ፍርድ ቤት በመድፈር ወንጀል ግንቦት 19 ቀን 2007 ዓ.ም. ጥፋተኛ የተባለውና በሽብር ወንጀል ተከሰው በክርክር ሒደት ላይ ከሚገኙት ጦማሪያን መካከል አንዱ የሆነው ጦማሪ አቤል ዋበላ፣ በአራት ወራት እስራት እንዲቀጣ ግንቦት 25 ቀን 2007 ዓ.ም. ፍርድ ተሰጠ፡፡
ተከሳሹ በሌሎች ቀጠሮዎች መልካም ፀባይ እንደነበረው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት ጠቁሞ፣ የአራት ወራት እስራቱን በሁለት ዓመታት ገድቦለታል፡፡
ጦማሪ አቤል ጥፋተኛ የተባለው ግንቦት 19 ቀን 2007 ዓ.ም. ዓቃቤ ሕግ በተከሳሾቹ ላይ አዲስ ሲዲ ለፍርድ ቤቱ ሲያቀርብ፣ የቀረበው ሲዲ ‹‹የሚመለከተው ሶሊያና ሽመልስን ብቻ ነው? ወይስ እኛንም ያካትታል?›› የሚል ጥያቄ ሲያቀርብ ፍርድ ቤቱ እንዳይናገር ሲከለክለው በመናገሩና ፍርድ ቤቱን ‹‹ራሳችሁ ሥነ ሥርዓት›› በማለት ኃይለ ቃል ተናግሯል ተብሎ መሆኑን መዘገባችን ይታወሳል፡፡