ሸራተን አዲስን ከ16 ዓመታት በላይ በዋና ሥራ አስኪያጅነት ሲመሩ የቆዩት፣ የዴንማርክና የፈረንሣይ ጥምር ዜግነት እንዳላቸው የሚነገረው ሚስተር ዢያን ቪ. ማኒጐፍ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፡፡
ከሸራተን አዲስ ማኔጅመንት የወጣው መረጃ እንደሚያስረዳው፣ ሚስተር ማኒጐፍ ላለፉት ወራት በከባድ ሕመም ሲሰቃዩ ከርመው በቅርቡ በሕክምና እየተረዱ ባሉበት አሜሪካ ሕይወታቸው አልፏል፡፡
ከ20 ዓመታት በላይ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደኖሩና ላለፉት 16 ዓመታት ሸራተን አዲስን ሲመሩ የነበሩት ሚስተር ማኒጐፍ፣ የአርመን ዝርያ እንዳላቸውም ተጠቁሟል፡፡
ዋና ሥራ አስኪያጁ ሆቴሉን እየመሩ በቆዩባቸው ጊዜያት፣ በተለይ ከሆቴሉ ሠራተኞች ጋር ባለመስማማታቸውና ከሠራተኞቹ ከፍተኛ ተቃውሞ ሲደርስባቸው መቆየቱም ይታወሳል፡፡ አንድ የውጭ ዜጋ በአገሪቱ ዜጐች ላይ በደል መፈጸም እንደሌለበትና ካለመኖሪያ ፈቃድ ለረጅም ጊዜ መኖር እንደሌለበት በመጠቆም፣ ሠራተኞቹ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተቃውሞ ደብዳቤ ማቅረባቸው መዘገቡ ይታወሳል፡፡ በርካቶችም ከሥራ መሰናበታቸው አይዘነጋም፡፡
ስለሚስተር ማኒጐፍ ሕልፈት የሸራተን አዲስ ማኔጅመንት ዝርዝር ማብራሪያ እንዲሰጠው ሪፖርተር ጥረት ቢያደርግም፣ ‹‹ፋክስ እናደርግላችኋለን›› ከማለት ባለፈ መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል፡፡
ሚስተር ማኒጐፍ ልጅም ሆነ ትዳር እንደሌላቸው በቅርብ የሚያውቋቸው የሪፖርተር ምንጮች ተናግረዋል፡፡