Thursday, April 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምባልቲሞርን ያረጋጋው የፍትሕ ፍንጭ

ባልቲሞርን ያረጋጋው የፍትሕ ፍንጭ

ቀን:

የባልቲሞር ከተማ ነዋሪ የነበረው የ25 ዓመቱ ጥቁር አሜሪካዊ ፍሬዲ ግሬይ በፖሊሶች ቁጥጥር ሥር በዋለ በሳምንቱ ሕይወቱ ማለፉ፣ በተለይ በባልቲሞር አለመረጋጋትን ከፈጠረ ቀናት ተቆጥረዋል፡፡

በምድረ አሜሪካ በነጭ ወይም በጥቁር ፖሊስ የጥቁሮች መገደል አዲስ ባይሆንም፣ በቅርብ ጊዜያትም በፈርጉሰን ተከስቶ የነበረ ቢሆንም፣ የባልቲሞሩ ግን ከዚህ ቀደም ከነበረው በተለየ ነዋሪዎችን አስቆጥቷል፡፡

የሰብዓዊ መብት ይከበርባታል፣ በአገሮች የሰብዓዊ መብት እንዲከበር ትሠራለች፣ እንዲሁም አስገዳጅ ፖሊሲዎችን ታራምዳለች በምትባለው አሜሪካ፣ በተለይ በጥቁሮች ላይ የሚፈጸመው ድብደባና ግድያ ዓለም አቀፍ ትኩረትን ስቧል፡፡ የፈርጉሰን ጉዳይ ሳይረሳ አሁን ደግሞ በባልቲሞር ተደግሟል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የ25 ዓመቱ ግሬይ በአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር በሚታወቀው በምዕራብ ባልቲሞር አካባቢ ሚያዝያ 4 ቀን 2007 ዓ.ም. ጠዋት ላይ ነበር በቁጥጥር ሥር የዋለው፡፡ በወቅቱ በአካባቢው ከነበሩ ፖሊሶች ጋር ዓይን ላይን ሲተያይ መሮጡን፣ ሦስት ፖሊሶችም አሯሩጠው እንደያዙት፣ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር በዋለበት ወቅት በኪሱ ውስጥ ተስፈንጣሪ ጩቤ (ሥለቱ በአጭር ቆመጥ ውስጥ የተደበቀ ሆኖ አስፈላጊ ሲሆን ማስፈንጠር የሚቻል) ይዞ መገኘቱን ዎል ስትሪት ጆርናል ዘግቧል፡፡

ፖሊሶች ግሬይን ለመያዝ ጥረት ሲያደርጉ ከእርሱ በገጠማቸው እንቢተኝነት ከመሬት አጋጭተውታል፣ ደብድበውታል፡፡ ከፍተኛ ጉዳትም አድርሰውበታል፡፡ ሕክምና እንዲያገኝ ሲጠይቅም ምላሽ አላገኘም፡፡ በመሆኑም እስር ቤት በገባ በሳምንቱ ሕይወቱ አልፏል፡፡

የግሬይ በፖሊሶች ተደብድቦ መሞት የባልቲሞር ነዋሪዎች ከፖሊስ ጋር እንዲጋጩ ምክንያት ሆኗል፡፡ ከተማዋም ሳትረጋጋ ሳምንታት አሳልፋለች፡፡ የግሬይ ሞት በፈርጉሰን በ18 ዓመቱ ብራውን ላይ እንደተፈጸመው ግድያ፣ ፍትሕ አልባ ይሆናል ሲሉም የባልቲሞር ነዋሪዎች ያሰሙት ተቃውሞ የፍትሕ ፍንጭ አሳይቷል፡፡

በግሬይ ላይ ኢሰብዓዊ ድርጊት ፈጽመዋል የተባሉት ስድስት የባልቲሞር ፖሊሶችን ጉዳይ ለማየት የተሰየመው ፍርድ ቤት ፖሊሶቹ ግሬይን ያሠሩት በሐሰት የእስር ክስ ነው፡፡ ይኼም ሕገወጥ ነው ብሏል፡፡ ግሬይ በፖሊስ ከተያዘ በኋላ በደረሰበት ድብደባ ኅብረሰረሰሩ ላይ ጉዳት መድረሱንም አስታውቋል፡፡ ይህም በባልቲሞር ሁለት ዓይነት ስሜቶች ፈጥሯል፡፡

አንዱ ወገን ፖሊሶቹ የውሸት ክስ መሥርተው አስረዋል መባላቸው፣ በሌሎች ፖሊሶች ላይ መተማመንን ያሳጣል፣ ሥራቸውን በአግባቡ እንዳይሠሩ ያደርጋል፣ ሌሎች ወደ ሥራው እንዳይገቡ ይገድባል የሚል ሲሆን፣ አንዱ ወገን ደግሞ የዚህ ዓይነት ውሳኔ መተላለፉ ፖሊሶች በተለይ በጥቁሮች ላይ የሚያደርሱትን በደል ቆም ብለው እንዲያጤኑ፣ ፍትሕ ያለ መሆኑንም እንዲገነዘቡ ያስችላል ብሏል፡፡

