Monday, December 5, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  በሐዋሳ ከ3.5 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገነባው የሀያት ሪጀንሲ ሆቴል ውዝግብ አስነሳ

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  በደቡብ ክልል በሐዋሳ ከተማ ከ3.5 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጎበት የሚገነባው የሀያት ሪጀንሲ ሆቴል ፕሮጀክት የመሬት ይገባኛል ውዝግብ ተነሳበት፡፡ ሆቴሉ ሊገነባበት በታሰበበት ቦታ ላይ የይገባኛል ጥያቄ ያነሳው የመከላከያ ሚኒስቴር መሆኑም ታውቋል፡፡

  ይህ በዓለም አቀፍ ደረጃ ስመ ጥር የሆነን ሆቴል በሐዋሳ ለመገንባት  የይሁንታ ደብዳቤ በከተማ አስተዳደሩ ተሰጥቶኛል የሚሉት ባለሀብቱ አቶ ቴዎድሮስ ሽፈራው፣ ሆቴሉን ለማስገንባት ዲዛይን ለማሠራት ያደረጉት እንቅስቃሴ መደናቀፉን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

  ባለሀብቱ ሆቴሉን ለመገንባት ያሰቡትን መሬት ያገኙት ለኢትዮጵያ ሚሊኒየም በከተማ መስተዳድሩ ጥሪ በክልሉ ኢንቨስት እንዲያደርጉ በተጋበዙበት ወቅት ነበር፡፡ በወቅቱ የከተማ መስተዳደሩ ባለሀብቱ የወጣቶች መዝናኛ ማዕከል እንዲገነቡበት ስምንት ሺሕ ካሬ ቦታ ሰጥቷቸዋል፡፡ ባለሀብቱም ይህንን ቦታ በ6,720,000 ብር አጠቃላይ ዋጋ የአምስት በመቶ ቅድሚያ ክፍያ በመክፈል በ2000 ዓ.ም. ተረክበው ነበር፡፡

  ምንም እንኳን ባለሀብቱ በወቅቱ ከከተማው የተረከቡትን መሬት ለወጣቶች የመዝናኛ ማዕከል ለመገንባት አቅደው የነበረ ቢሆንም፣ በኋላ ላይ ትልቅ ኢንቨስትመንት ውስጥ ለመግባት ወስነው የሆቴሉን ፕሮጀክት ይጀምራሉ፡፡ በዚህም መሠረት ይህን ዓለም አቀፍ ሆቴል ለመገንባት ለሁለት ዓመት ያህል የፈጀ ድርድር ከሆቴሉ ጋር አድርገዋል፡፡ ሆቴሉንም ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣት ለተደረገው ድርድር ከአሥር ሚሊዮን ብር በላይ ለአደራዳሪዎቹ ተከፍሏቸዋል፡፡

  የከተማ መስተዳድሩንም የመዝናኛ ማዕከል ግንባታውን በሆቴል ፕሮጀክቱ መቀየር እንደሚችሉ ባለሀብቱ በደብዳቤ ጠይቀው፣ መስተዳድሩ ጳጉሜን 3 ቀን 2009 ዓ.ም. በጻፈላቸው ደብዳቤ ባለአምስት ኮከብ ሆቴል መገንባት እንደሚችሉ ገልጾላቸዋል፡፡

  ሆኖም ባለሀብቱ የግንባታውን አካል የሆነውን ዲዛይን ለማሠራት ከውጭ የቀጠራቸውን ባለሙያዎች ይዘው ሰሞኑን ወደ ሐዋሳ ቢያቀኑም፣ ከከተማ መስተዳድሩ ያገኙት ምላሽ አሳዝኗቸዋል፡፡ የሆቴሉን ዲዛይን ለሚሠራው ፒ ኤንድ ቲ አርክቴክትስና ኢንጂነርስ ኩባንያ 1.8 ሚሊዮን ዶላር ለመክፈል ተስማምተው የ30 በመቶ ክፍያ እንደፈጸሙ የጠቆሙት ባለሀብቱ፣ ሰሞኑን የክልሉ መስተዳድር በዲዛይኑ ላይ አስተያየት እንዲጥበትና የክልሉን ባህል ለማንፀባረቅ የከተማው ባለሥልጣናት ግብዓት እንዲሰጡበት ታስቦ የነበረው ስብሰባ ሳይካሄድ መቅረቱን ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

  የሐዋሳ ከንቲባ አቶ ቴዎድሮስ ጊቢባ ባለሀብቱ ቦታውን በሕጋዊ መንገድ መረከባቸውን ገልጸው፣ ይዞታው ላይ ግን የመከላከያ ሠራዊት አባላት እንደሚኖሩበት ተናግረዋል፡፡ ሆቴሉ ሊገነባበት የታሰበው ቦታ ላይ መከላከያ ሚኒስቴር የይገባኛል ጥያቄ ያነሳበት መሆኑን የተናገሩት ከንቲባው፣ መሬቱ ለባለሀብቱ ከመሰጠቱ በፊት በክልሉ መስተዳድር ቦታው ነፃ መደረግ እንደነበረበት ይገልጻሉ፡፡

