Thursday, April 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልቋንቋ የወሰናቸው ቀልዶች

ቋንቋ የወሰናቸው ቀልዶች

ቀን:

የኔቢጤው ‹‹ስለኪዳነ ምሕረት›› እያለ ይለምናል፡፡ በአጠገቡ የሚተላለፉ ሰዎች ይመጸውቱታል፡፡ ወዲያው አለማመኑ ይቀይራል፡፡ ‹‹ስለ ተክለሃይማኖት›› ማለት ጀመረ፡፡ አላፊ አግዳሚው ግራ ገብቶት ‹‹ዕለቱ ኪዳነ ምሕረት አይደል እንዴ?›› ብሎ ይጠይቃል፡፡ የኔቢጤው ‹‹በፈረንጅ ተክለ ሃይማኖት ነው፤›› ብሎ ይመልስላቸዋል፡፡ ለካ በአጠገቡ ፀጉረ ልውጥ እያለፈ ኖሯል፡፡ ይህም የየኔቢጤው ልዩ አለማመን ዘዬ ነበር፡፡ ይህ ከቀልድ የተቀነጨበ ሲሆን፣ ገንዘብ ሳይቸገሩ በልመና የተሰማሩ ሰዎችን ምግባር በመተቸት ይቀጥላል፡፡   

ኮሜዲያኑ ሐፍቱ ገብረጻድቅ የተወለደው መቐለ ነው፡፡ ሐፍቱ ከልጅነቱ ጀምሮ በተገኘባቸው ቦታዎች ቀለል ያለ ስሜት እንደሚፈጥር ሰዎች ይነግሩታል፡፡ ጨዋታ አዋቂ እየተባለ መድረክ የመምራት ሚናም ይሰጠዋል፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪ ሳለ በክፍለ ጊዜዎች መካከል በሚኖር ክፍተት ‹‹ሐፍቱ እስኪ አንድ ነገር አቅርብልን፤›› ይባል እንደነበር ያስታውሳል፡፡ ዛሬ ለደረሰበት ደረጃ መሠረቱ የትምህርት ቤት ተሞክሮው እንደሆነ የሚናገረው ሐፍቱ ‹‹የመምህሮቼ ውጤት ነኝ፤›› ይላል፡፡ ለመድረክ የበቁ ብዙ ባይሆኑም የመቐለ ሕዝብ ጨዋታ አዋቂ ነው ይላል፡፡ የሕዝቡ አኗኗር ድባብ ኮሜዲያን ለመሆኑ አስተዋጽኦ እንዳለውም ያምናል፡፡

ኮሜዲያንነትን በትግርኛ እውቅና አግኝቶ እንደ ሙያ ከያዘው ዘጠኝ ዓመታት አስቆጥሯል፡፡ ጐን ለጐን ቧንቧ ጥገና ይሠራል፡፡ ስድስተኛ ደረጃ ኮንትራክተርም ነው፡፡ በትግርኛ ተናጋሪዎች ዘንድ በይበልጥ ይታወቃል፡፡ በትግርኛ የቴሌቪዥን መርሐ ግብሮች፣ አሸንዳን በመሰሉ ዓመታዊ ክብረ በዓሎች ላይና በልዩ ልዩ መድረኮች ቀርቧል፡፡ በዩቲዩብ የተለቀቁ ቀልዶቹ በርካታ ተመልካች አግኝተዋል፡፡ በኢትዮጵያ ሚሊኒየም በቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ ሜዳልያ ተሸልሟል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ኑሮውን ከመቐለ ወደ አዲስ አበባ ካዞረ ሁለት ዓመት ተቆጥረዋል፡፡ አሁን አሁን የአማርኛ ቀልዶችን ማቅረብ ጀምሯል፡፡ በዚህ ዓመት መባቻ ለእንቁጣጣሽ በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ቀልዶቹ መስተናገዳቸው ይታወሳል፡፡ ብዙዎች የትግርኛ ኮሜዲያን እንዲሆን ይገፋፉት እንደነበር ይናገራል፡፡

ሐፍቱ በአማርኛ ቢቀልድም ልቡ የሚያዘነብለው ወደ ትግርኛ ነው፡፡ ዘርፉ ትኩረት እንዲቸረው ጽኑ ፍላጐት አለው፡፡ ‹‹ከሞላ ጐደል መሳቅ የማይፈልግ ሰው የለም፤›› የሚለው ኮሜዲያኑ፣ ቋንቋ ሥራዎቹን ሲገድባቸው እንደሚታይ ግን ይገልጻል፡፡ ከአማርኛ ውጭ በተለያየ ቋንቋ የሚሠሩ ቀልዶች ትኩረት እንዳልተሰጣቸው ይገልጻል፡፡

ኮሜዲያኑ ለሙያው የሚሰጠው ክብር ማነስና ቅድመ ምርመራ ፈትነውኛል ይላል፡፡ ለመቀለድ የመረጣቸውን ርዕሰ ጉዳዮች አስቀድሞ እንዲያሳውቅ ያለአግባብ የተጠየቀባቸው አጋጣሚዎች አሉ፡፡ ሌላው ተግዳሮት ለሙያው የሚሰጠው ዝቀተኛ ግምት ነው፡፡ ‹‹ሙያው ክፍያ የማያስፈልገው የሚመስላቸው ጥቂት አይደሉም፤›› ይላል ከገጠመኞቹ በመነሳት፡፡ በተለያዩ የጥበብ ዘርፎች የተሰማሩ ባለሙያዎች በአሁኑ ወቅት ከተሰጣቸው የበለጠ ክብርም ገንዘብም የሚገባቸው ናቸው ሲል ያክላል፡፡

