Tuesday, March 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊከመንግሥት ሥራ የለቀቁ ግለሰቦች የኮንዶሚኒየም ልዩ የዕጣ ዕድል በመነፈጋቸው ተቃውሞ አቀረቡ

ከመንግሥት ሥራ የለቀቁ ግለሰቦች የኮንዶሚኒየም ልዩ የዕጣ ዕድል በመነፈጋቸው ተቃውሞ አቀረቡ

ቀን:

‹‹ጉዳዩ የአስተዳደሩን ውሳኔ የሚጠይቅ ነው››  የቤቶች ልማት አስተዳደር ኤጀንሲ

  የጋራ መኖሪያ ቤቶች (ኮንዶሚኒየም) ተጠቃሚ ለመሆን መንግሥት በ2005 ዓ.ም. መጨረሻ አካባቢ አዳዲስ ተመዝጋቢዎችን ሲመዘግብ በወቅቱ የመንግሥት ሠራተኛ ሆነው የተመዘገቡ የአሥረኛው ዙር ዕጣ ቢወጣላቸውም፣ ሥራቸውን በመልቀቃቸው ምክንያት ዕድሉ ‹‹አይገባችሁም›› መባላቸውን ተቃወሙ፡፡

      ለተቃውሟቸው መነሻ ምክንያት የሆናቸው በቅርቡ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በወጣ ሰርኩላር የመንግሥት ሠራተኛ መሆናቸውን የሚገልጽ የድጋፍ ደብዳቤ ካልያዙ፣ በዕድሉ ተጠቃሚ መሆን እንደማይችሉ ስለተነገራቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በመንግሥት የሃያ በመቶ ልዩ የዕጣ ዕድል የተፈቀደላቸው በሰርኩላር መሻር የለበትም ብለዋል፡፡

የመንግሥት ሠራተኞች ሆነው ምዝገባውን ከፈጸሙ በኋላ በተለያዩ ምክንያቶች በተለያዩ ጊዜያት ሥራቸውን በመልቀቃቸው ልዩ ዕድሉን ሊነፈጉ እንደማይገባ የሚናገሩት የዕጣ ዕድለኞች፣ መንግሥት የግድ ‹‹እኔ ዘንድ ካልሠራችሁ ዕድል አይኖራችሁም፤›› ማለት የለበትም ብለዋል፡፡ እንደማንኛውም የመንግሥት ሠራተኛ የዕድሉ ተጠቃሚ ሊያያቸው እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

መንግሥት ዜጎቹ መጠለያ እንዲያገኙ የማድረግ ግዴታ እንዳለበት ጠቁመው፣ ባወጣው ፕሮግራም መሠረት ተጠቃሚ ማድረጉ ጥሩ ቢሆንም ያገኙትን ልዩ ዕድል እንዳያገኙ ማድረግ ግን ተገቢ አይደለም ብለዋል፡፡ በተጨማሪ ማንኛውም ዜጋ በራሱ ሥራ የመፍጠርና ራሱን መቻል እንዳለበት ከሚገልጸው ጋር እንደሚጣረስም አስረድተዋል፡፡ ቆሜለታለሁ ከሚለው ቤት አልባዎችን ባለቤት ከማድረግ ዓላማ ጋርም የሚጋጭ ነው ብለዋል፡፡

የዕድሉ ተጠቃሚ በመሆናቸው ተደስተው የሚፈለጉባቸውን መሥፈርቶች በማሟላት በተመደቡበት ክፍለ ከተማ ሲሄዱ፣ ‹‹በ2005 ዓ.ም. የተመዘገባችሁት የመንግሥት ሠራተኛ ሆናችሁ ነበር፡፡ መንግሥት ልዩ ዕድል እንድታገኙ አድርጎ የዕድሉ ተጠቃሚ ስለመሆናችሁ የድጋፍ ደብዳቤ ይዛችሁ መቅረብ እንዳለባችሁ፣ በአዲስ አበባ ከተማ የኮንስትራክሽንና ቤቶች ልማት ቢሮና የቤቶች ልማት አስተዳደር ኤጀንሲ ሰርኩላር አስተላልፏል፤›› ተብለው እንደተመለሱ አስረድተዋል፡፡

