Sunday, March 26, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ኢትዮጵያን መታደግ ይቅደም!

የአገሪቱን ተተኪ ጠቅላይ ሚኒስትር ለመሰየም በዝግጅት ላይ የሚገኘው ኢሕአዴግ ከፊቱ በርካታ ፈተናዎች ይጠብቁታል፡፡ ከፈተናዎቹ መካከል አንደኛው በጋራ መግባባት ላይ የተመሠረተ ዕጩ መምረጥ ነው፡፡ በ2004 ዓ.ም. የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ፣ ተተኪያቸውን በመግባባት ላይ በመመሥረት በመሰየም የተፈጠረውን ክፍተት መሙላት ተችሎ ነበር፡፡ አሁን ግን በኃላፊነት ላይ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር መልቀቂያ አቅርበው ተተኪያቸውን ሲጠባበቁ፣ በኃላፊነት ስሜት አዲሱን ተሿሚ ማቅረብ ይጠበቃል፡፡ አገሪቱ አሁን ከገባችበት ውጥረት አንፃር ከአገር በላይ ምንም ነገር የለም በማለት ብልኃትና ቅንነት ማሳየት ያስፈልጋል፡፡ አዲሱን ተሿሚ ለመምረጥ በሚደረገው ጥረት ከምንም ነገር በላይ የአገርንና የሕዝብን ዘለቄታዊ ጥቅም ማስቀደም የግድ መሆን አለበት፡፡ የኢሕአዴግ አራቱ ብሔራዊ ድርጅቶች አመራሮችም ሆኑ በየደረጃው ያሉ ሹማምንት መገንዘብ ያለባቸው፣ የዓለም ዓይኖች ኢትዮጵያን በሥጋትና በጥርጣሬ እየተመለከቱ መሆኑን ነው፡፡ ወቅቱም የጎሪጥ እየተያዩ የባሰ ችግር መፍጠሪያ ሳይሆን፣ ለአገርና ለሕዝብ የሚበጅ መሪ በጋራ ጥረት ማስገኛ መሆን ይኖርበታል፡፡ ተወደደም ተጠላም ይህንን አሳሳቢ ጊዜ በብልኃት መሻገር የሚጠቅመው ለሕዝብና ለአገር ህልውና ነው፡፡

ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ለመግለጽ እንደተሞከረው ኢትዮጵያ ሰላማዊትና ዴሞክራሲያዊት አገር እንድትሆን ከተፈለገ ለሕግ የበላይነት መገዛት የግድ ነው፡፡ አሁንም በኃላፊነታቸው ላይ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ሲተኩም ሕግና ሥርዓትን መከተል እንዳለ ሆኖ፣ የነገውን የአገሪቱንና የሕዝቡን መፃኢ ዕድልም አሸጋግሮ ማየት ያስፈልጋል፡፡ ባለፉት ሦስት ዓመታት አገሪቱን የገጠሟት ፈተናዎች ክቡር የሆነውን የሰው ሕይወት ቀጥፈዋል፡፡ አገሪቱም ከቀውስ ወደ ቀውስ እየተሸጋገረች ለሁለተኛ ጊዜ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተደንግጓል፡፡ በዚህ ፈታኝ ወቅት በመግባባትና በመርህ ላይ በመመሥረት ውሳኔዎች ካልተላለፉ አገሪቱ ለአደጋ ትጋለጣለች፡፡ ይህንን አሥጊ ጊዜ በሰላም ወደሚቀጥለው ምዕራፍ ለማሸጋገር ብቃትና ጥንካሬን ከሥነ ምግባር ጋር የተላበሰ መሪ ማግኘት የግድ ይላል፡፡ ለአገሩ ራዕይ ያለው፣ ለሰላምና ለዴሞክራሲ የማያወላውል አቋም የሚያሳይና ይህንን አሳሳቢ ጊዜ በብልኃት መወጣት የሚችል መሪ ለመምረጥ አገርን ማስቀደም ይገባል፡፡ ከቡድን መጓተትና አሻጥር በመውጣት ኢትዮጵያ ተስፋ ያላት ጠንካራ አገር መሆኗን ለዓለም ማሳየት ያስፈልጋል፡፡ ኢሕአዴግ በአፍሪካ ካሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተሻለ ቁመና ላይ ያለና የአገሪቱ ህዳሴ ፋና ወጊ መሆኑን እየተናገረ፣ የገዛ ራሱን ውርስ (Legacy) አንኮታኩቶ አገሪቱንም የማትወጣው ችግር ውስጥ ከጣለ በታሪክ ፊት ተጠያቂ ይሆናል፡፡ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን መታደግ ያስፈልጋል መባል ያለበት አሁን ነው፡፡ ጉም ለመዝገን መሮጥ አያዋጣም፡፡

