Tuesday, February 7, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ከእኔነት በላይ እኛነት ሲናፍቅ!

ሰላም! ሰላም! አንዳንድ ቀን የለም? ድብርና ድብትብት የሚያደርጋችሁ? እንዲያ ባለው ቀን ምን ሆነ መሰላችሁ? መቼም ቶሎ ወደ ገደለው እየገባን ካልተጫወትን ነዳጁን አንችለው። አሉባልታና ወሬ ሲሆን ያልተሳቀቅን ደግሞ ለቁም ነገር አትሉኝም? ታዲያስ! ዛሬ ትንሽ በምሑር ሒሳብ ነው የማጫውታችሁ። አደራ እናንተም እንደዋልጌው በየፌስቡኩ ገጽ የስድብና የዘረኛ አስተያየት ካልሆነ አናነብም የሚል ትክትክ እንዳይጋባባችሁ ጠንቀቅ በሉ። ምን ይታወቃል ዘንድሮ የሥጋ ሕመሙ ወደ መንፈስ፣ የመንፈሱ ወደ ሥጋ እየተቀያየረ ነው እኮ ያስቸገረን። ዋሸሁ እንዴ?

እናላችሁ ሿ ይላል ዝናቡ፤ ሰኔ ሳይገባ። አንዳንድ ሥራዎችን በስልክ እየተከታተልኩ ከወዳጄ ጋር ኮሚሽን እኩል ልንካፈል ተስማምተን የግል ዕረፍት ወስጄ ሰነበትኩ። ደላላ ስንባል ‹ሮቦት› እንጂ ሰው የማንመስለው ስንት አለ? የሚደክመን የሚታክተን የማይመስለው። ለነገሩ ምን ያድርግ? የዘመኑ ገንዘብ ሳይታሰብ፣ ሳይቆጠር ደርሶ ዝርግፍ ይልና ሲሄድ እንደ ባላንጣ መጥፊያው አይታወቅም። ታዲያ እንኳን ደላላው ደህነኛውስ ሰው ቺንጋው እስኪበጥስ ሲሽከረከር ስታዩት ሰው ይመስላል? አልመሰለንም እኮ። አኗኗራችን አለማማሩ ሳያንስ ደግሞ ‘ኤክስፓየርድ’ ስናደርግ አንጀት እንበላለን። (“ወይ ጉድ! ይኼ አንጀት እህል ከበላበት ጊዜ ራሱን የበላበት አይበልጥም አንበርብር?” ያለኝ ማን እንደሆነ ረሳሁት።

ግን ለምን ትዝ አለኝ አሁን? ተውት የራሱ ጉዳይ፤) ብቻ የፈራሁት እንደዚህ ከቀጠልን ታመን እንደወጉ፣ ዘመድ አዝማድ አስታሞን ለመቀበር መላዕክት ዕጣ አዘጋጅተው እኛ ሎተሪ መቁረጥ እንዳንጀምር ነው። እውነቴን እኮ ነው! ምን እኮ? ‘ሲሄድ ሞተ’ ሲባል ትሰማላችሁ። እየተራመደ! . . . አይገርምም? ‘እያወራ ደህና እየሳቀ ክልትው አለ’ማ የተለመደ ሆኗል። የባሻዬ ልጅ እስካሁን ያልሰማሁት አለኝ (ምን ሊል ነው ብዬ ስሰማው) “ትራንስፖርት ሲጠብቅ ሰልፉ መሀል ተዘረረ’ ሲባል ነው።” አለኝ። “በቁም የሞተውንማ ሞት መቼ ያስታውሰዋል” ልለው ብዬ ከአፌ መለስኩት። ዕረፍት አማረኝ ያልኩት ቤቴ እንጂ ማረፊያ ቤት መሰላችሁ እንዴ? ሆሆ!

