Friday, March 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

​​​​​​​‹‹ሌላው ዓለም የቡናን ጥራት እንዴት መጠበቅ እንዳለበት ራሱን ሲያሻሽል እኛ ግን ቆመናል ››

አቶ አማን አድነው፣ የመታድ እርሻ ልማት ድርጅት ባለቤት

አቶ አማን አድነው ዋና መቀመጫውን አሜሪካ ባደረገው ዓለም አቀፍ የሎጂስቲክስ አቅራቢ ድርጅት በዲኤች ኤልና እዛው በሚገኘው በኖርዝ ዌስት አየር መንገድ በኃላፊነት ደረጃ የሠሩ ሲሆን፣ በተባበሩት መንግሥታት በኩል ተቀጥረው  በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ቺፍ ኦፕሬሽን ክፍል ኃላፊ  በመሆን ሠርተዋል፡፡ ኤአይቲ የሚባል የሙዚቃ አሳታሚ ድርጅትም ባለቤት ናቸው፡፡ መታድ የእርሻ ልማት ድርጅት ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል አንዱ የቡና ልማትና ንግድ ነው፡፡ በዚህ ዙሪያ ድርጅቱ የሚሠራውን እንዲሁም ጠቅላላ የአገሪቱ የቡና ምርትና ንግድ ምን እንደሚመስል ታምራት ጌታቸው አቶ አማን አድነውን አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የመታድ ምሥረታ እንዴት ይገለጻል?

አቶ አማን፡- መታድ በ2002 ዓ.ም. ነው የተቋቋመው፡፡ በሦስት ሚሊዮን ብር መነሻ ካፒታል ነበር የተቋቋመው፡፡ ለሥራው የሚሆነውን የመሬት ጥያቄ ምላሽ ያገኘው ከሦስት ዓመታት በኋላ ነበር፡፡ በወቅቱ የኢትዮጵያ ምርት ገበያን (ኢሲኤክስ) እያቋቋምኩ ስለነበር ይኼንን ደርቦ መሥራት አልቻልኩም፡፡ ስለዚህም የማቋቋም ሒደቱ እንዳለቀ ውጭ አገር ለአንድ ዓመት ቆየሁ፡፡ በኋላ መንግሥት ባደረገው ጥሪ መሠረት ወደ አገሬ ሙሉ በሙሉ ጠቅልዬ ተመለስኩ፡፡ በወቅቱ ያቀረብነው የመሬት ጥያቄም ተመልሶ ስለነበር በ2005 ዓ.ም. ቀጥታ ወደ ሥራው ገባን፡፡ ከዛ በፊት ግን ከኢሲኤክስ ቡና እየገዛሁ እሸጥ ነበር፡፡ በመቀጠል ከጉጂ ዞን ሀመበላ ወረዳ ባገኘነው መሬት ላይ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በምርምር የተገኙ ምርጥ የቡና ችግኞችን በማፍላት የአካባቢው ገበሬዎች በነፃ እየወሰዱ እንዲተክሉ አደረግን፡፡ ምክንያቱም ወረዳው ቡና አብቃይ አልነበረም ጎመንና በቆሎ ነበር በብዛት የሚመረትበት፡፡ ሌላው በአጎራባች ያሉ ቡና አብቃይ የነበሩ ዞኖች ያረጁ ቡናዎችን በአዲስ እንዲተኩ በማድረግ ለአካባቢው ማኅበረሰብም ምርጥ ቡና ምን ዓይነት ነው የሚለውን አስተማርን፡፡ እኛም ጎን ለጎን በተሰጠን መሬት ላይ ማምረት ጀመርን በዚህ መልኩ ነው ሥራ የጀመርነው፡፡

ሪፖርተር፡- ቡና ለእርስዎ ምንድነው?