በባልቲሞር በወጣቱ ላይ የተፈጸመው ኢሰብዓዊ ድርጊትን ተከትሎ የተቀሰቀሰው አለመረጋጋት የከተማዋን የንግድ እንቅስቃሴ አዳክሟል፡፡ በፖሊሶችና በነዋሪዎች መካከልም ግጭትን ቀስቅሷል፡፡ ሱቆች እንዲዘጉ አድርጓል፡፡ በዚህም ምክንያት በከተማዋ የተፈጠረውን አለመረጋጋት ለመታደግ ወታደሮች ተሰማርተው የነበረ ሲሆን፣ ከሰኞ ምሽት ጀምሮ ግን ከከተማዋ እንዲወጡ ውሳኔ ተላልፏል፡፡ ተጥሎ የነበረው የሰዓት እላፊ ገደብ የተነሳ ሲሆን ሱቆች በተወነሰ ደረጃ መከፈት ጀምረዋል፡፡

ከተማዋ በቅጡ ሳትረጋጋ ወታደሮች እንዲወጡ መወሰኑ ነዋሪዎችን ሥጋት ላይ የጣለ ቢሆንም፣ የባልቲሞር ከንቲባ ስቴፈኒ ራውሊንግስ ግን፣ ‹‹በማንኛውም ቦታ ቢሆን አስፋላጊ ከሆነው ወቅት ውጪ ሰዓት እላፊ መጣል አያስፈልግም፤ ወታደሮቹም ወደሚፈለጉበት ቦታ ይሄዳሉ፤›› ብለዋል፡፡

የግሬይን ሞት ተከትሎ ከሚያዝያ 15 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ በባልቲሞር በተቀሰቀሰ ግጭት 486 ሠልፈኞች በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውለዋል፡፡ የባልቲሞር ፖሊስ ዲፓርመንት ቃል አቀባይ ካፒቴን ጄ ኤሪክ ባለፈው እሑድ እንደተናገሩት፣ በቁጥጥር ሥር ከዋሉት ውስጥ ከግሬይ ሞት ጋር በተያያዘ ከወጡት በተጨማሪ ሌላ ሁከት ለመፍጠር የተሰባሰቡም ይገኙበታል፡፡

እስከ ቅዳሜ ሚያዝያ 24 ቀን 2007 ዓ.ም. ድረስ 113 የፖሊስ አባላት የተጎዱ ሲሆን፣ በዕለቱ ብቻም 46 ሰዎች ታስረዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አራቱ ሰላማዊ ሠልፍ ለመውጣት ዕድሜ የማይፈቅድላቸው ናቸው፡፡ ሚያዝያ 19 ቀን 2007 ዓ.ም. በባልቲሞር በፖሊስና በተቃውሞ አድራጊዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት 200 የንግድ ማዕከላት ከጥቅም ውጪ ሲሆኑ፣ አብዛኞቹም የመድን ዋስትና እንደሌላቸው ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡

በአሜሪካ ሚዙሪ ፈርጉሰን ከተማ በነጭ ፖሊስ የተገደለው የ18 ዓመቱ ማይክል ብራውን ፍትሕ አለማግኘቱ የፈርጉሰን ነዋሪዎችን አስቆጥቶ ነበር፡፡ ብራውን በፖሊስ በጥይት በተመታበት ወቅት ምንም ዓይነት መሣሪያ ያልታጠቀ ቢሆንም፣ በዳኞች የፀናው ፖሊሱ ብራውንን የገለደው ራሱን ለመከላከል ባደረገው ጥረት ነው የሚለው  ነበር፡፡ በወቅቱ የፈርጉሰን ነዋሪች ተቃውሞ ወጥተው የነበረ ቢሆንም፣ የባልቲሞሩ የከፋ መሆኑን ዎል ስትሪት ጆርናል ዘግቧል፡፡ ከፍትሕ አንፃር ሲታይም የባልቲሞሩ ከዚህ ቀደም ከነበረው የተሻለ ፍንጭ አሳይቷል፡፡

በአሜሪካ ሜሪላንድ ከሚገኙ ከተሞች ባልቲሞር ትልቁን ሥፍራ ትይዛለች፡፡ በሕዝብ ብዛትም በአገሪቱ ካሉ ከተሞች በ26ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ እ.ኤ.አ. በ2013 የወጣው ሪፖርት እንደሚያሳየው በከተማው የሚኖረው ሕዝብ ብዛት ከ600 ሺሕ በላይ  ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...