– ጭማሪው በካሬ ሜትር ከ27 እስከ 45 በመቶ መሆኑ ተጠቁሟል
‹‹አስተዳደሩ ያደረገው ጭማሪ 15 በመቶ ብቻ ነው›› የቤቶች ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መጋቢት 13 ቀን 2007 ዓ.ም. ለአሥረኛ ጊዜ ዕጣ ያወጣባቸው 41 ሺሕ የጋራ መኖሪያ ቤቶች (ሰባት ሺሕ ለልማት ተነሽዎች ናቸው)፣ በዋጋቸው ላይ ከፍተኛ ጭማሪ መደረጉን ካቢኔው ሊቀበለው ባለመቻሉ፣ ልዩ ኮሚቴ ተቋቁሞ የዋጋ ጥናት እየተደረገ መሆኑ ተሰማ፡፡
የተወሰኑ የካቢኔ አባላት ሚያዝያ 26 ቀን 2007 ዓ.ም. በከንቲባው ጽሕፈት ቤት ስብሰባ አድርገው በኮንዶሚኒየሙ ወጪ ላይ መግባባት ባለመደረሱ፣ ልዩ ኮሚቴ ተቋቁሞ የዋጋ ጥናት እንዲደረግ ስምምነት ላይ መደረሱን ምንጮች ገልጸዋል፡፡
ቀደም ብሎ ተቋቁሞ የነበረው ኮሚቴ ስለ ኮንዶሚኒየም ቤቶች ያጠናው ጥናት ከመጠን በላይ የተጋነነ በመሆኑ፣ ከሁሉም ዘርፍ የተወጣጣ ልዩ ኮሚቴ ተቋቁሞ ዋጋው እንደገና መጠናት እንዳለበት ውሳኔ ላይ መደረሱን ምንጮች አስረድተዋል፡፡ አዲስ የተቋቋመው ኮሚቴ የመጀመርያ ስብሰባውን ግንቦት 3 ቀን 2007 ዓ.ም. ማድረጉንም አክለዋል፡፡
የከተማ አስተዳሩ ለቤቶች ልማት ፕሮግራም ከስድስት ቢሊዮን ብር በላይ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መበደሩን የሚያስታውሱት ምንጮቹ፣ ለቤቶች ግንባታ የወጣው ወጪና በባንክ ያለው ገንዘብ ሊጣጣም ባለመቻሉ ሁለቱን አጣጥሞ ለመቀጠል በቤቶቹ ላይ ዋጋ መጨመር እንዳለበት የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ እምነት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በተለይ የቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት የተወሰኑ ሠራተኞች የአሥረኛው ዙር ዕድል ተጋሪ በመሆናቸው፣ ጽሕፈት ቤቱ ሥራውን እንዴት እየሠራና ምን ዓይነት ወጪ ለምንና እንዴት እየወጣ እንደሚገኝ በቅርበት ስለሚያውቁ፣ ጠንከር ያሉ ጥያቄዎችን ያቀረቡ መሆኑንም ምንጮች ገልጸዋል፡፡
በቤቶቹ ላይ መደመር የሌለባቸው የተለያዩ ወጪዎች በብክነት ወይም በሌላ ወጪ መመዝገብ ሲገባቸው በቤቶቹ ላይ በመደመራቸው፣ ለግንባታና ለዲዛይን ወጪ ተገምቶ ሥራውን ለምርምር ብድር የተወሰደ ቢሆንም፣ ከባንክ ጋር የተገባውን ብድር ማፋለሱን ገልጸዋል፡፡ ካቢኔውም በተሠራው የግንባታና የዲዛይን ዋጋ መሠረት ጽሕፈት ቤቱ መሥራት ሲገባው፣ የተጋነነ ዋጋ መቅረቡ ትክክል አለመሆኑን መግለጹን ምንጮቹ ገልጸዋል፡፡ የጽፈሕት ቤቱም ሠራተኞች ወጪው ለብቻ መያዝ እንዳለበት በመግለጽ የካቢኔውን አቋም እየደገፉ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
የካይዘን ኢንስቲትዩት ባደረገው ጥናት መሠረት በቤቶች ግንባታ ላይ 33 በመቶ ብክነት መኖሩን ለካቢኔው ማሳወቁን የገለጹት ምንጮች፣ ብክነቱን በተለያዩ ነገሮች ማወራረድ ሲቻል በቤቶቹ ዋጋ ላይ መደመር አግባብ አለመሆኑን ካቢኔውም ሆነ የዕጣው ዕድለኞች የሚስማሙበት ሐሳብ መሆኑንም ምንጮች አስረድተዋል፡፡
