Thursday, April 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዝንቅክብር ከደቡብ አፍሪካ ለደራርቱ ቱሉ

ክብር ከደቡብ አፍሪካ ለደራርቱ ቱሉ

ቀን:

በኢትዮጵያም ሆነ በጥቁር አፍሪካ ኦሊምፒክ ታሪክ ሁለት ወርቅ ሜዳሊያ ያገኘችው ደራርቱ ቱሉ ባለፈው ሳምንት ከደቡብ አፍሪካው ዌስተርን ኬፕታውን ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ተቀበለች፡፡ ከኦሊምፒክ በተጨማሪ በዓለም ሻምፒዮንም ሆነ በተለያዩ አህጉርና ዓለም አቀፍ ውድድሮች ቁንጮ በመሆን ታላቅነቷን ማስመስከሯ ይታወሳል፡፡ ደራርቱ ለመጀመርያ ጊዜ በባርሲሎና ኦሊምፒክ (1984 ዓ.ም.) በ10,000 ሜትር ተወዳድራ የወርቅ ሜዳልያውን ያገኘችው የቅርብ ተፎካካሪዋንና የዓለም አቀፍ ውድድሮች ልምድ የነበራትን ደቡብ አፍሪካዊቷን ኤሌና ሜየርን በረዥም ርቀት ጥላት በማሸነፍ ነበር፡፡ ፎቶግራፉ ደራርቱ የክብር ዶክትሬቷን ከተቀበለች በኋላ ከዩኒቨርሲቲው ምክትል ፕሬዚዳንት ሐኔኮም (በግራ) እና ከዩኒቨርሲቲው ሬክተር ፕሮፌሰር ብሪያን አ ኮኔል ጋር ሆና ያሳያል፡፡ ሁለተኛው ፎቶ በባርሴሎና ኦሊምፒክ 10000 ሜትር ሩጫ ተከታትለው የገቡት ደራርቱ ቱሉና ኤሌና ሜየር ከድላቸው በኋላ ለተመልካቹ ደስታቸውን ሲገልጹ ያሳያል፡፡

*********

              ቤቴ

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ልቤ ቤት ሠርቶልኝ

ደም ቧምቧው አጠገብ

ቁልቁል ሲለኝ ቁልቁል

ሽቅብ ሲለኝ ሽቅብ፡፡

ሲዞ…ር እዞራለሁ

ልቤ መኖሪያዬ ከሱ እታገላለሁ፡፡

ቢሆንም

ከዚህኛው ቤቴ ይሻላል የልቤ

አድሺኝ አይለኝ አዲስ ነው ሃሳቤ፡፡

አልወዳደርም ከሌላው ቤት ጋራ

በእንጨት በብነበረድ በጡብ ከተሠራ፡፡

ቢመሽ አያስጠጉኝ

ብጠፋ አይፈልጉኝ

ሁሉ በሩን ዘግቶ ይተረካከማል

ኑሮውን በምላጭ ይከረካክማል

ሊያስወጣ ሊያስገባ ይወጣል ይገባል፡፡

እኔ ብዙም የለኝ ከዚህኛው ቤቴ

እንዳሻው ያድርገኝ ልቤ ጎረቤቴ፡፡

  • ፊርማዬ ዓለሙ (07/04/89)

 

************

አሸናፊው ማነው?

ከተለያዩ ከተሞች የመጡ ሰዎች ስለየከተማቸው ውበት ሲወያዩ ይቆዩና፣ ‹‹የትኛዋ ከተማ ይበልጥ ቆንጆ ነች›› በሚለው ጥያቄ ላይ ግን መጨቃጨቅ ይጀምራሉ፡፡ ይሁንና ስምምነት መድረስ ስላልቻሉ ከጥቂት ቀናት በኋላ ሁሉም የየከተማቸውን ልዕልና እንዲያስረግጡ ይወሰንና ይለያያሉ፡፡

የሃስኛው ተወላጅ የአንድ ሙሉ በግ አሮስቶ፣ የያምቦሌው ሰው ወፍራም ሾርባ፣ የቦርጋሱ ተወላጅ የተጠበሰ ዓሣ፣ የጎርና አር የሆሺስታው ቋሊማ፣ የቶልቡክኑ ትኩስ ዳ፣ የፕሎቩዲቡ ፍራፍሬ፣ የሶፍያው የተጠበሰች ዶሮ፣ የካርሎቮው የተቆላ ኦቾሎኒ፣ የትሮያ ብራንዲ፣ የአቤኖቩግራዱ የወይን ጠጅ፣ የራዝግራዱ እርጎ ሲያመጡ፣ ጋብሮቫዊው ግን ወንድሙን ይዞ መጣ፤ እንዲያባላቸው!

