– ጦማሪ አቤል ዋበላ ችሎት በመድፈር ጥፋተኛ ተባለ
በተጠረጠሩበት የሽብርተኝነት ወንጀል ከአንድ ዓመት በላይ በእስር በቆዩት ጦማሪያንና ጋዜጠኞች ላይ ተጨማሪ ምስክሮችን ለማሰማት፣ ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ ግንቦት 18 ቀን 2007 ዓ.ም. ለፍርድ ቤት ያቀረበው ጥያቄ ውድቅ ተደረገ፡፡
ክሱን እየሰማ የሚገኘው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት የዓቃቤ ሕግን የተጨማሪ ጊዜ ጥያቄ ውድቅ ያደረገው፣ የተከሳሾቹ ጠበቆች ያቀረቡትን መቃወሚያና ራሱ ፍርድ ቤቱ ቀደም ባለው ችሎት የሰጠውን ትዕዛዝ መሠረት አድርጎ ነው፡፡
ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ ቀደም ባሉት ችሎቶች 18 የሰው ምስክሮችን አሰምቶ ቀሪ ምስክሮችን ሊያገኛቸው እንዳልቻለ በመግለጽ ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጠውና ቀሪ ምስክሮችን ለማቅረብ ሲጠይቅ፣ ፍርድ ቤቱ “ለመጨረሻ ጊዜ” በማለት ተጨማሪ ምስክሮችን እንዲያቀርብ ማዘዙን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
ዓቃቤ ሕግ ግንቦት 18 ቀን 2007 ዓ.ም. በነበረው ቀጠሮ ቀርቦ ምስክሮቹን ሊያገኛቸው እንዳልቻለ በመግለጽ፣ ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቆ ነበር፡፡
የተከሳሾች ጠበቆች ቀደም ብሎ በነበረው ችሎት ዓቃቤ ሕግ ጥያቄውን ማንሳቱንና ፍርድ ቤቱም “የመጨረሻ” ብሎ ትዕዛዝ ሰጥቶት እንደነበር አስታውሰው፣ ድጋሚ ጥያቄው ውድቅ እንዲደረግ ጠየቁ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ጠበቆቹ ቀደም ባለው ችሎት ዓቃቤ ሕግ በኤግዚቢትነት እንዳስያዛቸው ለፍርድ ቤቱ ያሳወቀውን ሲዲዎች ኮፒ እንዲሰጣቸው አመለከቱ፡፡
ዓቃቤ ሕግ በበኩሉ ተከሳሾችም ሆኑ ጠበቆቻቸው የማያውቁት አዲስ ቪሲዲ እንዳለው ለፍርድ ቤቱ ሲያመለክት፣ የተከሳሾች ጠበቆችም እንዲሰጣቸው ጠየቁ፡፡
ፍርድ ቤቱ የተከሳሾቹ ጠበቆች ያቀረቡትን ተቃውሞና አዲስ የቀረበውን ቪሲዲ ይሰጠን ጥያቄ ላይ እንዲሁም ዓቃቤ ሕግ ባቀረበው ቪሲዲ ላይ ብይን ለመስጠት በይደር ቀጠሮ ሰጥቶ ችሎቱ ተጠናቀቀ፡፡
ፍርድ ቤቱ በማግሥቱ ግንቦት 19 ቀን 2007 ዓ.ም. ተሰይሞ ዓቃቤ ሕግ ምስክሮቹን እንዲያሰማ የተሰጠው ጊዜ ለመጨረሻ መሆኑን በመንገር፣ ተጨማሪ የጊዜ ጥያቄውን ውድቅ ማድረጉንና ምስክሮቹን እንደማይሰማ አስታወቀ፡፡
በኤግዚቢት የተያዙ ሲዲዎች ተገልብጠው (ኮፒ) ተደርገው እንዲሰጣቸው የተከሳሾች ጠበቆች ያቀረቡትን ጥያቄ በሚመለከት ፍርድ ቤቱ በሰጠው ምላሽ፣ ሲዲዎቹ የተዘጋጁት ከተከሳሾቹ ላፕቶፖች ላይ ተገልብጠው በመሆኑና ዓቃቤ ሕግ በሰነድ አዘጋጅቶ ያቀረባቸው ወይም ለተከሳሾችም የተሰጡ ዶክመንቶች ተመሳሳይ ስለሆኑ በድጋሚ መስጠቱ አስፈላጊ አለመሆኑን አስረድቷል፡፡
ዓቃቤ ሕግ አዲስ ያቀረበውን ቪሲዲ በሚመለከት “ማስረጃ ይሆናል ወይስ አይሆንም?” የሚለውን ፍርድ ቤቱ በቅድሚያ አይቶ ሰኔ 8 ቀን 2007 ዓ.ም. ብይን እንደሚሰጥበት ገልጿል፡፡
ፍርድ ቤቱ በይደር ያቆየውን የዕለቱን ሥራ በማጠናቀቅ ላይ እያለ ከጦማሪያኑ መካከል፣ ጦማሪ አቤል ዋበላ እጁን በማውጣት ጥያቄ እንዳለው በማመልከት “ቪሲዲው ሶሊያና ሽመልስን ብቻ የሚመለከት ነው ወይስ እኛንም ይጨምራል?” የሚል ጥያቄ ሲያቀርብ ፍርድ ቤቱ ‹‹አልተፈቀደልህም ተቀመጥ›› አለው፡፡ አቤል ጥያቄውን በመቀጠሉ ፍርድ ቤቱ ‹‹ሥነ ሥርዓት ተቀመጥ›› ሲለው ‹‹ራሳችሁ ሥነ ሥርዓት›› የሚል ምላሽ ሰጠ፡፡
የተከሳሾቹ ጠበቃ ወደ አቤል በመጠጋት ካረጋጉትና እንዲቀመጥ ካደረጉት በኋላ ለችሎቱ አመለከቱ፡፡ ተከሳሹ መጠየቅ የፈለገው ዓቃቤ ሕግ ያቀረበው ቪሲዲ የሚመለከተው ሶሊያናን ብቻ ወይም እነሱንም ያጠቃልል እንደሆነ ለማወቅ እንደሆነና ለችሎቱም ምላሽ የሰጠው በስሜታዊነት ስለሆነ ፍርድ ቤቱ ይቅርታ እንዲያደርግለት ጠየቁ፡፡
ፍርድ ቤቱ የጠበቃውን ማመልከቻ ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ ‹‹ራሱ ሊናገር ያሰበውን ገልጾ ይቅርታ ይጠይቅ›› በማለት አዘዘ፡፡
ጦማሪ አቤል ዋበላ ምንም ያጠፋው ነገር እንደሌለና ይቅርታ የሚያስጠይቀው ነገር አለመኖሩን ሲናገር፣ ፍርድ ቤቱ በችሎት መድፈር ጥፋተኛ ብሎታል፡፡
በዚህ ጊዜ ሁሉም ተከሳሾቹ (9ኙም) ከተቀመጡበት ተነስተው አቤል የተናገረው የሁሉም እንደሆነ በመግለጽ እሱ ብቻ ተነጥሎ ጥፋተኛ መባል እንደሌለበት በመግለጽ፣ አንድነታቸውን ለማሳየት ቢሞክሩም ፍርድ ቤቱ በውሳኔው ፀንቷል፡፡ ጠበቃውም ችሎቱ በተግሳጽ እንዲያልፈው የቅጣት ማቅለያ አቅርበዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ፍርድ ለመስጠት ለግንቦት 25 ቀን 2006 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