አቶ አማን፡- ቡና በጣም ነው የምወደው፡፡ ገንዘብ ስለሚገኝበት አይደለም፣ እሱ በኋላ የመጣ ነው፡፡ ቤተሰቦቼ በሐዋሳ ዙሪያ በዋናነት ደግሞ በሐረር ዙሪያ ሰፋፊ የቡና እርሻዎች ነበራቸው፡፡ ልጅ ሆነን ለእረፍት ወደ እርሻዎቹ ስንሄድ ደስ ይለኝ ነበር፡፡ ብዙ ሰዎች ይመጣሉ ይወያያሉ በቃ ወሬው ሁሉ ቡና ነው፡፡ በአፍሪካ የመጀመሪያዋ ሴት ፓይለት የነበረችው ሴት አያቴም በሄደችበት አገር ሁሉ ይኼንን ምርት ታስተዋውቅ ነበር፡፡ ይኼን ሁሉ እየተመለከትኩ ስላደግኩ ፍቅሩ አደረብኝ፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የሰብል አመራረትና ንግዱ የተዛባ በመሆኑ አንዱ ምግብ ተርፎ ይደፋል፤ ሌላው ጋ የሚበላው አጥቶ ይራባል፡፡ ይህን ለማስተካከልና ለማዘመን ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ለማቋቋም ለታሰበው የምርት ገበያ ኢሲኤክስ ድርጅት ቺፍ ኦፕሬተር ኦፊሰር በመሆን ከአሜሪካ መጣሁ፡፡ እዚህ ስደርስ ደግሞ መንግሥት ሥራው የቡና እንዲሆን በመፈለጉ በዚሁ ምክንያት ኢትዮጵያ ውስጥ ቡና አብቃይ አካባቢዎችን ሁሉ የመጎብኘት ዕድሉ ገጠመኝ፡፡ እግረ መንገዱንም የኢትዮጵያ ቡና አመራረት አነጋገድ ላይ የነበሩ ክፍተቶችን ለማየት ቻልኩ፡፡ እነዚህ ክፍተቶች ደግሞ በጣም በቀላሉ በመሙላት አሁን ካለው የተሻለ ገንዘብ ማምጣት እንደሚቻል ስለተረዳሁ ሥራውን የበለጠ እንድወደውና እንድገባበት አድርጎኛል፡፡

ሪፖርተር፡- ቡና እና ኢትዮጵያን መለያየት አስቸጋሪ ነው፡፡ እስካሁን ግን በዓለም ላይ በዚህ ዘርፍ ተፅዕኖ ፈጣሪ መሆን አልተቻለም፡፡ ችግሩ ምን ይመስልዎታል?

አቶ አማን፡- በዓለም ላይ እንደ ኢትዮጵያ ቡና ተፈላጊ የለም፡፡ አሁን የገቡትን ጨምሮ በተለይ ሐረር፣ ይርጋ ጨፌና ሲዳማ የኢትዮጵያ ቡና መለያ በመሆን በዓለም ገበያ ይሸጣሉ፡፡ ግን እነዚህ ስም ብቻ ሆነው ነው ያሉት፡፡ ሌላው ዓለም የቡናን ጥራት እንዴት መጠበቅ እንዳለበት ራሱን ሲያሻሽል እኛ ግን ራሳችንን ዘግተናል፡፡ ቡናችን በጣም ተፈላጊ በመሆኑ በሥራው ላይ የተሰማሩ በሙሉ መሸጡ አይቀርም በሚል እርሻውንና ንግዱን ከማስፋት ተቆጥቧል፡፡ ቡና ደረጃው ይጠበቅ ሲባል ከምርጥ ችግኝ ጀምሮ በሲኒ እስከሚጠጣው ሰው ድረስ ያለውን የጥራት ሁኔታ ማለት ነው፡፡ ሸጠህ የምትገላገለው አይደለም፡፡ ይኼ ደግሞ ከፍተኛ ወጪ ይጠይቃል፡፡ ይኼንን ሽሽት ጥራቱን የመጠበቅ ፍላጎት አነስተኛ ነው፡፡ ሌላው ገበያው በተወሰኑ ማኅበሮችና ግለሰቦች ተይዞ የቆየ ነው፡፡ ገዢዎችም በዚሁ መጠን ውስን ናቸው፡፡ ቬትናም በዓለም ሁለተኛ የቡና ላኪ አገር ነች፡፡ ቡና ማምረት የጀመረችው ግን ከኢትዮጵያ በሄዱ የቡና ልማት አሠልጣኞች ነው፡፡ ጣዕሙ ከኢትዮጵያ ጋር ምንም አይገናኝም፡፡ ቬትናሞች በአንድ ጊዜ የመንግሥትና የግል ግዙፍ እርሻዎች አቋቁመው ጥብቅ የጥራት ቁጥጥር ሥርዓት በመዘርጋት የራሳቸውን መለያ በመያዝ ወደ ገበያው ሰብረው መግባት ችለዋል፡፡ እኛ ግን እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ከዓለም ገበያ እየወጣን ከኬንያ ባነሰ ዋጋ ለመሸጥ ተገደን ነበር፡፡ በቡና ላይ ተከታታይ ሥራ ባለመሥራታችን ስማችን ብቻ ነበር እየተሸጠ የነበረው፡፡ ኢሲኤክስ ከተቋቋመ በኋላ ነው ልዩ ቡና በሚል አንድ የቡና ምርት ከየትኛው የኢትዮጵያ ክፍል መገኘቱን እስከ ገበሬው ድረስ የምርቱን ዱካ ተደራሽ በማድረግ፣ ጥብቅ የጥራት ደረጃ ማውጣትና ቁጥጥር ማድረግ የተቻለው፡፡ በዚህም ገበሬው ራሱ ቡናን እንዴት አዘጋጅቶ ማቅረብ እንዳለበት አውቆ እየሠራ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ቡና ከዚህ በኋላ ተስፋ አለው ማለት እንችላለን?