አረፈ ዓይኔ ሐጎስ ‹‹ቀልዶች ከጋብሮቮ ምድር›› (1979)

********

ራስ ሴላሥ

በሔድኩበት አገር ሁሉ የትምህርት መጨረሻ ቅኔ ሆኖ አገኘሁት፡፡ ለቅኔም የተሰጠው ክብር ሰው ለመላእክት ከሚሰጠው ክብር የተቃረበ ነበር፡፡ ቢሆንም የሚበዙት አገሮች ዘንድ ያለፉት ባለቅኔዎች የተሻሉ ናቸው መባሉ ይገርመኛል፡፡ ምክንያቱም ምናልባት ሌላው ሁሉ ዕውቀት በጊዜ ብዛት የሚገን ሆኖ ቅኔ ግን ወዲያውኑ ባንድ ጊዜ የማይገኝ ዕውቀትን ስለሆነ ይሆናል፡፡ ምናልባትም የሕዝቦች ሁሉ ቅኔ ግን ወዲያውኑ ባንድ ጊዜ የማይገኝ ዕውቀት ስለሆነ ይሆናል፡፡ ምናልባትም ደግሞ ቅኔ ፍጥረትንና ፍላጎትን የሚዘረዝር ስለሆነ /እነዚህም ሁለቱ አንድ ናቸው/ የመጀመርያዎቹ ባለቅኔዎች የሚያስደንቀው ነገር ሁሉ በዝርዝርና በሙሉ ስለተቀኙበት ያንኑ እየተለዋወጡና እያቀላቀሉ ከመቀኘት በስተቀር ለተከታዮቻቸው ምንም አዲስ ነገር ስላልተወላቸው ይሆናል፡፡ ምክንያቱም ማናቸውም ቢሆን ጥንታውያን ጸሐፊዎች ፍጥረትን መያዛቸውና ተከታዮቻቸው ደግሞ ማሳመርን መያዛቸው ይታያል፡፡ ጥንታውያን ጸሐፊዎች በቅኔአቸው ጉልህና አዲስነት፤ ተከታዮቻቸው ደግሞ በቅኔአቸው ማማርና መለዘብ ያይላሉ፡፡

እኔም ከዚህ ታላቅ ማኅበር ውስጥ ስሜን ለመቀላቀል ፈልጌ የፋርስንና የአረብን ቅኔ አጠናሁ፡፡ በመካ መስጊድ ተስቅለው ከሚገኙት መጻሕፍት ውስጥ በቃሌ ልጠቅስ እችል ነበር፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግን ማንም ሰው ሌላውን በመምሰል ትልቅ ሊሆን እንደማይችል ተረዳሁ፡፡ የሊቅነት ምኞቴም ሐሳቤን ወደ ፍጥረትና ወደ ሕይወት እንድመልስ አስገደደኝ፡፡ ፍጥረትን የቅኔ መሠረት፤ ሰውን የቅኔ ሰሚ ለማድረግ ቆረጥሁ፡፡ ያላየሁትን ለመዘርዘር አልችልም፤ ተስፋቸውን ሐሳባቸውን ለይቼ ያላወቅኋቸውን ሰዎች ደስ በሚያሰኝና በሚያስፈራራ ነገር ልባቸውን ለመንካት አልችልም፡፡››

ባለቅኔ ለመሆን ስለቆረጥሁ፣ ለሐሳቤ ሁሉ አዲስ ማደፋፈርያ አገኘሁ፤ ሐሳቤም የሚመለከተው ሁሉ በድንገት ሰፊ ሆነ፡፡ ማናቸውም ዕውቀት የማይናቅ ሆኖ ታየኝ ለምሳሌና ለማስረጃ እንዲሆነኝ ተራራንና አሸዋማ በረሃን የዘፈን ዓይነቶችና በየሸለቆውም የሚገኘውን አበባ በሐሳቤ ውስጥ አገባሁ፡፡ ለቅኔ እንዲሆነንም የየተራራውን አራዳ፣ የቤተ መንግሥቱን ሰቀላ በሐሳቤ ዓይን በጥንቃቄ ተመለከትኩ፡፡ አንዳንድ ጊዜ አንዳች አቃቂ ሲፈስ የሚከተለውን መንገድ እመለከታለሁ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በበጋ ወራት ደመና በሰማይ ላይ ሲጓዝ እመለከታለሁ፡፡ ስለቅኔ ይህ አይረባም የሚባል ነገር የለም፡፡ የሚያምረውም የሚያስቀይመውም  ሁሉ ለሐሳቡ የተገለጸ እንዲሆን ያስፈልጋል፡፡ ትልቅ በመሆኑ የሚያስገርመውንና ትንሽ በመሆኑ የሚያምረው ሁሉ ማወቅ አለበት፡፡ የምድረ አትክልትና አበባ ዕፅ ሁሉ የደን ህዋሳትና የሰማይ ከዋክብት ሁሉ ልዩ ልዩ ሐሳብ እንዲያሳድሩበት ያስፈልጋል፡፡ የሃይማኖትንና የህሊናን ነገር አጥብቆ ወይም አሳምሮ ለማስረዳት ማናቸውም ዓይነት ሐሳብ ይጠቅማል፡፡ ስለዚህ ብዙ ነገር የሚያውቅ ሰው የቅኔውን መሠረት በማስፋፋትና ያልታሰበ ጠቃሚ ሐሳብ በመግለጽ ያልታሰበ ምሳሌም በማምጣት አንባቢዎችን ደስ ለማሰኘት ይቻላል፡፡

