ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. መካሄድ ሲገባው፣ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ውሳኔ የተላለፈው ምርጫ ሰኔ 7 ቀን 2007 ዓ.ም. በደቡብ ክልል በካፋ ዞን፣ በቦንጋ ጊምቦ ገዋታና በዴቻ ወረዳ ተከናውኗል፡፡ የግል ዕጩውን ዶ/ር አሸብር ወልደ ጊዮርጊስና የደኢሕዴን/ኢሕአዴግ ዕጩ ዶ/ር መብራቱ ገብረ ማርያም ያፋጠጠው ይህ ምርጫ፣ ቀደም ብሎ ግጭት ስለተካሄደበት ነበር ለሌላ ጊዜ የተላለፈው፡፡ ለዚህ ምርጫ 67,707 መራጮች የተመዘገቡ ሲሆን፣ 95 በመቶ የሚሆኑ መራጮች ድምፃቸውን መስጠታቸውን የምርጫ ክልሉ ኃላፊዎች አስታውቀዋል፡፡ በውጤቱም ዶ/ር መብራቱ ዶ/ር አሸብርን በሰፊ ውጤት ማሸነፋቸውን በማግሥቱ በምርጫ ጣቢያዎች ከተለጠፉ ውጤቶች ለመረዳት ተችሏል፡፡ በምርጫ 2002 በወቅቱ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር የነበሩትን አቶ ብርሃኑ አዴሎን በሰፊ ልዩነት ያሸነፉት ዶ/ር አሸብር፣ በዘንድሮ ምርጫ አልቀናቸውም፡፡ ዶ/ር አሸብር በቅርቡ ለፓን አፍሪካ ፓርላማ ሁለተኛ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው ቢመረጡም፣ የዘንድሮ ምርጫ ከብዷቸዋል፡፡ ተፎካካሪያቸው ዶ/ር መብራቱ የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡ በምርጫ 2002 ለደቡብ ክልል ምክር ቤት ተወዳድረው ሲያሸንፉ፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለምርጫ የቀረቡት ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡ ባለፈው እሑድ በተካሄደው ምርጫ በምርጫ ጣቢያዎቻቸው ተገኝተው ድምፃቸውን የሰጡት ዶ/ር መብራቱ (በስተቀኝ)፣ ዶ/ር አሸብር (በስተግራ) ድምፃቸውን ለመስጠት ተሠልፈው ይታያሉ፡፡ የቦንጋን የዘገየ ምርጫ በተመለከተ የተዘጋጀው የነዓምን አሸናፊ ዘገባ ለመመልከት እዚህ ላይ ይጫኑ፡፡