አቶ አማን፡- በቅርቡ ያየሁት አንድ ጥናት እንደሚያመላክተው ቡና ከ20 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ኢትዮጵያውያን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መተዳደሪያ ነው፡፡ ቡናን ብናቆም የእነዚህን ሰዎች ገቢ መተዳደሪያ በምን ልንተካው ነው፡፡ ወደድንም ጠላንም ቡና ነው ዶላር እያመጣ ያለው፡፡ ቡና በደርግ ሥርዓት ጥሩ ቁጥጥርና እንቅስቃሴ ነበረው፡፡  በቅርቡ ግን ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ራሱን ችሎ ከተቋቋመ በኋላ ባለሥልጣኑም ትክክለኛ የቡና ተዋናዮችን በመለየት እየተመካከረ እየሠራ በመሆኑ በርካታ ተስፋ ሰጪ ለውጦች መታየት ጀምረዋል፡፡ በተለይ ይኼ ዓመት ትልቅ ማሳያ ይሆናል ብለን እንጠብቃለን፡፡ ሌላው አሁን እየተሠራ ያለው የውጭ ንግዱ ላይ ነው፡፡ የአገር ውስጥም ገበያ መታየት አለበት ትልቁ ነገር ግን ተስፋው ቀጣይነት እንዲኖረው ከታች ጀምሮ መሻሻልን ማምጣት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- መታድ ምን አዲስ ነገር ይዞ መጣ? በየትኞቹ አካባቢዎች ይሠራል?

አቶ አማን፡- መታድ የዛሬ 40 እና 30 ዓመት ሲሠሩ ከነበሩት ድርጅቶች በተለየ በአራት ዓመት ጊዜ ውስጥ ብቻ ገበያ ላይ መግባት መቻላችን አዲስ ነገር ይዘን እንደመጣን አንዱ ማስያ ነው፡፡ ሌላው እኛ ወደ ሥራ ከመግባታችን በፊት የራሳችንን ጥናት ሠርተንና ምርምሮችን አድርገን ነው፡፡ በጥናትና ምርምሩ የተገኙ ችግሮች በቀላል የሚፈቱ ሆነው ነበር ያገኘናቸው፡፡ ለምሳሌ ገዢው በሚፈልገው ጥራትና መጠን፣ በጊዜ አለማቅረብና ቃል አለመጠበቅ አንዱ ትልቅ ችግር ነበር፡፡ ሌላው ትልቅ ሥራ የሠራነው ቀዳሚ የሆነ የቡና ላብራቶሪ ማቋቋም ነው፡፡ እኛ የምንልከው ቡና የጉጂ ከሆነ የትም ዓለም ላይ ቢሸጥ የጉጂ ቡና ነው፡፡ ገዢዎች የምርቱን ዱካ ተከትለው ቢመጡ እንኳን ትክክለኛውን መነሻ ቦታ ማግኘት ይችላሉ፡፡ ከኛ ጋር የሚሠሩ ከአምስት ሺሕ በላይ ገበሬዎች አሉ፡፡ ለእነሱ ሥልጠና በመስጠት ጥሩ ቡና እንዲያቀርቡ ዕገዛ እናደርጋለን፡፡ ለኅብረተሰቡም ትምህርት ቤት በመገንባት ትምህርት እንዲያገኙ እናደርጋለን፡፡ ከዚህ በተጨማሪም እስከ ዩኒቨርሲቲ ድረስ ልከን እናስተምራቸዋለን፡፡ በፊት በብድር ቡናቸውን አስይዘው ይበደሩ የነበረውን ለማስቀረት ችለናል፡፡ በአጠቃላይ በጥናቱ የተገኙትን ችግሮች በመቅረፍ አዳዲስ ቡና አብቃይ ቦታዎችን በመጨመርና በአዲስ ስም ከቡናዋ ፍሬ ጀምሮ ለሚጠጣው ሰው እስከሚቀርብለት ድረስ ያለውን ሒደት ዓለም አቀፍ ሥርዓት እንዲከተል በማድረግ ቶሎ ገበያውን ለመቀላቀል ችለናል፡፡ አሁን እየሠራን ያለነው በኦሮሚያ ክልል በጉጂ ዞን ሀመበላ ወረዳ እንደዚሁም በደቡብ ክልል ገደብ ጌዶ ዞን ውስጥ ሲሆን፣ በዓመት ከ35 እስከ 40 ኮንቴይነር ቡና ለዓለም ገበያ እንልካለን፡፡

ሪፖርተር፡- መታድ ያለበት ችግር ምንድነው?

አቶ አማን፡- አንደኛ የምናቀርባቸው የኢንቨስትመንት ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ አያገኙም፡፡ ጥያቄዎቻችን ምላሽ ሳያገኙ እስከ ሦስት ዓመታት ድረስ ይወስዳሉ፡፡ ሌላው ያለብን ከባድ የመንገድ ችግር ነው፡፡ በአካባቢው ያለው መንገድ እንደ አገርም ትልቁ ትኩረት ተሰጥቶት ቶሎ ማለቅ የነበረበት ነበር፡፡ እኛንም ዋጋ እያስከፈለን ነው ያለው፡፡

ሪፖርተር፡- ባለቤትዎ አስቴር አወቀ ማነች ቢባል ዓለም ያውቃታል፤ በዚህ ሥራ ያላት ድርሻ ምንድነው?

አቶ አማን፡- የመጀመሪያ ድርሻዋ ካቡ ካፌን በመክፈት የምናመርተውን ቡናችንን ለኅብረተሰቡ ማቅመስና ማስተዋዋቅ ነበር፡፡ ካፌው በቅርቡ የተዘጋ ቢሆንም ያው እሷ በምትታወቅበት ድምጿ የቡና ዕድገትና ልማት ላይ ተፅዕኖ መፍጠር የሚችል እንደ ‹‹የኢኮኖሚ ዋልታ ቡና ቡና›› ያለ መዝሙር በመሥራት ላይ ትገኛለች፡፡ በአብዛኛው በዚህ ሥራ ያላት ተሳትፎ ማስተዋወቅ ላይ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ቡና ንግድ ዛሬም መንግሥትንና ላኪን ላኪንና ገዢን ያጨቃጭቃል ምንድነው ችግሩ?

አቶ አማን፡- የቡና ንግድ አሁንም ችግር እንዳለበት እኔም ነጋዴ ሆኜ እያየሁት ነው፡፡ የቡና ንግድ እንደሌላው ንግድ አይደለም፤ የትስስር ንግድ ነው፡፡ በትስስሩ ወቅት አንዱ ከሌለ ወይም ከተዛነፈ ሙሉ ትስስሩ ጤናማ አይሆንም፡፡ ችግሩ የዚያ ወይም የዚህ ነው ሊባል አይችልም፡፡ ሁሉም በቅንነትና በታማኝነት መሥራት አለባቸው፡፡ ሌላው እኛ ኢሲኤክስን አቋቁመን ስንወጣ የቅሬታ መጠኑ ከ0.4 በመቶ በታች እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ ድርጅቱ ካወጣው የጥራት ደረጃ በታች ያቀረቡ ካሉ በቀጥታ ነበር የምናባርረው፡፡ በቡና ገበያ ወቅት ኢስኤክስ በርካታ ግብይቶችን ነበር የሚያካሄደው በዚህም የአንዱ ቡና ከአንዱ እንዳይሳሳት እያንዳንዱ ኮሪደር ላይ ሰው በመመደብ ነበር የምንረከበው፡፡ ምክንያቱም በስህተት አንድ ጥራት የሌለው ቡና ቢቀመጥ ትልቅ ችግር ነው የሚፈጠረው፡፡ በዚህ ደረጃ በጥንቃቄ እየሠራን ነበር፡፡ ዛሬ እኔ እንደ ነጋዴ ሆኜ ስሄድ ከአንዳንድ መስተካከል ካለባቸው ጉዳዮች በስተቀር በሙሉ አቅሙ እየሠራ መሆኑን አይቻለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- መታድ ወደ ፊት ምን ያስባል? ኪሳራ ያሰጋዋል?

አቶ አማን፡- መታድ በጥናት ነው የተቋቋመው፤ እኔም ከ26 ዓመታት በኋላ በመንግሥት ጥሪ ስመለስ በምርጫና በፍላጎት ነው እየሠራሁ ያለሁት፡፡ የምንሠራውም ከተራው ገበሬ ተነስተን ዓለም ገበያ ድረስ በመሆኑ ሁሌ ክስረትን ለመከላከል አማራጭ ሐሳብ (ፕላን ቢ) አዘጋጅተን ነው የምንጠብቀው፡፡ ለቆ የመውጣቱ ጉዳይ የሚታሰብም አይደለም፡፡ እንደውም በቅርቡ ለገጣፎ አካባቢ በተረከብነው መሬት ላይ ቡናን በጥሬው፣ ቆልቶ፣ ለአንድ ዙር ብቻ የሚያገለግል ተፈልቶ የታሸገ ቡና ለዓለም ገበያ ለማቅረብ ዝግጅታችንን ጨርሰናል፡፡ ጎን ለጎንም ወደፊት በቅመማ ቅመሞች ሥራ ላይ መሳተፍ እንፈልጋለን፡፡

ሪፖርተር፡- በቅርቡ አሜሪካ ያወጣችው ሕግ የቡና ባለቤትነቱ በቆየው እንዲሆን የሚል ነው፡፡ ይህ በኛ ላይ የሚያመጣው ተፅዕኖ ምንድነው

አቶ አማን፡- በመጀመርያ ሕጉ የሚያስኬድ አይደለም፡፡ አሜሪካ በብዛት ስለምትቆላ ከአፍሪካም፣ ከእስያም የሄደው ቡና ‹‹የኔ ነው›› ለማለት እንዲመቻት ነው፡፡ ይኼ ደግሞ የሚያስኬድ አይደለም፡፡ በግድ ይተግበር ከተባለ ደግሞ ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን የዓለም የቡና ንግድ ሥርዓት ጭምር ያዛባዋል፡፡ ከባድ ጣጣ ነው የሚያመጣው፡፡ ዘንድሮ በአሜሪካ በተካሄደው የምግብና መጠጥ ውድድር ከተለያዩ አገሮች የተወጣጡ 257 ቡና ላኪዎች የተሳተፉት በቆይዎቻቸው በኩል ነበር፡፡ ይኼ ሁሉ የኔ ይሁን እንደማለት ነው፡፡ ችግሩ ግን የኢትዮጵያ ብቻ አይሆንም፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያም በዚህ ውድድር አሸናፊ እንደሆነች ተሰምቷል፡፡ ውድድሩን ስንተኛ ደረጃ ይዛ አሸነፈች?

አቶ አማን፡ውድድሩ በየዓመቱ የሚዘጋጅ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ በቋሚነት ትሳተፋለች፡፡ ዘንድሮ በውጭ ከተሳተፉ ከ2,057 በላይ ተወዳዳሪዎች 27ቱ ለዋንጫ አልፈዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል 25ቱ የኢትዮጵያ ናቸው፡፡ ከ25ቱ ደግሞ 11 የሚሆኑት መታድ ያቀረባቸው ቡናዎች ነበሩ፡፡

 

 

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

አሜሪካ ሕወሓትን በማሳመንና በመጫን በሰላም ሒደቱ ትልቅ ሚና መጫወቷን የኢትዮጵያ ዋና ተደራዳሪ አስታወቁ

የተመድና የአውሮፓ ኅብረት አበርክቶ አሉታዊ እንደነበር ጠቁመዋል በመንግሥትና በሕወሓት መካከል...

ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ የሚጓዙ በርካታ ሰዎች ወደ ከተማዋ እንዳይገቡ በፖሊስ መከልከላቸውን ገለጹ

‹‹የኦሮሚያ ክልል መፍትሔ እንዲሰጥበት አሳውቀናል›› የአማራ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ‹‹ጉዳዩ...

መንግሥት በግማሽ ዓመት 100 ቢሊዮን ብር ያህል ቀጥታ ብድር መውሰዱ ታወቀ

የአገር ውስጥ ብድር ከ1.6 ትሪሊዮን ብር በላይ ሆኗል የብሔራዊ ባንክ...

ቡና ባንክ ዓመታዊ ትርፉን ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ማሻገር ቻለ

ቡና ባንክ በ2014 የሒሳብ ዓመት ዓመታዊ የትርፍ ምጣኔውን ለመጀመርያ...