በአሥረኛው ዙር የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ ውል በመዋዋል ሒደት የሚገጥሙ የአሠራር ክፍተቶችን ለመሙላት የሚያስችል ሰርኩላር ሚያዝያ 26 ቀን 2007 ዓ.ም. መተላለፉን የገለጹት ዕድለኞቹ፣ መንግሥት ሁሉም ዜጎች በእኩልነት እንዲጠቀሙ በማድረግ ዕድሉ እንዳያመልጣላቸው የተቻለውን ሁሉ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል፡፡ ወጣ የተባለው ሰርኩላር ግን እነሱን በእጅጉ እንደሚጎዳ አስረድተዋል፡፡

የዕድሉ ባለቤቶች በሚያነሱት ተቃውሞ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡ ሪፖርተር ጥያቄ ያቀረበላቸው የቤቶች ልማት አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ መስፍን መንግሥቱ፣ ‹‹ጉዳዩ የአስተዳደሩን ውሳኔ የሚጠይቅ ነው፤›› ብለዋል፡፡

አሁን ባለው ሁኔታ የመንግሥት ሠራተኞች የዕድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉን የገለጹት አቶ መስፍን፣ ይህ የተደረገው የመንግሥት ሠራተኞችን ለመደገፍ  ነው ይላሉ፡፡ በመሆኑም በመንግሥት ሠራተኞች ኮታ ዕጣ የደረሰው ሰው የመንግሥት ሠራተኛ ካልሆነ ቤቱ እንደማይገባው ተናግረዋል፡፡ ይህንን አባባል በአጭሩ ሲያስረዱ፣ ‹‹በሴቶች ኮታ ወንድ ቢደርሰው አይሰጠውም፡፡ ምክንያቱም ኮታው የሴቶች በመሆኑ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ውሳኔው በኤጀንሲው የሚሰጥ ባለመሆኑ በሁሉም ክፍላተ ከተሞች ተመሳሳይ ችግሮች ተከስተው ከሆነ ተሰባስበው ሲመጡ ለከተማ አስተዳደሩ ይቀርብና ውሳኔ እንደሚሰጥበት አስረድተዋል፡፡

የዕጣ ዕድለኞች ብዙ ሥጋት እንዳይገባቸው ያሳሰቡት ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ በየተመደቡበት ክፍለ ከተማ በመሄድ አስፈላጊውን ፎርማሊቲ አሟልተው ውሳኔው እስከሚሰጥ ድረስ ይጠባበቁ ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል ዕጣ ደርሷቸው ቅድመ ክፍያ (20 በመቶ የቤቱን ዋጋ) መፈጸም ያቃታቸው አንዳንድ ዕድለኞች ነጠላቸውን አንጥፈው ሲለምኑ ተስተውሏል፡፡ አነስተኛ ተከፋይ የሆኑ ሠራተኞችም አንጥፈው ከሚለምኑት ባልተናነሰ ሁኔታ በሚሠሩባቸው መሥሪያ ቤቶች ዕርዳታ እንዲደረግላቸው ወረቀት እያዞሩ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡

አቶ መስፍን ለእነዚህ ዜጎች መንግሥት የተለየ ዕርዳታ የሚያደርግበት አሠራር እንዳለ ተጠይቀው፣ ‹‹በእርግጥ የኤጀንሲው የሥራ ዘርፍ አይደለም፡፡ ዋጋ የመቀነስና የተለያዩ እገዛዎች ካሉም የመቀነስና የማድረግ ሥልጣን የከተማ አስተዳደሩ ነው፤›› ካሉ በኋላ፣ ዕጣ ደርሷቸው መሠረታዊ የሆነ ችግር ያለባቸው ከተገኙ አማራጮች እንደሚፈለጉላቸው ገልጸዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ የቀበሌ ቤት የመስጠትና ሌሎችንም ድጋፎች ሊያደርግ እንደሚችል ጠቁመው፣ አስተዳደሩ የኮንዶሚኒየም ቤቶችን ዋጋ ይቀንስ ወይም አይቀንስ እንደማያውቁ አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹ከኦነግ ሸኔ ጋር ያለውን ግጭት በሰላም ለመፍታት ከፍተኛ ፍላጎት አለን›› ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ

መንግሥት ከ‹‹ኦነግ ሸኔ››ጋር ያለውን ግጭት በሰላም ለመፍታት ከፍተኛ ፍላጎት...

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...