የቤቶች ልማት ፕሮጀክት ማንኛውም ዓይነት ክትትልና ጥንቃቄ ቢደረግበት እንኳ እጅግ በጣም አስቸጋሪና ለምዝበራ የተጋለጠ መሆኑን፣ የቤቶች ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትሩ አቶ መኩሪያ ኃይሌ በቅርቡ በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የከተማ ልማትን በተመለከተ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ባደረጉት ክርክር ላይ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ቢሮ ኃላፊ በሚያዝያ ወር የመጀመርያ ሳምንት አካባቢ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ በአሥረኛው ዙር ዕጣ በወጣባቸው ቤቶች ላይ የተደረገው ጭማሪ እንደሚባለው የተጋነነ ሳይሆን፣ 15 በመቶ ብቻ እንደሆነ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ ነገር ግን አስተዳደሩ የነባር 20/80 ባለ አንድ፣ ሁለትና ሦስት መኝታ ቤቶችና እንዲሁም የስቱዲዮ ቤቶችን ለመሸጥ ካስቀመጠው ዋጋ ላይ ከ27 እስከ 45 በመቶ ጭማሪ ማድረጉን የዋጋውን ልዩነት ያሰሉ ነዋሪዎች እየገለጹ ነው፡፡
የ10/90 ተመዝጋቢዎች ዝቅተኛ ክፍያ በካሬ ሜትር 1,310 ብር የሚከፍሉ መሆኑን በምዝገባ ወቅት የተነገረ ቢሆንም፣ በአሥረኛው ዙር ግን በካሬ ሜትር 1,910 ብር እንዲከፍሉ ተደርጓል፡፡ ልዩነቱ 600 ብር ወይም 45 በመቶ መሆኑን ነዋሪዎቹ ይናገራሉ፡፡ ዝቅተኛው የስቱዲዮ ስፋት 29 ካሬ ሜትር ነበር፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታ ነባር የ20/80 ባለሁለት መኝታ ቤት ተመዝጋቢ በካሬ ሜትር የሚከፍለው 3,452 ብር የነበረ ቢሆንም፣ በአሥረኛው ዙር ዕድለኛ የሆነ ግን በካሬ ሜትር 4,394 ብር ይከፍላል፡፡ ሲመዘገብ ከሚያውቀው ዋጋ ጋር ያለው ልዩነት 942 ብር ወይም 27 በመቶ መሆኑን ነዋሪዎቹ አሥልተዋል፡፡ ዝቅተኛው ባለሁለት መኝታ ቤት ስፋቱ 65 ካሬ ሜትር ነው፡፡
በመሆኑም የዕጣው ባለቤቶች መንግሥት መሬት በነፃ፣ ሁሉንም የግንባታ ግብዓቶች ከአገር ውስጥ ባደረገበት ጊዜ ዋጋው ይኼንን ያህል ሊጋነን እንደማይገባ እየገለጹ ባሉበት ወቅት፣ አስተዳደሩ ዋጋው በልዩ ኮሚቴ እንዲጠና ማድረጉ ተገቢና ዕድለኞቹንም ያሰበ ሊሆን ይችላል በሚል ተስፋ ላይ መሆናቸውን ምንጮች አስረድተዋል፡፡ ነዋሪዎች የሠሩት ሥሌት ትክክል መሆን አለመሆኑንና አዲስ ስለተቋቋመው ኮሚቴም ማብራሪያ እንዲሰጡ የአስተዳደሩት ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ኃላፊዎችንና የከንቲባ ጽሕፈት ቤት ኃላፊዎችን ለማግኘት የተደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