Friday, March 31, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየአፍሪካ ኅብረት የምርጫ ታዛቢ ልዑክ በምርጫው ያያቸውን ግድፈቶች ይፋ አደረገ

የአፍሪካ ኅብረት የምርጫ ታዛቢ ልዑክ በምርጫው ያያቸውን ግድፈቶች ይፋ አደረገ

ቀን:

–  የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበራት ጥምረት የሕዝብ ድምፅ እንዲከበር ጥሪ አቀረበ

ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. ለአምስተኛ ጊዜ የተካሄደውን ምርጫ በታዛቢነት የተሳተፈው የአፍሪካ ኅብረት የምርጫ ታዛቢ ልዑክ፣ በምርጫው ያያቸውን ግድፈቶች በመጀመርያ ደረጃ ሪፖርቱ ግንቦት 18 ቀን 2007 ዓ.ም. በሒልተን ሆቴል ይፋ አደረገ፡፡

በቀድሞው የናሚቢያ ፕሬዚዳንት ፊኬፑኒያ ፓሃምባ የተመራው 59 አባላት ያሉት የምርጫ ታዛቢ ልዑክ፣ አዲስ አበባንና ድሬዳዋ አስተዳዳር ከተሞችን ጨምሮ በስምንት ክልሎች 356 ምርጫ ጣቢያዎችን፣ በ29 ታዛቢዎች ተዘዋውሮ የምርጫ ሒደቱን ሊታዘብ መቻሉን ፓሃምባ አስረድተዋል፡፡

ታዛቢ ልዑኩ ተዘዋውሮ ከተመለከታቸው የምርጫ ጣቢያዎች መካከል 22.7 በመቶ በሚሆኑት የምርጫ ጣቢያዎች አጠገብ መቀስቀሻ ፖስተሮች ተለጥፈው መመልከቱን፣ 23 በመቶ በሚሆኑት የምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ ቅስቀሳ ሲደረግ ማየቱን የልዑኩ መሪ ተናግረዋል፡፡ እንዲሁም 21.42 በመቶ በሚሆኑ ድምፅ መስጫ ጣቢያዎች ኮሮጆዎች ባዶ መሆናቸው ሳይረጋገጥ ድምፅ መሰጠት መጀመሩን እንደተመለከቱ፣ የልዑኩ መሪ ሚስተር ፓሃምባ ከልዑካን ቡድኑ መረዳታቻውን አብራርተዋል፡፡

የምርጫ ታዛቢ ልዑኩ ሌላው በምርጫው ወቅት የታዘባቸው ጉዳዮች ለድምፅ መስጫው ኮሮጆ ተከታታይ ቁጥር (Serialized) አለመኖሩ ሲሆን፣ ይኼም በግልጽነትና በተጠያቂነት ላይ፣ በተለይ መተማመን በማይታይባቸው የምርጫ አካባቢዎች ጥያቄ ሊያስነሳ እንደሚችል ታዛቢ ልዑኩ ጥቆማ መስጠቱን የልዑኩ መሪ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ በምርጫው ዕለት እንደገለጸው፣ የአፍሪካ ኅብረት የምርጫ ታዛቢ ልዑክም በአንዳንድ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የምርጫ ቁሳቁሶች ሳይሟሉ ወይም በወቅቱ ሳይደርሱ በመቅረታቸው፣ ምርጫው ለ24 ሰዓታት መራዘሙን ልዑኩ ማመልከቱንም የልዑኩ መሪ አክለዋል፡፡

የታዛቢ ልዑኩ ጉድለት ያየባቸው የምርጫ ጣቢያዎችን አድራሻ በግልጽ ባያሳውቅም፣ በምርጫው ዕለት ታዝቢያለሁ ካላቸው ጉድለቶች በስተቀር ተዘዋውሮ የታዘባቸው የምርጫ ጣቢያዎች፣ ከ98 በመቶ በላይ የሚሆኑት የድምፅ መስጫ ጣቢያዎች ከንጋቱ 12፡00 ሰዓት ጀምሮ ክፍት ሆነው አንዳገኛቸው የልዑክ መሪው ገልጸዋል፡፡

ምርጫው ተጠናቆ ቆጠራ ሲካሄድ የታዛቢ ቡድኑ በተከታተላቸው የምርጫ ጣቢያዎች ምንም ዓይነት ችግር እንዳላየ ገልጾ፣ ነገር ግን በሶማሌ ክልል ጂግጂጋ ከተማ ውስጥ በአንድ ድምፅ መስጫ ጣቢያ ቆጠራ ሲደረግ፣ ድምፅ ለመስጠት የተመዘገበው ሕዝብ ብዛትና የተሰጠው ድምፅ ሳይጣጣም ቢቀርም፣ በታዛቢነት የተገኙ የፓርቲ ተወካዮች ምንም ዓይነት ተቃውሞ አለማንሳታቸውን መታዘቡን መሪው አስታውቀዋል፡፡

