– አብረዋቸው የተከሰሱ የድርጅት ባለቤት በዋስ ተለቀቁ
በአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ግንባታ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት የግብዓት አቅርቦትና አስተዳደር መምርያ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ በፈቃዱ አሰፋ፣ ተጠርጥረው ከተከሰሱበት የሙስና ወንጀል ግንቦት 27 ቀን 2007 ዓ.ም. በነፃ ተሰናበቱ፡፡ አብረዋቸው ተጠርጥረው ክስ የተመሠረተባቸው የኤቢ ፕላስት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ አቶ አብርሃም ጌታቸው በየነ፣ የተጠረጠሩበት የሙስና ወንጀል ወደ ማታለል ወንጀል ተቀይሮ የ200 ሺሕ ብር ዋስ አስይዘው እንዲፈቱ ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡
ሁለቱም ተጠርጣሪዎች ተመሳጥረው በሕገወጥ መንገድ የ3,211,411 ብር የግዥ ውል እንዲፈረም በማድረግ በመንግሥትና በሕዝብ ጥቅም ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን በመጥቀስ፣ የሙስና ወንጀል ክስ መስከረም 7 ቀን 2007 ዓ.ም. ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 18ኛ ወንጀል ችሎት ያቀረበው የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ዓቃቤ ሕግ ነው፡፡ በቁጥጥር ሥር የዋሉት በሐምሌ ወር 2006 ዓ.ም. ነው፡፡
አስተዳደሩ ለሚያስገነባቸው የኮንዶሚኒየም ቤቶች ግብዓት የሚሆን የሳኒተሪ ዕቃ እንዲገዛ የወጣውን የጨረታ የግዥ አፈጻጸም መመርያን ባልተከተለ መንገድ፣ ከደረጃ በታች የሆነ የሳኒተሪ ዕቃ እንዲገዛ መደረጉን የዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡ ሁለተኛ ተከሳሽ ጨረታውን አሸንፈው ያቀረቡት ምርት ደግሞ ዩፒቪሲ መሆኑ ሲገባው ዩፒቪሲ የሚል ማኅተም የተለጠፈበት የፒፒሲ ምርት መሆኑን ክሱ ያስረዳል፡፡ ይኼም የሆነው ምክትል ሥራ አስኪያጁና ነጋዴው ተመሳጥረው መሆኑን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ጠቅሶ፣ በመንግሥትና በሕዝብ ላይ የ3.2 ሚሊዮን ብር ጉዳት እንደደረሰም አስረድቷል፡፡ ሁለተኛው ተከሳሽም በተደጋጋሚ በጨረታ እንዲሳተፉና አሸናፊ እንዲሆኑ አቶ በፍቃዱ እንደረዷቸው ክሱ ይገልጻል፡፡
አቶ አብርሃም ጌታቸው የተባሉት የፒቪሲ ፕላስት ድርጅት ባለቤት የሌሎችን ሰዎች አለማወቅ ተጠቅመው በፒፒሲ ምርት ላይ ዩፒቪሲ የሚል ማኅተም በማስቀመጥና በማታለል፣ በመንግሥት ላይ የ78,147,296 ብር ጉዳት ማድረሳቸውን የዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡
አቶ በፈቃዱ ሌላው የተከሰሱበት ወንጀል በጽሕፈት ቤቱ የግብዓት አቅርቦትና አስተዳደር መምሪያ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ሆነው ሲሠሩ ተገቢ ምክንያት ሳይኖራቸው፣ የ8551 ብር ባለ24 ካራት ስምንት ግራም ብራስሌት ወርቅ ቶፕና ሰላም ኮንስትራክሽን ከተባሉ ተቋራጮች መቀበላቸውን የሚገልጽ ነው፡፡
የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን አቅርቦ አሰምቷል፡፡ ፍርድ ቤቱ የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ያቀረባቸው የሰዎች ምስክሮች፣ የሰነድ ማስረጃዎችና የኤግዚቢት ማስረጃዎች በተጠርጣሪዎቹ ላይ የቀረቡት ክሶች ስለመፈጸማቸው አስረድተዋል? ወይስ አላስረዱም? የሚለውን ጭብጥ ይዞ መመርመሩን በውሳኔው ገልጿል፡፡
አቶ በፍቃዱ ሁለተኛው ተከሳሽ ጨረታ እያሸነፉ የሚያቀርቧቸው የሳኒተሪ ምሮቶች ከስፔስፊኬሸን በታች ስለመሆናቸው ጥቆማ ሲደርሳቸው፣ ሁለተኛው ተከሳሽ (ኤቢ ፕላስት) እንዳይሳተፍ የማድረግና ጨረታውንም የመሰረዝ ሥልጣን ተሰጥቷቸዋል? የሚለውን ከፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ የአደረጃጀትና የሥራ መዘርዝር መመርያ ላይ መመልከቱን እንዲሁም ከሁለተኛ ተከሳሽ ጋር መመሳጠራቸው በዓቃቤ ሕግ ማስረጃዎች መረጋገጥ አለመረጋገጡንም ጭብጥ ይዞ መመርመሩን ዘርዝሯል፡፡
አቶ በፈቃዱ ኤቢ ፕላስት የተባለው ድርጅት የሚያቀርበው የሳኒተሪ ዕቃ ከጥራት በታች መሆኑ ጥቆማ ሲደርሳቸው፣ ወደሚመለከተው የሥራ ክፍል መምራታቸውንና በኢትዮጵያ ምዘናና ተስማሚነት ተቋም ተልኮ እንዲመረመር መደረጉን ፍርድ ቤቱ በተጨማሪ አስረጂነት የጠራቸው የጽሕፈት ቤቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መመስከራቸውን ገልጿል፡፡ ከጥራት በታች መቅረቡ ተረጋግጦ ጨረታው መሰረዙን ማስረዳታቸውንም አክሏል፡፡ ቅሬታ ቀርቧል ተብሎ ሳይጣራ ጨረታ መሰረዝ እንደማይችልና ወደሚመለከተው ክፍል ተልኮ ማጣራት መደረጉን፣ ከምስክሩ መረዳት መቻሉን ፍርድ ቤቱ በስፋት ተንትኗል፡፡ አቶ በፍቃዱ ለሚመለከተው ክፍል መርተውና ለዋና ሥራ አስኪያጁ የክፍሉን ውሳኔ አቅርበው ጨረታውን ያሰረዙ በመሆኑ፣ በቀረበው ክስ የአቶ በፈቃዱ ኃላፊነት ነው ተብሎ በማስረጃነት የቀረበው እሳቸውን የማይመለከትና እሳቸውም ቢሆኑ ኃላፊነታቸውን የተወጡ መሆኑን ከማስረዳት ባለፈ፣ የሚያስጠይቃቸው ሆኖ አለመገኘቱን በውሳኔው ጠቅሷል፡፡
ጥራትን የመቆጣጠር ሥልጣን በጽሕፈት ቤቱ አደረጃጀት መሠረት የአቶ በፍቃዱ ሳይሆን የሌላ ኃላፊ መሆኑን፣ የተለያዩ ጽሕፈት ቤቱ ያወጣቸው መመርያዎች እንደሚያረጋግጡ ፍርድ ቤቱ በዝርዝር ገልጿል፡፡ ቀርበው በመሰከሩት ሰዎችም ሆነ የሰነድ ማስረጃዎች በአቶ በፈቃዱ ላይ ስላላስረዱባቸው በወ/መ/ሥ/ሥ/ቁ/141 መሠረት መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነፃ እንዲሰናበቱ ፍርድ ቤቱ በሙሉ ድምፅ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡
አቶ አብርሃም ጌታቸው የኤቢ ፕላስት ድርጅት ባለቤትም የተጠረጠሩበት ወንጀል ሙስና ሳይሆን ወደ ማታለል ወንጀል ተቀይሮላቸው በ200 ሺሕ ብር ዋስ ሆነው እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቷል፡፡ አቶ በፍቃዱ ላይ የቀረበው ስምንት ግራም ብራስሌት ወርቅን በሚመለከት ምስክሮች ካለመሰማታቸውም በተጨማሪ፣ ወርቁ የተገዛው በስማቸውና በአግባቡ መሆኑን ጠቅሶ በእሱም በነፃ እንዲሰናበቱ ብይን ሰጥቷል፡፡ አቶ በፍቃዱ ከእስር እንዲፈቱና ብራስሌት ወርቃቸው ከኮሚሽኑ ኤግዚቢት ክፍል እንዲመለስላቸው አዟል፡፡ በሁለተኛ ተከሳሽ ላይ የመከላከያ ምስክር ለመስማት ለሐምሌ 6 ቀን 2007 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