– የጥፋተኝነት ውሳኔ የተሰጠው በልዩነት ነው
በመስከረም ወር 2007 ዓ.ም. የ16 ዓመት ታዳጊ መሆኗ የተገለጸውን ሐና ላላንጐ፣ በታክሲ አፍነው ወደ ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ቀራኒዮ አካባቢ በመውሰድ፣ ተፈራርቀው በመድፈር ሕይወቷ እንዲያልፍ አድርገዋል በሚል ክስ የተመሠረተባቸው አምስት ወጣቶች፣ ግንቦት 7 ቀን 2007 ዓ.ም. ጥፋተኛ ተባሉ፡፡ የጥፋተኝነት ውሳኔው የተሰጠው በልዩነት ነው፡፡
ተከሳሾቹ ሳምሶን ስለሺ፣ በዛብህ ገብረ ማርያም፣ በቃሉ ገብረ መድኅን፣ ኤፍሬም አየለና ተመስገን ዘገዬ የተባሉ ከ19 እስከ 31 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ወጣቶች ሲሆኑ፣ የታክሲ ሾፌርና ረዳት መሆናቸው በክሱ መገለጹ ይታወሳል፡፡
ዓቃቤ ሕግ የወንጀል ሕግ 32(1ሀ) ማለትም በዋና ወንጀል ተካፋይነት፣ የወንጀል ሕግ 539(1ሀ)ን ማለትም ከባድ የሰው ግድያና የወንጀል ሕግ 626 (1)ን፣ ማለትም ዕድሜያቸው 13 በሆነና 18 ዓመት ባልሞላቸው ልጆች ላይ የሚፈጸም የግብረ ሥጋ ግንኙነትን በሚመለከት የተደነገገውን አዋጅ መተላለፋቸውን ጠቅሶ ክስ መሥርቶ ነበር፡፡
የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ የመሠረተውን ክስ ሲመረምር የከረመው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 3ኛ ወንጀል ችሎት (የክስ ሒደቱ የተካሄደው በዝግ ችሎት ነው)፣ ግንቦት 7 ቀን 2007 ዓ.ም. ሁሉንም ተከሳሾች በልዩነት ጥፋተኛ ብሎ ለቅጣት፣ አስተያየትና የቅጣት ውሳኔ ለመስጠት ለግንቦት 14 ቀን 2007 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
የተለዩት ዳኛ ከአንድ እስከ ሦስት ያሉት ተከሳሾች ላይ ከሌሎቹ ዳኞች ጋር ተመሳሳይ ሐሳብ ያላቸው ቢሆኑም፣ በአብላጫ የወንጀል ሕግ አንቀጾችን በልዩነት ያስቀመጡት፣ ተከሳሾቹ ማለትም ከአንድ እስከ ሦስት ያሉት ተከሳሾች ላይ የወንጀል ሕግ 539 (1ሀ) [ያገዳደል ሁኔታው ክብደት] እና የወንጀል ሕግ 620(3) [የአስገድዶ መድፈሩ ክብደት] ተገቢ ሆኖ ሳለ፣ በወንጀል ሕግ 620 (2መ) [ጭካኔና ስቃይ መፍጠር] ጥፋተኛ መባል የለባቸውም በሚል ነው፡፡ በአብላጫ ድምፅ በተደራቢነት የተጠቀሰውን የወንጀል ሕግ 620(4)ን [ጠለፋ] የተለዩትም ዳኛ ደግፈው፣ ነገር ግን ይኼ አንቀጽ ወደ ወንጀል ሕግ 585(1) [ከሕግ ውጭ ይዞ መቀመጥ] ስለሚወስድ በእሱ መሠረት ከአንድ እስከ ሦስተኛ ያሉት ተከሳሾች ጥፋተኛ ሊባሉ እንደሚገባ በመግለጽ ተለይተዋል፡፡ 4ኛና 5ኛ ተከሳሾች ግን በዓቃቤ ሕግ ስላልተመሰከረባቸው በነፃ ሊሰናበቱ እንደሚገባ ገልጸው ተለይተዋል፡፡