ኮሜዲያንነቱ ችግር የሚሆንበት ጊዜም አለ፡፡ በማኅበራዊ ሕይወቱ የሚገጥሙት ሰዎች ሁልጊዜ እንዲቀልድ ይጠብቃሉ፡፡ እንደ ኮሜዲያን ሳይሆን እንደ መደበኛ ሰው የሚታደማቸው ሁነቶች ላይ ‹‹እስኪ ቀልድልን›› ይባላል፡፡ እንደዚህ ያሉ አጋጣሚዎች ጥሩ ስሜት አይፈጥሩም፡፡

ኮሜዲያኑ የቧንቧ ሥራን በጣም እንደሚወደው ይገልጻል፡፡ ወደ ሙያው የገባው ውኃን የመሰለ የተፈጥሮ ፀጋ ለሰው ልጆች የሚደርስበትን መንገድ ማመቻቸት አስደሳች በመሆኑ ነው፡፡ በተለይ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ እየተዘዋወረ ውኃ ፍለጋ ለሰዓታት የሚኳትኑ ሰዎችን ሕይወት ቧንቧ በማስገባት ሲለውጥ ሐሴት እንደሚሰማው ይገልጻል፡፡

በትውልድ ቀዬው አካባቢ የሚያውቁት ሰዎች እንደ ኮሜዲያን ብቻ ስለሚያዩት አመለካከታቸው የቧንቧ ሥራው ላይ ተፅዕኖ እንዳሳደረ ይናገራል፡፡ አዲስ አበባ ከመጣ በኋላ ግን የሥራ ዕድሉ እንደሰፋ ይገልጻል፡፡

ከገጠር እስከ ከተማ የሚወስደው ቧንቧ ሥራው ለኮሜድያንነቱ እንደሚያግዘው ያምናል፡፡ ‹‹ቀልድ የማገኘው በማኅበረሰቡ የዕለት ከዕለት ሕይወት ከምታዘበው ነው፤›› ይላል፡፡ ‹‹ለእኔ የጥበብ ሥራዎች ትርጉም ይኼ ነው፤›› ይላል ስለሙያው ሲገልጽ፡፡

በማንኛውም ርዕሰ ጉዳይ ላይ ይቀልዳል፡፡ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ትችቶች በዋነኛነት ይጠቀሳሉ፡፡ እንደ ሁኔታው ለመድረኮች ተገቢ ናቸው የሚላቸውን ቀልዶች ይመርጣል፡፡

ኮሜዲያኑ አሁን 34 ዓመቱ ነው፡፡ የትግርኛ ኮሜዲ መድረኮች የማዘጋጀት ዕቅድ ቢኖረውም አዋጭነቱ ስለማያስተማምን ደፍሮ አልገባበትም፡፡ ቀልዶቹን በሲዲ የማሳተም ፍላጐት ቢኖረውም የኮፒ ራይት ጉዳይ አላላውስ ብሎታል፡፡ በርካታ ባለሙያዎች በላባቸው ውጤት ሳይጠቀሙ ሲቀሩ መመልከቱ ተስፋ እንዳስቆረጠው ይናገራል፡፡

የኮሜዲ ወጪውና ትርፉ ፈጽሞ እንደማይመጣጠን የሚገልጸው ሐፍቱ፣ ኮፒ ራይት ብዙ ባለሙያዎችን እጅ ከወርች እንዳሰረ ይናገራል፡፡ በዚህ ሳቢያ ሥራዎቹ በጥቂት መድረኮችና በዩቲዩብ እንዲወሰኑ ተገዷል፡፡ በዘርፉ ኮሜዲያኖችም ኃላፊነት እንዳለባቸው ይናገራል፡፡ ለታዳሚው ታማኝ ሆነው በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ አዳዲስ ቀልዶችን በየጊዜው ማቅረብ መቻል አለባቸው ይላል፡፡ ችሎታ ያላቸው ኮሜዲያኖች ወደ አደባባይ የሚወጡት ለሥራ የተመቸ ድባብ ሲፈጠር መሆኑን በአጽንኦት ይናገራል፡፡ ከኮሜዲያኖች ክበበው ገዳን ያደንቃል፡፡ በተለይ የማስመሰል ችሎታው ወደር የማይገኝለት ነው ይላል፡፡

መቐለ የሚገኘው ገዛ ገርላሰ የባህል ምግብ አዳራሽ ውስጥ በተደጋጋሚ ቀልድ አቅርቧል፡፡ ከወራት በፊት ቀልድ ለመመልከት ሐርመኒ ሆቴል ገብቶ በመድረክ መሪው እንዲቀልድ ተጋብዞ አቅርቧል፡፡ በሁለቱም መድረኮች ጥሩ ምላሽ አግኝቷል፡፡ መድረኮቹ በጣም የተደሰተባቸው ስለሆኑ ሲያወሳቸው በደስታ ተሞልቶ ነው፡፡ በቅርቡ ለአሸንዳ በዓል ቀልድ ለማቅረብ ወደ ሰሜን አሜሪካና ካናዳ እንደሚያቀና ገልጾልናል፡፡

     

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...