Thursday, March 23, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበውኃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት ደካማ አፈጻጸም ቦርዱ ማሳሰቢያ ተሰጠው

በውኃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት ደካማ አፈጻጸም ቦርዱ ማሳሰቢያ ተሰጠው

ቀን:

–  የግድብና የመስኖ ፕሮጀክቶች አፈጻጸማቸው ዝቅተኛ ነው ተባለ

የኢትዮጵያ የውኃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት ከውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ጋር ውል ፈጽሞ እያከናወናቸው ያሉ ፕሮጀክቶች አፈጻጸማቸው ዝቅተኛ ነው ተባለ፡፡ የውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር በሚኒስትሩ አቶ ዓለማየሁ ተገኑ ለሚመራው የድርጅቱ ሥራ አመራር ቦርድ አስቸኳይ ማስተካከያ እንዲያደርግ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ተጻፈለት፡፡

ለሥራ አመራር ቦርዱ የማሳሰቢያው ደብዳቤ የተጻፈው የርብ የመገጭና  የጊዳቦ ግድቦች፣ የከሰም መስኖ መሠረተ ልማት ግንባታና የተንዳሆ የኅብረተሰብና የስኳር ልማትና መጠጥ ውኃ ግንባታን ለማከናወን ውል የገባው የውኃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት፣ ፕሮጀክቶቹን በማጓተቱና አፈጻጸሙ ዝቅተኛ በመሆኑ ምክንያት ነው ለቦርድ ማስጠንቀቂያ የተጻፈው፡፡

በውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጂነር ወንድሙ ተክሌ ሚያዝያ 21 ቀን 2007 ዓ.ም. የተጻፈው ደብዳቤ ውኃ ሥራዎች ድርጅት ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጋር በገባው ውል መሠረት በአማራ ክልል የሚገኙትን የርብና የመገጭ ግድቦች ግንባታን፣ በኦሮሚያ ክልል የጊደቦ ግድብ ግንባታን፣ በአፋር ብሔራዊ ክልል የከሰም መስኖ መሠረተ ልማት ግንባታና የተንዳሆ የኅብረተሰብና የስኳር ልማትና የመጠጥ ውኃ ግንባታ ለማካሄድ ኮንትራት የወሰደ ቢሆንም፣ ፕሮጀክቶቹ በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ሊጠናቅቁ አለመቻላቸው ደብዳቤው ያስረዳል፡፡ ሚኒስቴሩ በተደጋጋሚ የቀረቡለትን የማራዘሚያ ጥያቄዎችም በመቀበል የውል ጊዜን ያራዘመ ቢሆንም፣ አንዳንዶቹ ፕሮጀክቶች ወደ ኪሳራ ሊገቡ መገደዳቸውንም ያክላል፡፡

የርብ ግድብ እ.ኤ.አ. ጥቅምት 2 ቀን 2007 ተጀምሮ እ.ኤ.አ. ሚያዝያ 30 ቀን 2011 የሚጠናቀቅ ቢሆንም፣ በተያዘው ዓመት እ.ኤ.አ. 2015 አፈጻጸሙ 76.5 በመቶ ነው ተብሏል፡፡ ነገር ግን እ.ኤ.አ. ከግንቦት 2011 እስከ ሰኔ 2014 ድረስ እንዲራዘም መደረጉን ለውኃ ሥራዎች ድርጅት ሥራ አመራር ቦርድ የተላከው የማሳሰቢያ ደብዳቤ ይገልጻል፡፡ የመገጭ ግድብ ግንባታም እ.ኤ.አ. መጋቢት 22 ቀን 2012 ዓ.ም. የተጀመረ ሲሆን፣ መጠናቀቅ ያለበት እ.ኤ.አ. ነሐሴ 30 ቀን 2016 ነው፡፡ በዚህ ዓመት ያለው የአፈጻጸም መጠን ግን 26.05 በመቶ ብቻ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

የጊዳቦ ግንባታ ግንባታ የተጀመረው ጥር 3 ቀን 2002 ዓ.ም. ሲሆን፣ ይጠናቀቃል የተባለው ጥር 3 ቀን 2004 ዓ.ም. መሆኑ ተገልጿል፡፡ ነገር ግን አራት ጊዜ ውሉ እንዲሻሻል ተደርጎ አሁን ያለበት አፈጻጸም 63.86 ብቻ መሆኑን ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡ በሌሎቹም ፕሮጀክቶች የሚታየው አፈጻጸም ተመሳሳይ መሆኑን የሚያብራራው የሚኒስቴሩ ደብዳቤ፣ ባለድርሻ አካላቱ ማለትም ሚኒስቴሩ የውኃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅትና አማካሪው የውኃ ሥራዎች ዲዛይንና ቁጥጥር ድርጅት ተመካክረው ቦርዱ እንዲያውቀው ያደረጉ ቢሆንም ሊሻሻል አለመቻሉን ያብራራል፡፡

ሦስቱ ባለድርሻ አካላት ባደረጉት ምክክር ድርጅቱ አጠቃላይ ያለበትን ሁኔታ ቦርዱ እንዲያውቀው ተደርጎ ለማበረታታት መሞከሩን፣ ድርጅቱ ያጋጠመውን የፋይናንስ ችግር በመረዳት ከክፍያ ተመላሽ የሚደረግ 250 ሚሊዮን ብር በብድር መልክ እንዲሰጠው መደረጉን ደብዳቤው ያስረዳል፡፡

ከመንግሥት ጋርም በመነጋገር ለርብና ለመገጭ ግድቦች ግንባታ ከሐምሌ 1 ቀን 2006 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆን አዲስ የዋጋ ማሻሻያ መደረጉን፣ እንዲሁም መንግሥት የድርጅቱ ካፒታል እንዲያድግ በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር በኩል የተወሰነ ክፍያ መፈጸሙንም ደብዳቤው ያብራራል፡፡ ነገር ግን ከላይ የተገለጹት ድጋፎች የተደረጉለት ቢሆንም የፕሮጀክቶቹ አፈጻጸም ሊሻሻል አለመቻሉንም ጠቁሟል፡፡ ፕሮጀክቶቹ ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻል ከማሳየት ይልቅ ዝቅተኛ አፈጻጸም ላይ መሆናቸውን ገልጾ፣ የውኃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት ሥራ አመራር ቦርድ ልዩ ትኩረት በመስጠትና ችግሮቹን በመፈተሽ በቀሪው ጊዜ አፈጻጸሙ የሚሻሻልበትን  የበኩሉን ሚና እንዲጫወት የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር በደብዳቤው አሳስቧል፡፡

የሥራ አመራር ቦርዱ ከሚኒስቴሩ በደረሰው ማሳሰቢያ መሠረት ምን እያደረገ እንደሚገኝ ማብራሪያ ለማግኘት የተደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...