የአፍሪካ ኅብረት ምርጫ ታዛቢ ልዑክ በኢትዮጵያ የተካሄደውን አምስተኛውን ጠቅላላ ምርጫ ሒደት በሚመለከት ከሁለት ወራት በኋላ ዝርዝር ሪፖርቱን በድረ ገጹ ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቆ፣ በኢትዮጵያ የተካሄደው ምርጫ ከጠቀሳቸው ችግሮች በስተቀር ሰላማዊ፣ ጥሩ መግባባት የታየበት፣ ሕዝቡ በተረጋጋና ታማኝነት በተሞላበት ሁኔታ ምርጫውን ሲያካሄድ መታዘቡን ሚስተር ፓሃምባ አስረድተዋል፡፡

ሌላው አምስተኛው ጠቅላላ ምርጫ በሁሉም መለኪያዎች ሲመዘን ደረጃውን የጠበቀ፣ ፍትሐዊ፣ አሳታፊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ነፃና ሰላማዊ መሆኑን ማረጋገጡን የገለጸው፣ 12 የሲቪልና የሙያ ማኅበራት ጥምረት ነው፡፡ ግንቦት 17 ቀን 2007 ዓ.ም. በኢሊሌ ሆቴል ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡  

የጥምረቱ ፕሬዚዳንት አቶ ታደለ ይመር እንደተናገሩት፣ ‹‹ለኢትዮጵያ አገራችን ዴሞክራሲያዊ፣ ሰላማዊ፣ ፍትሐዊና ነፃ በሆነ ተሳትፎ፣ ድምፃችንን በመስጠት ምርጫውን እንዳረጋገጥን ሁሉ፣ የተሰጠው የሕዝብ ድምፅ እንዲከበር ጥሪያችንን እናቀርባለን፤›› በማለት ተፎካካሪ ፓርቲዎቹን አሳስበዋል፡፡

የ2007 ጠቅላላ ምርጫ ከ2002 አገር አቀፍ ምርጫ በተሻለ ሁኔታ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች መሳተፋቸውን የጠቆሙት አቶ ታደለ፣ ምርጫው ሰላማዊ ቢሆንም የምርጫ አስፈጻሚዎችና የሕዝብ ታዛቢዎች ተሟልተው ሲገኙ፣ የዕጩ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ተወካዮች አለመገኘታቸውን ተናግረዋል፡፡

በማይፈቀድ ቦታ ላይ ቅስቀሳ ማድረግና ፖስተር መለጠፍና በተፈቀደ ቦታ ላይ ደግሞ ፓርቲዎች የለጠፉት ፖስተር መቀደድ በቅድመ ምርጫ የታዩ ችግሮች መሆናቸውን ያስታወሱት አቶ ታደለ፣ የተወዳዳሪ ዕጩ ፓርቲዎች ተወካዮች አለመገኘት፣ ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የድምፅ መስጫ ወረቀት ተሟልቶ አለመገኘት፣ በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በተወሰኑ ቦታዎች የድምፅ መስጫ ጣቢያዎች የተመቻቸ ቦታ ላይ አለመሆን፣ በምርጫው ወቅት የታዩ ችግሮች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ የድምፅ መስጫ ጣቢያዎቹ (አንዳንዶቹ) ለአካል ጉዳተኞች በጣም አስቸጋሪ እንደነበሩም የሲቪክ ማኅበራት ጥምረት ምርጫ ታዛቢ  ቡድን መታዘቡን አክለዋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ሚዳ ቀኝ ምርጫ ክልል፣ በአንድ የምርጫ ክልል በተፈጠረ አለመግባባት ምርጫው ከረፋዱ 4፡10 ላይ መጀመሩን፣ በአማራ ክልል በባህር ዳር ከተማ ምዕራብ ጎጃም ቡሬ ዙሪያ ወረዳ፣ ጫጫ የምርጫ ክልልና በአንዳንድ የኦሮሚያ ክልሎች ችግሮች እንደነበሩ የጥምረቱ ታዛቢዎች ማረጋገጣቸውን አቶ ታደለ ገልጸዋል፡፡ ጊቤ፣ ደምቢዶሎ፣ ጉደርና አምቦ በአንዳንድ አካባቢዎች ውጤት በወቅቱ አለመለጠፉን ታዛቢ ቡድኑ መመልከቱንም አቶ ታደለ ተናግረዋል፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተወግዘው የነበሩ ሦስቱ ሊቀጳጳሳትና 20 ተሿሚ ኤጲስ ቆጶሳት ውግዘት ተነሳ

_ቀሪዎቹ ሦስት ህገወጥ ተሿሚዎች የመጨረሻ እድል ተሰጥቷቸዋል ​ ጥር 14...

በሕወሓት አመራሮች ላይ ተመስርቶና በሂደት ላይ የነበረው የወንጀል ክስ ተቋረጠ

በቀድሞ የትግራይ ክልል ፕሬዚደንት ደብረጽዮን ገብረሚካኤ,(ዶ/ር)ና ባለፈው ሳምንት በተሾሙት...

[የምክር ቤቱ አባል ላቀረቡት ጥያቄ በተሰጣቸው ምላሽ አቤቱታቸውን ለክቡር ሚኒስትሩ እያቀረቡ ነው]

ክቡር ሚኒስትር እየሆነ ያለው ነገር ትክክል ነው? ምነው? ምክር ቤቱም ሆነ...

የጉራጌ የክልልነት ጥያቄ ትኩሳት

ቅዳሜ መጋቢት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. በጉራጌ ዞን ወልቂጤ...