ምን ነበር ላጫሁታችሁ አስቤ የነበረው? ዕረፍት ወጣሁ አላልኩም? ደብዛዬ የጠፋበት የመንደሩ ነዋሪ ያወራላችኋል። ኋላ እኮ ማንጠግቦሽ እኮ ናት የምትነግረኝ። አንድ ከሰዓት በኋላ በኖኅ ዘመን ተከፍቶ የተረሳ ከሚመስለው የቀላያት ሆድ እኔ ነኝ ያለ ዶፍ ይረግፋል። ጋደም ብዬ በካፖርቴ ምትክ ጋቢ ጣል አርጌ በአንድ ጣት ተቆጥረው ከሚያልቁ የአገራችን ጋዜጦች አማርኛ አማርኛውን ፉት አድርጌ አንብቤ፣ እንግሊዝኛው ላይ ቀላውጬ ልብ ወለድ ማንበብ ቀጥያለሁ። ይኼኔ ማንጠግቦሽ አንገቷን ስብርብር እያደረገች፣ መዳፋን ከመዳፏ እያፋተገች፣ እየተቅለሰለሰች አጠገቤ መጥታ ስትቀመጥ ሁኔታዋ አላማረኝም። “እኔ ምለው” ስትለኝ “አንቺ የምትይው” አልኳት። “መቼም ይኼን ያህል ዓመት አብረን ኖረናል። ከዚህ በላይ ምንም ስላንተ የማላውቀው፣ አንተም የማታውቀው ያለ አይመስለኝም። ግን የሰሞኑን ሁኔታህ (አብዝተህ ከቤት አለመውጣትህ) ‘ለካ ባል ባዳ ነው’ የሚባለው እውነት ነው እንድል እያደረገኝ ነው። ንገረኝ ዕዳ ውስጥ ገብተህ ከሰው ተደብቀህ ነው? ከሰው ተጣልተህ ነው? ከመንግሥት ተጣልተህ ነው? ንግረኝ ምን ሆነህ ነው?” አትለኝ መሰላችሁ።

 ይኼ ከእሷ ጭንቅላት ብቻ እንዳልፈለቀ ወዲያው ነቄ አልኩላችሁ። በተለይ ‘ከመንግሥት ተጣልተህ ነው?’ ስትለኝ ‘አይ ሴራ አለ’ አልኩ።  “ምን ሰምተሽ ነው?” ስላት (አይ ማንጠግቦሽ? የዋህ እኮ ናት) “ምን የማልሰማው አለ?” ብላ ተረተረችው። በምን ብጠረጠር ጥሩ ነው ጎበዝ? “ደላላው አንበርብር ምንተስኖት የሰው ሚስት አባብሎ አሸፍቶ አረገዝኩ ብትለው ኮቴ ሳያሰማ አውሮፓ ገባ፤” እየተባለ ይወራል። “ተመስገን በል። ብቻህን ያሸሹህ ቢያዝኑልህ ነው። ‘ካረገዝሽ አይቀር የምትወልጂው አሜሪካ ነው’ ብሎ ሴትዮዋን ጭምር ይዟት ሄደ ብትባል ምን ትሆን ኖሯል?” ሲለኝ የባሻዬ ልጅ ውሎ አድሮ ስነግረው፣ “እሱማ ምን እሆን ኖሯል?›› ብዬ ዝም አልኩ። ቴሌ ግን አንዳንዴ ‘ኔትወርክ’ ቢያጠፋብን ይፈረድበታል?

ተጣድፎ ከሚያጣድፈኝ የድለላ ሥራዬ አረፍ ብዬ ውስጤን ላዳምጥ ስል የማዳምጠው የጎረቤቶቼን የፈጠራ ታሪክ ሆነ። እየተበሳጨሁ አይተውኝ ይፈሩ ብዬ በዚያ ዶፍ ካፖርቴን ሳልደርብ ብወጣ ደግሞ፣ “እዩት ለካ አብዶ ቤት ተደብቆ ነው፤” ተባልኩ አሉ። ያ ዝናብ እየወረደብኝ ፈጣሪን ‘ምን ዓይነት አገር ነው የፈጠርከኝ? እያልኩና እየተነጫነጭኩ የባሻዬን ቤት አንኳኳሁ። ባሻዬ ከሌላው ቀን ይልቅ ተረጋግተው መጸሐፍ ቅዱሳቸውን እያነበቡ በቆሎ እሸት ይጠብሳሉ። ቀና ብለው ሲያዩኝ ጤና ነው አላሉም። ዘመድ የሞተብኝ፣ ማንጠገቦሽ አንድ ነገር የሆነች መስሏቸው ከመቀመጫቸው ብድግ አሉ። በዚያ ዝናብ ሲያንቀዥቅዥ በንዴት ከቤቴ ያስወጣኝ ግን የአሉባልተኞች ሥራ እንደሆነ ሲያውቁ ከት ብለው ሳቁ። የባሰ አልበሽቅም ይኼኔ? “እንዴት ይስቃሉ ባሻዬ? ነውር አይደለም? ሰው ምን አለበት ዝም ብሎ የራሱን ኑሮ ቢኖር? ማንጠግቦሽ እኮ የሚባለውን ለማመን ምንም አልቀራትም ነበር?” ብዬ ተንጨረጨርኩ። ልክ ባሻዬ ጥሩንባ ነፍተው ወሬውን የነዙት ይመስል። አይ እኛ። ጥሎብን አስታማሚዎቻችን ላይ የምንጮኸውን ሩቡን እንኳን አጥቂዎቻችን ላይ አንጮህም። ችግራችን ይህ ሆኖ ነው እንጂ ስንት ችግር እንፈታ ነበር? ዳሩ የሰውን ኑሮ ማን ይኑርልን?

ባሻዬ “ቁጭ በልማ። ማነሽ እስኪ ፎጣ አምጡለት…” ብለው ሲያበቁ፣ “አንበርብር ‘ሰው በኃይሉ አይበረታም’ ሲለኝ ነው መጽሐፉ አንተ የደረስከው። ለሁሉም ነገር አንተ መልስ ልትመልስ አትችልም። ለሁሉም ችግር መንግሥት መፍትሔ ማምጣት፣ ተጠያቂ መሆንም አይችልም። አንዳንዴ ጊዜን አሳልፈህ ለራሳቸው ለነገሮች መስጠት አለብህ። እከሌ ያለውን ይበል። አንተ ብልጥ ሁን። ውስጥህን ልትመረምር አቋምህን ልትፈትሽ አይደል ቤት የምትውለው? ስለዚህ ጀማውን ስታስብ አንተን፣ አንተን ስታስብ ጀማውን እያየህ ተመራመር። ቡና ትጠጣለህ?” ብለው ቡና አስቀዱልኝ። አይ ባሻዬ! አየችሁ እንዴት እንዴት ነገሩን እንዳጠላለፉት?

ታዲያስ ባሻዬ እንዳሉኝ ‘እኔ ማን ነኝ?’ ስልላችሁ ጉድ እጎለጉልላችሁ ጀመር። ቤቴ ተመልሼ ሳወጣና ሳወርድ እኔ ጨዋታ ለማሳማርና ጆሮ ለማግኘት የማላውቀውን እንደማውቅ፣ የማልደርስበትን እንደማላንሰው አድርጌ የነዛሁት የፈጠራ ወሬ ትዝ እያለ ጭንቅላቴ ታመመ። በወሬ፣ በጓዳቸው በር ገብቼ በግቢያቸው በር የወጣሁባቸው ሰዎች ትዝ አሉኝ። መሳቢያዬን ብስበው እነሱ ያልቆጠሩትን የላምና የበሬ ርቢ እኔ ያሰላሁባቸው ወረቀቶች ተጠፍረው ብቅ አሉ። በሰፈርኩት መሰፈሬ ገባኝ። ‘ሰው ምን ነካው?’ ስል የነካኝ እንደነካው ገባኝ። ያማጡና ፍሬያቸውን ታቅፈው የሳሙ ወዳጆቼ ለማየት ያፀይፋሉ ብለው በአፍ ቦምብ ሲደበድቡዋቸው ተደርቤ ዘምቻለሁ። የሌለሁበት ጥግ አጣሁ። ምን ልሁን? ጨነቀኝ ስላችሁ። ይኼው!

 ‘የእከሌ ሚስት አሜሪካ ሄዳ የወለደችው በመንግሥት በጀት ነው’ ሲሉ አዎ ብያለሁ። እነእከሌ ፎቅ ያቆሙት እነእከሌን ዘርፈው ነው’ ሲባል ማኅተም ያደረግኩት እኔ ነበርኩ። በየአሉባልታውና ፈጠራ ወሬው ሁሉ እጄን እንደ ጲላጦስ ታጥቤ ከደሙ ንፁህ ነኝ ማለት ሲገባኝ አብሬ አቡክቻለሁ። ለመንደሬ ሰዎች፣ ኃጥያታቸው ከኃጥያቴ ምንጭ የፈለቀች፣ በደሌም የበደላቸው ውርስ ሲሆን ራሴን ወቀስኩ። አቤት! ግን ቆም ብሎ ራስን የመመርመርና የማስመርመር ‘ፎብያ’ ባይኖርብን ዛሬ የት ደርሰን ነበር? አንድ ወዳጄን እንዲህ ብዬ ጠይቄው፣ “ነገረ ሥራችን ሁሉ ጭልጥ ብሎ ወደ ካፒታሊዝም ባህል ባይሰደድ ነበራ ይኼን የምትጠይቀው?” ብሎኛል። እኔም መልሼ፣ “ዛሬም ይኼ ካፒታሊዝም፣ ሶሻሊዝም  ብሎ ነገር አልቀረም እንዴ?” ብዬ ስጠይቅ በቀለም ትምህርት አለመግፋቴን አስፎግሬ ቁጭ። የጠየቅኩት ወዳጄም፣ “እንዲህ ያለ የአንደኛ ክፍል ጥያቄ የምትጠይቀው አውቀህ፣ ‘እኔ የጠቀምኳት እንጂ አገሬ የጠቀመችኝ ያገዘችኝ ምንም ነገር የለም ለማለት ፈልገህ ነው? አንተስ ማን ነህ አገር ማለትስ ማን ነው?” ሲል አፈጠጠብኝ። ፋታ ወስዶ፣ “በእኛ ውስጥ አንተ በአንተ ውስጥ ከእኛ ነን። ሌላ ማንም የለም፤” ሲለኝ የምከሰው ተጠያቂ የማደርገው እያሳጣኝ መሆኑ ታውቆኝ ጭጭ አልኩ። ዝምታ አንዳንዴ እንዴት ገላጋይ መሰላችሁ!

በሉ እንሰነባበት። የሥራ ባልደረባዬ አሳልፌ የሰጠሁትን ሥራዎች ጨራርሶ በስምምነታችን መሠረት የሚደርሰኝን ቆርጦ ከሰጠኝ በኋላ አንዳንድ እንበል ብለን የተለመደችዋ ግሮሰሪ ተሰየመን። ከብዙ ማስጠንቀቂያና ማጉረምረም በኋላ ንፋስ የቀላቀለ ከባድ ዝናብ መጣል ሲጀምር በረንዳ ተቀምጠው የነበሩ ታዳሚዎች ንፋሱና ዝናቡን ሙልጭ አርገው እየተሳደቡ ወደውስጥ ገቡ። “ብለን ብለን ደግሞ ከሰማይ ሠራዊት ጋር የትጥቅ ትግል አማረን? አይ ሐበሻ…” አለ የማውቀው ድምፅ። ዘወር ስል የባሻዬ ልጅ ኖሯል። በሰዎቹ ያለቅጥ መበሳጨት ያልተደነቀ የለም። “ዝናብና ንፋስ ላይ እንደዚህ የመጮህ ጉልበት ካለን ለምን መልስ መስጠት ለሚችል አካል አንበረታም ታዲያ?” ሲል ደላላ ወዳጄ፣ “መቼ ዝም አልን ዝም የሚያሰኘን በዝቶ እንጂ፤” አለ ወዲያ ማዶ። ጨዋታው ከቁጥጥራችን ውጭ ሲሆን ደስ አላለኝም። “አይ ሐበሻ! በቃ ሐበሻ ስንባል በረባ ባረባው መተቸት፣ ሸክም ከላያችን ላይ አራግፈን ጣት መቀሳሰር፣ መቀናናት፣ አለመተማመን የሚቀናን ፍጡሮች እኮ ነን። እንዲያው ምን ይሻለናል?” ሲል የባሻዬ ልጅ፣ “እኔ ብለን ስንጀምር፤” አልኩት። “አቤት?” ሲለኝ፣ “እኛ ከእኔ ይጀምራል። እኔ ላይ ስንሠራ በኅብረት ውስጥ ያለው እኛችን ያምራል። አይመስልህም?” ብዬ ቺርስ አልኩት። ተጋጨ ብርጭቆው። ብርጭቆው ሲጋጭ ከእኔነት በላይ እኛነት ናፈቀኝ፡፡ መልካም ሰንበት!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት