖ እስካሁን ዘልቋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ያለውና የከንቲባው መቀመጫ ዘመናዊ ሕንፃም በፎቶው ይታያል፡፡ 

******

ሕፃን ሲጠይቅ

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

(በአቤ ጉበኛ)

‹‹ስሚኝ እናት ዓለም!››

‹‹እሺ ምንድን ነው የኔ ዓለም?››

‹‹ያቺ ነገር ምንድን ናት?››

‹‹የት አለች? የት ነው ያየኻት?››

ሕፃኑም ዘረጋና እጆቹን ወደ ሰማይ!

ጨረቃዋን አሳያት ስታበራ ባናታቸው ላይ!

‹‹እሷማ ጨረቃ ናት!››

ብላ መለሰች እናት፡፡

‹‹ጨረቃ ማለት ምንድነው?››

‹‹ይኸ ልጅ ምንድነው የሚለው?››

‹‹እናት ዓለም ጨረቃን አንቺም አታውቂያት?››

‹‹እንግዲህ አታስቸግረኝ ጨረቃ ጨረቃ ናት፡፡››

‹‹ጨረቃስ እሺ ትሁን ታዲያ ተዚያ ላይ ማን ሰቀላት?

‹‹እግዚሐር ነው የፈጠራት፡፡››

‹‹እግዚአብሔር ማለት ምንድነው?››

‹‹ይህ ልጅ ምንድነው የሚለው?

እግዚሐር ማለት ሠሪ ነው አንተን እኔን የሠራ!

ጨረቃንም የፈጠራት በሌሊት እንድታበራ!››

‹‹እኔን የሠራ እግዚሐር ነው?››

‹‹አዎን የሠራህ እግዚሐር ነው!››

‹‹ታዲያ አንቺ ምንድኔ ነሽ እናት ዓለም!››

‹‹እኔማ የወለድሁህ እናት ነኝ የኔ ዓለም!››

‹‹እንዴት አድርገሽ ወለድሽኝ?››

‹‹ውልድ! አድርጌ ነዋ በቃ እንግዲህ አታድርቀኝ››

‹‹ምንድነው እናት ዓለሜ ስጠይቅሽ ምትቆጭኝ››

‹‹እሽ የኔ ዓለም ጠይቀኝ››

‹‹እንዴት አድርገሽ ነው የወለድሽኝ?››

‹‹አንተ ልጅ ዝም በል ብያለሁ!››

እራስህ አድገህ ድረስበት፤

አሁን እኔ ሥራ ልሥራበት!››

ብርሃኑ ገበየሁ ‹‹የአማርኛ ሥነግጥም›› (2003)

*****

የዘመናዊው ሥልጣኔ ቅድመ አያቱ

 “ታሪክ ጸሐፊ ሁሉ የዓለምን ሥልጣኔ አጀማመር በሚመዘግብበት ጊዜ ሀተታውን የሚጀምረው ከአፍሪካዊው፣ ከኢትዮጵያዊው ዓባይ በመነሣት ነው፡፡ የዓባይን ሥልጣኔ የሚቀድም እስከ ዛሬ አልተገኘም፡፡ ብዙ ተመራማሪዎች ምናልባት ከዓባይ የሚበልጥና የሚቀድም ሥልጣኔ ይኖር ይሆን በማለት ጣሩ ጋሩ፡፡ ግን የዓባይ ሐቅ እንደ ዓባይ እየገነነ፣ ከሌላው ሁሉ እየላቀ ሄደ፡፡ በዚህም ምክንያት ታሪክ ጸሐፊዎች ሁሉ የዓባይን የሥልጣኔ ምንጭነትና የዓለም ታሪክ መነሻነት በመቀበል፣ ለዓለም ታሪክ መቅድም፣ መግቢያ፣ ፊታውራሪ፣ አዋጅ ነጋሪ፣ ተስፋ አብሳሪ ማድረግ ግድ ሆኖባቸው ይታያል፡፡

“ይህ የዓባይ፣ ብሎመ የአፍሪካ ሥልጣኔ፣ በምሥር፣ በግብፅ፣ በኑብያ፣ በኢትዮጵያ ተዘርግቶና ተንሰራፍቶ የነበረው ነው፡፡ ዓባይ ከመነሻው ኢትዮጵያ እስከ መድረሻው ግብፅ ድረስ በሥልጣኔ ማሸብረቅ የጀመረው የዛሬ ስድስት ሺሕ ወይም ሰባት ሺሕ ዓመት ጀምሮ ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ፣ እንደ ግብፃውያኑ፣ ኑብያውያኑ፣ ኢትዮጵያውያኑ በቤተመንግሥተና በቤተመቅደስ መካከል እየተመላለሰ ሕግንና ሥርዓትን ከመተርጐም ደረጃ አልደረሰም ነበር፡፡ በሃውልትና በፒራሚድ መካነ መቃብርን እንኳ ሳይቀር ማስጌጥ የዓባይ ሰዎች ችሎታ ብቻ ነበር፡፡ በሐውልቶቹና በሕንፃዎቹ ላይ የታየውም የሂሳብና የጆሜትሪ ስሌት እስከ ዛሬ ድረስ በመደነቅ ላይ ያለው የኛው ነው፡፡ ይህ ሁሉ ዝና አፈታሪክ ሳይሆን ራሳቸው ባለታሪኰቹ በራሳቸው ጽሕፈት የመዘገቡት ነው፡፡ የዓባይ ጥንታዊ ታሪክ እጅግ አስገራሚ በመሆኑ ሁሉንም ለመግለጽ ቃላት ያጥሩኛል፡፡

የግሪክ ሥልጣኔ የተገኘው ከግብፁ ሥልጣኔ ነው፡፡ እንዲህ እንደ ዛሬው፣ እንደ እኛ፣ ባለሙያዎች ከአፍሪካ ተሰደዱ፡፡ በአገራቸው በግብፅ ውስጥም የመኖር ችግር ስለገጠማቸው በስደት ባሕሩን አቋርጠው በአቴንስና በዛሬዋ ግሪክ አካባቢ ሠፈሩ፡፡ በዚያም የምህንድስና፣ የቅርፃቅርፅ፣ የሃውልት ሥራቸውን፣ በጠቅላላውም ሥልጣኔያቸውንና ፍልስፍናቸውን አስተማሩ አሻሻሉ፡፡ የባለሙያዎች መሰደድ በዚያን ጊዜም መኖሩን ይህ ታሪክ ይጠቁመናል፡፡

 የዘመናዊ ሥልጣኔ የትውልድ ሐረጉ እንዲህ ነው፤ አፍሪካዊው ዓባይ የግብፅን ሥልጣኔ ወለደ፤ የግብፅ ሥልጣኔ የግሪክን ወለደ፤ የግሪክ ሥልጣኔ የሮምን ሥልጣኔ ወለደ፤ የሮም ሥልጣኔ የአውሮፓን ሥልጣኔ ወለደ፤ የአውሮፓ ሥልጣኔ የምዕራብ ዓለምን ሥልጣኔ ወለደ፤ በመሆኑም የዘመናዊ ሥልጣኔ መገኛው ቅድምአያቱ የአፍሪካዊው የዓባይ ሥልጣኔ መሆኑን ሰዎች ሁሉ ያውቁ ዘንድ አጠንክረን እናስተምራለን፤ እንሰብካለን፡፡

ፍቅረ ድንግል በየነ ‹‹የሳይንስ ራዕይ›› (1987)

****

የማይረሳው የሰኔው የኢትዮ ኮርያ ወንድማማችነት

ከስድሰት አሠርታት በፊት የኢትዮጵያው ቃኘው ጦር በተባበሩት መንግሥታት ሥር ኮርያ ዘምቶ ነበር፡፡ ሰኔ 21 ጠዋት ለልዩ ልዩ የጥገና የጠቅላላ አገልግሎት ሥራ ከጦሩ ጋር የተመደቡ የአገሬው  የደቡብ ኮሪያ ዜጎች የቃኘውን 1ኛ ሻምበል የግንባር መከላከያ ለማጠናከር የመሰናከል ሽቦዎችን እየዘረጉ ነበር፡፡ አንድ የደቡብ ኮርያ ሲቪል ከግንባሩ መስመር አጠገብ ይህንኑ ሥራ ሲያከናውን ጠላት እንቅስቃሴውን ተከታታሎ ኖሮ በከባድ ሞርታር ድብደባ ይጀምራል፡፡

ከመካከላቸው ሁለቱ ተኩስ እንደተከፈተ ሽፋን ለማግኘት ፋታ አልነበራቸውም፡፡ በዚህ ወቅት አንደኛው ክፉኛ፣ ሌላኛው በመጠኑ ይቆስላሉ፡፡ አስር አለቃ መለሰ ብርሃኑ የሻምበሉ ባልደረባ የሞርታሩን ጥይት አወዳደቅ ለማየት ከምሽጉ ይወጣል፡፡ እንደወጣም የእርዱኝ፤ የድረሱልኝ የስቃይ ድምፅ ከአንድ ኮርያዊ ይሰማል፡፡ ኢትዮጵያዊው መለሰ ቋንቋውን ስለማያውቅ ኮርያዊው የሚለውን ነገር አልተረዳም፡፡ ሆኖም አሰቃቂው የስቃይ ጩኸት ጆሮውንም፣ ልቡንም ዘልቆ ገብቶ አሳዝኖታል፡፡ ይህንን የስቃይ ጩኸት የሰማው አስር አለቃ መለሰ ከፊቱና ዙርያውን እየወደቀ ያለውን የሞርታር ጥይት ከመጤፍ ሳይቆጥር የቆሰለውንና ዕርዳታ የጠየቀውን ኮርያዊ ለማዳን ወደ ወደቀበት አመራ፡፡ ሆኖም ኮርያዊውን በእቅፉ እንደያዘና ፊቱን ወደ ምሽጉ እንዳዞረ አጠገባቸው በወደቀ የሞርታር ጥይት ሁለቱም ይሰዋሉ፡፡ በአንድም ይቀበራሉ፡፡

(ኢኮዘማ፣2003)

******

‹‹ልትሾም ነው››

‹‹ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ሰው በውድቅት ሌሊት አፍላ እንቅልፍ ጭልጥ አድርጎ ወስዶት ሳለ አሰቃቂ ሕልም ያያል::

ሕልም አላሚው በሁኔታው ተደናግጦ አይ ዘንድሮስ መሞቴ ነው መሰል አለ:: በዚህም ምክንያት የመንፈስ መረጋጋት ስላጣ ባቅራቢያው ወደሚገኝ ሕልም ተርጓሚ ካህን ሔደና ‹ዛሬ አሰቃቂ ሕልም አየሁ፣ መሞቴ ነው መሰለኝ› አለው::

‹ሕልምህ ምንድን ነው? እስቲ ንገረኝ አለው› ሕልም ተርጓሚው ካህን፤

‹በውድቅት ሌሊት አፍላ እንቅልፍ ጭልጥ አድርጎ ወስዶኝ ሳለ፣ እጅ እግሬ ሽባ ሆኖ፣ ዓይኔ ታውሮ፣ ጆሮዬ ደንቁሮ አየሁ:: ብንን ብል ሕልም ሆነ› አለው::

‹አትሞትም አይዞህ፣ አትሞትም፣ ልትሾም ነው› አለው ተርጓሚው ካህን::

‹እንዴት ልትሾም ነው?› አለና የሕይወት ሞት ሞተ ሕልመኛው:: ሕልም ተርጓሚው እንደተገለጠለት ሕልሙን ይተረጉምለታል::

‹ስማ! እጅ እግርህ ሽባ ሆኖ ማየትህ፣ ዱሮ ወዲህና ወዲያ እየተሯሯጥክ ላገርህ፣ ለወገንህ፣ ለራስህ የሚጠቅም ሥራ ትሠራ ነበር:: ከተሾምህ ግን ይህ የትሩፋት ሥራ የለም:: ሹም ነህ ተብለህ፣ እጅ እግርህን ኮርትመህ መቀመጥህ እኮ ነው:: ዓይንህን ታውሮ ያየኸውማ ላገር፣ ለሕዝብ፣ ለወገን ጉዳይ ሰው ሊያነጋግርህ በግር በፈረስ ሲፈልግህ ይህን ጋጋታ ማየት አትፈልግም:: ከበር የሚቆመው አጋፋሪህ ከእንግዳ ጋር ናቸው፤ ሥራ ይበዛባቸዋል፤ ወደ ውጭ ሊሔዱ ነው፤ ከዚህ ወግድ እያለ ፈላጊህን ሁሉ ያባርረዋል:: ስለዚህ ዓይንህ ከሌላው ሰው ይሰወራል ይጨፈናል::

‹ጆሮህ መደንቆሩ ደግሞ ድሀው ሕዝብ፣ ሥራ አጡ፣ በሽተኛው፣ አቤት ባዩ፣ መንገደኛው፣ ፍርድ የጐደለበት፣ ግፍ የተሞላበትም ሁሉ ዋይ ዋይ፣ አቤት አቤት፣ ሲል የድሀውን ዋይታ፣ የድሀውን አቤቱታ አትሰማም› አለውና አጠቃልሎ አስረዳው::››

ዜና ማርቆስ እንዳለው ‹‹ቅኔ ለወጣቶች›› (2003)

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...