ዘለቄታዊ ሰላም፣ ዴሞክራሲና ዕድገት የሚገኘው በመነጋገርና በመደራደር ብቻ ነው፡፡ ሰላማዊው የፖለቲካ ትግል ችግር ውስጥ የገባው ለመነጋገርና ለመደራደር የሚያስችል ዓውድ በመጥፋቱ ነው፡፡ በተጠራቀሙ ብሶቶች ሳቢያ ተቃውሞ ተቀስቅሶ ወደ ሁከት እየተቀየረ በርካታ ዜጎች ሞተዋል፡፡ ከፍተኛ የሆነ የአገር ሀብትም ወድሟል፡፡ ችግሮች ሲፈጠሩ ከሥር ከሥር ለመፍታት ባለመቻሉም ለሁለተኛ ጊዜ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጇል፡፡ አገር በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆና የሚያወላዳ ጊዜ ላይ ባንገኝም፣ ደግመን ደጋግመን ማሰብ የሚኖርብን ከዚህ አጣብቂኝ ውስጥ እንዴት መውጣት እንደሚቻል ነው፡፡ አሁንም ቀሪ እስረኞችን መፍታት ይገባል፡፡ ቅራኔዎችን ማርገብ ይጠቅማል፡፡ በሠለጠነ መንገድ ለመነጋገርና ለመደራደር አለመሞከር፣ ከድጡ ወደ ማጡ እንጂ የትም አያደርስም፡፡ ኢሕአዴግ በውስጡም ሆነ ከተፎካካሪዎቹ ጋር የሚያደርገው ግንኙነት ለዘቄታዊ ሰላምና መረጋጋት የሚረዳ መሆን አለበት፡፡ በሕመም ላይ ያለች አገር በቶሎ ፈውስ አግኝታ ማገገም ይገባታል እንጂ፣ ሌላ ዙር ሁከትና ትርምስ እያስተናገደች መቀጠል የለባትም፡፡ በመነጋገርና በመደራደር መጪውን ጊዜ ማሳመር ሲገባ በንትርክና በግትርነት ዘራፍ እያሉ የበለጠ ትርምስ መፍጠር የሚጎዳው ሕዝብንና አገርን ነው፡፡ አሁን ወቅቱ ከአገር በላይ ምንም እንደሌለ ማሳያ መሆን አለበት፡፡ አገር ከትርምስ የምታገኘው ነገር ቢኖር ውድመትን ነው፡፡ የሕዝብ ሰቆቃን ነው፡፡ ከዚህ ዓይነቱ ቅርቃር ውስጥ በፍጥነት መውጣት ያስፈልጋል፡፡ ኢሕአዴግ ከታሪክ ተጠያቂነት ማምለጥ የሚችለው ለዚህች አገር ውለታ በመዋል ነው፡፡ ይህ ውለታም የአገርን ህልውና በማስቀጠል ሕዝብን ማስደሰት ነው፡፡