  ምንም እንኳ መሬቱ ለባለሀብቱ የተሰጠው እሳቸው በነበሩበት ወቅት ባይሆንም፣ ቀድሞ የነበረው የከተማው አመራር ቦታውን ነፃ ሳያደርግ ለባሀብቱ ሕጋዊ ማስረጃዎች መስጠቱ ስህተት መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ቦታውን ባለሀብቱ እንዲያለሙት በታቀደበት ወቅት ለመከላከያ ሚኒስቴር 20 ሚሊዮን ብር ካሳ ተሰጥቶት መሬቱን ለከተማ መስተዳድሩ ለማስረከብ ስምምነት ነበር፡፡ በዚሁ መሠረት አምስት ሚሊዮን ብር ለመከላከያ ሚኒስቴር ገቢ መደረጉን የገለጹት ከንቲባው፣ ቀሪ ክፍያ ስለመፈጸሙ ግን ምንም ዓይነት ማስረጃ ሊገኝ አለመቻሉን ተናግረዋል፡፡

  ባለሀብቱ ቦታውን ከተረከቡ በኋላ ግንባታ ለመጀመር የተለያዩ ጥረቶችን ቢያደርጉም፣ ከዚህ ቀደም ሠራተኞቻቸው ሳይቀር ለእስር መዳረጋቸውን ገልጸዋል፡፡ ባለሀብቱ፣ ‹‹የአገሪቱንም ሆነ የክልሉን ስም በዓለም አቀፍ መድረክ ሊያስጠራ የሚችል ትልቅ ፕሮጀክት ይዤ፣ ይህን ያህል እንግልት ሊገጥመኝ አይገባም፤›› በማለት ምሬታቸውን ገልጸዋል፡፡

  የሐዋሳ ከንቲባ ቦታውን ለባለሀብቱ ለማስረከብ ይቻል ዘንድ የሐዋሳ ከተማ ምክትል ሥራ አስኪያጅና የክልሉ የዳያስፖራ ጉዳዮች ኃላፊ ከመከላከያ ሚኒስቴር ጋር እየተደራደሩ ነው ብለው፣ ጉዳዩ ገና እልባት ላይ እንዳልተደረሰበት አስረድተዋል፡፡

  ለበርካታ ባለሀብቶች የከተማ መስተዳድሩ ቦታ እየሰጠ ይህን ለአገር ትልቅ ፋይዳ የሚያመጣ ፕሮጀክትን ማጓተት ተገቢ አለመሆኑን የሚገልጹት ባለሀብቱ ቢያንስ ተለዋጭ ቦታ ሊሰጣቸው እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡  ሆቴሉን ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣት ከሁለት ዓመት በላይ ከመፍጀቱም በላይ፣ ድርድሩን ላደረጉት ዓለም አቀፍ ተቋማት ከአሥር ሚሊዮን ብር በላይ ማውጣታቸውን ባለሀብቱ ገልጸው፣ በጉዳዩ ላይ መንግሥት አፋጣኝ ምላሽ የማይሰጣቸው ከሆነ ክስ ለመጀመር መዘጋጀታቸውን  ተናግረዋል፡፡

  ባለሀብቱ በሐዋሳ የሚገነቡትን ባለአምስት ኮከብ ሆቴል ወጪ 25 በመቶ ብቻ ማዋጣት እንደሚጠበቅባቸው ገልጸው፣ ቀሪውን ዓለም አቀፍ ባንኮች ፋይናንስ ለማድረግ መስማማታቸውን አስረድተዋል፡፡

  ባለሀብቱ በተመሳሳይ በሀያት ሪጀንሲ ስም በአዲስ አበባ ለገሐር አካባቢ ባለ34 ፎቅ ሆቴል ለመገንባት የቦታ ርክክብና የካፒታል ማሳየት ሥራ እንደ ቀራቸው ገልጸዋል፡፡

  በሐዋሳ በሚገነባው ሆቴል መሬት ላይ የይገባኛል ጥያቄ ያነሳውን መከላከያ ሚኒስቴር በጉዳዩ ላይ ለማነጋገር የተደረገው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

  ሀያት ሪጀንሲ ሆቴል በዓለማችን ከሚታወቁ ስመ ጥር ሆቴሎች መካከል አንዱ ሲሆን፣ በ57 አገሮች 739 ሆቴሎች ያስተዳድራል፡

  spot_img
  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

  - ማስታወቂያ -

  በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች