ኢትዮጵያዊቷ ናርዶስ በቀለ ቶማስ የዘንድሮው አፍሪካን ውሜን ኦፍ ኤክሰለንስ ተሸላሚ ሆኑ፡፡ በፖለቲካ፣ በማኅበራዊና በኢኮኖሚያዊ ዘርፍ የላቀ አስተዋጽኦ ያበረከቱ አፍሪካውያትን ለማበረታታት የተዘጋጀውን ሽልማት ሰኔ 8 ቀን 2007 ዓ.ም. በሳንድተን ከተማ ማይክል አንጀሎ ሆቴል ይቀበላሉ፡፡
ናርዶስ ለሽልማቱ የተመረጡት በዓለም ላይ በተለያዩ ቦታዎች ላሉ ሴቶች ባበረከቱት አስተዋጽኦ መሆኑን የአፍሪካን ውሜን ኦፍ ኤክሰለንስ ሽልማት አስተባባሪዎች ገልጸዋል፡፡ ሽልማቱ ከናርዶስ ጋር ከሚበረከትላቸው እንስቶች መካከል ኤለን ጆሀንሰን ስርሊፑና ጆይስ ባንዳ ይጠቀሳሉ፡፡
ሽልማቱ የሚዘጋጀው በአፍሪካ ኅብረት ዳያስፖራ አፍሪካን ፎረምና የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ትብብር ሲሆን፣ የአፍሪካ ጉባኤ ከሰኔ 1 እስከ ሰኔ 8 በደቡብ አፍሪካ ጆሀንስበርግ ይካሄዳል፡፡ የዘንድሮው ክብረ በዓል ‹‹ውሜን ኢምፓወርመንት ኤንድ ዴቨሎፕመንት ቱዋርድስ አፍሪካስ አጀንዳ 2063›› በሚል ይከበራል፡፡
ዩኤንዲፒ በድረ ገጹ እንዳተተው፣ ናርዶስ በአፍሪካ ኅብረት ስር በአፍሪካና የአውሮፓ አገሮች ሠርተዋል፡፡ ቤኒን፣ ኒውዮርክ፣ ህንድና የኮሞሮስ ደሴቶች ተጠቃሽ ናቸው፡፡
የአፍሪካ ቢዝነስ ድራጅቶችን የተመለከቱ በርካታ ጥናቶች ሠርተዋል፡፡ ሴቶችና ወጣቶችን በማበረታታትና በጥቃቅንና አነስተኛ ንግድ ምክር በመስጠትም ይታወቃሉ፡፡ የፖሊሲ ጥናቶች በማካሄድና የኢንተርፕረነርሺፕና የሥራ ፈጠራ ሥልጠና በመስጠት አገልግለዋል፡፡
ናርዶስ ከኒውዮርክ ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክ ዴቨሎፕመንት ሞኒተሪ ኢኮኖሚክና ኢኮኖሜትሪክስ የማስተርስ ዲግሪ አላቸው፡፡ በዩኒቨርሲቲው የፒኤችዲ ዕጩም ናቸው፡፡