ሌላው አሳሳቢ በቀጣዮቹ ስድስት ወራት ውስጥ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሊያጋጥም የሚችለው ጉዳይ ነው፡፡ እንደሚታወቀው በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ዴሞክራሲያዊና ፖለቲካ መብቶች ቢገደቡም፣ የሰብዓዊ መብቶች ጉዳይ ግን በእጅጉ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ መንግሥት በዚህ አዋጅ አማካይነት የተለጠጠ ሥልጣን ሲይዝ ከምንም ነገር በላይ በሕገ መንግሥቱ የሠፈሩ ሰብዓዊ መብቶችን ማክበር አለበት፡፡ በደህናው ጊዜም ሆነ በቀውስ ውስጥ፣ በሰላምም ሆነ በጦርነት ጊዜ የሚገዛንና የምንገዛው ለሕግ ብቻ መሆን ይኖርበታል፡፡ በአዋጁ አፈጻጸም ወቅት የሚወሰዱ ዕርምጃዎች ኢሰብዓዊ እንዳይሆኑ የመቆጣጠርና የመከታተል ኃላፊነት የመንግሥት ነው፡፡ ምንም እንኳ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የፀደቀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በፓርላማ መፅደቅ ቢኖርበትም፣ ለሕግ የበላይነት መገዛት ግን የመንግሥት ኃላፊነት መሆን አለበት፡፡ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁም ሥርም ሆነ በመደበኛው ጊዜ ለሕግ የበላይነት መገዛት የሚጠቅመው፣ ሥርዓት ያለው መንግሥታዊ ቅርፅ ለመፍጠርና ዴሞክራሲን ለመገንባት ነው፡፡

መንግሥት በተለመደው የሕግ ማስከበር ሥርዓት ለመቋቋም የማይቻልና በአገር ላይ ያንዣበበ አደጋ አጋጥሟል በማለት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሲያወጣና የአስቸኳይ ጊዜ ሥልጣኑ ሲጨምር፣ ዋናው ዓላማና ግብ መሆን ያለበት የአገርና የሕዝብ ዘላቂ ሰላምና ጥቅም ነው፡፡ ንግድና ኢንቨስትመንት፣ ቱሪዝምና የመሳሰሉት ዘርፎች ከሚያጋጥሟቸው ችግሮችና ከአገር ገጽታ በተጨማሪ፣ የሕዝብ ሰብዓዊ መብቶችና ፍላጎቶችም አፅንኦት ይፈልጋሉ፡፡ ሕዝብ መሠረታዊ የሆኑ ሰብዓዊ መብቶቹን የሚጎናፀፍበትና ዕለት ተዕለትም መብቶቹን የሚያጣጥምበት ጤናማ ምኅዳር መፈጠር አለበት፡፡ አደጋዎችን ከማስወገድ ጎን ለጎን ለሚያነሳቸው መሠረታዊ ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት ይገባል፡፡ በዚህ አስጨናቂ ጊዜም ከሰብዓዊ መብቶቹ በተጨማሪ የደኅንነቱ ጉዳይ ማሳሰብ ይኖርበታል፡፡ የሕግ አስከባሪ አካላትንና የፀጥታ ኃይሎችን ዕለታዊ እንቅስቃሴ ነቅቶ የመቆጣጠር ኃላፊነት የመንግሥት ነው፡፡ ለትርጉም የሚጋለጡና ለዘፈቀደ ዕርምጃ የሚያመቻቹ ክፍተቶች የበለጠ አደጋ እንዳይፈጥሩ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል፡፡  የአገር ህልውና አሳሳቢ በሆነበት በዚህ ጊዜ በችግር ላይ ችግር መደራረብ ራሱን የቻለ ቀውስ ነው፡፡ ለአገርም አይበጅም፡፡

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁም ውስጥ ተሁኖ የሕግ የበላይነት መቀጠል ይኖርበታል፡፡ የሕግ የበላይነት ሕገወጥ አሠራሮችን ለማስወገድና ፍትሕ ለማስፈን ይረዳል፡፡ የተጨናገፈውን የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ለማስቀጠል የሚያስችሉ ሕጋዊ ማዕቀፎችን ለመቅረፅ ይጠቅማል፡፡ ለሁከትና ለትርምስ በር የሚከፍቱ ኢዴሞክራሲያዊ ድርጊቶችን ያስወግዳል፡፡ ለአገር የሚበጁ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ውይይቶች፣ ክርክሮችና ድርድሮች የሚደረጉባቸው መድረኮች እንዲፈጠሩ ያግዛል፡፡ በመርህ የሚመሩ ዴሞክራቶች በነፃነት የሚነጋገሩበት የሐሳብ ገበያ እንዲኖር ዕድሉን ያመቻቻል፡፡ ‹‹የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው›› የሚባለው የደካሞችና የመርህ የለሾች ቅዥት ሳይሆን፣ በንድፈ ሐሳብና በተግባር የዳበረ ዕውቀት እንዲናኝ ያደርጋል፡፡ በደህናም ሆነ በክፉ ጊዜ ወቅቱን እያዩ እንደ ገበቴ ውኃ የሚዋልሉ ሳይሆኑ፣ የፖለቲካ ጨዋታው የገባቸው ልሂቃን የአደባባይ ሰዎች እንዲሆኑ ያደፋፍራል፡፡ በሕግ የበላይነት ሥር የምትመራ አገር መፍጠር የሚቻለው በዚህ መንገድ እንጂ በንፋስ አመጣሽ አስተሳሰብ አይደለም፡፡ ለዚህም ሲባል ለአገር በመርህ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ አሁን መቅደም ያለበት ኢትዮጵያን መታደግ ነው!

 

 

 

 

 

 

 

 

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

መንበሩ ካለመወረሱ በስተቀር መፈንቅለ ሲኖዶስ መደረጉን ቤተ ክህነት አስታወቀ

ቅዱስ ሲኖዶስ ከነገ ጀምሮ ውይይት እንደሚጀምር ተነገረ ‹‹እኛ ወታደርም ሆነ...

የአየር መንገድ ተጓዦች በሻንጣ የሚያስገቡትን የልብስና የጫማ ብዛት የሚገድብ ረቂቅ መመርያ ተዘጋጀ

ከቀረጥ ነፃ ይገቡ የነበሩ ዕቃዎች 87 በመቶ እንዲቀንሱ ተደርጓል መንገደኞች...

ግራ አጋቢው የኤሌክትሪክ መኪና ጉዳይ

በያዝነው ዓመት መጀመሪያ በወርኃ ጥቅምት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ 39...

ነባር ‹‹ላዳ›› ታክሲዎችን መሸጥና መለወጥን ጨምሮ ለሌላ ማስተላለፍ ተከለከለ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተለምዶ ‹‹ላዳ ታክሲ›› ተብለው የሚታወቁትን...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...

ብሔራዊ ባንክ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን ይፋ ሊያደርግ ነው

የፋይናንስ ዘርፉን ለማረጋጋት የሚረዳ ሪፎርም ማጠናቀቁን የገለጸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ግልጽነትና ተጠያቂነት የጎደለው አሠራር ለአገር አይበጅም!

ሰሞኑን የአሜሪካና የኢትዮጵያ መንግሥታት በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ተፈጽመዋል በተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና የጦር ወንጀሎች መግለጫ ላይ አልተግባቡም፡፡ አለመግባባታቸው የሚጠበቅ በመሆኑ ሊደንቅ አይገባም፡፡ ነገር ግን...

የምግብ ችግር ድህነቱን ይበልጥ እያባባሰው ነው!

በአገር ውስጥና በውጭ የተለያዩ ተቋማት የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ከ22 ሚሊዮን በላይ ዜጎች አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ያስፈልጋቸዋል፡፡ እነዚህ ወገኖች በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት፣...

መብትና ነፃነትን የሚጋፉ ድርጊቶች ይወገዱ!

ኢትዮጵያውያን በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል የመዘዋወር፣ የመኖር፣ የመሥራትና ሀብት የማፍራት ሕጋዊ መብት አላቸው፡፡ ይህ መብት በግልጽ የተደነገገው በሥራ ላይ ባለው ሕገ መንግሥት ሲሆን፣ አሁንም ሕገ...