ስለዚህ የፍጥረትን መለዋወጥ በጥንቃቄ ተመለከትኩ፤ የጎበኘሁትም አገር ሁሉ ለቅኔዬ ውብነት ረዳት ሆነብኝ፡፡

የባለቅኔ ሥራ ጠቅላላውን እንጂ ዝርዝርን መመርመር አይደለም፡፡ መሠረታዊውንና ጉልሁን ይመለከታል እንጂ በቅጠል ላይ ያለውን መስመር አይቆጥርም፤ በደን ውስጥ ካሉት ዞኖች ውስጥ የያንዳንዳቸውን የቀለም ደማቅነት መለየት የለበትም፡፡ የፍጥረትን ዋና ዋናውን ምልክትና የሚያስደንቀውን ክፍል ዘርዝሮ፤ አንባቢን ሰሚ ሁሉ እንዲገልጽ የተፈለገው ነገር ምን እንደሆነ ለመረዳት እንዲችል ማድረግ አለበት፡፡ ስለዚህ ምናልባት ለአንዳንድ ሰው የሚያመልጠውን ለአንዳንዱ ደግሞ የሚታየውን ትንንሹን ዝርዝር ትቶ፤ ተመልካች ቀርቶ ችላ ባዩ እንኳን ሊያየው የሚችለው ነገር መምጣት አለበት፡፡

ሲራክ ኅሩይ ‹‹የራስ ሴላሥ መስፍነ ኢትዮጵያ ታሪክ›› (1957 ዓ.ም.)

*********

ከእኔ ለእናንተ

ወሲብ ጥበብ ነው – ታላቅ ኃይል፡፡ ሰውም ታላቅ ጥበብ ነው፡፡ ታዲያ በተፈጥሮ ሁላችንም ይህን ጥበብ ገና ስንፈጠር ተቸረነዋል፡፡ በግብር ለማዋል ስንነሣ ተሰጥኦአችንን እንተረጉመዋለን፡፡ ኃይሉ ምን ያህል ከባድ እንደሆነም የምንረዳው በፍቅር – በግብረገብነት በሌሎች ሕይወት ውሰጥ አስርጸነው ነፋሪቱ እነሱን ለውጦ እነሱም እኛን ሲለውጡ ነው፡፡ የሰጠነው ኃይል ሳይባክን ሲመለስ፡፡ ኃይሉ ከባከነ ሕይወት ትናወጣለች – ትናጣለች፡፡ መንፈስም ሕብረ – ሚዛን ያጣል፡፡ ሕግም ይዛባል፡፡ ይህ ሲሆን ኃየሉን ማንነታችንን ለመፈተሽ ወደ እራሳችን ውስጥ ማስረጽ ይገባል፡፡ በእዚህም ጊዜ ቋጠሮው ይገኛል፡፡ መፍታታም አዳጋች አይሆንም፡፡

ሕይወት እንደገና ታንሰራራ፡፡ የሙዚቃ መሣሪያዋንም ታንሣ፡፡ ቅኝቷንም ትግፋበት፡፡ ዝማሬዋ ይሰማ፡፡ ይህ ሲሆን የሰጠችው ምስጢር ተተርጉሟል፡፡ የዘራችው አጎንቁሏል፡፡ መከርንም ይናፍቃል፡፡

ቅኝቱ ከተዛባ ሙዚቃው ከተሳከረ ሕይወት ትርጉም ያጣል፡፡ ቅሬውም ይወይባል፡፡ ቃናውም ይማልጋል -ምቱ፡፡ ፍቅር ይናኝ ይሰጥ ገኖ፡፡ ፈጽሞ አይቀርም ባክኖ- ኳትኖ፡፡ እሱም በእሷ እሷም በእሱ ይሰርጻሉ፡፡ እኔነትን በማስቀረት በአንድነት ይነግሣሉ፡፡ በመግባባት ይከንፋሉ – ያርጋሉ፡፡ ወሲብ ፍቅር – ፍቅርም ወሲብ ነው ይላሉ፡፡ ልዩ ጸጋን ተጎናጽፈው አንዱ የሌላው እስትንፋስ እና ሕይወት ሆነው በፍጹምነት እኔነትን ድል ነስተው፡፡ የምድርን ሁሉ በሽታ – ዝገት ፍቀው . . . ይኖራሉ አዲስ የህሊና ዓለም አዋቅረው . . . እኔነትን ሰርዘው . . .

  • አሸናፊ ዘድባብ ‹‹ፍቅር እና ወሲብ ለማወቅ የሚሹት መጠየቅ የሚያፍሩት›› (1992)
spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...