የግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አል ሲሲ የአገራቸው መከላከያ ሠራዊት ከአሸባሪው ቡድን አይኤስ ያዳናቸውን 27 ኢትዮጵያውያን በካይሮ አውሮፕላን ማረፊያ ተቀብለዋል፡፡ አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ እንደዘገበው፣ አሸባሪው በድን ሊቢያ ውስጥ ይዟቸው የነበሩ ኢትዮጵያውያን እንዴት ነፃ እንደወጡ በዝርዝር ባይታወቅም ‹‹በግብፅና ሊቢያ መከላከያ ሠራዊት ትብብር ነፃ ወጥተዋል፤›› የሚል መልዕክት ተላልፏል፡፡
ፕሬዚዳንቱ በካይሮ አውሮፕላን ማረፊያ እንደገለጹት ኢትዮጵያውያኑን በሰላም ወደ ግብፅ ለማስገባት ርብርብ ተደርጓል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያውያን ወንድሞቻችንን ከአደጋ ለመከላከል የግብፅ ኃይል ከፍተኛ ጥረት አድርጓል፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ከሳምንታት በፊት 30 ንፁኃን ኢትዮጵያውያን በአሸባሪው ቡድን ሕይወታቸውን ማጣታቸው እንዳሳዘናቸው ተናግረዋል፡፡ በጦርነት እየተናጠች ከምትገኘው ሊቢያ ኢትዮጵያውያኑን ያወጡትም ለዚሁ ነው፡፡ ሊቢያ ወደ ሰላማዊ አገርነት መመለስ እንዳለባትና የአገሪቱ ጉዳይ ሁሉንም እንደሚመለከት ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል፡፡
ሊቢያን ለዓመታት የገዙት ሙአመር ጋዳፊ ከሥልጣን ከወረዱ በኋላ ሥልጣን ለመቆጣጠር ፍላጐት ያላቸው የጦር ኃይሎች አገሪቱ እየተተረማመሰች ነው፡፡ ከኢትዮጵያውያኑ በፊት 21 የግብፅ ኮፕቲክ ክርስቲያኖች በአማጺው ቡድን መገደላቸውና ግብፅ በምላሹ የአየር ድብደባ ማካሄዷ ይታወሳል፡፡ አል ሲሲም በተደጋጋሚ ጥምር የዓረብ መከላከያ ሠራዊት እንዲመሠረት ወትውተዋል፡፡ በዓረብ ሊግ ላይ የተሰለፉት የዓረብ አገሮች በሐሳቡ መስማማታቸው ይታወሳል፡፡